Print this page
Sunday, 25 February 2018 00:00

ጥቁሮች የነገሱበት “ብላክ ፓንተር” ፊልም ታሪክ እየሰራ ነው

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ባሳለፍነው ሳምንት በይፋ ተመርቆ የወጣውና አፍሪካዊ ፊልም ባህር የመሻገር ብቃት የለውም የሚለውን አመለካከት እንዳከሸፈ የተነገረለት “ብላክ ፓንተር” ፊልም፣ ገና ለእይታ በበቃ በአራት ቀናት ውስጥ ብቻ 241.9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ በዚህ ገቢውም ከ”ስታር ዎርስ” ቀጥሎ በመቀመጥ ታሪክ ሰርቷል፡፡
ወንጀልን ለመታገል ቆርጦ በተነሳ የአንዲት ምናባዊ የመካከለኛው አፍሪካ አገር መሪ የስኬት ጉዞ ላይ የሚያጠነጥነውና በጥቁሩ ዳይሬክተር ሪያን ኮግለር የተሰራው “ብላክ ፓንተር”፤ ለእይታ በበቃ በቀናት እድሜ ውስጥ በርካታ የቦክስ ኦፊስ ክብረ-ወሰኖችን መሰባበሩን ተያይዞታል፡፡ ባለፈው ሳምንት ብቻ በትዊተር ማህበራዊ ድረገጽ ከ5 ሚሊዮን በላይ ፊልሙን የተመለከቱ ጽሁፎችና መልዕክቶች የተሰራጩለት ፊልሙ፤ በአለማችን ታሪክ በትዊተር እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተጠቃሚዎችን  ያነጋገረ ቀዳሚው ፊልም ሆኗል፡፡
ፊልሙ ከአሜሪካ የቦክስ ኦፊስ የደረጃ ሰንጠረዥ በተጨማሪ በእንግሊዝ፣ አየርላንድ፣ ቻይና፣ ሩስያ፣ ጃፓንና ሌሎች በርካታ የአለማችን አገራት የፊልሞች ገበያና የገቢ የደረጃ ሰንጠረዦች የሚደንቅ ክብረ ወሰን እየጨበጠ እንደሚገኝ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ በሆሊውድ መንደር ባልተለመደ ሁኔታ አፍሪካውያንን ባለስኬት ጀግኖች አድርጎ የሚያሳየው ይህ ፊልም፣ የቀድሞዋ የአሜሪካ ቀዳማዊት አመቤት ሚሼል ኦባማን ጨምሮ አለማቀፍ ዝነኞች በአደባባይ አድናቆታቸውን እየቸሩት ነው ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
“ብላክ ፓንተር” 200 ሚሊዮን ዶላር ያህል ወጪ እንደተደረገበት የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፤ በታሪክ ከፍተኛው በጀት የተመደበለት በጥቁር ጀግኖች ዙሪያ የሚያጠነጥንና በአብዛኛው ጥቁር የፊልም ባለሙያዎችን ያሳተፈ ቀዳሚው ፊልም እንደሆነ አመልክቷል፡፡

Read 2487 times
Administrator

Latest from Administrator