Saturday, 24 February 2018 12:04

መሪያችንን ከፈጣሪ እንጠብቅ ወይስ ከምርጫ ኮሮጆ?

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

 … “መሪ ይወለዳል እንጂ አይገኝም” ብሎ በሚያምን ማህበረሰብ ውስጥ ነው ያለሁት። … እግዜር የመረጠው ነው መሪ የሚሆነው … ወይንም ኮከቡ ለመሪነት የተቀጠቀጠ ብቻ ነው መሪ የሚሆነው እንደ ማለት ይመስለኛል፡፡
ልክ እንደ ንጉስ ዳዊት በእረኝነት ተነስቶ እግዜር ካለ፣ ንጉስ ይሆናል ማለታቸው ነው፡፡ ዳዊትን የላከው እኮ ንጉሱ ነው፡፡ ሙሴም ቤተ መንግስት ውስጥ እንደ ልዑል ሆኖ ያደገ ነበር፡፡ እጣ ፈንታቸው ከኮከባቸው ወይንም ከእግዜር የተላከ ከሚመስለው ይልቅ ማህበረሰባቸው ውስጥ ካሳለፉት ተሞክሮ የመነጨ ይመስለኛል፤ እኔ፡፡
አንዳንድ ጊዜ የኮከብ ቆጠራ እንደ DNA (blue print) የመሰለ ባህሪ አለው፡፡ ለምሳሌ የሁለት መንትዮችን (Identical twins) አሻራ ዲ.ኤን.ኤ መፍታት የሚቸገርበት ጊዜ አለ፡፡ የኮከብ ቆጠራም በአንድ ሰዓት የተወለዱ መንትዮችን እጣ ፈንታ ለያይቶ መተንበይ አይችልም፡፡ … በኮከብ ቆጠራም.. በዲ.ኤን.ኤም መሪ የሚሆን ሰውን እጣ ፈንታ በማያሻማ መንገድ ማወቅ ያስቸግራል፡፡ ለዚህ ነው “ምርጫ” የሚባለው ነገር የግድ አስፈላጊ የሆነብን፡፡ … “ስዩመ እግዚአብሔር” ነኝ ወይንም “ኮከቤ ለመሪነት ተመርጧል” ያለ ንጉስ፤ ለልጆቹ ኮከቡን በዘረ መል (ደም) እያወረሰ የሚቆይበትን መንገድ ያፀናል፡፡ … መሪነትን በድምዕ፣ መሪነትን በኮከብ - ሁለቱም ተመሳሳይ አካሄድ ናቸው። ምርጫ የላቸውም፡፡ “እኔም መርጬ አይደለም የምመራችሁ -- እናንተም መርጣችሁ አይደለም በእኔ የምትመሩት … ስለዚህም አትመራመሩ!” የሚሉ ናቸው፡፡ “መሪ ይወለዳል እንጂ በማማረጥ አይገኝም” የሚሉ ሁሉ፣ ለዚህ ምርጫ ቢስ የአስተሳሰብ መዋቅር የተመቻቹ ናቸው፡፡
ሸርለኮምስ “… When you have eliminated the impossible, whatever remains however improbable must be the solution” ይላል፤ “የብየና ሳይንስ” (science of deduction) ህጉን በአጭሩ ሲያስቀምጥ፡፡ … እምነትና ምክኒያታዊነት የሚለያዩበትን ድንበር እያሰመረ ነው፡፡
“ኮከቡ ተቆጥሮለት” የመጣ መሪ ቢሆን እንኳን … የማይሆን ከሆነ “Impossible” ተብሎ ይወገዳል። … ኮከብ የሌለው ሆኖ ለስፍራው የተመቸ ከሆነ ደግሞ “መፍትሄ ልትሆን ትችል ይሆናል” ተብሎ ይሞከራል፡፡ … ምክኒያታዊነትና ምርጫ ሲኖር የጨዋታው ህግ ይሄ ነው፡፡ … ሳይሞክር ትክክል የሚሆንም ሆነ አይሆንም የሚባል ነገር ሁሉ ከእምነት እንጂ ከምክኒያታዊነት የመጣ አይደለም፡፡
… በቅርቡ አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ “በራሴ ፈቃድ ራሴን ኢሊሚኔት አድርጌአለሁ” ብሏል። “ኤሊሚኔት” ማድረግና አለማድረግ በግሉ ምርጫ የሚወሰን ሳይሆን እንደራሴ የሆነው ህዝብ መወሰን የነበረበት ጉዳይ ስለመሰለኝ ነው፡፡ … ግን ህዝብ መቼ፣ ማንን መጀመሪያውኑ ምራኝ ብሎ  ስልጣን ላይ  አወጣ? … የሚል ጥያቄ ያመጣል፡፡ … ምክኒያታዊ መሆን በማያስፈልግበት ነጥብ ላይ ለምን ምክኒያታዊ ለመሆን እንደምጋጋጥ አላውቅም። … የመሸነጋገል ባህሉን ትንሽ ልኮርኩመው ብዬ ነው፡፡
… አሁን ደግሞ ሌላ ሰው ሊሰየም እየተሞከረ ይመስላል፡፡ … ሁሉም በልቡ የሚያስበውን መሪ እዛው ፌስ ቡክ ላይ ሲያሞጋግስ እየተመለከትኩ ነው፡፡ “ማን ከማን ይሻላል?” ይመስለኛል ጥያቄው። … እዛው በገዢው ፓርቲና በአካባቢው ባለ ምህዳር ውስጥ አባል ሆኖ ያደገ ሰው ብቻ ነው ሊመረጥ የሚችለው፡፡ በዚሁ “ቁጥብ” የተመራጮች “ቅንፍ” ውስጥ ያሉ ሰዎችን “impossible” ወይንም “Improbable” ማለት ይቻላል ወይ? የሚለው ጥሩ ጥያቄ ይመስለኛል፡፡
ፓርቲው በጥቅሉ “የማይሆን ነው” ተብሎ፣ በዛው ፓርቲ ውስጥ ያለ አንዱ ጎን ደግሞ “መፍትሄ ነው” ሊባል ይችላል? የአመክኒዮ ግጭት አይፈጥርም?
በመሰረቱ ምርጫ በሌለበት ምክኒያታዊነት ሊኖር አይችልም፡፡ በምክኒያታዊነት ባንዲራ እነዛኑ (የኮከብ ቆጠራ፣ የእግዜር ሹመኛ) እምነቶችን ቀስ ብሎ ለማስረግ ነው  የሚሞክረው፡፡
… በመሰረቱ ጥሩ ምርጫ እንዲኖር “እውቀት” አስቀድሞ መኖር አስፈላጊ ነበር፡፡ መራጩ ስለሚመርጣቸው ነገሮች በደንብ ሳያውቅ ጥሩ ምርጫ ሊያደርግ አይችልም፡፡ “impossible” ብሎ ለማስወገድ የሚሞክረውን ነገር በድጋሚ ለመምረጥ ሲጣጣር ይታያል፡፡ በ “impossible” እና በ“whatever remains however improbable” በሚሉት ልኮች መሀል ያለውን ልዩነት ጠንቅቆ ሲያውቅ ብቻ ነው መምረጥ የሚችለው፡፡ … ወይንም ለመምረጥ የሚቋምጠው፡፡ … መራጩማ ህዝብ አይደለም፡፡
ህዝብ ለግዜው መምረጥም፣ የሚፈልገውን ጠንቅቆ ማወቅም አይችልም፡፡ ህዝብ ለጊዜው መቋመጥ ነው እጣ ፈንታው፡፡ እስካሁን የህዝብ ኮከብ አንድ አይነት እጣ ፈንታ ነው ያለው። መበደልና ጥሩ መሪ ፈጣሪ እንዲሰጠው መቋመጥ። ህዝብ እዛው እምነት ውስጥ ነው ያለው፡፡ መሪ ከፈጣሪ የሚወጣ ገፀ በረከት ነው የሚል ህልም ውስጥ፡፡
ቅድም የእጣ ፈንታ አስተሳሰቦች ከዘረ መል ጋር ተመሳሳይ ናቸው ብዬ ነበር፡፡ … አስትሮሎጂ ውድቅ እንደሆነ በቀላሉ የጠቆመው ፓይታጎረስ መሆኑ ይነገራል፤ ከሁለት ነጥብ አምስት ሺ ዘመናት ቀደም ብሎ፡፡ “ሁለት Identical twins አንድ አይነት እጣ ፈንታ ወይንም ህይወት አይኖራቸውም” ብሎ ተናግሯል፤ ሰውየው፡፡
ተመሳሳይ ዘረ መል ያላቸውም መንትዮች፣ ተመሳሳይ ህይወት አይኖራቸውም፡፡ ይህ የሚያሳየው ከዲ.ኤን.ኤ በበለጠ የህይወት ተሞክሮ (environment) ተመሳሳይ ዘረ - መልንም ቢሆን መልሶ የመስራት አቅም እንዳለው ነው፡፡ …
ይሄ ድምዳሜ በቀላሉ መታየት የሌለበት ነው። …. ከዚህ ድምዳሜ በመነሳት አንድ ሰው በዘሩ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ወይንም ሌላ ከሆነው በበለጠ የኖረበት ማህበረሰብ ወይንም ያሳለፈው ተሞክሮ ነው ማንነቱን በበለጠ የሚቀርፅለት ማለት ነው። … በአንድ ፓርቲ አስተሳሰብ ውስጥ በተለያየ ብሔርም ቢሆን ተደራጅተው የቆዩ አባሎች … ብሔራቸውንም … ህዝቡንም ከሚመስሉት ይልቅ (በተሞክሯቸው ምክኒያት) የቀረፃቸውን ፓርቲ በበለጠ ይመስላሉ ማለትም ነው፡፡ በአጭሩ ባህል … ከዘርም ሆነ … በእጣ ፈንታ ከሚሰጥ ኮከብም የበለጠ ሰውን የመስራት አቅም አለው የሚል አንደምታን ለእኔ ይሰጠኛል፡፡
የመሪ ዝርያ ቢኖር ኖሮ፤ “ምርጥ ዝርያ” ለማግኘት ብዙ ጣጣ ውስጥ ባልተገባ ነበር፡፡ ሴት ወንድን በአቋሙና ድምፁ ለፍቅር እንደምትመርጠው፣ መሪም በዝርያው ገና ሲወለድ እጣ ፈንታው ያለ ማንም ምርጫ “ሙሴ” አድርጎ ባጨው  ነበር፡፡
የሰለጠኑ “ጠረን አነፍናፊ” ውሾች በማሽተት የጠረኑን ባለቤት ብዙ ርቀት ተከትለው ማውጣት ይችላሉ፡፡ … በማሽተት የሰውን ዘረ መል የመለየት አቅም እንዳላቸው አጥኚዎች አረጋግጠዋል። … ምናልባት ወደፊት ማን፣ የማን ልጅ እንደሆነ በDNA ቤተ ሙከራ ሳይሆን በውሾቹ አፍንጫ የማረጋገጥ አጋጣሚ ሊፈጠርም ይችላል፡፡ የሚገርመው ውሾቹም ልክ እንደ ኮከብ ቆጠራው ሳይንስ በተመሳሳይ መንትዮች (Identical twins) መሀል ልዩነት አነፍንፈው ማውጣት አይችሉም። … ወንጀለኛን እንደ ማግኘት ጥሩ መሪን ማግኘት ቀላል አይደለም፡፡ ቢሆን ኖሮ የጥሩ መሪ ጠረንን (ጥሩ መሪ ብለን ከተስማማንባቸው) በማሽተት ተመሳሳይ ጠረን ወይንም ዘረ - መል ያለውን እንዲያፈላልጉልን ባደረግን ነበር፡፡ ያኔ ጠረኑን ለውሾቹ አሸትቶ እንዲፈልጉ የላካቸው አካል፣ እንደ ሚካኤል ስዑል “King maker” በተባለ ነበር፡፡ … ለነገሩ ጥሩ መሪ ማለት “ጥሩ ወንጀለኛ” ማለት ነው ብዬም የማስብበት ጊዜ አለ፡፡
… ግን ነገሩ እንደዛ ቀላል አይደለም፡፡ … የማፍረስና የመገንባት ሂደት ነው፤ ሳይንስ። … ትክክሉን ለመምረጥ መሞከርና ማወዳደር ያስፈልጋል፡፡ ሳይንስ ውስጥ “perfect” ብሎ ነገር የለም፡፡ … ስለሌለም ነው መሪዎች ወደ ስልጣን በሀይልም ሆነ በምርጫ ሲወጡና በህዝብ ተጠልተው ሲወርዱ የሚታየው፡፡
ዘንድሮ ደግሞ “ለእናንተ ስል ራሴን በራሴ ፈቃድ ከስልጣን አውርጃለሁ” የሚል መሪ ተከስቷል፡፡ … “ይበል የሚያሰኝ ጅምር ነው” ለማለት የማልደፍርባቸው ብዙ ምክኒያቶች አሉኝ። … ብዙ ነገሮች ወደ ግልፅነት ገና አልመጡም፡፡ … ለምን? እንዴት? እና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችል መረጃ፣ አሁንም (እንደ ቀድሞው) ከመጋረጃ ጀርባ እንደተደበቀ ነው፡፡ ግልፅነት፣ መረጃና እውቀት በሌለበት … ምርጫ ማድረግ የማይቻል ነገር ነው፡፡ በጥቅሉ ግን፤ በድብልቅል የአስተሳሰብ ውሀ ልክ ላይ ትክክለኛ ንባብ ለማግኘት የሚተራመሰው ይበዛል፡፡ በእምነት ላይ የተመሰረተ ምክኒያታዊነት - ወይንም በኮከብ ቆጠራ ላይ የተመሰረተ አመክንዮ ወይንም በዘረኝነት (ዘረ መል) ላይ የሚሾር እውነት - እንደ ምክኒያታዊ ምርጫ ማየት ይከብደኛል፡፡

Read 1716 times