Sunday, 25 February 2018 00:00

ሥልጣን በፈቃድ መልቀቅ በኢትዮጵያ

Written by  ሰሎሞን አበበ ቸኮል
Rate this item
(0 votes)

  (ታሪካዊ ዳራ)
                
     ኢሕአዴግ ከሰሞኑ በጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በኩል፣አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን፤ “በኢትዮጵያ ታሪክ በገዛ ፈቃድ ከስልጣን በመልቀቅ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር” በማለት  ፋና ወጊ አድርጎ ጠቅሷቸዋል፡፡ እውነት በታሪክ የመጀመሪያው ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው የለቀቁ የሀገሪቱ መሪ ናቸውን?  
ለነገሩ ኢህአዴግ “ኢትዮጵያንም የፈጠርኳት እኔ ነኝ” እስከ ማለት የደረሰ በመሆኑ ይሄ አባባሉ ብዙም አያስደንቅም፡፡ ወደ እውነታው ስንመጣ ግን ጠ/ሚኒስትሩ ሥልጣን በፈቃድ በመልቀቅ በታሪካችን የመጀመሪያው መሪ አይደሉም ብሎ መሞገት ይሄን ያህል አዳጋች አይደለም፡፡ ከታሪክ መዝገብ በመጥቀስ ማስረጃዎችን ለማየት እንሞክራለን፡፡
ከአኵሱም ዘመነ መንግሥት በፊት፣ ለ4 መቶ ዓመታት ያህል የመንግሥት ማዕከል በነበረችው ሣባ (“ከሣባ ዘመንም” ቀደም ብሎ) የነገሰው ዐጼ፤ ከሥልጣን ጋር በተገናኘ ባመነጨው አዲስ ሃሳብ ተጠቃሽ ነው፡፡ ራሷን ሳባ ከተማን የቆረቆራት ከኢትዮጵያ አስደናቂና ታላላቅ ነገስታት አንዱ የነበረው ይኼው ዓፄ፤እንዴት ወደ ሥልጣን እንደወጣም በታሪክ ተመዝግቧል፡፡  
አሪስቶትል የሳይንስ አባት ሊያስብለው የቻለባቸውን ሥራዎችን እንዳከናወነ የሚነገርለት፣ ተመራማሪ፣ ፈላስፋ፣ አዳቃይ፣ ጦረኛና የብዙ ሥራዎች ፋና ወጊ የነበረው ዓፄ የተባለው ንጉሠ ነገሥት፤ ገና በልዑልነቱ ዘመን፣ “ሥልጣን በመወለድ ብቻ ሳይሆን ሌላ ተጨማሪ መወዳደሪያ ሊኖረው ይገባል፣” ሲል ተነሳ፡፡ “ብኵርና ብቻ ለምን?” ባይ ሆነ፡፡ እርሱ ከንጉሠ ነገሥቱ ልጆች የመጨረሻው ነበር፡፡ የመጀመሪያው ወንድ ልጅ ወራሽ ነውና፣ ታላቅ ወንድሙ ኩግናእ ነበር ዐልጋ ወራሽ፡፡
የንቦችን ንጉሣዊ ፍልሚያ አይቶ፤ “ልዑላኑም በነፃ ትግል ተፋልመው ይንገሱ” አለ፡፡ “ከስነ ፍጥረት ትምህርትንና አብነትን እናገኝ ዘንድ ባለ አእምሮዎች ነን!” የምትል መሠረታዊ የፍልስፍና ሐሳብ አጥብቆ ያቀነቅን የነበረው ዓፄ፤ ለአውራሽ ንጉሠ ነገሥት አባቱም ይህንኑ ገለጸ፡፡
በመወለድ ሁላችን እኩል ነን፤ ሁላችን እኩል ልዑል ነን፤
ስለዚህ እኩል የዐልጋ ወራሽነት መብትም ይኖረናል!
ነገር ግን፣ ዐልጋውን አንዱ ብቻ ስለሚወርስ፣ ለዚህም ልዑላኑ ተፋልመው የአሸናፊዎች አሸናፊ የሆነው ዐልጋውን ይሸለም፡፡
ንጉሠ ነገሥት አባቱ፤ “ልጆቼን ተዋጉ ብዬ እንዳጋድላቸው ነው የምትሻው?” ብለው እንደማይሆን ለጎረምሳው ልዑል ነገሩት፡፡ እርሱ ግን አቋሙ ይኼው እንደኾነ በመግለጽ፣በየዐሥር ዓመቱ እንዲኹ በፍልሚያ ውድድር እየተደረገ፣ ንጉሠ ነገሥትነት ይሁን ንጉሥነትም በፈረቃ እንደሚሆን ቁርጡን ተናግሮ ወጣ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ አባታቸው ሲሞት፣ ዐልጋ ወራሹ ኩግናእ (ቁግናእ) ንግሥና ተቀባ፡፡ ነገር ግን የመጨረሻው ታናሽ ወንድሙ የኾነው ዓፄ፣ ተከታዮች ያሉት ኃያል ልዑል ነበርና ለዐልጋው ጦር ሊያነሳም እንደሚችል ያወቀው ታላቅ ወንድሙ፣ ባለው ሕገ መንግስት መሠረት ተቀብቶ ዐልጋውን በወረሰ በሁለተኛ ዓመቱ፣ “ንጉሠ ነገሥትነቱ ለዓፄ ነው የሚገባው፣” ብሎ ለታናሽ ወንድሙ፣ ፈቅዶ ዙፋኑን ለቀቀ፡፡ ይህ ተመዝግቦ የተገኘው በ1500 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ላይ ነበር - በ4001 ዓመተ ዓለም ዓለም፡፡
ዓፄ የሚለው ስም የነገሥታት የክብር መጠሪያ ሆኖ የታወጀው፣ ለዚህ ታላቅ ንጉሠ ነገሥት ክብርና መታሰቢያ ሲባል መሆኑም ተመዝግቧል፡፡ ከርሱ በኋላ አኵሱምን የመሠረታት አኵሡማይ፣ ነበር ያወጀው፡፡ ከእርሱ ጀምሮ ለሃያ ስምንት መቶ 58 ዓመት ያህል ኢትዮጵያን ዓፄ የሚባሉ ነገሥተ ነገሥታት ገዝተዋል፡፡
በ“ሂስትሪ”ም ከታወቀው ከዓፄ ካሌብ በፊት፣ ከልደት ወዲህ በመጀመሪያው መቶ ዓመቶች ውስጥ ብቻ ሁለት የታወቁ ነገሥታት ሥልጣናቸውን ለወራሾቻቸው አስረክበው ወደ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ሄደዋል፡፡ ከነዚህ ቀዳሚው፣ ክርስቶስ በሚወለድበት ጊዜ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት የነበረው የዓፄ ቢዘን (ሎዛ ቤዛ) ልጅ፣ ራስዳሸ ወይም ዓፄ ጽንፈ አርእድ (9-31 ዓ.ም) ነበር፡፡ በነገሠ በ22ኛ ዓመቱ፣ በሜሮዌና ታኅታይ ኑብያ ላይ ቅንዳኬ ንግሥት አድርጓት የነበረችቱን ታናሸ እህቱን እቴ ህንደኬን፣ “ንግሥተ ነገሥታት እቴ ጌርሣሞት” ብሎ ካነገሠ በኋላ፣ እርሱ “የዚህን ዓለም አዱኛ ንቆ… መነነ፡፡” (“ቅንደኬ የኢትዮጵያ ንግሥት” ተብላ በሐዋርያት ሥራ ምዕ 8፡26 የተጻፈችው ናት፡፡ ዣንደረባዋ ባኮስ በክርስትና የመጀመሪያው ተጠማቂ መኾኑም በዚኹ የሐዋርያት ግብር መጽሐፍ ላይ ከሰፈረው  መረዳት ይቻላል፡፡)
በሌላ በኩል የዚህች ንግሥት ስም (ጌርሣሞት) በአክሡም ከተገኙት ሣንቲሞች በአንዱ ተቀርጾም ተገኝቷል፡፡ “ገርሠመተ- በከረሠተሰ ዘመአተ” ይላል፡፡ “በክርሥቶስ የሞተች ጌርሣሞት” ተብሎ ይነበባል፡፡
ኹለተኛው፣ ከዚህች ንግሥት በኋላ በ39 ዓ.ም የነገሠው፣ የወንድሟ የዓፄ ጽንፈ አርእድ ልጅ ሶረን ነው፡፡ እርሷ በድንገት ስትሞት ሶረን፣ ዓፄ ዑዛና (ስ) ተብሎ ነገሠ፡፡ ይህ ንጉሠ ነገሥት ከወርቅ፣ ከብርና ከነሐስ የተሰሩ “ድሪም” ይባሉ የነበሩ ሣንቲሞችን በስሙ አስቀርፆ፣ መለዋወጫና መገበያያ አድርጓል። ሣንቲሙም በአክሡም ይገኛል፡፡
ዑዛናስ በዘመኑ ኃያል የነበረችቱ ሮም፣ በቀይ ባሕር መስመርና አካባቢው ፍላጎት አሳድራ፣ በደቡብ ዓረብያ የሚገኙ ሀገሮችን የወረረችበት ጊዜም ነበርና እንደ ዓፄ ካሌብ ቀይ ባሕርን ተሻግሮ ራውዛን፣ ሳላትንና ናግራንን (ናጂራን) ከቄሳር ጦር ነፃ አወጣ፣ በአዱሊስ የባሕር ኃይል አቋቋመ፤ አዱሊስን “ንጉሠ ባሕር” ወይም “ባሕረ ነጋሽ” በሚል ማዕረግ የሚነግሥ ገዥ የሚቀመጥባት አድርጎ የመሠረታትም እሱ ነው፡፡ የመጀመሪያው “ንጉሠ ባሕር” ያደረገው ደግሞ ልጁ ከተብን ነበር። በዓለም አቀፍ ደረጃ በታወቀው “ፔሪፒሊስ ኦፍ ሬድ ሲ” በግሪክ ተጽፎ እንደተገኘው፣ የአዱሊሱ ንጉሥ “ዞስቃለስ” ማለትም ይኼው ንጉሥ ነበር፡፡
ዑዛናስ በ59 ዓ.ም ንጉሠ ባህር ዞስቃለስን እንደራሴ በማድረግ፤ ሴት ልጁን፣ ልዕልት ብልባላን “እቴ ህንደኬ ሣልሳዊት ዣን ንግሥተ ነገሥታት” አስብሎ ዙፋኑን አወረሳት፡፡ እንዲህ አድርጎ፣ እርሱ ወደ ምናኔ ገባ፡፡ “ናዝራዊ በመኾን (ቀሪ) ዕድሜውን በዋሊ ገዳም ጨረሰ እንጂ፣ ወደ አክሱም አልተመለሰም፣” ይላል፡፡ ዋሊ የተባለው ዛሬ ዋልድባ የሚባለው ነው፡፡
ከእነዚህ ቀጥሎ ነው ዓፄ ካሌብን የምናገኘው። ካሌብ ከየመን በተመለሱ በአምስተኛው ዓመት፣ መንግሥታቸውን ለልጃቸው ለገብረመስቀል  አስረክበው መነኑ፡፡ በአባ ጴንጠሌዎን ገዳም አጠገብ ባለ ዋሻ ውስጥ ገብተው ቀሪ ዘመናቸውን በዚያው ጨረሱት፡፡ ዘውዳቸውንና በትረ መንግሥታቸውን ወደ ኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳሳት ወደ አባ ዮሐንስ ልከው፣ “ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ደጃፍ ስቀሉልኝ፤” ብለው ሰደዱላቸው፡፡ ስለዚህም ነበር ተከታዩ አርኬ በግዕዝ የተደረሰላቸው፡፡
“ሰላመ ለካሌብ ትእምር ተሕድገታ ለብዕሉ፤ አንተ ፈነወ አክሊሉ፣ በኢየሩሳሌም ይሰቅሉ፤ ዝንቱ ኃያል ኢይትመካህ በኃይሉ፤ በእዴሁ ሠራዊተ ሣባ ተቀትሉ ዘእንበለ ኢይትርዓዩ አሐደ እምእሉ፡፡”
“በእጁ የሣባ ሠራዊት ተገድሎም በሃይሉ ያልተመካ፣ አክሊሉን (ዘውዳን) በኢየሩሳሌም እንዲሰቅሉት የላከ፣ ዓለሙን የተወ” መኾኑን ነው፣ ሰላምታው የሚያወሳው፡፡
ዓፄ ካሌብ አንዴ ዓለማቸውን ንቀው እንደመነኑ፣ እንደገና ወደ ቤተ መንግስት ያልተመለሱ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን በመንግሥታዊ ሥልጣን ጉዳይ በወራሾች መካከል ውዝግብ ተፈጥሮ እንደነበር ይነገራል፡፡ እርሳቸው ወደ ምናኔ ከመግባታቸው በፊት ዐልጋውን እንዲወርስ የተናዘዙት ዝባዳር ውድድም ከተባለችው እቴጌ ለሚወለደው ገብረ መስቀል ነበር፡ “በነበረው ልማድና በመጽሐፈ ነገሥትም፣ ወራሽ የሚኾነው የበኩር ልጅ ነው፣ በማለት ታላቅየውን ቤተ እስራኤልን መኳንንቱ በዙፋኑ አስቀምጠውት ነበር፡፡
በሌላ በኩል ሠራዊቱና ቤተ ክህነት ደግሞ የካሌብን ኑዛዜ መጠበቅ አለብን ብለው ከፍተኛ ፍጥጫ ላይ ነበሩ፡፡ ሠራዊቱ ያለበት ኃይል አሸንፎ፣ ገብረ መስቀል፣ አፄ እለ ሐታዝ ተብሎ በ523 ዓ.ም ነገሠ፡፡ እርሳቸው ዞር ከማለታቸው ይህን የመሰለ ሽኩቻ ቢፈጠርም፣ ከዘጉበት በዓት ወጥተው ትርምሱ ውስጥ አልገቡም፡፡ አንዴ ጥለውት ከወጡበት ጨዋታ እንዳልተመለሱ ይታወቃል፡፡  
ከካሌብ ዘመን ኹለት መቶ ዓመቶች ከተቆጠሩ በኋላ፣ በነገሠ በግማሽ ቀን ዕድሜው በሞት ያለፈውን አይዜርን (779) ዓ.ም ተከትሎ የነገሠውን የዓፄ አልፌሬም ልጅ ውድድምን እናገኛለን፡፡ እርሱም እንዲኹ ሥልጣኑን ትቶ ነው የመነነው፡፡  
በ784 ዓ.ም ዓፄ ዳንኤል ተብሎ ነገሠ፡፡ በሥልጣኑ ላይ ግን 10 ዓመት ያህል ብቻ ነው የቆየው፡፡ በ794 ዓ.ም ዐልጋውን ትቶ ገዳም ገባ።
ከዚህ በኋላ ደግሞ፣ ወደ ላስቴዎች ዘመን ስንገባ፣ እንዲኹ ሥልጣናቸውን በፈቃድና በሕግ የተዉ ነገሥታትን እናገኛለን፡፡
 ብዙዎቹ ወደ ምናኔ ሲሔዱ የነገሥታት ንጉሥነታቸውንና ዐልጋቸውን በመተው ይታወቃሉ፡፡ አፄ ድልአድ የተባለው ግን ሥልጣኑን ለቅቆ፣ ወደ እርባታ ሥራ የገባ ንጉሥ ነበር፡፡ አፄ ድልአድ (1012-1052) ለአርባ ዓመታት ከገዛ በኋላ ልጁን ሀርበይን አንግሦ፣ ሣህላ ወደ ተባለው በረሃ ገብቶ፣ የፍየል ርባታን እንደ ያዘ በትውፊታዊው የነገሥታት ታሪክ ተጽፏል፡፡ እርሱን የተካው ሐርበይ፣ /አፄ ሐርየነ መስቀለ/ (1056-1069) ነበር፡፡
በላስቴዎቹ ዘንድ 40 ዓመት የመንግሥ ሕግ የነበረ ቢኾንም በ17 አመታቸው ነበር ሥልጣናቸውን ለቅቀው የወጡት፡፡ በላስቴዎቹ ነገሥታት ዘንድ የአንድ ነጋሽ በሥልጣን ላይ የመቆየት ጊዜው ከአርባ ዓመት እንዳይበልጥ ሕገ መንግሥት አድርገው ይዘውት ስለነበር፣ እያንዳንዱ 40 40 ዓመት ነበር የገዙት፡፡ በሕይወት መቆየት ከቻለ፣ ከ40 ዓመት በላይ መለፍ እንደማይቻል አውቀው፣ ሁሉም 40 ዓመቱን ቆጥሮ ከሥልጣኑ ዞር ይል ነበር፡፡
ይህ ሕግ “ህዳር 12 ቀን 919 ዓ.ም በአዜብ (አዘቦ) ንጉሥ” በኾነው በመራ ተክለሃይማኖት የተደነገገ ቢኾንም፣ እርሱ በ13 ዓመት የግዛት ዘመኑ ዐርፏል፡፡ በዚህ የትውፊት ታሪክ መሠረት፤ ቀጣዩ ጠጠውድም (አፄ ፀር ሠገድ (932-972)፣ ቀጣዩ ዣን ሥዩም ግርማ ሥዩም (972-1012)፣ መራሪ (አፄ ድል ነአድ) (1012-1052)፣ እየገዙ ሥልጣናቸውን ለቅቀዋል፡፡
አፄ ገብረመስቀል የተባለው ሐርቤይ፣ ንጉሠ ነገሥት በኾነ በ40 ዘመነ መንግሥቱ፣ የመልቀቂያው ጊዜ ስለደረሰ በፈንታው እንዲነግሥ ለወንድሙ ለላሊበላ ለቀቀ፤ በ1172 ዓ.ም፡፡
ላሊበላም እንዲኹ ለ40 ዓመት ገዝቶ ነበር፤ የገዛ ልጁን ትቶ የወንድሙን የሐርቤይን (አፄ ገ/መስቀል) ልጅ ነአኩቶ ለአብን ያነገሠው፡፡
ነአኩቶ ለአብም፣ “የሸዋ ዘመነ መንግሥት” ሊባል በሚገባው ዘመን መጀመሪያ ላይ ለነገሠው ለተስፋ ኢየሱስ (አፄ ይኵኖ አምላክ) 40 ዓመቱን እንደ ፈፀመ ሊያስረክብ አስቀድሞ በአቡነ ተ/ሃይማኖት አማካይነት ተዋውሎ ነበር፡፡ በዚያው መሠረትም ፈጸመ፡፡
እነዚህ ኹሉ፣ ልክ 40 ዘመናቸውን እንደፈጸሙ ለሕገ መንግሥታቸው ተገዥ ኾነው ሥልጣናቸውን ለቅቀዋል፡፡
ከሸዋው ዘመነ መንግሥትም እንዲሁ ኹለት ያህል ይገኛሉ፡፡ ኹለቱም ከዓፄ ዳዊት የተወለዱ፣ ከዓፄ ዘርዓያዕቆብ በፊት የገዙ ናቸው፡፡ አንዱ ልዑል ይስሐቅ ዳዊት ነበር፡፡ ዓፄ ገ/መስቀል ተብሎ በ1399 ዓ.ም ነግሷል፡፡ በ13ኛው ዘመነ መንግሥቱ ለወለደው ለልዑል እንድርያስ አስረክቦ መነነ፡፡
እንድርያስም በ1414 ዓ.ም ዓፄ ዣን ሃርባ ተብሎ ነገሠ፡፡ ዓፄ ዣን ሃርባ ከ6 ወር በኋላ ስለሞተ፣ አጎቱ ፣ የአፄ ዳዊት ልጅ ተክለ ማርያም (ዓፄ ሕዝብ ናይ) ነገሠ፡፡ ከ4 ዓመት በኋላ በ1419 ለልጁ ለሥርወ ኢየሱስ (ዓፄ ምህርካ ናኝ) ፈቅዶ ለቀቀለት፡፡ መልቀቁ እንጂ፣ ለቅቆ ምን እንደኾነ የተመዘገበ መረጃ አልተገኘም፡፡  
ወደ ጎንደሩ ዘመነ መንግሥት ስንገባ ደግሞ እነ ዓፄ ሱስንዮስን፣ እነ አድያም ሰገድ ኢያሱን፣ እነ ተክለሃይማኖትን እናገኛለን፡፡ ሱስንዮስ በሮማውያን ምክንያት የደረሰው የእርስ በርስ ጦርነት እንዲያከትም፣ “ፋሲል ይንገሥ” ብለው ሥልጣናቸውን ለቅቀዋል፡፡ አድያም ሰገድ ኢያሱም እንዲኹ ሥልጣናቸውን ፈቅደው ለቅቀዋል፡፡ የአፄ ተክለ ሃይማኖትን ከሥልጣን መልቀቅ በተመለከተ ጀምስ ብሩስ፤ “ነገረ ሥራቸው ኹሉ እንደ መነኩሴ ነበር፤ በመጨረሻ ዓለሙን ጣጥለው መንነዋል፡፡” ሲል በጽሁፉ አስፍሮታል፡፡
እነዚህ ኹሉ ነገሥታት ከሥልጣናቸው በፈቃዳቸው የለቀቁባት ሀገር ናት - ታላቋ ኢትዮጵያችን፡፡
ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ ከሥልጣን ለመልቀቅ ማመልከታቸው የሚታወቅ ነው። ለአገራችን ነገስታት፣ በገዛ ፈቃድ ከሥልጣን መልቀቅ፣ እንደ ዛሬው ብርቃቸው አልነበረም፡፡ የተለመደ ተግባራቸው ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ባለፈው ሳምንት ከሥልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡት ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ፤ ”በታሪክ  ሥልጣን በፈቃድ የለቀቁ የመጀመሪያው መሪ” የሚለው አገላለጽ ነው የቀድሞ ነገስታትን ታሪክ እንድናስታውስ ያስገደደን፡፡ ለዚህም ኢህአዴግ ምስጋና ይገባዋል፡፡

Read 859 times