Saturday, 03 March 2018 11:04

የኢትዮጵያ እግር ኳስ የከፋ አደጋ ላይ ነው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

• የፌደሬሽኑ አመራሮች ምርጫ ለ4ኛ ጊዜ በፊፋ አስገዳጅነት ተራዝሟል፡፡
   • በስፖርት ላይ ጥፋት የሚያደርሱ ሁሉ በህግ መጠየቅ አለባቸው፤ (የህግ ባለሙያ አቶ ተፈራ ደንበል)
   • የዓለም ዋንጫን ብንጎበኝም ህልም ያለን ግን አይመስልም፡፡
   • የቻን 2020 መስተንግዶ አጠያያቂ ሆኗል፡፡

   ዛሬ በአፋር ዋና ከተማ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የፌደሬሽን ፕሬዝዳንትና ስራ አስፈፃሚዎች ምርጫ በፊፋ ማሳሰቢያ ለአራተኛ ጊዜ መራዘሙ፤ ስፖርቱ በተለያዩ የውዝግብ አጀንዳዎች መጓተቱ እና ለሚደርሱ ጥፋቶች ሃላፊነቱን የሚወስድና የሚጠየቅ አካል አለመኖሩ፤ በዓለም ዋንጫ የአዲስ አበባ ጉብኝት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚገባውን ያህል አለመነቃቃታቸው፤ እንዲሁም ከ19 ወራት በኋላ  ቻን 2020ን የማስተናገዱ ሁኔታ አጠያያቂ እየሆነ መምጣቱ የኢትዮጵያን እግር ኳስ የከፋ አደጋ ላይ ጥሎታል፡፡

የፌደሬሽኑ አመራሮች ምርጫና የውዝግቦቹ መዘዝ
የፌደሬሽኑን አመራሮች ምርጫ የሚያስተናግደው ጠቅላላ ጉባኤ ለአራተኛ ጊዜ እንዲራዘም የተወሰነው ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር  በላከው ደብዳቤ አስገዳጅነት ነው፡፡  የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንን ወቅታዊ ትርምስ በቅርበት እንደሚከታተል በደብዳቤው ያመለከተው ፊፋ የምርጫውን ሂደትና አጠቃላይ ሁኔታዎች የሚታዘብ ልዩ ልዑኩን በመጋቢት ወር አጋማሽ እንደሚልክና ከዚያም ጠቅላላ ጉባኤው የሚካሄድበትን ቀን እንደሚወስን አመልክቷል፡፡ የፊፋ ዋና ፀሃፊ ፋትማ ሳሙራ ፊርማ ባረፈበት ደብዳቤ እንደተገለፀው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚያከናውነው ምርጫ የፊፋን መርህ የሚያሟላ፤ በግልፅና መልካም ሁኔታዎች የታጀበ እንዲሆን ይፈለጋል፡፡ የፊፋ ልዑክ አስፈላጊውን ማጣራትና ግምገማ ከሰራ በኋላም የፌደሬሽኑ አመራሮች ምርጫ በተገቢው ወቅት መካሄድ እንደሚኖርበትም ያሳስባል፡፡
የፌዴሬሽኑ አመራሮች የምርጫ ሂደት ጠቅላላ ጉባኤው ተካሂዶ ካልተቋጨ በቀር በተወሰኑ ደረጃዎች በፊፋ መርሕና የሕግና ድንጋጌዎች ላይ የተደረጉ ጥሰቶች አገሪቱን ሊያስቀጡ ይችላሉ፡፡  የመንግሥት ጣልቃ ገብነትን የሚያጎሉ ክስተቶች ገነው በመውጣት ተገቢውን ድጋፍ ያሳጣል፡፡ በዓለም አቀፍ የስፖርት አመራር ተቋማት ለኢትዮጵያ የስፖርት አስተዳደር የሚኖረው ተዓማኒነት ይጓደላል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድኖችና ክለቦች ከአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎ የሚታገዱበትና የሚቀጡበትን አደጋ ይፈጥራል፡፡  በተለይ ደግሞ ለቻን 2020 የሚደረግ ዝግጅትን በማጓተት የመስተንግዶውን እድል በማሳጣት የኢኮኖሚ፤ የቱሪዝምና የዲፕሎማሲ ክስረት የሚፈጥርም ይሆናል፡፡

‹‹በስፖርቱ ላይ ጥፋት የሚያደርሱ በህግ መጠየቅ አለባቸው፡፡››
የህግ ባለሙያው አቶ ተፈራ ደንበል
አቶ ተፈራ ደንበል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ ትምህርት ዲግሪያቸውን የሰሩ ሲሆን በጥብቅና ሙያ ለ20 ዓመታት በመስራት ልምድ አላቸው፡፡ ከስፖርቱ በተያያዘ ደግሞ በ70ዎቹ መጀመርያ የበራሪ ኮከብ ክለብ ተጨዋች ነበሩ፡፡ ከዚያም በዳኝነት ኮርሶችና ስልጠናዎችን ወስደው ከሃያ ዓመታት በላይ በእግር ኳስ ዳኝነት እስከ ፌደራል ዳኛ ማዕረግ አገልግለዋል፡፡ አቶ ተፈራ ላለፉት 10 ዓመታት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የዲስፕሊን ኮሚቴ በአባልነትና ሰብሳቢነት እየሰሩ እንደመቆየታቸው በፌደሬሽኑ ላይ የሚታዩት ሁኔታዎች አሳስቧቸዋል፡፡
በሰብሳቢነት የሚመሩት የፌደሬሽኑ ዲሲፒሊን ኮሚቴ ከምርጫው ጋር በተያያዘ በፌደሬሽኑ አመራር የሚታዩ የሃላፊነት ክፍተቶችና የአመራር መጓደሎች  ተገቢውን ስራ ለማከናወን የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች አደናቅፏል የሚሉት አቶ ተፈራ፤ በፌደሬሽኑ የአመራሮች ምርጫ ዙርያ  ሽኩቻዎች መብዛታቸው የስፖርት ቤተሰቡን ከማሰላቸትም በላይ ስፖርቱን ወደ ኋላ መጎተታቸውን ያመለክታሉ፡፡ የስፖርቱ አስተዳደር በአገር ውስጥ በዓለም አቀፍ የስፖርት  ህገ ደንቦች የሚመራ በመሆኑ እንጂ  አገር የሚጎዱ፤ ስነ-ምግባር የጎደላቸው  እና በሃላፊነት የሚያስጠይቁ ጥፋቶች በስፋት እየታዩ ናቸው በማለትም የህግ ባለሙያው ስጋታቸውን ይገልፃሉ፡፡   
የፌዴሬሽኑ አመራሮች ምርጫ በአራት የተለያዩ ጊዜያት መራዘሙን በማስመልከት  አቶ ተፈራ ለስፖርት አድማስ አስተያየት ሲሰጡ ለጠቅላላ ጉባኤው መራዘም በአባላቱ፤ በተወዳዳሪዎችና፤ በአስመራጭ ኮሚቴው የሚሰጡ ምክንያቶች የአገሪቱን ስፖርት ማዕከል ያደረጉ ናቸው ብዬ አላምንም ብለው  ከግል አጀንዳዎች መያያዛቸው ደግሞ የሚያሳዝን ነው መሆኑን በቁጭት ይናገራሉ፡፡  በፌደሬሽኑ አመራሮች ምርጫ ላይ ፊፋ ይገኝ አይገኝ የሚለው ሀሳብ ሽፋን ነው እንጂ የጭቅጭቁና ንትርኩ ዋና ምክንያት ማሸነፍ አለብኝ  የሚል የግል አጀንዳ ነው በማለትም ባለድርሻ አካላት አገሪቷን የሚያገለግሉ አመራሮችን ለመምረጥ ከመንቀሳቀስ ይልቅ በተወዳዳሪዎች ተፅዕኖ ስር በወደቀ አቅጣጫ ማዘንበላቸውን ወቅሰዋል፡፡
 ከምርጫው በተያያዘ የተነሱ የውዝግብ አጀንዳዎች እግር ኳሱን ወዳልተፈለገ አዘቅት እያወረዱት ናቸው የሚሉት አቶ ተፈራ፤  መንግሥት የተፈጠሩትን ችግሮች ከዳር ሆኖ  መመልከት እንደማኖርበት ፊፋን በማማከር የአገሪቱን ስፖርት ከጉዳት መታደግ የሚችልበትን ስትራቴጂ በመቀየስ እንዲሰራም ጥሪ ያቀርባሉ፡፡ ፊፋ በመጋቢት ወር መጥቶ ግምገማ ሲያካሂድ ሁሉም ነገሮች ተስተካክለው ካላገኛቸው  መፍትሄ ለማፈላለግ በሚል “ኖርማላይዜሽን” ኮሚቴ እንዲቋቋም ሊወስን ይችላል። ይህ ደግሞ የብሔራዊ ቡድንና የክለብ ውድድሮችን የሚጎዳ ከፊፋ እና ከካፍ ጋር የሚኖረውን መልካም ግንኙነትም የሚያጎድፍ ነው፡፡
በስፖርት ውስጥ ተመርጦ፤ በምርጫና ከምርጫ ውጪ ሆኖ ያጠፋና ህገ ወጥ ስራ የሰራ ይቀጣል የሚል ግልፅ ወይም የተብራራ ህገ ደንብ አለመኖሩ እንደሚያሳስባቸው የሚያስረዱት የህግ ባለሙያው፤ ስለሆነም አመራሮች በያዙት ኃላፊነት ሁሉ ተጠያቂ የሚሆኑበት፤ በሚያደርሷቸው ጥፋቶች በመደበኛው ህግ የሚቀጡበት የህግ ስርዓት እንዲዘረጋም ያመለክታሉ፡፡  በአገሪቱ ስፖርት በተለይም በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ደንብ ላይ እንዲህ አይነት መጓተቶችና ውዝግቦች በሚያደርሱት ጥፋት ልክ የሚጠየቁበት ሁኔታም የለም ፡፡በአጠቃላይ በስፖርቱ ጥፋት ለሚያደርሱ አካላት ሊጠየቁበት የሚያስችል የፍትሐብሔር ወይንም የወንጀል ኃላፊነት አልተለመደም፡፡ በተያያዥ ህጎች ላይ መላላት ይስተዋላል ይህም መቀየር አለበት መስራት የሚገባቸው ሳይሰሩ የሚያልፉ፣ መሰራት የነበረበትን  የሚያጓትቱና በስፖርቱ ላይ ጥፋት የሚያደርሱ ሁሉ በህግ መጠየቅ አለባቸው ነው-የህግ ባለሙያ ምክር፡፡

የዓለም ዋንጫ ጉብኝት እና ደብዛዛው ኳሳችን
ልክ የዛሬ ሳምንት የዓለም ዋንጫ አዲስ አበባ ስትገባ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል ካደረጉላት የስፖርት አመራሮች መካከል የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩ እርስቱ ይርዳ፤ የኦሎምፒክ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ እና የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ ይገኙበታል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ደግሞ የዓለም ዋንጫዋን በኢዮቤልዩ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ተረክበው ወደላይ ባነሱበት ስነስርዓት ዋንጫው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣቱ መደሰታቸውና በሕዝቡ ስም ፊፋን እንደሚያመሰግኑ ተናግረው ወጣቱና እግር ኳስ አፍቃሪያን የሚነሳሱበት አጋጣሚ ነው ብለዋል። የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ እርስቱ ይርዳ  የዓለም ዋንጫ ሕዝቦችን በአንድ ሜዳ ላይ ያስተሳሰረ ትልቅ ሽልማት መሆኑን ሲናገሩ፤ አቶ ጁነዲን ባሻ በበኩላቸው ለዋንጫው መምጣት  ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን መሥራችነት የነበራት ሚናና በስፖርቱ መስፋፋት የደጋፊዎች ብዛት በሂደት እያደገ መሆኑ አስተዋፅኦ እንደነበራቸው አውስተዋል፡፡
የዓለም ዋንጫዋ በብሄራዊ እዮቤልዩ ቤተመንግስት ከተደረገላት አቀባበል በኋላ በማግስቱ በሂልተን ሆቴል ለህዝብ ጉበኝት የቀረበች ሲሆን ከ3ሺ በላይ ስፖርት አፍቃሪዎች በዕይታና በፎቶ መነሳት ታድመዋታል፡፡
የዓለም ዋንጫዋ ኢትዮጵያን ስትጎበኝ በስምንት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የባለፈው ሰሞን ለሁለተኛ ጊዜ ነበር፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች የብሄራዊ ቡድኖች የወረደ አቋም፤ የሊግ ውድድር አለመጠናከር፤ የአመራሮች ውዝግብና ድክመት የእግር ኳስ ደረጃውን ማደብዘዙ በዓለም ዋንጫ ጉብኝት መሆኑ ሊፈጠር የሚችለውን መነቃቃት አጉድሎታል፡፡ ቢያንስ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 30፤40ና 50 ዓመታ ለዓለም ዋንጫ ታልፋለች የሚሉ እቅዶችን ባለድርሻ አካላት በልበሙሉነት መናገር ነበረባቸው፡፡

6ኛውን ቻን ለማዘጋጀት ይቻላል፤ ወይስ አይቻልም…
 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕን በ2020 እኤአ ላይ ለማስተናገድ ከካፍ ባንዲራን ከተቀበለ ወር ሊሞላ ቢሆንም በይፋ ዝግጅቱን አለመጀሩ የሚያሳስብ ነው፡፡ ከወር በፊት 5ኛው ቻን በሞሮኮ አዘጋጅነት እና ሻምፒዮናነት ሲፈፀም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንና የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር የአዘጋጅነቱን ባንዲራ ከካፍ መረከባቸው የሚታወስ ነበር፡፡ ፌደሬሽኑ በኢትዮጵያ ፌደራሊዊ ዳሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ መንግስት ሙሉ ድጋፍ 6ኛውን ቻን ለማዘጋጀት እንደሚቻል ተስፋ ማረጋቸውን አቶ ጁነዲን ባሻ በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡ ይሁንና የሻምፒዮናው መስተንግዶ  በቀረው የ19 ወራት ጊዜ ስታዬሞችን በተሟላና ዙርያ ገብ አቅም በማዘጋጀት፤ ብሄራዊ ኮሚቴ በማቋቋም፤ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር፤ የስፖንሰርሺፕ ድጋፎችን በማፅደቅ እንዲሁም የውድድሩን ሎጎ፤ መርህና ሌሎች ማስተዋወቂያዎችን ለመስራት በቂ እንደማይሆን  ከአየቅጣጫው  እየተገለፀ ነው፡፡  ኢትዮጵያ የውድድሩን የመስተንግዶ እድል በካፍ ውሳኔ ካገኘችበት ወዲህ እንቅስቃሴዎች ቢጀመሩ ኖሮ ሁሉንም ተግባራት  በበቂ ዝግጅት ለማከናወን በታቸለ ነበር፡፡ ይሁንና ባለፉት 6 ወራት በፌደሬሽኑ አስተዳደርና የአመራሮች ምርጫ ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ውዝግቦችና ትርምሶች ብዙ ወራት ያለስራ እንዲያልፉ ምክንያት ሆኗል፡፡
ፌደሬሽኑ ቻን 2020ን ለማስተናገድ ለካፍ ሲያመለክት ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ሶስት የአፍሪካ ዋንጫዎችን በብቃት ማስተናገድዋን ከመጥቀሱም በላይ ባለፉት አምስት ዓመታት እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ሆኖባቸው በየክልሉ የተገነቡ ስታድዬሞች ዝግጅቱን የተሳካ እንደሚያደርጉት በርግጠኛነት ገልፆ ነበር፡፡
አሁን በፌደሬሽኑ አካባቢ በሚስተዋለው ሁኔታ ለቻን 2020 ብሄራዊ ኮሚቴ በማቋቋም ኦፊሴላዊ ሎጎ በማስተዋወቅ፤ ባለድርሻ አካላትን በስፖንሰርሺፕ እና በተለያዩ ድጋፎች በማስተባበበር ስራውን መጀመር የሚቻል አይመስልም፡፡ ምናልባትም እነዚህ ቁልፍ ተግባራት የሚጀመሩት ከ3 እና 4 ወራት በኋላ ሊሆን ይችላል፡፡  ቻን 2020ን በተሟላ የዝግጅት አቅምና ብቃት ለማስተናገድ የካፍን የአህጉራዊ ሻምፒዮና የአዘጋጅ አገር መስፈርቶችን በማጥናት መስራት የሚጠበቅ ቢሆንም በዚህም ረገድ ጎላ ያሉ ጥረቶች እየተስተዋሉም አይደለም። ይህም በፌደሬሽኑ ላይ በቂ መተማመን ለማግኘት የሚቻልበትን ሁኔታ አዳጋች አድርጎታል፡፡
የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፑን ለማዘጋጀት ከካፍ እና ከውድድሩ አብይ ስፖንሰር ከሚገኙ የበጀት ድጋፎች ባሻገር አዘጋጅ አገር ብዙ ሊያሟላቸው የሚገቡ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ይሁንና ምንም አይነት እንቅስቃሴ የማይታይ በመሆኑ ለበርካታ ቅድመ ዝግጅቶች ከየአቅጣጫ ፈተናዎች የሚያጋጥሙ ይመስላል፡፡  የመጀመርያው ፈተና የተሳታፊ አገራትን መስተንግዶ ለማከናወን  እስከ 200 ሚሊዮን ብር ማስፈለጉና ይህንንም በብሄራዊ ደረጃ በተቋቋመ ኮሚቴ ለማስፈፀም ጅምር ስራዎች አለመኖራቸው የሚፈጥረው መጓተት ነው፡፡ በሌላ በኩል ውድድሩን የሚያስተናግዱ አራት እና 5 ስታድዬሞች የካፍን መስፈርት አሟልተው በወቅቱ ስለመድረሳቸው ማረጋገጫ ለማግኘት መክበዱ ነው፡፡ በክልል የሚገኙት አዳዲስ ስታዬሞች የሃዋሳ፤ የባርዳር፤ የመቀሌ ስታድዬሞች ሙሉለሙሉ ግንባታቸው የተጠናቀቁ አይደለም፡፡ ግንባታው መቶ በመቶ ያለቀው የወልዲያ ስታድዬምም ቢሆን በሆቴልና በመንገድ መሰረተልማቶች ያልታጀበ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በአጠቃላይ ቻንን ለማስተናገድ ሁሉም ስታድዬሞች በውስጣቸው ተገቢውን የተመልካች መቀመጫ፤ የድምፅና የብርሃን ግብዓቶች፤ የሚዲያ ትሪቢውን፤ በዙርያቸው የልምምድ ሜዳዎች አሟልተው ውድድሩ ከመጀመሩ 3 ወራት በፊት በካፍ የእውቅና ማረጋገጫ ሊሰጣቸው ያስፈልጋል። በተጨማሪም ስታድዬሞቹ ለሆቴል፤ለትራንስፖርት ቅርብ እና የተመቹ የፀጥታና ደህንንት ማስተማመኛ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በተጨማሪ የመክፈቻና የመዝጊያ ጨዋታዎችን ያስተናግዳል ተብሎ የሚጠበቀውና ከ63ሺ በላይ ተመልካች የሚያስተናግደው የአዲስ አበባው አደይ አበባ ስታድዬም በወቅቱ ስለመድረሱ ማረጋገጫ አለመገኘቱም የሚያስጨንቅ ነው፡፡ የአደይ አበባ ስታድዬም ግንባታ ከተጀመረ ከ24 ወራት በላይ ሲሆነው 65 በመቶ መጠናቀቁ ቢገለፅም በሚቀጥለው አንድ ዓመት መጨረሱ ያጠያይቃል፡፡
የአፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ሻምፒዮንሺፕን የማዘጋጃ ህገ ደንቦች በካፍ ድረገፅ በይፋ የተለቀቀ ሲሆን፤ በ47 ምዕራፎች፤ በ107 ድንጋጌዎች በ42 ገፆች የተዘጋጀ ነው፡፡ ለአዘጋጅ አገር ብዙ ማሳሰቢያዎች ባሉበት ይህ ሰነድ ኢትዮጵያ ለቻን 2020 ገና ብዙ እንደሚቀራት መገንዘብ ይቻላል፡፡ በተያያዘ ፌደሬሽኑ ለቻን ዝግጅት ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት በተደጋጋሚ ቢያንፀባርቅም በአመራሮች ምርጫ የተፈጠሩ ውዝግቦች ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በፍጥነት ለመስራት አያስችልም። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቻን 2020ን የማስተናገድ እድል የሚታዩት መቀዛቀዞች በኬንያ ላይ የደረሰውን እጣ ዳግም እንዳይፈጥር የሚያሰጋ ይሆናል፡፡ በ2018 እኤአ ላይ ከሩዋንዳ በኋላ ሁለተኛዋ የቻን አዘጋጅ የምስራቅ አፍሪካ አገር ኬንያ ትሆን ነበር፡፡   የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ግን የኬንያን መስተንግዶ በመንጠቅ ለሰሜን አፍሪካዋ ሞሮኮ አዘጋጅነቱን ምትክ አድርጎ ሰጥቷታል፡፡ በወቅቱ ካፍ በልዩ ካቢኔ ኬንያ ለመስተንግዶ የምታደርገው ዝግጅት በቂ ፍጥነት የለውም የሚል ምክንያት በማቅረብ አስቸኳይ ውሳኔ  ማሳለፉ የሚታወስ ነበር፡፡
በየአገራቱ ሊጎች የሚጫወቱ ተጨዋቾችን በሚያሰልፉ ብሄራዊ ቡድኖች  የሚደረገው ቻን የየአገራቱን ሊጎች ለማጠናከር፤ የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ፍልሰትን ለመከላከል፤ እንዲሁም አገራት ውድድሩን በማዘጋጀት የስፖርት መሰረተልማቶቻቸውን እንዲያጠናክሩ በማገዝ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ ከ2014 እኤአ ወዲህ የቻን ግጥሚያዎች በፊፋ እውቅና በማግኘት ነጥብ የሚሰጣቸው መሆኑና ለእግር ኳስ ደረጃ መሻሻል አስተዋፅኦ ማድረጉ የሚጠቀሱ ይሆናል፡፡
ቻን በየጊዜው በአዘጋጅ አገራት መዘናገት፤ ለተሳትፎ በቂ ትኩረት ባለመሰጠት ቢንገዳገድም ከ2016 እኤአ አንስቶ እስከ 2024 እኤአ ድረስ በፈረንሳዩ የነዳጅ ኩባንያ ቶታል አብይ ስፖንሰርነት መደገፉ የውድድሩን ህልውና ታድጎታል፡፡ የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕን በ2009 እኤአ ላይ ኮትዲቯር፤ በ2011 እኤአ ላይ ሱዳን፤ በ2014 እኤአ ላይ ደቡብ አፍሪካ፤ በ2016 እኤአ ላይ ሩዋንዳ እንዲሁም በ2018 ኬንያ  በመተካት ሞሮኮ እንዳዘጋጇቸው ይታወቃል፡፡

Read 6136 times