Sunday, 25 February 2018 00:00

አማላይዋ! (The Neighbor ፊልም

Written by  ኢ.ካ
Rate this item
(7 votes)

 በእነ ማይክ ግቢ መናፈሻ ውስጥ በተሰናዳው የባርቢኪው (የሽቦ ጥብሳ ጥብስ) ዝግጅት ላይ ነባር  ወዳጆችና ባልንጀሮች ተሰይመዋል፡፡ በቅርቡ የተንጣለለውን መኖርያ ቤት ገዝተው፣ የእነ ማይክ ጎረቤት ለመሆን የበቁት ወጣት ጥንዶችም  እንኳን አልቀሩም - ቴድና ጄና፡፡ ገና የቤት እቃቸውን አስጭነው የመጡ ዕለት ነበር ማይክ የጋበዛቸው፡፡
ሁሉም ቦታ ቦታቸውን ይዘው፣ ቢራና የወይን ጠጃቸውን እየተጎነጩ  ያውካካሉ፡፡ ማይክና ሚስቱ፤ እንግዶቻቸውን በተቻላቸው አቅም  ለማስደሰት ተፍ ተፍ ማለት ይዘዋል፡፡ በተለይ  ማይክ፣ የተለያዩ የስጋ ዘሮችን (ሀምበርገር፣ሶሴጅ፣ወዘተ--) በቁም ምድጃው ላይ የመጠባበስ ከባድ ሃላፊነቱን በትጋት  እየተወጣ ነው፡፡
 ከሚሸተው የባርቢኪው ጥብሳ ጥብስ  ቀድሞ  ለመቅመስ የተጣደፈው ቴድ፣ ሚስቱ ሄዳ ታመጣለት ዘንድ ይጠይቃታል - በፍቅር በተጠቀለለ ትህትና፡፡  ጄና ከተቀመጠችበት ከመቅጽበት ተነስታ፣ ወደ ማይክ  ታመራለች - የባለቤቷን ፍላጎት ለማሟላት፡፡ ማይክ ግን የባርቢኪው ጥብስ ብቻ ሰጥቶ አይሸኛትም፡፡ ለትውውቅ  የሚሆን ጥያቄ ይጠይቃታል፡፡  
“ከተጋባችሁ ምን ያህል ጊዜ ሆናችሁ?”  
“አራት ወራችን ነው፤ ግን ከዚያ በፊት አብረን ብዙ ጊዜ ቆይተናል”
ጄናም ትቀጥላለች፡፡ የሞቀ ፈገግታዋን እየረጨች፡፡     
“ማይክ፤የመናፈሻ ሥፍራውን ብታየው ትርምስምሱ የወጣ  ነው፤ የትኛውን ማስወገድና  የትኛውን መተው እንዳለብኝ አላውቅም፤አንዴ ብቅ ብለህ ምክር ልትለግሰኝ ትችላለህ ?”
“እችላለሁ፤ችግር የለም !” ይላታል፤ትክ ብሎ እየተመለከታት፡፡
“ግን ምንድን ነው ሥራህ?” ጄና ትጠይቀዋለች።
“የቴክኒካዊ ጉዳዮች ጸሃፊ ነኝ፤ከቤቴ ሆኜ ነው የምሰራው”
ጄና ከማይክ ጋ የጀመረችውን ጭውውት አቋርጣ ለመሄድ የምትገደደው፣ ባለቤቷ ሲጠራት ነው፡፡ የማይክን ትከሻ በእጇ መታ አድርጋና አመስግና ወደ ቴድ  ትበራለች - ሃምበርገሩን ይዛ። ማይክ ደግሞ ማራኪ የልጅ ቁመናዋን ከኋላዋ በዓይኑ ይከተላል፡፡ ባለቤቷ ከንፈሯ ላይ ሲስማት ግን በንዴት ስሜት ዓይኑን ይነቅላል፡፡  
አንድ ምሽት እንደተለመደው፣ እንደ ቢሮ ከሚጠቀምበት የመኖርያ ቤቱ ክፍል ውስጥ ተቀምጦ፣ላፕቶፑ ላይ ሥራውን ይከውናል - ማይክ። በመሃል ግን  ዓይኖቹ  በሻተር መስኮቱ በኩል ተሻግረው፣ አዲሶቹ ጎረቤቶቹ ቤት  ዘው ይላሉ - በከፊል በተገለጠው መጋረጃ፡፡ ቴድ ሚስቱን እያሻሸ፣ ልብሷን ሲያወልቅላት ነው የሚመለከተው። በከፊል የተገለጠው መጋረጃ ሲሸፈን ግን ለአፍታ ልቡን ያንጠለጠለው አጓጊ ትዕይንት ይቋጫል። ማይክም ከሥራው ተናጥቦ፣ ወደ መኝታ ክፍሉ ያመራል፡፡ ሚስቱ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወስዷታል። እንደ ምንም ደባብሶ ይቀሰቅሳታል፡፡ ግን ምን እንደፈለገ እንኳን ሳይጠይቅ  ቅስም የሚሰብር ምላሽ ትሰጠዋለች፡፡ “ዛሬ ደክሞኛል፤ተወኝ” ብላ ወደ እንቅልፉ ትመለሳለች፡፡  የጋለ ስሜቱን አዳፍኖ፣ ጀርባውን ሰጥቷት  ይተኛል - በመካከለኛ ዕድሜው ላይ የሚገኘው ማይክ፡፡
ሁሌም ጠዋትና ማታ፣ በሻተር መስኮቱ በኩል ወደ ጎረቤቶቹ  ግቢ አሻግሮ መመልከት ሱስ የሆነበት ይመስላል፡፡ ዓይኑ አጥብቆ ለማየት የሚሻው ደግሞ ሌላ ማንንም ሳይሆን አማላይዋን ወጣት ነው - የቤቱን እማወራ  ጄናን፡፡ የዚያኑ ሰሞን የዘወትር ምሱን  ሊያደርስ በመስኮቱ በኩል ዓይኖቹን ሲልክ የተመኘው  ይገጥመዋል። ጄና የውስጥ ሱሪ የመሰለች  ቁምጣ ታጥቃ፣ የመናፈሻውን  አበቦች ቆማ ትመለከታለች፡፡ ማይክ ጊዜ አላባከነም። ከመቅጽበት ነጠላ ጫማውን ቀይሮ ከቤቱ ይወጣል።    
“ጎረቤቴ! እንዴት ነሽ?” ይላታል፤በፍጥነት አጠገቧ ደርሶ፡፡
አጸፋውን በሞቀ ፈገግታ ትመልስለታለች። የእሱን መምጣት በጉጉት የምትጠባበቅ  ነበር  የምትመስለው፡፡ ወፍ ዘራሽ የሚመስሉትን  አበቦችና ዕጽዋት እንዴት ደርዝ ማስያዝ እንደሚቻል፣ በውብ አገላለጽ ይነግራታል፡፡ በልምዱና በማብራሪያው ትመሰጣለች፡፡ በአነጋገር ለዛውም ጭምር፡፡ የግል ህይወቱን የተመለከተ ጥያቄም ታነሳበታለች፡፡    
“ልጆች የሉህም እንዴ?”
“ወንድ ልጅ አለኝ ፤አሌክስ ይባላል”
“አሌክስ?!”
“አዎ፤ ምናልባት አንቺን ሳያክል አይቀርም”
ማይክና ጄና በተገናኙ ቁጥር የሚያወጉት አያጡም፡፡ ጄና ተፈጥሮ የቸራትን እንደ ጸሃይ የሚሞቅ ፈገግታ ሳትሰስት ከመለገስ ወደ ኋላ ብላ አታውቅም፡፡ ማይክም ይሄን የተፈጥሮ ጸጋዋን በልቡ ከማድነቅና በግላጭ ከመፍዘዝ ተቆጥቦ አያውቅም፡፡ ይሄ ሁኔታቸው ግን ወዴት ሊያመራ እንደሚችል  ከፈጣሪ በቀር ማንም የሚያውቀው አይመስልም፡፡ ህይወት እንደ ወትሮው ቀጥላለች፡፡  
የማይክና ባለቤቱ ብቸኛ ልጅ የሆነው አሌክስ፣ ከኮሌጅ  ለዕረፍት በመምጣቱ የተደሰተችው እናቱ ብቻ ነበረች፡፡  ገና ከመምጣቱ ከአዲሶቹ ጎረቤቶች ጋር አርቦሽ ሆኖ፣ በነጋ በጠባ ቁጥር ወደነሱ ቤት መመላለሱ ማይክን አላስደሰተውም፡፡  የገዛ ልጁ የማይጋፋው ባላንጣው እንዳይሆንበት ክፉኛ ሰግቷል፡፡ ጭንቅ ጥብብ ቢለው ለባለቤቱ በዘዴ ስሞታ ያቀርባል፡፡
“አሌክስ፤ ጎረቤታችን ቤት እግር ማብዛቱን አልወደድኩትም፤ አየሽ ልጅቷ ወጣት ስለሆነች ከባሏ ጋር እንዳይጋጭ እሰጋለሁ”
እውነቱ ግን ሌላ ነው፡፡ ማይክ አፍ አውጥቶ ባይናገረውም ቅናት ቢጤ ጀማምሮታል፡፡ የገዛ ልጁ፣ ጄናን በፍቅር እንዳያጠምድበት ፈርቷል፡፡  
“ተወው ወጣት ነው ይዝናና፤ለራሱ የሚበጀውን ራሱ ይወስን” ትለዋለች- ውድ ሚስቱ፡፡  
እንዲያም ሆኖ ግን ማይክ፣ ሰበብ እየፈለገ፣ ወደ ጄና ጎራ ብሎ፣ “ጎረቤቴ፤እንዴት ነሽ?” ከማለት አልተቆጠበም፡፡ በየአጋጣሚው በሚያደርጉት ጭውውትም፣ የ4 ወራት ዕድሜ ያስቆጠረው የጥንዶቹ ትዳር፣በችግር የታጀበ እንደሆነ ይገነዘባል። ይሄ ደግሞ ይበልጥ ቅርርቦሹን ለማጥበቅ  የልብ ልብ የሰጠው ይመስላል፡፡   
አንድ ቀን ማይክ የግቢውን  ፍራፍሬዎች እየተዘዋወረ ይመለከታል፡፡ ልቡ ግን ጄና ጋ ነበር። በዚህ መሃል ከጎረቤት ሃይለኛ ንትርክ ይሰማል፡፡ ቴድና ጄና ናቸው፡፡ ሁለቴ ማሰብ አላስፈለገውም። የግንቡን አጥር እንደ ጎረምሳ ዘሎ፣እነ ጄና  ግቢ ዱብ አለ፡፡ ቅንጣት ሳያቅማማም በቀጥታ  ወደ ዋናው ቤት መግቢያ በር በጥድፊያ ተራመደ፡፡ እንደ ራሱ ቤት በሩን ከፍቶ ዘው ብሎ ገባ፡፡ ጄና ወለሉ ላይ ተንበርክካ፣ የተሰበረ የራስጌ መብራት ስብርባሪ ትጠራርጋለች፡፡ ቴድ በማይክ ድንገተኛ መከሰት ተገርሞ ፣ድምጹን ከፍ አድርጎ ሲያወራ የነበረውን ሞባይል ያቋርጣል፡፡
“ማይክ፤ እንዴት መጣህ?” በመገረም ይጠይቀዋል፡፡
“አንዳች ችግር የተፈጠረ መስሎኝ ነው” ማይክ ይመልሳል፡፡
“የራስጌ መብራቱ ተሰብሮባት ነው፤ችግር አለው?” ቴድ ይጠይቀዋል፡፡
“አንቺ ግን ደህና ነሽ፤ አልተጎዳሽም?” ማይክ ይጠይቃታል - ጄናን በስስት ዓይን እየተመለከተ፡፡
“ደህና ነኝ፤ አልተጎዳሁም” ትልና ነገር ለማብረድ፣ ወደ ውስጥ ትገባለች፡፡
ማይክ ግን እንደፈዘዘ ቆሞ ይቀራል፡፡ በማይክ ነገረ ሥራ ግራ የተጋባው ቴድ፤ “ደህና ነኝ አለችህ እኮ፤ ሌላ ምን ፈለግህ?” ብሎ  ይጮህበታል፣ በቅናትና በመደፈር ስሜት፡፡ ማይክ ቤቱን ለቆ ይወጣል - አንዳች ነገር እያጉተመተመ፡፡ ቤቱ ሲገባ ሚስቱ በጥያቄ ትቀበለዋለች፡፡  
“ምንድን ነው? ምን ተፈጠረ?”
“አይ-- ጎረቤት ጠብ ሰምቼ ሄጄ ነው”
“ለምን አልነገርከኝም?”
“ትደነግጪያለሽ ብዬ ነው”
“ተጣሉ  እንዴ?”
“እንደዚያ ነው የተሰማኝ”
“ለምን ፖሊስ ጋ አልደወልክም?”
“ያንን ለማሰብ  ጊዜ አልነበረኝም”
“የሆነውን ነገር አልወደድኩትም!”
“እኔም አልወደድኩትም” አለ ማይክ፤ ስለ ድብደባው መስሎት፡፡
“በሰው ጉዳይ ጣልቃ መግባትህን ነው ያልወደድኩት!” ታርመዋለች፤ በኃይለ ቃል፡፡
ማይክ እንደፈዘዘና እንደነዘዘ አፍጥጦ ይቀራል። ሚስቱ ተቆጥታ ጥላው ትወጣለች፡፡ ቁጣዋ በሰው ጉዳይ ጣልቃ በመግባቱ  ብቻ ግን አይመስልም። የጠረጠረችው ነገር እንዳለ የዓይን ውሃዋ ይመሰክራል፡፡ በገጽታዋ ላይ ስጋትና ፍርሃት ይነበባል፡፡
በአንድ ጉደኛ ምሽት ማይክና ጄና፣ ማን ያየናል ሳይሉ፣ ራሳቸውን በተንጣለለው መኖሪያ ቤት ውስጥ ያገኙታል፡፡ ማሪዋና  እያጨሱም፣ የሆድ የሆዳቸውን ያወጋሉ፡፡ ጄና ባለቤቷ ጥሩ ሰው እንዳልሆነ፣ ትዳሯም ዕድሜ እንደማይኖረው በመተረክ፣ዕድለ ቢስነቷን ለማይክ ትነግረዋለች። ብሶቷን በመተንፈስ ሰበብም፣ ደረቱ ላይ ተለጥፋና አንገቱ ላይ ተጠምጥማ፣ተንሰቅስቃ ታለቅስበታለች። በማከያውም በእሷ ተነሳሽነት እንደ ጉድ ይሳሳማሉ፡፡ ጄና ስሞሹን እንደ እንባ ማድረቂያ የቆጠረችው ይመስላል፡፡
ማይክ ግን እቤቱ ገብቶ ረዥም ሰዓት የፈጀ  ሻወር ይወስዳል፡፡ የምሽት ሃጢያቱን ለማጠብ ይመስላል፡፡ ከሻወር ሲወጣ   ከሚስቱ ዱብዕዳ ጥያቄ ይቀርብለታል፡፡ “ጎረቤታችን ቤት ነበርክ? ወጣቷ እንዴት ናት፤ቆንጆ ነች አይደል?!” ስትል  ታስደነግጠዋለች፡፡
“ምንድን ነው የምታወሪው? ያምሻል! ልጃችን ትሆናለች እኮ ?!” ይላትና፣ ጀርባውን ሰጥቷት ይተኛል፡፡
ሚስቱ ሁሉንም ነገር እንደተረዳች የዓይን ውሃዋ ይመሰክራል፡፡ በእርግጥም  ለዘመናት የምታውቀው ውድ ባለቤቷ፣ አካሉ እንጂ ልቡ አብሯት እንደሌለ በቅጡ ተገንዝባለች፡፡ በዚህም የተነሳ ለጥቂት ጊዜ መለያየት እንዳለባቸው ትነግረዋለች፡፡ በወጣቷ ፍቅር የነፈዘው ማይክ ግን ለምን ብሎ እንኳን  አጥብቆ አይጠይቃትም፡፡  በነጋታው ሻንጣውን ሸክፎ ከቤት ይወጣል፡፡ መኪናውን አስነስቶ ከመሄዱ በፊት ግን ጄናን  ቤቷ ሄዶ  ያገኛታል፡፡ እሷም  ባሏን  ጥላው ለመሄድ እንዳቀደችና አማራጭ በማጣት፣ የቀድሞ ፍቅረኛዋ ቤት እንደምታርፍ ትነግረዋለች፡፡  ይሄኔ ነው፤ እሱም ከሚስቱ ተጣልቶ  ከቤት መውጣቱን  የሚገልጽላት፡፡ ጄና በጣም  ታዝናለች፡፡ እሱ ግን እንደ መልካም አጋጣሚ ሳይቆጥረው አልቀረም፡፡ የእብደት የሚመስል ሃሳብ ያቀርብላታል፡-
“የምከራየው የሆቴል ክፍል ለአንድ ሰው ከበቂ በላይ ነው፤ ከፈለግሽ  እኔ ጋ ልታርፊ ትችያለሽ፤ሁለት አልጋዎች ይኖሩታል--”  
“ማይክ፤ ይሄ ጥሩ  ሃሳብ አይመስለኝም---ላደረግህልኝ ነገር ሁሉ ግን አመሰግንሃለሁ”   
“እርሽው በቃ፤ችግር የለም” አለ ማይክ፤ራሱን ለማረጋጋት እየሞከረ፡፡
ጄና እጁን ትጨብጠውና ትሰናበተዋለች። በፍጥነት ወደ ቤት ገብታም በሩን እላዩ ላይ ትዘጋበታለች፡፡ ማይክ ከመፍዘዝ ውጭ ግን አልተቀየማትም፡፡ ፍቅሯ ማሪዋና እንዳጨሰ ሰው፣ አፍዝዞት እንዴት ሊቀየማት ይችላል፡፡ በመጨረሻ እሱም መኪናውን ውስጥ ገብቶ ይፈተለካል - ወደ ሆቴል ክፍሉ፡፡
ከሚስቱ ጋ መለያየቱን ለልጁ የነገረው፣ ከቤት ከወጣ በኋላ ነው፡፡
“መቼም ከእናትህ ሳትሰማው አትቀርም፤ ከቤት ሻንጣዬን ሸክፌ ወጥቻለሁ፤ለጥቂት ጊዜ ተለያይተን ለመኖር ወስነናል፤ እርግጠኛ ነኝ አስፈልጋታለሁ፤ ቢሆንም ለትንሽ ጊዜ ተለያይተን  መኖራችን ክፉ አይደለም---”
“የመካከለኛ ዕድሜ ቀውስ ነው አይደል?!” ይላል፤ አሌክስ፡፡
“እንዲያ ነው የምትሉት!?” ማይክ በሃፍረት ድምጸት ይመልሳል፡፡
ማይክን የከበደው ከሚስቱና ከልጁ ተለይቶ መኖር አልነበረም፡፡ ለሱ ጭንቅ የሆነበት ጄናን ሳያይ ውሎ ማደሩ ነው፡፡ ያቺን አማላይ ጎረቤቱን ፈጽሞ ከልቡና ከአዕምሮው ሊያስወጣት አልቻለም፡፡
አንድ ተሲያት በኋላ  ጄናን  እንዲጠብሳት ከገፋፋው ጓደኛው ጋር ተገናኝቶ ቢራ ይጠጣሉ፡፡ የጨዋታ ርዕሳቸው   ደሞ የፈረደባት ጄና ናት፡፡
“አሁን እኮ ግማሽ ርቀት ሄደሃል፤ ጨርሰው እንጂ!” ሲል ያደፋፍረዋል፤ ጓደኛው፡፡
“አሁን እኮ የለችም፤ የቀድሞ ፍቅረኛዋ ጋ እንደምትሄድ ነግራኛለች” አለ ማይክ፤ በልቡ ባትሄድ ብሎ እየተመኘ፡፡
“ዛሬ ጠዋት ያንን ቁምጣዋን ለብሳ፣ ነዳጅ ስትቀዳ አይቻታለሁ” አለመሄዷን አረጋገጠለት፡፡
ማይክ ከጓደኛው እንደተለያየ፣ መኪናውን አስነስቶ ወደ ተባረረበት መኖርያ ቤቱ ተፈተለከ - በምሽት፡፡ በቀጥታ ወደ እሷ ቤት መሄድ እንደማይችል ያውቀዋል፡፡ መጀመሪያ ወደ ራሱ መኖሪያ ቤት በማምራት ማን እንዳለ ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ደግነቱ ማንም አልነበረም፡፡  በራሱ ቁልፍ ከፍቶ ገባ - ወደ ቀድሞው መኖሪያ ቤቱ፡፡ በቀጥታም ያመራው እንደ ቢሮ ወደሚጠቀምባት ክፍል ነው - በሻተር መስኮቱ በኩል ወደ እነ ጄና ግቢ አሻግሮ ለመመልከት፡፡ ዓይኑ ያረፈው በናፍቆት የታመመላት  ወጣት ላይ ነበር፡፡ ውጭ ቆማ ሲጋራ ታጨሳለች - ጄና፡፡ ቅንጣት ሳያመነታ፣በቀጥታ እሷ ወዳለችበት አመራ፡፡ ድንገት ስታየው ተገረመች። ትክ ብሎ ፈዞ እያያት፣ ደህንነቷን ጠየቃት፡፡ ወደ ቀድሞ ፍቅረኛዋ ቤት የመሄድ ዕቅዷን መሰረዟን ነገረችው፡፡  ከቴድ ጋር የትዳር አማካሪ መጎብኘት በመጀመራቸው፣ ግንኙነታቸው እየተሻሻለ መምጣቱን  አወጋችው፡፡ እሷም በተራዋ  ወደ ቤት መመለሱን  ጠየቀችው፡፡ እሷን ለማየት አልሞ ብቻ መምጣቱን መች አላወቀች!
የአፍታ ዕድሜ ብቻ የነበረውን ጨዋታቸውን ያናጠበው  የቴድ ጥሪ ነው፡፡  ጩኸቱና አነጋገሩ ሞቅ እንዳለው ያስታውቃል፡፡ በእጁ የቆርቆሮ ቢራ ይዞ ነው የወጣው፡፡ ማይክን ሲመለከተው በንዴት ደሙ ይፈላል፡፡  የጄና ሲጋራ ማጨስ ግን ትኩረቱን ይወስደዋል፡፡  ሲጋራዋን በሃይል አስጥሎ እየተቆጣና እያመናጨቀ፣ ወደ ቤት ሊያስገባት ሲሞክር ማይክ አላስቻለውም፡፡ “እንደሱ አታድርጋት! አትንካት!” እያለ ይከተለዋል፡፡ ተደፈርኩ ባዩ ቴድ፤ “አንተ ስለኛ ምን አገባህ” ብሎ ዞር ሲል፣ማይክ ቡጢ ይሰነዝራል፡፡ ቴድ ትንሽ ተንገዳግዶ አጸፋውን ይመልሳል፡፡ ማይክ መሬት ላይ ይዘረራል፡፡ ጄና እየጮኸች መጎዳቱን ልታረጋግጥ  ስትሞክር፣ ቴድ እየጎተተ ወደ ውስጥ ይዟት ይገባል፡፡ ከገቡም በኋላ ግን ጠባቸው አልበረደም፤ተባባሰ እንጂ፡፡ ማይክ ይሄን ሰምቶ፣በእልህ ከወደቀበት ይነሳና፣ ጄናን ከገዛ ባለቤቷ ጥቃት ሊታደጋት፣ ወደ ውስጥ አመራ፡፡
“ውጣ! ከዚህ ቤት ውጣ!” አለ ማይክ፣ ቴድን እንዳየው፡፡  
ከገዛ ቤቱ ውጣ መባሉ ያስገረመው ቴድ፤ በተደበላለቀ ስሜት ውስጥ እንዳለ፣ወደ ማይክ ተጠግቶ፣ ኃይለኛ ቡጢ አሳረፈበት፡፡ ማይክ በር ስር  ወደቀ፡፡ ጄና፤ “ገደልከው!” እያለች መጮህ ጀመረች።  አሁን ማይክ ክፉኛ የተጎዳ ይመስላል፡፡ አፍንጫው ደምቷል፡፡ ቴድም ከመደንገጡ የተነሳ “ይሄ ሁሉ ያንቺ ጥፋት ነው!” ብሎ በሚስቱ ማሳበብ ጀመረ።  በዚህች ቅጽበት ግን ማይክ አጠገቡ ያገኘውን ረዥም ብረት አፈፍ ያደርግና፣ አጠገቡ ወደ ቆመው ቴድ በሃይል ይሰነዝራል፡፡ መሃል ግንባሩን ይመታዋል፡፡ ዓይኑ እንዳፈጠጠ ወለሉ ላይ በቁሙ ይደፋል፡፡ ጄና ያየችውን ማመን አቅቷት በድንጋጤ ፈዝዛ ትቀራለች፡፡  የምትመለከተው ሁሉ እውነተኛ ህይወት ሳይሆን ትራጄዲ ድራማ ይመስላታል። ድንጋጤ---ሳግ---እንባ የለሽ ሃዘን--ብስጭት። በተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ሆና ለማድረግ የቻለችው ብቸኛ ነገር ቢኖር፣የሞባይል ስልኳን አንስታ ለመደወል መሞከር ነው፡፡ ለፖሊስ፡፡ በዚህ መሃል ማይክ ከወደቀበት ተነስቶ፣ ቃላት ገጣጥሞ ለመናገር ይሞክራል፡፡ ጄና ግን ታምባርቅበታለች፡፡  
“ውጣልኝ! ከዚህ ቤት ውጣልኝ! አሁኑኑ ውጣልኝ!”  
ጩኸቷን ሊቋቋመው አልቻለም፡፡ ሹልክ ብሎ ወጣ፡፡ አፍንጫው እየደማ መሆኑን ያወቀው እንኳን ከቤት ውስጥ ከወጣ በኋላ ነበር፡፡ እንደፈዘዘና እንደደነዘዘ ከመኖርያ ቤቱ ደጃፍ ላይ ሄዶ  ይቀመጣል፡፡ ወዲያው  የፖሊስ መኪና የሳይረን ድምጽ አካባቢውን ያናውጠዋል፡፡       

Read 3036 times