Saturday, 24 February 2018 12:25

የዘነበ ወላ መፅሐፍ ሲዳሰስ …

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   (ከሣህለ ሥላሴ ብርሃነ ማርያም)
          ርዕስ፡- መልህቅ
          ደራሲ፡- ዘነበ ወላ
        የሕትመት ዘመን፡- 2010 ዓ.ም
        የትረካ ሥፍራዎች፡ - ምጽዋ ፥ አስመራ ፥ አሰብ ፥ እና አዲስ አበባ በጨረፍታ
        የገጽ ብዛት፡- 448
        ዋጋ፡- 150 ብር


    ይህ መጽሐፍ ልብ ወለድ ነው እንዳንል ጥናት ላይ እንደተመሰረተ ጽሁፍ ዋቢ መጻህፍት ታክለውበታል፤ ያውም በአማርኛና በእንግሊዝኛ የተጻፉ በርካታ መጻሕፍትና ሌሎችም ምንጮች። በሌላ በኩል እውነተኛ ታሪክ ነው እንዳንል አቀራረቡ የታሪክ ሳይሆን የልብ ወለድ ድርሰት የአጻጻፍ ዘዴን ነው የተከተለው፡፡ ታዲያ የድርሰቱ ዓይነት ምንድነው ብለን እንመድበው? ምናልባት ከደራሲው ዘነበ ወላ ጋር በመስማማት፣ በልብ ወለድ መልክ የቀረበ እውነተኛ ሁነት ነው ብንል አያስኬድም ይሆን?
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተለመደው የልብ ወለድ አጻጻፍ ዘዴ ወጣ ያሉ ፥ የቤተ ሙከራ ዓይነት ጽሑፎች ብቅ ብቅ ማለት መጀመራቸውን እንገነዘባለን፡፡ ልብ ወለዶች ናቸው እንዳንል አጽመ ታሪክ የሌላቸው፤ በውቅር (“ፕሎት”) ወይም በምክንያትና ውጤት ላይ ያልተመሰረቱ፤ ላይ በላይ እንደ አሸዋ በተከመሩ ሁነቶች ላይ ብቻ የተገነቡ ጽሑፎች ከአንድም ሁለት በላይ መከሰታቸው ተስተውሏል፡፡ “መልህቅ” ከእነዚህ አፈንጋጭ መሰል ጽሑፎች አንዱ ይሁን ወይም አይሁን በእርግጠኝነት ለመናገር ያዳግታል፡፡
ለማንኛውም ይዘቱ በደርግ ዘመን (ሥርዓቱ ተንኮታኩቶ ከመውደቁ ቀደም ባሉት ሁለት ዓመታት) በአስራ አምስቱ ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ባህር ኃይል አካባቢ የነበረውን የሕይወት ሁኔታ አጉልቶ የሚያሳይ መጽሐፍ ነው፡፡ በባህር ኃይሉ የነበሩት የጦር መርከቦች ዓይነት፤ የባህረኞቹ (የአዛዦቹና የታዛዦቹ) የሕይወት ዘይቤ፤ የዕለት ተዕለት የተግባር እንቅስቃሴአቸው፤ የቅኝታቸው ጉዞና መልስ፤ የባህሩ መናወጥና መልሶ መርጋት፤ በተለይ በጉዞ ላይ የሚደርሱ ፈተናዎች፤ የየዕለቱ ምግብና መጠጥ፤ አልፎ አልፎ የሚከናወኑት የመዝናኛ ዝግጅቶች፤ የባህረኞች (በተለይም የወጣቶቹ) የወሲብና የፍቅር ሕይወት፤ የአብዮቱ ዘመን ይፈጥረው የነበረው ፍርሃትና ጭንቀት፤ አንዳንድ ባህረኞች ሥርዓቱን መሸከም አቅቷቸው ወደ ባዕድ አገር ለመሰደድ የሚያደርጉት ሙከራ፤ የተፈጥሮ አስደናቂ ክስተቶች፤ በተለይም የአንዳንድ አሳዎች፥ የየብስ ተንፏቃቂ ነፍሳትና አእዋፍ አስገራሚ የሥጋ ተራክቦና የሚከተለው የሕይወት ሕልፈት፤ የአሳዎች ዝርያዎች ዓይነትና ባህርያቸው፤ በአጠቃላይ በባህርና በየብስ የባህረኞችና የሌሎች ፍጡራን ሕይወት ምን እንደሚመስል ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ መጽሐፍ ነው - “መልህቅ”፡፡
ዘነበ ወላ በዚህ መጽሐፉ ከቀድሞዎቹ ሦስት መፅሐፎቹ (ህይወት በባህር ውስጥ ፥ ማስታወሻ ፥ እና ልጅነት) በበለጠ ደረጃ ጥንካሬ ያሳየው በገለጻ ኃይሉ ነው ብንል ሞጋች የሚነሳ አይመስለኝም፡፡ ዋቢ እንዲሆን ቀጥሎ ያለውን እንመልከት፤
“ወደ ራስ ዱሜራ ስንቀዝፍ ቀይ ባህር እንደ ራስ ዳሽን ተራራ ይከመራል፡፡ ጀልባችን ባህሩን በርቅሳው ለማለፍ ትጥራለች፡፡ ባህሩ አፍታም ሳይቆይ እንደሊማሊሞ ገደል ይናድና ቁልቁል ወደ መቀመቅ ጅው እንላለን፡፡ ከላይ ውሃ እንለብሳለን፤ ከስር ውሃ መቀመቅ ውስጥ እንሰጥማለን…” (ገጽ 10)
ተጨማሪ ምሳሌ ቢያስፈልግም እነሆ፤
“7,000 የፈረስ ጉልበት የሚያመነጨው የጀልባዋ ሞተር እንደ አንዳች ያጓራል፡፡ ማዕበሉን ሰንጥቆ ለማለፍ የጀልባዋ መቅዘፊያዎች እንደ አንዳች ይሽከረከራሉ፡፡ ባህሩ ተበርግዶ እልም ያለ ገደል ይፈጥራል፡፡ ጀልባዋን ሙሉ በሙሉ ይውጣትና መልሶ ተጉመጥምጦ እንደተፋት ሁሉ ባህሩ ደረት ላይ ትገኛለች፡፡ ቀይ ባህር ካለው ጥልቀትና ስፋት አኳያ 118 ቶን የሚከብደው የጀልባዋ አካል የቡሽን ያህል አትከብደውም፡፡ ከማዶ እንደ ጥቀርሻ የጠቆረ የባህር አካል ተንደርድሮ መጥቶ ይላተመዋል። እሷም እንደ ሰይፍ ሰንጥቃው ወደፊት ትመነጨቃለች፡፡ አንዳች ዓይነት የቁጣ፥ የመዓት ድምጽ በድፍን ባህሩ ላይ ያስተጋባል” (ገጽ 104)
የመጽሐፉ ባለታሪኮች በርካታ ናቸው። በይበልጥ ጎልተው የሚታዩት ግን ከወንዶቹ መሐከል ያሬድ ሐጎስ፥ ስንታየሁ፥ በብዙ ቦታ ባናየውም ሊረሳ የማይቻለው ሌናተናንት አሸናፊ ዋቅጅራ (የጀልባ 202 አዛዥ)፤ ከሴቶች መሐከል ደሞ ገነት አስገዶም፥ ዓወት ግርማይ ፥ እና ኮማሪቷ አበባ አድማሱ ይገኙባቸዋል፡፡ እነዚህ የመጽሐፉ ባለታሪኮች በገሐዱ ዓለም የነበሩ ይሁኑ ወይ ደሞ የፈጠራ ገጸ ባህሪያት ይሁኑ አንባቢው ለይቶ ለማወቅ ከቶም አይቻለውም፡፡ ነገር ግን የፈጠራ ታሪክ ገጸ ባህሪያት ከሆኑ በገሐዱ ዓለም ሞዴል እንዳላቸው ሊያጠራጥር አይችልም፤ ታሪኩ በእውነተኛ ሁነት ላይ የተመሰረተ ነው ስለተባለ፡፡
ለመሆኑ የመጽሐፉ ዓላማ ምንድነው? የገጸ ባህርያቱን ስሞች ስናጤን እያንዳንዳቸው ከየት ብሔረሰብ እንደፈለቁ ይጠቁሙናል፡፡ ከሁለት የተለያዩ ብሔረሰቦች የተፈጠሩም አሉ። ነገር ግን ሁሉም ለማለት ይቻላል እንደ ውሁድ ኢትዮጵያውያን ይተያያሉ እንጂ የብሔረሰብ ማንነታቸውን ከቁም ነገር ሲያስገቡ አናይም፡፡ ትንሽ ያፈነገጠ አመለካከት ያላቸው ቢኖሩ ከሰሜን ጫፍ በኩል ያሉት ብቻ ናቸው፡፡
በትረካው መጨረሻ አካባቢ ሌፍተናንት አሸናፊ ወደ ሱማሌ ከመኮብለሉ በፊት የፈጸመው ድርጊት አንባቢውን ግራ ያጋባዋል፡፡ መርከበኞቹ ከመርከቡ ዘልለው ወርደው ባህር ውስጥ እንዲገቡ ያዝዛቸዋል። እነሱም በዋና ነፍሳቸውን ለማዳን ሲጥሩ ይታያሉ፡ የሞቱት ሞተው የተቀሩት ይተርፋሉ፡፡ ግን የሌተናንት አሸናፊ ድርጊት ምን ትርጉም አለው? እነዚህ መርከበኞች በእሱ ስር ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ በደል ሰርተውበት እንደሆነ የተነገረ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ለከፋ አደጋ አጋልጧቸው መኮብለሉ ትርጉሙ ምንድን ነው? ነገሩ እንቆቅልሽ ይሆንብናል፡፡
የእነዚህ መርከበኞች ዕጣ ፈንታ ይህ ብቻ ቢሆን ኖሮ ቢያሳዝንም “መቼስ ምን ይደረጋል!” ተብሎ ሊታለፍ ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን በዚህ ጦስ ምክንያት ባልፈጸሙት ወንጀል ተከስሰው ለፍርድ ሲቀርቡ እናያለን፡፡ እነሱ የአዛዣቸው ሰለባ ከመሆን በስተቀር አንዳችም የፈጸሙት ወንጀል የለም፤ ያሬድ ሀጎስ ቀደም ብሎ ለመሰደድ ያደረገው ያልተሳካ ሙከራ እንዳለ ሆኖ፣ ታዲያ ለምንድነው ለፍርድ የቀረቡት? ምክንያቱን ለመረዳት አሁንም ከመጽሐፉ መጥቀስ ግድ ይላል፤
“የኢትዮጵያ አብዮተኞችም እንዲሁ ራሳቸውን ከወንጀል ለማጽዳት ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት የቀጠለውን የጦስ ፍየል መስዋዕት የማድረግና ማርከሻውን መፈክር አሰምቶ የማለፍ ልምድ፤ ዛሬ የጦስ ፍየል አራጁ የነገ ተረኛ እየሆነ ሞትን በቅብብሎሽ አኖሩት፡፡ ይህ የጦስ ፍየል ከምድር ጦር ፥ ከአየር ኃይል ፥ ከባህር ኃይል ፥ ከሲቪሉ ሕብረተሰብ እየታደነ የአብዮታዊያኑን ጦስና ጥንቡሳስ ይዞ ይገደልና በሟች ሬሳ ላይ መፈክር ይሰማል፡፡ ዛሬም ያሬድና ጓደኞቹ ባልሰሩት ወንጀል እንደ ወንጀለኛ ታፍነው ደህንነት ቢሮ በመገኘታቸው የጦስ ፍየል ሊያደርጓቸው መወሰኑ ወለል ብሎ ታየው፡፡” (ገጽ 440)
ስለ አስራ ሰባቱ ዓመታት የጨለማ ዘመን በርካታ ልብ ወለዶችና ኢ - ልብ ወለድ መጻሕፍት ከዚህ ቀደም ተጽፈዋል፤ የበዓሉ ግርማ “ኦሮማይ”፥ የአማኑኤል ሐዲስ “አስተኳሹ”፥ የባቢሌ ቶላ “የትውልድ ዕልቂት” (አውግቸው ተረፈ እንደተረጎመው) እና ሌሎችንም ለመጥቀስ ይቻላል። “መልህቅ” ከእነዚህ አንዱ መሆኑ ነው፡፡ የአብዮቱ ዘመን ታሪክ በእነዚህ ብቻ ሊወሰን የሚችልም አይደለም፡፡ አሳታሚ በማጣት በየጠረጴዛው ኪስ ውስጥ ተዘግቶባቸው የሚኖሩ ልብ ወለዶችና ኢ - ልብወለድ መጻሕፍት እንዳሉ በቀላሉ መገመት ይቻላል፡፡ ከድርጊቶቹ አስከፊነት የተነሳ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ወደፊት ከአምሳና መቶ አመታት በኋላም በታሪካዊ ልብ ወለድ መልክ ሌሎች በርካታ መጻሕፍት እንደሚዘጋጁ ለመገመት ነቢይ መሆን አያሻውም፡፡     

Read 2204 times