Sunday, 25 February 2018 00:00

የዘመኑን ተግዳሮት ለመፍታት፣ ዘመናዊ አስተሳሰብና አመለካከት ያስፈልጋል

Written by  ብርሃኑ አሰፋ (ዶ/ር -ኢንጂ) አዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ
Rate this item
(2 votes)

   · ዓምና ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ የተመደበው 10 ቢ. ብር ምን ውጤት አመጣ?
     · የዘመኑን የለውጥ ማዕበል፣ በልማዳዊ የችግር አፈታት ማስተናገድ አይቻልም
      
    የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታን እንደምረዳው፡-
ሀገራችን ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰብ sት ናት፡፡ የተለያዩ እምነት ተከታይ ሕዝቦች አብረው በመተሳሰብ የሚኖሩበት ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ የዜጎቿን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ብልጽግና ሊያረጋግጥ የሚችል የተፈጥሮ ሀብት አላት፡፡ የአፍሪካ ውሃ ማማ ናት፡፡ ብዙ ሚሊዮን ሔክታር ለእርሻ ተስማሚ የሆነ መሬት ባለቤት ናት፡፡ በከርሰ ምድሯ በሚሊዮን ቶኖች የሚገመት የወርቅ፣ የታንታለም፣ የብረትና ለተለያዩ የኢንዱስትሪ ልማት ግብዓት ሊውል የሚችል ማዕድን  ተሸክሟል‹::
ሀገሪቱንና የሕዝቧን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የኢሕአዴግ መንግሰት ባለፉት 27 አመታት ብዙ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ በትምህርት ተደራሽነት ትልቅ እምርታ አሳይቷል፡፡ በጤናው ዘርፍ በጣም የሚደነቅ ወጤት ተመዝግቧል፡፡ በኢኮኖሚው ረገድ ተስፋ የሚሰጥና ብዙዎችን ከድህነት ያወጣ እድገት ተገኝቷል፡፡ ነገር ግን እነዚህ የተመዘገቡት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጦች ምን ያክል መሰረት መያዛቸውንና እውቀት በተሞላበት መንገድ የተሰሩ መሆኑን ጥርጣሬ ውስጥ የሚከቱ ክስተቶች ማየት ከጀመርን ሰንብተናል፡፡
ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የታየው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በጣም የተዳከመ ነው። ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ተብሎ በቅርቡ የተደረገው የውጪ ምንዛሬ ምጣኔ ማስተካከያ፤ የችግሩን ምንጭ በሚገባ ያላጤነ መሆኑ ውሎ ሳያድር መታየት ጀምሯል፡፡ የውጪ ምንዛሬ እጥረትን አባብሷል፡፡ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ከውጪ የሚገቡ መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች እጥረት እየተከሰተ ይገኛል፡፡ ብዙ ፋብሪካዎችን ሠራተኛ እንዲቀንሱ በማስገደድ ጥሬ እቃ ከውጪ ሀገር መግዛት ባለመቻላቸው የተነሳ ምርት ማምረት አቁመዋል፡፡ ውሎ አድሮ ይህ የውጪ ምንዛሪ ችግር ፋቢሪካዎቹን ሠራተኛ እንዲቀንሱ በማስገደድ የስራ አጦችን ቁጥር የሚጨምር እርምጃ ሊያስወስዳቸው ይችላል፡፡ ለእለት ፍጆታ የሚውለውም ሆነ ለግንባታ የሚውሉ እቃዎች ከሳምንት ሳምንት ዋጋቸው እየጨመረ ነው፡፡ ለምሳሌ ለግንባታ የሚውል የብረት ዋጋ ዛሬ ከእጥፍ በላይ ጨምbል፡፡
በማሕበራዊ ረገድ ተመዝግበው የነበሩ ድሎች ላይ ጥላ እያጠላበቸው ይገኛል፡፡ ለምሳሌ  የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ወረርሽኝን ለመግታት የተሰራው ሥራ ወደኋላ ተመልሷል፡፡ ብዙ ወጣቶች የአጉል ሱስ ተገዥ ሆነዋል፡፡ ለብዙዎች ተስፋ ሰጥቶ የነበረው የድህነት ቅነሳ ባለበት የቆመ ይመስላል፡፡ ይልቁንም በፍጥነት በሚያድገው የሀገራችን ህዝብ ብዛት የተነሳ የድሀው ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ነው፡፡ በትምህርት ተደራሽነት ተመዘገበ የተባለው ውጤት፤ በጥራት መውደቅና በተገቢነቱ ውስንነት (የኢኮኖሚ ፍላጎትን ማዕከል ባለማድረጉ) ምክንያት  ለኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ችግር መባባስ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፡፡
በየዓመቱ ከ500 ሺ በላይ ተማሪዎች የመጀመሪያ ዙር አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት  ያጠናቅቃሉ፡፡ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥ፣ ፈጣንና ተወዳዳሪ የኢንዱስትሪ ልማት ለመገንባት የሚፈልገውን የሰው ኃይል ለማቅረብ እንዲቻል 80 ፐርሰንት ሁለተኛ ደረጃ የጨረሱ ተማሪዎች የቴክኒክና ሙያ ተግባር ያማከለ ስልጠና እንዲወስዱ፣ የ20 ፐርሰንቱ 70 ፐርሰንት የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን በተፈጥሮ ሳይንስና በምሕንድስና የማስተማር ዕቅድ ከተያዘ አስር አመታትን አስቆጥሮአል፡፡ ሆኖም የፖሊሲ አመንጪዎች፣ እቅዱን ከኢኮኖሚው የማጣጣም የአቅም ውስንነትና የአስፈጻሚዎች እቅዱን የመረዳትና የመተግበር ድክመት ሳቢያ የታሰበውን ውጤት ሊያመጣ አልቻለም፡፡ ከዚህ የተነሳ ዛሬ በየክልሉ በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ተመርቀው ሰርተፍኬት ቢሸከሙም በሥራ አጥነት ጊዜያቸውንና እድሜያቸውን እያባከኑ ይገኛሉ። ባለፈው አመት መንግስት የሥራ አጥነትን ችግር ለመፍታትና ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ የመደበው አስር ቢሊዮን ብር ሥርዓት ባለው መንገድ ሥራ ላይ ባለመዋሉ ለብዙ ሥራ አጥ ወጣቶች ትርጉም ያለው ውጤት አላመጣም፡፡
በሌላ በኩል በሀገራችን፣ ከተሞች በሚገርም ፍጥነት እያደጉ ነው፡፡ ከተሞቻችን የገጠር እርሻ መሬትን በከተማ ቦታነት ከልለው ከመያዝ በስተቀር የኢንዱስትሪ መነሐሪያ ለመሆን አልቻሉም፡፡ ስለሆነም ከተሞች በሥራ አጥ ወጣቶች ተጨናንቀዋል፡፡ በገጠርም ለም የእርሻ ማሳዎች፣ ገበሬዎችን በማፈናቀል ያለ አመርቂ ተለዋጭ ሥራ ለትላልቅ የአትክልትና አበባ እርሻና ለኢንዱስትሪ ግንባታ  ውለዋል፡፡ ሆኖም የገጠሩን ኢኮኖሚያዊ ችግር ለማቃለልና ማህበራዊ ሕይወት ለማሻሻል ብዙ አስተዋጽኦ እያደረጉ አይደለም የሚል ስሞታ እየቀረበባቸው ነው፡፡ በተጨማሪ ከከተሞቹና ከኢንዱስትሪዎቹ የሚመነጩት ፈሳሽና ደረቅ ቆሻሻዎች፤ የከተሞችና የገጠሩን ሕዝብ ለኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ቀውስ ከመዳረጋቸው በላይ በአካባቢ ምሕዳር ላይ ጉዳት እያስከተሉ ይገኛሉ፡፡
የመንግስት ሥራ አስፈጻሚዎችና በየደረጃው የሚገኙ የሚመለከታቸው የቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም ቢሮክራሲው፣ ይህንን ችግር በፍጥነት የመፍታትና ለሕብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ መልስ ለመስጠት የሚያስችል ቁርጠኝነት፣ ተነሳሽነት፣ ብቃትና አቅም ያላቸው አይመስልም፡፡ ብዙዎች የእጅ መንሻ ለሰጡአቸው ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ ሆነዋል፡፡ የነዚህ ሁሉ ችግሮች ድምር ውጤት ሕዝቡ በመንግስትና በባለስልጣናት ቅሬታ እንዲይዝና ተቃውሞ እንዲያነሳ እያደረገው ይገኛል።  በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ከጊዜ ወደ ጊዜ  የሥራ አጥነት ችግር፣ የኑሮ ውድነት ምሬትና የማሕበራዊ ዋስትና እጦት እየበዛ በመሔዱ፣ ሕዝቡ በተለይም ወጣቶች በመንግስት ላይ በቀጥታ ለተቃውሞ እንዲነሳሱ አድርጓቸዋል፡፡ ገዥው ፓርቲና መንግስት የሕዝቡን በተለይም የወጣቶችን ቅሬታና ተቃውሞ ተገቢነት  በተደጋጋሚ ቢያምንም ጥያቄዎችን ለመመለስና ችግሮችን ለመፍታት የቁርጠኝነት፣ የተነሳሽነትና የተግባራዊነት ጉድለት ለውጤት አላበቃውም፡፡ ከዓመት ዓመት፣ መንግስት ራሱ መፍትሔ የሚለውን እንኳ መተግበር ባለመቻሉ የበለጠ ችግሮችን እያወሳሰበ፣ ዜጎች ከመንግስት ጋር ያላቸውን ቅራኔ እያከረረ ይገኛል፡፡
የዘመኑ የለውጥ ማዕበልና
የልማዳዊ ችግር አፈታት ውስንነት፡-
በዚህ ዘመን ሕዝቡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ፤ መንግስትና  ገዥው ፓርቲ የእርሱን ምኞትና ፍላጎት ለማስተናገድ የሚመጥን ርዕዮተ-አለም፣ እውቀትና ክህሎት አላቸው ብሎ የማያምንበት ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስላል፡፡ ዜጎችን ጥያቄያቸውንና ፍላጎታቸውን የማያስተናግድ የመንግስት ስርዓት ለመቀበልና ለመታዘዝ አይፈልጉም፡፡ በዚህ ዘመን መንግስት የፈለገውን ያክል አምባገነን ቢሆን፤ የቱንም ያህል ትላልቅ የጸጥታና የደህንነት ኃይላት ቢኖሩት፣ እጅግ ሰፊ የፕሮፓጋንዳ ተsምና አያሌ የካድሬ ወይም ጉዳይ አስፈፃሚ አደረጃጀት ይዞ መንቀሳቀስ ቢችልም… እንደ ዱሮ ዜጎችን ባሻው መንገድ መምራት፣ መከልከል፣ ማገድ ወይም ጸጥ ለጥ አድርጎ መግዛት አይችልም፡፡ ይህ ክስተት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ዓለማቀፋዊ እውነታ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ብዙ የዓለማችን  ሀገራት የዲሞክራሲ ሥርዓታቸው፣ ወጣቱን ትውልድ የሚያዳምጡበት መድረክ ፈጥሮላቸዋል፡፡ እንደውም አንዳንድ ሀገሮች ወጣቶችን ወደ መሪነት  አምጥተዋቸዋል፡፡ ለምሳሌ  የፈረንሳይ፡ የኦስትሪያና የኢጣልያን መሪዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ወደማይፈለግ ፍጥጫና ግጭት ከመግባት ይጠብቃል፡፡ አለበለዚያ ማንም አሸናፊ ወደ ማይሆንበትና ሁሉንም ወደ ጥፋት የሚመራ አዘቅት ውስጥ ያስገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሶሪያን፣ ሊብያንና የመን መመልከት ትልቅ ትምህርት የሚሆን ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ የትውልድን ፍላጎት፡ ስነልቡና፣ የሕይወት አመለካከት የሚመጥን የመፍትሔ አቅጣጫ፤ የፖለቲካ ሥርዓትና የመንግስት አወቃቀር ያስፈልጋል፡፡
የዚህ ዓለማቀፋዊ ክስተት ምክንያት ሙሴ ናይም፤ የኃይል መጨረሻ (The End of Power)  በሚለው መጽሐፉ እንዳመለከተው፤ ባለፈው 30 ዓመታት በዓለማችን ላይ በተፈጠሩ ወይም እየተፈጠሩ ባሉ ሦስት ፈጣን መሠረታዊ የለውጥ ማዕበሎች ወይም አብዮቶች (Revolutions) ምክንያት መንግስታትና ትላልቅ ተቋማት፣ በሕዝብ ላይ በሚፈልጉት መንገድና መጠን ተጽዕኖ የማድረግ አቅማቸው እየተዳከመ መጥቷል፡፡ በአንጻሩ ትናንሽ የዜጎች ስብስቦች ወይም ኃይላት (micro powers) እየጠነከሩና የመንግስትንና የትላልቅ ተቋማትን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማሕበራዊ ሥራ እየተፈታተኑ፣ እያዳከሙና አንዳንዴም የበላይነት የሚይዙበት አጋጣሚ ይፈጥራል፡፡ ለዚህም ተግዳሮት ምክንያት የሆኑትን የብዛት (More) ለውጥ ማዕበል ወይም አብዮት’ የእንቅስቃሴ (Movement) አብዮት እና የአመለካከት (Mentality) አብዮት ሲል ይመድባቸዋል፡፡ እነዚህ የለውጥ ማዕበላት በመረጃና በኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ በመረጃ-መረብ (Interent) ተደግፈው በሚገርም ሁኔታ የተለመዱ የመንግስትና ሌሎች ግዙፍ ተቋማትን የማስፈፀም ኃይልና አቅም በፍጥነት እያዳከሙ ይገኛሉ፡፡
የመጀመሪያው የብዛት አብዮት፣ ባለፉት 30 ዓመታት፤ በሀገሮች፡ በከተሞችና በየመንደሩ በፍጥነት እየጨመረ የመጣውን የሕዝብ፣ የተማሩና ነገሮች ቶሎ መረዳት የሚችሉ (talented) ወጣቶች፣ ልዩ ክህሎት ያላቸውና የማሕበረሰብ መሪዎች (innovative and community leaders) እና ባለሀብቶች ብዛት እንዲሁም በዓለማችን ላይ ያለው የአዳዲስ እውቀትና መረጃ፣ ሰዎች የሚከተሉት እምነትና የሕይወት ዘይቤ ብዛት፤ አዳዲስ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች (የመረጃ-መረብ፣ ፌስቡክ፣ ቲውተር፣ ኢሜይል . . .) እና ቁሳቁስ (ኮምፒዩተር፣ ራድዮ፣ ቴሌቭዥን፣ ተንቀሳቃሽ ስልክ፡ አይፎን . . .) ብዛትና የሚጠቀሙ ሰዎች በፍጥነት እያደገ መምጣት፣ በመንግስት አሰራር ላይ እያስከተለ የሚገኘውን ተፅዕኖ ይመለከታል፡፡
ሁለተኛው የእንቅስቃሴ አብዮት፣ በትራንስፖርት ቴክኖሎጂ በብዛትና ፍጥነት ማደግ ምክንያት የሰዎች፡ የቁሳቁሶችና የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በዓይነትና በመጠን መበርከት፣ በደቂቃዎችና በሰዓታት፣ ከቦታ ቦታ፣ “ከመንደር፣ መንደር ከከተማ ከተማ፣ ከሀገር ሀገር፣ ከአህጉር አህጉር ማንቀሳቀስ መቻልን፣ በመረጃ መረብና በመገናኛ ቴክኖሎጂ ምክንያት እውቀት መረጃና ገንዘብ በሰከንዶች ከቅርብም ከሩቅም መለዋወጥና መላላክን እውን አድርጓል፡፡ በእንቅስቃሴ አብዮት የተነሳ ዛሬ ዓለማችን አንድ መንደር ሆናለች። ከሀገራችን ዜጎች እንኳን አንድ የቤተሰቡ አባል ወይም ዘመዱ ወይም የቅርብ ጓደኛው ወደ ሌላ ከተማ ወይም ሌላ ሀገር በትምህርት በሥራ ወይም በስደት ያልሔደበት አይገኝም፡፡ የእንቅስቃሴ አብዮቱ የተለያዩ ሀገር ዜጎች እንዲተዋወቁ፡ የግልና ሀገራዊ ተሞክሮአቸውን እንዲለዋወጡ ዕድል ከፍቶላቸዋል፡፡ በገንዘብ በሀሳብ፣ በቴክኖሎጂ ቁሳቁስም ሆነ አጠቃቀም የመተጋገዝ አቅም ፈጥሮላቸዋል፡፡ ስለሆነም የእንቅስቃሴ አብዮት፤ አብዛኛው ወጣት የመገናኛ ቴክኖሎጂ መሳሪያ በተለይም ተንቀሳቃሽ ስልክና አይፎን በመጠቀም በአጭር ጽሑፍ፡ ፌስቡክ፡ ቲዊተር፡ ኢሜል . . . ሀሳብና መረጃ ለመቀያየር አስችሎታል፡፡   
ሦስተኛው አብዮት በትውልዱ ዘንድ በፍጥነት እያደገና እየተለወጠ የመጣውን የአመለካከት፡ የሕይወት ፍልስፍና ዘይቤ ይመለከታል፡፡ ይህ ለውጥ በብዛትና እንቅስቃሴ ፈጣን ለውጦች የተነሳ በዓለማችን በፍጥነት ከሚያድገው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማሕበራዊ እውቀት መገብየትና የልምድ ልውውጥ ማድረግ መቻል የተነሳ፣ እንደ ሀገሮች ነባራዊ ሁኔታ በወጣቶች በተለይም በተማሩት ዘንድ የአመለካከት፣ የሕይወት ፍልስፍና፣ የፖለቲካ ሥርዓት እውቀትን አስፍቷል፡፡ እንኳን በትልልቆቹ ዘንድ በመዋለ-ሕጻናት በሚውሉ ልጆችና ወላጆች መሐከል ያለውን ፍጥጫ ማየት፣ እነዚህ ዓለማቀፋዊ ማዕበላት በዜጎች አመለካከትና ስነ-ልቡና ላይ ያመጡትን የለውጥ መጠን ለመገመት ያስችላል፡፡
ሦስቱ የለውጥ ማዕበላት ለዜጎች
የሰጣቸው አቅሞች፡-
እነዚህ የለውጥ ማዕበላት በየሀገሩ ያሉ ዜጎችን ባለፉት 30 ዓመታት ተፅዕኖ አድራጊ ከነበረው ትውልድ አመለካከት የተለየ የአስተሳሰብና የሕይወት ፍልስፍና እንዲሁም የፖለቲካ ግንዛቤ እንዲይዙ አድርጓቸዋል፡፡ ወጣቱ ትውልድ ለማንኛውም የመንግስት ተቋማትም ሆነ ሌሎች አካላት የራሱን ፍላጎት ለመግለጽና ቅሬታዎቹን ለማሰማት የተሻለ አቅምና ጉልበት የሚፈጥሩ፤ ርካሽ የሆኑ ጊዜ የማይወስዱና አካላዊ ጉዳት መቀነስ የሚያስችሉ መሳሪያዎች ወይም አቅሞች አጎናጽፏቸዋል፡፡
መፍትሔና ማጠቃለያ፡-
ከላይ በተጠቀሰው ነባራዊ ሁኔታ የሚያልፍ ትውልድ የመብት ጥያቄዎችን ሲያቀርብ እንዴት ነው የምናስተናግደው? ልማዳዊ የአስተዳደር ስርዓትና የችግር አፈታት መንገዶችን በመጠቀም ትውልዱ በግድ እንዲቀበል እስከ ጥግ ከመግፋታችን በፊት ከብዛት፡ ከእንቅስቃሴና ከአመለካከት ፈጣን ለውጦች የተነሳ ሀገራችን አሁን ላለችበት ሁኔታ ያለውን አንድምታ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ወጣቱ ትውልድ የሕግ የበላይነት፣ የዜጎች እኩልነትና እውነተኛ ዲሞክራሲ ለሀገሮች ልማትና ለዜጎች የተሻለ ኑሮ መምራት ግብዓት እንደሆኑ ተምረው አውቀውታል፣ ሄደው አይተውታል፣ ኖረው ቀምሰውታል፡፡ ፍትሃዊ የፖለቲካ ሥርዓት ቢኖር፤ ዜጎች ጥራትና ተገቢነት ያለው ትምህርትና ስልጠና ቢያገኙ፣ የጤናና ደህንነት ዋስትና ቢኖራቸው… የራሳቸውን የቤተሰባቸውን፣ የማሕበረሰባቸውንና የሀገራቸውን እድገት ለማፋጠን እንደሚችሉ ይገነዘባሉ፡፡ መንግስትን ለሕዝብ  ጥቅም የቆመ ሳይሆን ለተወሰኑ የገዥው ፓርት አባላትና የጥቅም ግንኙነት ላላቸው ሰዎች የሚሰራ ነው ብለው ይከሳሉ፡፡ ይህንን እምነት ቀይሮ ትውልዱ በመንግስት ላይ  እምነት እንዲፈጥር የሚያደርግ ሥርዓት መገንባት የግድ ይላል፡፡  ለዚህ መሳካት በሀገራችን ለመንግስታዊ ስርዓት ተሐድሶ የሚከተሉትን ነጥቦች ከግንዛቤ ውስጥ ቢገቡ መልካም ይመስለኛል፡፡
1ኛ- በሕዝቦችና ፖለቲከኞች መካከል ለወደፊት ጤናማ ግንኙነት መሰረት መጣል፡፡ ዛሬ የሚታዩት ኢ-ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲሁም የፖለቲካ ተሳትፎ ክፍተት ከኃይለ ሥላሴ ዘመን ጀምሮ ተደማምረው የሚመጡ ችግሮችና ጉድለቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ያለፈውን ጥፋት ኦዲት ማድረግ ትቶ፣ የወደፊቱን ለመያዝ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
2ኛ- የዋናዎቹን ባለድርሻ አካላት ፍላጎት በየጊዜው ሊታረም የሚችል፣ በማቻቻል፣ ሀገራዊ የኢኮኖሚ፡ የፖለቲካና ማሕበራዊ ልማት የማምጣት አቅምና ቁመና ያለው መንግስት መመስረት ያስፈልጋል፡፡ ከልማቱ ባሻገር የአመለካከትና ርዕዮተ-ዓለም ብዝሃነትን የሚያስተናግድና ነባራዊ ተቃርኖዎችን የሚያስታርቅ የፖለቲካ ሥርዓትና መንግስት ለመፍጠር መትጋትም የግድ ይላል፡፡
3ኛ- የግለሰቦችን ሀብት የማፍራት ነጻነት ሳይጋፋ፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና ማሕበራዊ ደህንነት የሚያረጋግጥ የኢኮኖሚ ሥርዓት መገንባት ያስፈልጋል፡፡
4ኛ- መንግስት፤ የክልሎችና የሀገሪቱን ሕዝብ በሕይወቱ ምሳሌነት፣ ለሀገሩና ለሕዝቦቿ ባለው ፍቅርና ራዕይ  በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ቅቡልነት ባለው መሪ መወከል አለበት፡፡ እንዲህ አይነት መሪ የሚመራው መንግስት፣ የኢኮኖሚያዊ፡ ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ለውጥ ለማምጣት በሚነደፉ እቅዶች ዙሪያ ዜጎችን ማሰባሰብ ይችላል፡፡
ያኔ ፖለቲካችንን ከዜሮ ድምር ቁማር በማውጣት፣ ሁላችንም አዎንታዊ ትርፍ ወደምናገኝበት ጨዋታ ልንቀይረው እንችላለን፡፡ ያኔ አገራችን የብሔር ብሔረሰቦች እንዲሁም የተለያዩ እምነቶችና አመለካከቶች ቋትነቷ ውበቷ ይሆናል፡፡ ያኔ ለዜጎች የደስታ ደሴት ከመሆን አልፋ  ለአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ብሎም ፖለቲካዊ ውሕደት ሞዴል ትሆናለች፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!!!  
ፀሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡-
  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1310 times