Print this page
Sunday, 04 March 2018 00:00

ትራምፕ በ3.9 ቢ. ዶላር፣ 2 ልዩ ቦይንግ አውሮፕላኖችን ሊገዙ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ እየተጠቀሙበት የሚገኘውን ኤርፎርስ ዋን የተሰኘ ልዩ ፕሬዚዳንታዊ አውሮፕላን የሚተኩ 2 እጅግ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን፣ በ3.9 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት፣ ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ባደረጉት ድርድር መስማማታቸው ተዘግቧል፡፡
ቦይንግ ኩባንያ እጅግ ዘመናዊ እንደሆኑ የተነገረላቸውን ሁለት ቦይንግ 747 - 8 አውሮፕላኖች፣ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለመሸጥ ከዓመታት በፊት ለዋይትሃውስ ዋጋ አቅርቦ እንደነበር ያስታወሰው ኤንፒአር የዜና ወኪል፤ በቢዝነስ ድርድር የላቀ ችሎታ እንዳላቸው የሚነገርላቸው ትራምፕ ግን ተደራድረው፣በ3.9 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት መስማማታቸውን የዋይትሃውስ ቃል አቀባይ ሆጋን ጌሊ፣ ባለፈው ረቡዕ እንዳስታወቁ ዘግቧል፡፡
ትራምፕ በዋጋ ድርድር ብቃታቸው ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ማዳናቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ቦይንግ ኩባንያ አውሮፕላኖቹን ለዋይትሃውስ የሚያስረክብበት ትክክለኛ ጊዜ አለመታወቁን አመልክቷል፡፡
እጅግ የረቀቁ የደህንነት መሳሪያዎች የተተከሉላቸው እነዚህ እጅግ ዘመናዊ የቦይንግ አውሮፕላኖች፤ የሽብር ጥቃቶችን በብቃት የመመከት ችሎታ እንዳላቸውና የኒውክሌር ጦርነትን ጨምሮ በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ያለ አንዳች ችግር ረጅም ርቀት መብረር እንደሚችሉ ገልጧል፡፡
ትራምፕ እና ቦይንግ ኩባንያ 1ሺህ ማይል ርቀት የመብረር አቅም እንዳላቸው የተነገረላቸውን አዲሶቹን ቦይንግ 747 - 8 አውሮፕላኖች፣ በተጠቀሰው ዋጋ ለመገበያየት ስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን በቀጣይም ህጋዊ የግዢ ውል ይፈጸማል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡

Read 2032 times
Administrator

Latest from Administrator