Sunday, 25 February 2018 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

   “ውሃ ባለበት ህይወት፣ ሰው ባለበት ስህተት …”
               
    ሰውየው ጠቢብ ነው ይባላል፡፡ አንድ ቀን የከተማዋ ትልቅ ሱቅ ባለቤት ወደ እርሱ መጥቶ …
“እባክህ ወደ ሌላ ከተማ ደርሼ እስክመለስ ንብረቴን ጠብቅልኝ” በማለት ለመነው፡፡ … “እንቢ፣ አይሆንም፣ አይደለም…” የሚሉ ቃላቶችን ከአፉ ለማውጣት የሚቸገረው ይኸ ቅን ሰው ትንሽ አሰበና ….
“እሽ”… በማለት ስለተስማማ ባለንብረቱ ወደ ጉዳዩ ሄደ፡፡ ሰውየውም በሱቁ ውስጥ የተከማቸውን ውድ ዕቃዎች፣ ጌጣ ጌጦች፣ ገንዘብና የመሳሰሉትን እየተዘዋወረ ሲመለከት አንዲት፣ የብረት ሳጥን ዓይኑን ሳበችው። ብድግ አድርጎ ሲያስተውላት ከውስጧ ድምፅና እንቅስቃሴ ተሰማው፡፡ እየተገረመ ክዳኗን ብድግ ሲያደርግ ቀይ እግር፣ አረንጓዴ ክንፎችና ቢጫ አፍ (bic) ያላት፣ ቆንጅዬ ወፍ ተፈትልካ በረረች፡፡
ከአግራሞቱ መለስ ሲል በአንድ በኩል የወፊቱን ነፃነት ባይቃወምም፣ በሌላ በኩል ግን እንዲጠብቅ አደራ የተሰጠውን ንብረት ለማየት በመፈለጉ፣ ተፀፀተ … በሀሳብ ተውጦም ሳለ ባለ ሱቁ በጣም የምታምር የመስተዋት ጎጆ (glass cage) አንጠልጥሎ ከተፍ አለ፡፡ … ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላም ሰውየው፤ …
“ወንድሜ ይቅርታ! ተሳስቼአለሁ” አለው፡፡ ባለ ሱቁም ቀልቡን ሁሉ የብረት ሳጥኗ ላይ አድርጎ፤
“ምነው? … ምን ሆነ?” … ብሎ ጠየቀው፡፡ የሰውየው ዓይኖች የብረት ሳጥኗ ላይ ማረፋቸውን ሲያስተውል፣ የተከሰተው ነገር ገባው፡፡ ወዲያውኑ ዕንባው ያለማቋረጥ መውረድ ጀመረ፡፡ አሰርቶ ያመጣው የመስታወት ጎጆም ከእጁ ወድቆ ተሰበረ፡፡ ሰውየውም በሁኔታው እያዘነ፤ “… በአጋጣሚ ነው የሆነው…” … እያለ ሊያስረዳውና ሊያፅናናው ሞከረ፡፡ ባለንብረቱ ግን፤
“በከተማው እንዳንተ ታማኝና ጨዋ ሰው የለም ብዬ አደራ ብተውልህ እዚህ ካከማቸኋቸው፣ ወርቅና ገንዘብ የበለጠ የምታወጣውን፣ ውድ ወፍ አስመለጥክብኝ” … እያለ፣ እራሱን ይዞ እዬዬውን ቀጠለ፡፡
“ና … ወደ ዳኛ እንሂድ” … በማለትም ሰውየውን እየጎተተ፣ ከከተማው ኃላፊ ዘንድ ወሰደው፡፡ …
ዳኛው፤ ከሳሽንም፣ ተከሳሽንም ያውቋቸዋል፡፡ ከሳሽን በሀብቱና ባካባቢው ባለው ተሰሚነት፣ ተከሳሽን ደግሞ “ሃሳቦቹና ድርጊቶቹ ከኛ ሃሳብና ውሎ ጋር የማይስማሙ ናቸው” እያሉ ያካባቢው አውደልዳዮች በሚያቀብሉት ወሬ!!
ዳኛው ክሱን ካዳመጡ በኋላ ሰውየው የተባለችውን ልዩ ወፍ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ፈልጎ ካላመጣ እንደሚሰቀል ፈርደውበት በቀጠሮና በዋስትና አሰናበቷቸው፡፡
ዓመት ሞላና የቀጠሮው ጊዜ ደረሰ፡፡ ከሳሽ፣ ተከሳሽ፣ ዳኛና የአካባቢው ሰዎች በአደባባይ ተገናኙ፡፡ …
ዳኛ፡- “እህሳ ተከሳሽ…? ወፊቱን አገኘሃት?”
ተከሳሽ፡- “አዎን አግኝቻታለሁ” አለ፡፡ … ያልታሰበ ነገር በመሆኑ ሁሉም ተንጫጩ፡፡ … የሰሙትን ማመን ያቃታቸው ዳኛ፤
“አገኘሁዋት አልክ?... እንዴት ሆኖ?” በማለት ጠየቁ።
“የወፍ ቋንቋ የሚችል መንገደኛ ገጥሞኝ፣ አስጠራኋትና ያዝኳት” … ሲል ተከሳሹ መልስ ሰጠ፡፡ በሰሙት ነገር ግራ የገባቸው ዳኛም፤ … “ለካስ በሰውየው ላይ ‹እብድ ነው› እየተባለ የሚወራው እውነት ነው” እያሉ፣ በውስጣቸው ፈገግ አሉና፡-
“ታዲያ … የት አኖርካት?” ከማለታቸው …. ሰውየው ፈጠን ብሎ ትንሽ የእንጨት ሳጥን ከጉያው አውጥቶ አቀበላቸው፡፡ … ዳኛውም … መጨረሻውን ለማየት የሚያስካካውን ተሰብሳቢ እየተቆጡ፣ የተቀበሉትን ሳጥን በጉጉት ከፈት ሲያደርጉ፣ ቆንጆይቱ ወፍ አፈተለከች፡፡ ዞራ ዞራ እዛው አካባቢ አረፈችና ትቁለጨለጭ ጀመር። ተሰብሳቢው እተተራመሰ ሊይዛት ቢሞክር አልቻለም፡፡ አመረረችና በረረች!!
ወዳጄ፡ የወፊቱን ነገር እንመለስበታለን፡፡ … የፍትህን፣ የተፈጥሯዊነትን ወይም የዕድልና የሰብዓዊነትን ትርጉም እንርሳ፡፡ … ተረት ስለሆነ!! ነገር ግን አንድ ጥያቄ ልብ በል፡፡ “ስህተት” ምንድነው?
እኔ እንደሚመስለኝ … ሰውና ስህተት አንድ ላየ ነው የተፈጠሩት፡፡ ስህተት ሰብዓዊ ባህርይ ነው፡፡ የመጀመሪያው ሰው፣ የመጀመሪያው ቤተሰብ ተሳስቷል። ሁለተኛውም ትውልድ (የአቤልና የቃየል) ተሳስቷል። ሶስተኛውም፣ አራተኛውም … አንተና እኔም … መጪውም ይሳሳታል፡፡ “ውሃ ባለበት ህይወት አለ” … እንደሚባለው፣ ሰው ባለበት ስህተት ያለ ይመስለኛል፡፡
ስህተት ጥፋት የሚሆነው ትምህርት ሊሆነን ካልቻለ ነው፡፡ ስህተት የሚከፋው ሲደገም ነው፡፡ ከቶስ የማይሳሳት ማን አለ? … ከስህተት የምንማረው ጠቃሚና የማይረሳ ትምህርት ነው ይላሉ አዋቂዎች፡፡ … ከስህተቱ የማይማር ፈንጂ አምካኝ ብቻ ነው … የሚባለውም ያለ ነገር አይደለም፡፡ እዛ ጋ … ‹ተሳሳተ› ማለት ‹ሞተ› ማለት ሊሆን ይችላልና!! የሚማርበት፣ የሚታረምበት ዕድል ባለመኖሩ ያሳዝናል፡፡
ሊቃውንቶች፤ “አንዴ ከመናገርህ በፊት ሁለት ጊዜ አስብ፣ አስር ጊዜ ለክተህ፣ አንድ ጊዜ ቁረጥ” ሲሉ … “መልሰህ የምታቃናበት ዕድል የለም፡፡ ቢኖርም ትንሽ ነው ተጠንቀቅ” ለማለት ይመስለኛል፡፡
አንዳንድ ጊዜ ያንተ ስህተት አንተን ብቻ ሊጎዳና ሊያልፍ ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ አንተንም ሌሎችንም ይጨምራል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አንተን ጎድቶ፣ ሌሎችን ሊጠቅም ይችላል፡፡ የስህተት ገፁ ብዙ ነው። ስህተት አልፎ አልፎ ፍትህ የሚሆንበት አጋጣሚም አለ። እስኪ እነዚህን ዓረፍተ ነገሮች ልብ በል፡፡
`Kill him, not leave him`
`Kill him not, leave him`
አንዲት ኮማ የተከተበችበት ቦታ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ሆኗል፡፡ ካልተሳሳትኩ ‹ዛዲግ ወይም ዕድል› በተባለው የሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ መጽሐፍ ውስጥ ባለታሪኩን ለማስገደል በገዛ እጁ የተላከው ማስታወሻ ላይ ኮማዋ በስህተት በሁለተኛው ዓረፍተ ነገር ላይ እንደተከተበችው ሆና በመጻፏ ምስኪኑ ሰው ተርፏል፡፡ በሌላ ታሪክ ላይ ደግሞ እንደ መጀመሪያው ዓረፍተ ነገር በመከተቧ የማይመለከተው ሰው (innocent victim) እንዲሰናበት ሆኗል፡፡
ወዳጄ፡- ሰው ለመመረዝ የተቀመመ መርዝ፤ ጠንሳሹን ሲመርዝ፣ ለባላንጣ የተቀባበለ መሳሪያ ባለቤቱን ሲገድል፣ ለሰው የቆፈሩት ጉድጓድ ለራስ መቀበሪያ የሆነበትን አጋጣሚ በኑሮም፣ በሲኒማም፣ በቴአትርም አይተናል፡፡ … ሰምተናል፡፡ … “ስራ ለሰሪው፣ እሾህ ላጣሪው፤ ደባ ራሱን፣ ስለት ድጉሱን” እንደሚባለው!!
ወደ ወፋችን ስንመለስ፡- ሰው ለመርዳት በመፈለጉ የተፈረደበት ተከሳሽ፤ አስተዋይ እንደነበር አንብበናል፡፡ በአስተዋይነቱም ጥቂት ወዳጆች ቢኖሩትም እሱ ባለበት ‹ትንሽ› የሆኑ የሚመስላቸው፤ የማይመቻቸው የከተማዋ አውደልዳዮች ደግሞ ነበሩ፡፡
እነዚህ ግለሰቦች አጋጣሚውን ተጠቅመው፣ ተከሳሹን ለመጉዳት፣ ከሳሽ ክሱን እንዳያነሳ በመጫናቸው፤ በመጨረሻው የፍርድ ውሳኔ … “ጥፋቱ የከሳሽ የራሱ ነው፣ ይህንንም በራሴ ደርሶ (ለሁለተኛ ጊዜ ወፊቱ የበረረችበትን አጋጣሚ ማለት ነው) አይቻለሁ” … በማለት ዳኛው በተከሳሽ ቦታ ከሳሽ እንዲቀጣና እንዲክስ ፈርደዋል፡፡
በነገራችን ላይ ወዳጄ፡- ተከሳሽ ወፊቱን አስጠርቶ አልያዛትም፡፡ የዳኛውን ኢ-ፍትሃዊነት እንዳወቀ ትንሽ የወፍ ጫጩት አምጥቶ በሚስጢር አሳደገ፡፡ የቀጠሮው ጊዜ እንደቀረበም አፏን፤ ክንፎቿንና እግሯን በቀለም አስውቦ፣ የመጀመሪያዋን ወፍ አስመሰላት። ችሎት በታየችበት ጊዜም ማም አልተጠራጠረም፡፡ በሀሳቡ ግዝፈት ወፏንም ራሱንም ነፃ በማድረግ ፍርዱን ገልብጦታል፡፡
ወዳጄ፡- ስህተት ሰብዓዊ ባህርይ ነው ብለን ነበር። ስህተትን ጥፋት የምናደርገው ግን እኛ ነን!! … ለማንኛውም “ከሳሽ የተከሳሽን መልስ ቢያውቅ ኖሮ አርፎ ይቀመጥ ነበር” የሚባለው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡
ሠላም!!

Read 4214 times