Sunday, 25 February 2018 00:00

እውነተኛ ዴሞክራሲን ለመገንባት የተሻለ ዋስትና ያለው አማራጭ

Written by  ሳህሉ ቦኩ
Rate this item
(6 votes)

  መንደርደርያ
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንዳሉት፤ “ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ነው”። እዚህ አባባል ላይ ከፊቱ መጨመር ያለብን “እውነተኛ” የምትል አንዲት ቃል ብቻ ነው፡፡ በትክክልም እውነተኛ ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ስለሆነ ከልማትም በፊት ቅድሚያ ሰጥተን ልንሰራው፣ ከልማትም በላይ ዋጋ ከፍለን ልንጠብቀው የሚገባ እሴት ነው፡፡
አገራችን አሁን ያለችበት የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ የገባችው፣ከልማት ፈፅሞ አለመኖር የተነሳ በተፈጠረ የህዝብ ብስጭት ሳይሆን ህዝብ የሚለው እውነተኛ ዴሞክራሲ ስለሌለ ነው፡፡ ለዚህም ነው “ሰብአዊ መብቶቻችን ተጨፈለቁ፣ የህግ የበላይነት ተሸራረፈ፣ ሙስናው ቅጥ አጣ፣ ፍትሃዊ አስተዳደር የለም፣ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ራሱን እንጂ ህዝብን አይሰማም፣” የሚል እሮሮ የበዛው፡፡
መንግስትም በቅርቡ በተደጋጋሚ በሰጣቸው መግለጫዎች፤ ”ስህተቶች ሰርተናል፣ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ለማስተካከል እንሰራለን” ባለው መሰረት፣ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታቱና በጣም ዘግይቶም ቢሆን ማእከላዊ የተባለውን የማሰቃያ ቦታ መዝጋቱ አስፈላጊ ጅምሮች ናቸው፡፡ የተጀመረው ለውጥ የተሟላና የሚያዛልቅ እንዲሆን ከእነዚህ እርምጃዎች በተጨማሪ ሌሎች ወሳኝ የሆኑ ስራዎች መሰራት አለባቸው፡፡ አሁን አገራችን ያለችበት አጣብቂኝ “ህይወቴን የሚነካ ስለሆነ ይመለከተኛል” የሚል ዜጋ ሁሉ፣ ለችግሮቹ የአጭር ወይም የረጅም ጊዜ መፍትሄ ይሆናሉ የሚላቸውን ሃሳቦች በማዋጣት የድርሻውን ማበርከት ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ነው የምንገኘው፡፡  
በዚህ መሰረት ዜጎች በየጊዜው ከሚያቀርቧቸው ሃሳቦች መካከል በጠቃሚነታቸው ሚዛን የሚደፉት ተወስደው ተግባር ላይ ሊውሉና እውነተኛ ዴሞክራሲን በመገንባት ታላቅ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሊያግዙ እንደሚችሉ አምናለሁ፡፡ በዚህች አጭር ፅሁፍ  የተጠቀሰውን የመፍትሄ ሃሳብም ያቀረብኩት፣ ከዚህ መነሻ በመነጨ ነው፡፡
የሚያዋጣው እውነተኛ
ዴሞክራሲ ብቻ!
በአሁኑ ዘመን በርካታ አገሮች የውክልና ዴሞክራሲ ስርአት አራማጆችና ገንቢዎች እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ብዙዎች ይህን ስርአት እየመረጡ ያሉት ሲተገበር ቀላል የሆነ ስርአት ስለሆነ፣ ያለ ውጣ-ውረድ ፈጣን የኢኮኖሚና የማህበራዊ እድገትን ስለሚያመጣ፣ ሁሉንም ህዝብ አርክቶና ደስተኛ አድርጎ ማኖር ስለሚችል፣ ማናቸውም አይነት ችግሮችና ጥያቄዎች በሙሉ መልስ የሚያገኙበት ስርአት በመሆኑ አይደለም፡፡
በጥሩ ሁኔታ የተመሰረተና የሚመራ እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርአት፣ ከሌሎቹ ሁሉ ተመራጭ የሆነው በትክክል ሲተገበር የህዝብ ሰብአዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ወዘተ ፍላጎቶች፣ መብቶችና ምርጫዎች “እኛ እናውቅልሃለን” ከሚሉ ቡድኖች ጫናና ቁጥጥር ነፃ ሆኖ መተግበርንና ሲያስፈልግ ደግሞ መለወጥን የሚያስችል ስለሆነ፤ ለጥቂት አስርት አመታት ብቻ የሚቆይ ሳይሆን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚዘልቅ፣ የፖለቲካ መረጋጋትን የመፍጠር እድል የሚሰጥ ስርአት ነው፡፡ ይህም በመሆኑ አገር በእርስ-በእርስ የውስጥ ጦርነት እንዳትታመስ የተሻለ ዋስትና ይሰጣል፡፡ ከሌሎች የፖለቲካ አመራር ፍልስፍናዎች ጋር ሲነፃፀር፣ እውነተኛ ዴሞክራሲ የሚያዛልቅና አዋጪ ስርአት የሆነበት ስረ-መሰረታዊ ምክንያቱ ከሰው ተፈጥሮአዊ ፍላጎቶች ጋር የሚጣጣም ብቸኛ ስርአት በመሆኑ ነው፡፡
ተጨባጭ ማስረጃዎቹም እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርአት ከመገንባታቸው የተነሳ በመቶዎች ለሚቆጠሩ አመታት በተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ እየኖሩ ያሉት፣ በአለም ካሉ አገሮች ሁሉ በከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የእድገት ደረጃ ላይ የደረሱት፣ በሰብአዊ መብቶችና ነፃነቶች ጉዳይ ለአለም ሁሉ እንደ ምሳሌና መለኪያ የሚጠቀሱት የምእራብ አውሮፓና   የሰሜን አሜሪካ አገሮች ናቸው፡፡ እንደ እነ ቻይናና ራሺያ ያሉ አገሮች፣ ያለ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ባለፉት ጥቂት አስርት-አመታት ውስጥ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትና ድህነትን በከፍተኛ መጠን የመቀነስ ውጤት ቢያመጡም ህዝባቸው በሙሉ ሰብአዊ ነፃነቶች የሚኖሩባቸው አገሮች ስላልሆኑ፣ ከፊታቸው ገና ከባድ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል፡፡
ወደ አገራችን ስንመጣ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ዴሞክራሲን እየገነባሁ ነው ይላል፤ ህዝብ ደግሞ በኢትዮጵያ እውነተኛ ዴሞክራሲን የመገንባት ተስፋ ከጨለመ ቢያንስ 13 አመታት ሆኖታል ይላል - ከዝነኛው ምርጫ 97 ጀምሮ፡፡ አሁን ያለንበት የፖለቲካ ቀውስም ለዚህ ምስክር ስለሆነ እውነተኛ ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ገና መገንባት ያለበት ጉዳይ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡ ዴሞክራሲ እንዳለ የሚያስመስሉ እንደ ምርጫ፣ ጥቂት የግል ሚዲያዎች፣ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖር፣ ወዘተ እውነተኛ ዴሞክራሲ ለመኖሩ ማረጋገጫዎች አይደሉም፡፡ ስለዚህ እውነተኛውን የዴሞክራሲ ስርአት ለመገንባት በአዲስ ሃሳብ፣ አካሄድ፣ ቁጭትና ቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ከዚህ ትውልድ የሚጠበቅ የታሪክና የህሊና ግዴታ ነው፤ አማራጭም የለም። ኢህአዴግ ዴሞክራሲን ለመገንባት እስካሁን የሄደበት መንገድ ተፈላጊውን እውነተኛ ዴሞክራሲን ማምጣት ባለማስቻሉ በአዲስ አስተሳሰብ መጓዝን ይጠይቃል፡፡
ሁለቱ አማራጮች
እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርአትን እንደገና ስለመገንባት ስናነሳ፣ ያሉን ሁለት አማራጭ መንገዶች ይመስሉኛል፤ አማራጭ-አንድ እና አማራጭ-ሁለት እንበላቸው፡፡ አማራጭ-አንድ፤ የውክልና ዴሞክራሲ ስርአት አሁን በአለም ላይ በሚታወቅበት ሁኔታ በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች የተመሰረተውን የአወቃቀር ቅርፅና ዋና ዋና ባለድርሻ አካላት የሚሄዱበትን አካሄድ ምንም ሳይነካኩ እንዳለ ተቀብሎ፣ በዛ ላይ የተጠናከረ የህዝብ ተሳትፎ ከተጨመረበት እውነተኛ ዴሞክራሲ  ሊመጣ ይችላል ብሎ ተስፋ በማድረግና መጓዝ ነው፡፡ የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ይሻላል የምለው ግን አማራጭ-ሁለትን ሲሆን እሱም የውክልና የዴሞክራሲ ስርአት በሚታወቅበት የአወቃቀር ቅርፅ ላይ ተጨማሪ አንድ ክፍል (4ኛ ክፍል) በመፍጠርና በዋና ዋና የዴሞክራሲ ባለድርሻ አካላት አካሄድ ላይ ወሳኝ የማጠናከሪያ ስራዎች እንዲጨመሩ በማድረግ መሄድ ነው፡፡
የመጀመሪያውን አማራጭ መንገድ መከተልን በተመለከተ፣ በብዙ ታዳጊ አገሮች በተደጋጋሚ እንደታየው በሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እጦት ምክንያት ህዝብ ከሚገባው በላይ ተማርሮ የተከሰቱ አመፆችና ብጥብጦችን ተከትሎ ዴሞክራሲን እናመጣለን ያሉ አዳዲስ መሪዎች ወይም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወደ ስልጣን ቢመጡም በጣም ከጥቂቶቹ አገራት በስተቀር በበርካቶቹ ህዝብ የጠበቀውን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ነፃነት የማግኘት ምኞቱ፤ ቀስ በቀስ ውሃ እየበላው ቀልጦ ቀርቷል፡፡ ከነዚህም አገራት ውስጥ እነ ራሺያ፣ ግብፅ፣ ቱርክ፤ ሩዋንዳ ይገኙበታል፡፡
ወደ አገራችን መለስ ስንል ደግሞ ብዙ ወጣቶች ውድ የወጣትነት ዘመናቸውን ሰውተው፣ ከህዝብ ጋር በጋራ በመታገል ከፍተኛ የህይወት መስዋእትነትና የንብረት ውድመት ዋጋ ተከፍሎ፣ ሰው-በላው የደርግ ስርአት ወድቆና ኢህአዴግ ስልጣን መያዙን ተከትሎ፤ ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርአት ይገነባል ብለው ብዙዎች ከፍተኛ ተስፋ አድርገው ነበር፡፡ በኢህአዴግ አመራር ለመጀመሪዎቹ ጥቂት አመታት፣ መልካም የዴሞክራሲ ግንባታ ጅምሮች እንደነበሩ የማይካድ ቢሆንም በተለይ ምርጫ 97ን ተከትሎ ህዝብ የሰጠው ፍርድ፣ ኢህአዴግ እውነተኛ ዴሞክራሲ የመገንባት ስራውን አሽቀንጥሮ እንደጣለው አሳይቷል፡፡  
አሁን በአገራችን የዴሞክራሲ መብራት እንደ እነ ኤርትራ ከነአካቴው ባለመጥፋቱ ብቻ “ዴሞክራሲ እየገነባሁ ነው” ሊያስብል አይችልም፤ የዴሞክራሲ መዋቅሮቹ ከአሰልቺ ፕሮፓጋንዳ ጋር ቢኖሩም እውነተኛ ዴሞክራሲ ግን ቀስ በቀስ እየከሰመ ሄዷል፡፡ ይህ ማለት ኢህአዴግ አገርን የሚጠቅም ምንም ስራ አልሰራም ማለት አይደለም፡፡ ህዝብ ለኢህአዴግ ያጨበጨበለት በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ አንፃራዊ ሰላምና ፀጥታ በማስፈን፣ መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት፣ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን፣ ጥራቱ የወረደና የብዙ ዜጎችን የወደፊት ተስፋ ያቀጨጨ ቢሆንም በትምህርት የተገኘው ከፍተኛ ሽፋን፣ የጤና ማዳረስ በኩል ወዘተ የተሰራው ትልቅ ስራ ወዘተ--
እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርአትን በመገንባት ጉዳይ ላይ ግን ፈተና የሰጠው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ኢህአዴግ ፈተናውን ወድቋል ብሎ ውጤቱን አሳውቋል፡፡ ኢህአዴግም ይሄን አልካደም፡፡ ስለዚህ ራሱን እየገመገመና በደጋፊዎቹ እያስገመገመ ስር-ነቀል በሆነ ሁኔታ ራሱን አስተካክሎ ወደ ፊት ለመጓዝ መዘጋጀት ይሻለዋል፡፡ ወደ ቅርቡ የኋላ ታሪካችን መለስ ስንል፣ በአገራችን አፄ ኃይለ ስላሴም ሆነ ደርግ፣ ከውጪ አገራት ደግሞ የጋዳፊም ሆኑ የሙጋቤ መንግስታት እስኪወድቁ ድረስ “ትክክል ነን፣ ህዝብ ይደግፈናል፣ ህዝቡ ከጎናችን ነው፣ በእኛ ብቃት ያለው አመራር አገር አሳድገናል” ወዘተ ይሉ ነበር፡፡ ሲወድቁ ያየነው ግን ከጫፍ-እስከ-ጫፍ አገር ንቅል ብሎ ወጥቶ አምባገነኖቹ መውደቃቸውን በደስታና በፌሽታ ለቀናት ሲያከብር ነው፤ የህዝብ ስሜት በትክክል የሚታወቀው ሲለቀቅ ብቻ ነው። እነዚህ ሥርዓቶችና መሪዎች ከደረሰባቸው አይነት ሞትና ቀብር ኢህአዴግ ራሱን ለማዳን ፈጣን እርምጃ መውሰድ አለበት፤ በማስመሰል፣ በማለሳለስና የጊዜ ገደቡ በማይታወቅ ተሃድሶ እቀጥላለሁ ካለ ግን ከታሪክ ሰሪነት ታሪኩ ወደሚወራለት ድርጅት ራሱን ማሻገሩ አይቀሬ ነው፡፡
ቀደም ሲል ለምሳሌ ያህል በጠቀስናቸው አገሮች የተከሰቱት ውጤቶች የሚያሳዩን ጨቋኝ አገዛዞች ከተገረሰሱ በኋላ አማራጭ-አንድን መንገድ ይዞ “ዴሞክራሲያዊ ነኝ” የሚል አዲስ መንግስት በመከሰቱና ጥቂት ለውጦች በመታየታቸው እውነተኛ ዴሞክራሲ ይመጣል ብሎ ወደ እርግጠኝነት የቀረበ (probable) ድምዳሜ ላይ መድረስ እንደማይቻል ነው፡፡  በእነዚህ “ያልታደሉ” አገሮች ዴሞክራሲን መገንባት ያልተቻለው የዴሞክራሲ ፅንሰ-ሃሳብ፣ መዋቅሮቹ፣ ህጎቹ፣ አማራጭ ፓርቲዎች፣ የህዝብ ትግል፣ ወዘተ ስለሌሉ አይደለም፡፡ የመንግስትን ስልጣን የሚይዘው የአዲሱ ስራ አስፈፃሚ (አመራር) ስብስብ የተለያዩ ምክንያቶችን እየሰጠ ቀስ በቀስ ተመልሶ አምባገነን እንዳይሆን ራሱ ላይ ገደብ የሚጥል ውስጣዊ ህጋዊ ስርአት ማበጀት ባለመቻሉና ከዚሁ ጋር ተያይዞ መሰራት ያለባቸው የማጠናከሪያ ስራዎች ስላልተሰሩ ነው ባይ ነኝ፡፡
እውነተኛ የዴሞክራሲ ሥርዓት የመገንባቱ ሂደት እየተሳካላቸው ያሉ ጥቂት አገሮችስ እንዴት ሆነላቸው የሚለውን ስንመለከት የምንገነዘበው አንድ ዋና ቁም ነገር አለ፡፡ ባለፉት ጥቂት አስርት አመታት ከጨቋኝ (ከአምባገነን) ስርአት ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲ እየተጓዙ ያሉ እንደ ደቡብ አፍሪካና ናይጄሪያ ያሉ አገሮች አማራጭ-አንድን ይዘው ከሞላ ጎደል እየተሳካላቸው የመጡት ከዋናው ለውጥ በኋላ ስልጣን የጨበጡት አመራሮች ዴሞክራሲያዊ ስርአት እንዲያድግ በተግባር የታየ ከፍተኛ ቁርጠኝነትና ፈቃደኝነት ስላሳዩ ነው። እነዚህ ሁለት ነገሮች - በተግባር የታየ ከፍተኛ ቁርጠኝነትና ፈቃደኝነት - በጣም ውድ እሴቶች ናቸው፡፡
ከለውጥ በኋላ ስልጣን ላይ የሚወጡ ብዙ አዳዲስ መሪዎችና ግብረአበሮቻቸው እነዚህን እሴቶች ተጠቅመው እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርአት በመገንባት፣ ስልጣንን በሰላም ለቀጣይ የአገር መሪዎች ለመስጠት ፈቃደኞች አይደሉም፤ ለዚህም ነው በብዙዎቹ አገሮች ለውጡ ተመልሶ አፈር-ድሜ የሚበላውና ህዝብ እንደገና ለስቃይ የሚዳረገው። ለዚህ ነው አማራጭ-አንድ መንገድን መከተል፣ በአብዛኛው “የእድል ጉዳይ፣ የእምነት ጉዳይ፣ የተስፋ ጉዳይ” ስለሆነ ሁለተኛው አማራጭ መንገድ የተሻለ ዋስትና አለው የምለው፡፡
የተሻለ ዋስትና ያለው አማራጭ
አማራጭ-ሁለት መንገድን በተመለከተ ስንነጋገር፣ በቅድሚያ መረዳት ያለብን ቁልፍ ነገር፣ በበርካታ በማደግ ላይ ባሉና የውክልና ዴሞክራሲ ስርአት አራማጆች ነን በሚሉ አገሮች ስርአቱ በትክክል እንዳይሰራ መስመር የሚያስተው፣ ከሚገባው በላይ ስልጣን በእጁ ያለው ህግ አስፈፃሚው (ወይም ስራ አስፈፃሚው) ክፍል፣ በሌሎቹ ሁለቱ ክፍሎች ላይ ቀስ በቀስ በሚፈፅመው ጣልቃ የመግባትና የማኮላሸት ስራ የተነሳ ነው። በሌላ አባባል እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርአት እንዳይገነባ ዋነኛውን ሚና የሚጫወተው ስራ አስፈፃሚው፤ ህግ አውጪውንና የፍትህ አካሎችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በተለያዩ መንገዶች ቀስ በቀስ በመቆጣጠርና ሚዛን የማስጠበቅ ስራው እንዲበላሽ ምክንያት በመሆን ነው፡፡
ለዚህ መፍትሄው በተለመደው የውክልና ዴሞክራሲ መዋቅር ውስጥ አንድ ተጨማሪ (4ኛ) ክፍል መፍጠርና ከስራ-አስፈፃሚው ስራና ስልጣን ላይ ጥቂት ወሳኝ የሆኑትን ወስዶ ለአዲሱ ክፍል መስጠት ነው፡፡ አዲሱን ክፍል ”4ኛው ክፍል” ወይም ”ሚዛን አስጠባቂው ክፍል” ልንለው ወይም ሌላ ስም ልንሰጠው እንችላለን፡፡ ለዚህ ፅሁፍ ይህን አዲስ ክፍል ”ሚዛን አስጠባቂው ክፍል (በአጭሩ ሚአክ)” እንበለውና፣ ይህ ክፍል ስለሚኖረው ቁመና የሚታየኝን አብረን እንቃኘው፡፡
የሚከተሉት ስራዎች ስራ አስፈፃሚው በፍፁም የማይደርስባቸው የሚአክ ዋና ዋና ተግባራት ይሆናሉ፡፡ (እያንዳንዳቸው በውስጣቸው በርካታ ስራዎች ያላቸው በመሆኑ ዝርዝሩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ወደፊት የሚሰሩ ይሆናል፡፡)
የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማደራጀትና አሰራራቸውን መከታተል፣
አገራዊ የምርጫ መዋቅሮችን፣ ተቋማት ማደራጀትና አፈፃፀማቸውን መቆጣጠር፣
መንግስት የሚጠቀምባቸውን ጨምሮ ሚዲያዎችን በሙሉ ማደራጀትና አፈፃፀማቸውን መከታተል፣
የጠቅላይ አቃቤ ህጉን ክፍል ጨምሮ የፍትህ ስርአቱንና ተቋማትን አደረጃጀት መወሰንና አሰራራቸውን መከታተል፣
እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርአት ፅንሰ-ሃሳብና ትግበራ በአገሪቱ ሁሉ ወጥነት ባለው መልኩ ስር-እንዲሰድ ከላይ እስከ ታች የማስተማርና የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል እንዲገነባ የማድረግ ስራን ማከናወን፣
ህዝብ በስልጣን ላይ ባለው ስራ አስፈፃሚ ላይ በማናቸውም ጊዜ እምነት ካጣና ይህም በህግ በሚወሰን አግባብ ሲረጋገጥ፣ ህዝብ የመተማመኛ ድምፅ እንዲሰጥ ማድረግና ይህንንም ተከትሎ የሚመጣውን የለውጥ ውሳኔ ማስፈፀም፣
ስራ አስፈፃሚው ህገ-መንግስቱን የሚጥስ የህግ ማውጣት ወይም ሌሎች አፍራሽ ስራዎች እየሰራ ነው ብሎ ህዝብ ሲያምን ያንን ስራ መርምሮ ትክክል ሆኖ ከተገኘ ማስቆም ወይም ማናቸውም በስራ ላይ ያሉ ህገ-መንግስቱን የሚፃረሩ እንደሆኑ የሚታመንባቸው ህጎች ካሉ እንዲሻሻሉ ወይም እንዲሻሩ ማድረግ፣
ስራ አስፈፃሚው ሊያወጣቸው የሚገባ ነገር ግን ቸል ያላቸው ጠቃሚ ተብለው የሚታመንባቸው ህጎችና አሰራሮች በአገር ደረጃ እንዲተገበሩ ለህግ-አውጪው አካል የህግ-ሃሳቦችን ማቅረብና አፈፃፀሙንም መከታተል፣
የስራ አስፈፃሚውን ክፍል ደሞዝና ጥቅማ ጥቅሞች መወሰን፤ በየ5 አመቱም የክለሳ ስራ መስራትና ለህዝብ ማሳወቅ፣
የመንግስት ባለስልጣናትን የስራ አፈፃፀም፣ ህጋዊና ሞራላዊ አካሄዳቸውን፣ ያላቸውን ሃብትና ንብረት መግለጫ፣ ወዘተ ሪፖርት በየአመቱ ማዘጋጀትና ለህዝብ ማሳወቅ፣
የፀረ-ሙስና፣ የህዝብ እምባ ጠባቂና የሰብአዊ መብት መስሪያ ቤቶችን ማዋቀር፣ መሪዎቻቸውን ማስመረጥ/መምረጥ፣ አፈፃፀማቸውን መከታተልና ውጤቱን ለህዝብ መግለፅ፣ ወዘተ ይሆናል፡፡
በተጨማሪም ከፍተኛ አገራዊ አንደምታ ያላቸው ፖሊሲዎችና ከባድ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ (ለምሳሌ የአገር ሉአላዊነት መደፈር፣ የአገር መከላከያ ፖሊሲ፣ የትምህርት ፖሊሲ፣ የጤና ፖሊሲ፣ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ የገንዘብና የፊስካል ፖሊሲ፣ ወዘተ) ውሳኔ የሚሰጠው በስልጣን ላይ ባለው የፖለቲካ ፓርቲ(ዎች) እሳቤ ልክ ብቻ እንዳይሆን ከስራ አስፈፃሚው ጋር አብሮ በመሰብሰብ የውሳኔ ድምፅ መስጠት፡፡
ሌሎችም በሚአክ መሰራት አለባቸው የሚባሉ ስራዎች መኖራቸው ስለማይቀር ተካትተው፣ ከነዚህም ላይ የግድ መቀነስ አለባቸው የሚባሉ ካሉ ተቀንሰው ሊዘጋጁ ይችላሉ፤ መቀነስ ሲታሰብ ግን ጥንቃቄ የሚፈለገው አስተማማኝና ጥብቅ የዴሞክራሲ ስርአት እንዲፈጠር የሚያደርጉ ወሳኞቹን ነጥቦች ለይቶ ማወቅና እነሱን በፍፁም አለመንካትና አለማስነካት ነው፡፡  
ስራ አስፈፃሚው ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት በህግ ለሌላ ክፍል ሲያስረክብና ለውጡ በሌሎች ወሳኝ ማጠናከሪያዎች ታጅቦ ሲተገበር እውነተኛ ዴሞክራሲ በዘላቂነት እውን የመሆኑ ጉዳይ ከአማራጭ-አንድ መንገድ ይልቅ በጣም አስተማማኝ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ሰፊ ውክልና ይዞ እንዲመጣና ነገሮችን በጥልቀት ተመልክቶ ፍሬያማ ስራዎችን እንዲሰራ ሚአክ ከውስጡ በሚመረጥ አንድ ሊቀ-መንበርና ሌሎች አጋዦች የሚመራ ከ50 እስከ 60 አባላት ያሉት ቢሆንና ስብጥራቸውም ከምሁራኑ ክፍል፣ ከአገር መከላከያ፣ ከንግዱ ህብረተሰብ፣ ከእምነት ተቋማት፣ ከተለያዩ ዋና ዋና የአገሪቱ ክፍሎች፣ ወዘተ ቢሆን ጥሩ ይሆናል። አባላቱ የሚመረጡትም በአገራዊ አስመራጭ ኮሚቴ አማካኝነት በቀጥታ በህዝብ ይሆናል፤ ተጠሪነታቸውም ለህዝቡ ይሆናል፡፡ በስልጣን ላይ ያለው ስራ አስፈፃሚ፤ ለጉዳዩ አስፈላጊ ሀኔታዎችን ማመቻቸት እንጂ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሚአክ አባላት ምርጫ ውስጥ አይገባም።
ተመራጭ አባላት ጠንካራ በሆኑ  መለኪያዎች ተመዝነው ብቃት ያላቸው ብቻ ይመረጣሉ። መለኪያዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡- በትውልድ ኢትጵያዊያን መሆናቸው በማያሻማ መልኩ የሚረጋገጥ፣ በአገር ወዳድነታቸውና ለህዝብ ወገንተኛ በመሆናቸው የተመሰከረላቸው፣ በሰሯቸው አገርን የሚጠቅሙ ስራዎች ወይም በአመራራቸው ከፍተኛ ውጤት ያመጡ፣ በህዝብና በአገር ላይ ከዚህ በፊት ከፍተኛ ሊባል የሚችል ክህደትና ጉዳት ያልፈፀሙ፣ በህግ አክባሪነታቸው፣ በስነ-ምግባራቸውና በሞራላዊ ህይወታቸው ለትውልድ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ፣ እድሜአቸው ከ45-70 ክልል ውስጥ ያሉና የአእምሮ ጤንነታቸው የተረጋገጠላቸው፣ ቢያንስ ላለፉት 10 ተከታታይ አመታት በየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ምንም አይነት ተሳትፎ ያልነበራቸው፣ በሚአክ ለአገልግሎት ከተመረጡ በኋላም ለሚመጡት 10 አመታት በየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ መሳተፍ የማይችሉ፣ ህገ-መንግስቱንና የሚአክን አላማዎች በሚገባ የተገነዘቡና ለአገር ጥቅምና ለክብራቸው ሲሉ ሙሉ ጊዜአቸውን ሰጥተው ይህን ከባድ ሃላፊነት ያለበትን አገርን የማገልገል ስራ ለመስራት ፈቃደኛ የሆኑ፡፡
አንድ የሚአክ አባል የአገልግሎት ጊዜ 5 አመት ይሆናል፡፡ አንድ አባል ከ3 ጊዜ በላይ በተደጋጋሚ ማገልገል አይችልም፡፡  ሚአክ የራሱ የውስጥ አደረጃጀት፣ በቂ በጀት፣ የራሱ ፅ/ቤትና ቀጥሮ የሚያስተዳድራቸው ሰራተኞች ይኖሩታል፡፡ ሚአክ ስራውን በከፍተኛ ብቃት ለመወጣት የአገር ውስጥና የውጪ ባለሞያዎችንና አማካሪዎችን ከፍሎ ማሰራት ይችላል፡፡ ሚአክ የአገሪቱ የስነ-ምግባርና የአፈፃፀም ልቀት ምሳሌና ሞዴል መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ሚአክ የሚወስናቸው ማናቸውም ውሳኔዎች ህጋዊ አስገዳጅነት የሚኖራቸው ከአባላቱ 75 እጅ የደገፉዋቸው ውሳኔዎች ብቻ ይሆናሉ፡፡ እያንዳንዱ አባል እኩል ድምፅ ይኖረዋል፡፡ የሚአክ አባላት ሙሉ ጊዜአቸውን በዚህ ሃላፊነት ላይ የሚያጠፉ ስለሆነ ተመጣጣኝ ደሞዝ ሊከፈላቸው ያስፈልጋል፤ ደሞዝና ጥቅሞጥቅሞቻቸውን በተመለከተ በህግ አውጪው ወይም በሌላ አግባብ ባለው ክፍል ይወሰናል፡፡
በተሰጣቸው የስራና የስልጣን ክልል ውስጥ ከተሰጣቸው ሚዛን የማስጠበቅ ስራና ባህሪ የተነሳ አንዳንድ የሚአክ ውሳኔዎች ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ፍርድ ቤቶችም ሆኑ ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ውሳኔዎች ጋር የሚጋጩ ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔታ እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡ ይህ ሲከሰት የሚአክ ውሳኔዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከፍርድ ቤቶችና ከሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ውሳኔዎች በላይ ገዢነት እንዲኖረው ማድረግ የግድ ይመስለኛል፡፡ በዚህም መሰረት የአገሪቱ የፖሊስ፣ የአገር ደህንነት፣ ፍርድ ቤቶች፣ የአገር መከላከያ ሰራዊትና ሁሉም ዜጎች ለሚአክ ውሳኔ የመገዛትና ትእዛዙን የመፈፀም ህጋዊ ግዴታ አለባቸው። በእንዲህ አይነት ጊዜ ስራ አስፈፃሚው ወይም ሌሎች አካላት አንታዘዝም ሊሉ የሚችሉበት ሁኔታ ቢፈጠር፣ ውሳኔዎቹን በሃይል ለማስፈፀም የሚረዳው ተጠሪነቱ በቀጥታ ለሚአክ የሆነ 10 ሺህ የሚሆን የጦር ሃይል ይኖረዋል፡፡ ይህ ሃይል የሚመረጥበትና የሚተዳደርበት ሁኔታ ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል፡፡
ከዚህ እንደምንገነዘበው ሚአክን ማቋቋምና መምራት ውስብስብና አደገኛ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ይህን ፈርተን ሚሊዮን ዜጎችን ለሞት፣ ለውርደትና ለፍትህ-አልባ ስርአት አሳልፎ መስጠት በፍፁም ትክክል አይደለም፡፡ ታላቅ አገር መገንባት ከፈለግን፣ ሚዛን ለማስጠበቅና የምንፈልጋቸውን አንኳር ግቦች እንድንፈፅም እስከረዱን ድረስ ህጋዊ የሆኑ ውስብስብ ተቋማትና አሰራሮችን እየገነባን መሄድ ግድ ነው፡፡ የትኛው ታላቅ አገር ነው የተወሳሰበ ስርአት የሌለው?
እዚህ ላይ ጥቂት ጥያቄዎች ሊነሱ እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡ እነሱም፡- ሚአክ እንደ ስራ አስፈፃሚው እየተንሸራተተ የሚሄድ ሃይል ሊሆን እንደማይችል ዋስትናው ምንድን ነው? ሚአክ ለሱ ብቻ የሚታዘዝ ወታደራዊ ሃይል እንዲኖረው ማድረግ በአንድ አገር ሁለት ተፃራሪ አላማ ያነገቡ ወታደራዊ ሃይላት እንዲኖሩ ማድረግ አይሆንም ወይ? ችግር ፈጣሪስ ሊሆን አይችልም ወይ? ምላሾቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
ቁልፍ የሆነው መረዳት ያለብን ነገር፣ የሚአክ አባላት ሆነው የሚመረጡት ግለሰቦች ህዝብ የሚመርጣቸው፣ እንደ አገር ሽማግሌና ከዚያ ጋር ሊመጣጠን የሚችል ሰብእና ያላቸው፣ የአገር ጉዳይ በጣም ከብዶ የሚታያቸውና ህሊናቸው ከግል ጥቅም ይልቅ አገራዊ አደራ ጠባቂነትን ያስቀድማል ተብሎ የሚታሰቡ፣ የተሰጣቸውን ከባድ ሃላፊነት በብስለት፣ በብቃትና በቁርጠኝነት መወጣት ይችላሉ፣ ወዘተ ብሎ የገመገማቸውንና የሚያምናቸውን ነው፡፡ እንዲህ አይነት የከበረ ሰብእና ያላቸው ዜጎች ስብስብ በከፍተኛ ባለሙያዎች እየታገዙ ሲሰሩ የሚፈለገውን እውነተኛ ዴሞክራሲ በአገራችን እንዲመሰረት፣ እንዳይናጋና ስር-እንዲሰድ የማድረግ (ከዚህም የተነሳ ታላቅ አገርን የመገንባት) ውጤት ሊያመጡ እንደሚችሉ በብዙ እጅ እርግጠኛ መሆን ይቻላል። የዚህ አዲስ ህጋዊ ሃይል ዋና ተግባሩም ሆነ ሃላፊነቱ ስራ-አስፈፃሚው ክፍል ቀስ በቀስ በህግ ከተፈቀዱለት ተግባሮች እየወጣ አምባገነን እንዳይሆን መከላከል ነው። ከላይ በተጠቀሰው የምርጫ መስፈርት መሰረት የሚአክ አባላት ሆነው የሚመረጡት ዜጎች  እንደ አገር እንቁዎች የሚቆጠሩ በመሆናቸው ባልታደሉት አገሮች ህግ-አስፈፃሚው እንደሆነው እነዚህም ይሆናሉ ብሎ መስጋት ምክንያታዊ ያልሆነ ፍርሃት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይሄ ግምታችን ፈፅሞ ስህተት ሆኖ እነሱም አምባገነኖቹን ከተደባለቁ አገሪቱ የከበረች አገር ለመሆን ተስፋ የሌላት ብሎ መደምደም የሚቻል ይመስለኛል፡፡      
ሚአክ ለእሱ ብቻ የሚታዘዝ ወታደራዊ ሃይል የሚያስፈልግበትን ምክንያት ለመግለፅ በቅድሚያ የአምባገነኖች አደገኛ ባህርያትን በጥሞና ደጋግሞ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ አምባገነን መሪዎች አምባገነን ከመሆናቸው በፊት ለህዝብና አገር ጥቅም ተቆርቋሪና የነፃነት ታጋዮች ናቸው። በሂደት ግን የሚያመጡትን በጎ ውጤቶችና የደጋፊዎቻቸውን ብዛት ሲያዩ ጭንቅላታቸው እንደ እነሱ ያለ በእውቀትና በጥበብ የተሞላ ማንም የለም ብሎ ማሰብ ይጀምራል፤ ስህተት ሲሰሩና ልክ አይደላችሁም የሚላቸው ሲገጥማቸው፣ ከምክንያታዊነት ወጥተው ፍፁም በስሜታዊነትና በጀብደኝነት ቁጥጥር ስር ስለሚወድቁ ህዝብን እያስገደሉም እንኳ እነሱ ትክክል ያሉትን አላማዎች ከማሳካት ወደ ኋላ አይሉም፤ ከዚህም የተነሳ ቀስ በቀስ ህሊናቸው በቀላሉ የማይወቀስና እየደነደነ የሚሄድ ይሆናል፤ በጥላቻ የተሞሉ፣ ቂመኞችና ተበቃዮች ይሆናሉ፡፡ ወዘተ ወዘተ። ምናልባት በጥቂት አገሮች ካልሆነ በስተቀር እንዲህ አይነት የጥፋት ሰዎች ከስልጣን የሚወርዱት ወይ በከፍተኛ ብጥብጥና እልቂት ወይ ደግሞ ሲሞቱ ነው፡፡
ታዲያ እንዲህ አይነት መጀመሪያ ስልጣን ላይ ሲወጡ መልካም ነገሮችን የሚሰሩና የሚወደዱ ነገር ግን እየቆዩ ሲሄዱ ወደ አደገኛነት የሚቀየሩ ሰዎችን ለቅድመ-መከላከል በተዘጋጁ ወታደራዊ ሃይል እንጂ በምን መገደብ ይቻላል? “ሳይቃጠል በቅጠል” እንደሚባለው፣ ሚአክ የራሱ ወታደራዊ ሃይል የሚያስፈልገው አምባገነኖቹ ሰልጣን ላይ ሲቆዩ የሚያመጡትን “እሳት” ከእንጭጩ ለማጥፋት የሚጠቅም “ቅጠል” ሆኖ እንዲያገለግል ነው፡፡ ሊመጣ ያለ ችግርን ከእንጭጩ ከመከላከል የተሻለ ምን አማራጭ አለ? በጥሩ ሁኔታ የተዘጋጀ የአገር መከላከያ ሰራዊት ያላት አገር ምንም ያህል ቢቋምጥ በሌላ አገር በቀላሉ ለመደፈር የማትችለው የሰራዊቱ መኖር በሚሰጠው መልእክትና በስነ-ልቦናዊ ጫናው እንደሆነ ሁሉ፣የራሱ ሰራዊት ያለው ዴሞክራሲም፣ በአምባገነኖች በቀላሉ እንዳይደፈር ከሩቁ ጠንካራ መልእክት ስለሚያስተላልፍ አስፈላጊነቱ ሳይታለም የተፈታ ነገር ነው፡፡
አዎን ይህን ስናደርግ አንድ መንግስት ብቻ ባለበት አንድ አገር ውስጥ በሁለት የመንግስት ክፍሎች ለየብቻ የሚመራ የተለያየ ወታደራዊ ሃይል እየፈጠርን ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን በቅርበት ጉዳዩን ስናየው ነገሩ እንደዚያ አይደለም፡፡ ለሚአክ ብቻ የሚታዘዘው ወታደራዊ ክፍል በዋናነት ስራው፣ እውነተኛ የዴሞክራሲ መዋቅሮች፣ ተቋሟት፣ አሰራሮች ቀስ በቀስ እንዳይናዱ ጠባቂ ሲሆን ሌላኛው የአገሪቱ ወታደራዊ ክፍል ደግሞ በዋናነት የአገር ሉአላዊነት ጠባቂ ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ ለሚአክ የሚታዘዘው ሰራዊት፤ ህዝብን “ከውስጥ ወራሪ ሃይላት” የሚጠብቅ ሰራዊት ልንለው እንችላለን፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚታዘዘው ሰራዊት ደግሞ ህዝብን “ከውጪ ወራሪ ሃይላት” የሚጠብቅ ሰራዊት ነው፡፡ ሁለቱም የሰራዊት ክፍሎች ህዝብ በውስጥም በውጪም በነፃነት ተከብሮና ተፈርቶ እንዲኖር ታላቅ የጀግንነት ስራ የሚሰሩ፣ ለአንድ አላማ የቆሙ ሰራዊት ናቸው፡፡ ሰራዊቱ እርስ በእርሱ የሚቃረን አላማ ለማስፈፀም የሚሰራ ሰራዊት አይደለም፤ ይልቁኑ ህዝብ በሁሉም ረገድ ተከብሮ መኖር እንዲችል በሁለት ዋና ዋና “የነፃነት ግምባሮች” ላይ የቆመ፣ በሁለት “ጀነራሎች” የሚመራ አንድ ታላቅ ሰራዊት ነው፡፡ አንዱ የሌላው ስራ የተሟላ እንዲሆን የሚያደርግ ስራ የሚሰራ ነው። የሚቃረኑ አላማዎችንም ለማስፈፀም የሚሰሩ ስላልሆነ ችግር ይገደባል እንጂ ችግር ይፈጠራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ታዲያ ይህን ታላቅ ውጤት - ማለትም በውስጥም በውጪም ሙሉ ነፃነት ያለው የተከበረና የተፈራ ህዝብ - እንዲመጣ እስከረዳን ድረስ ሁለት ዋና ዋና ግምባሮች ላይ የሚሰለፍ ሰራዊት እንዲኖረን ከመወሰንና ከመተግበር ለምን እንቸገራለን?
ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርአትን መልሰን በመገንባት ታላቅ አገርን ለመፍጠር ካለምን ካልን ሚአክን በመፍጠር ማቆም የለብንም፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በዴሞክራሲ ስርአት ውስጥ ያሉት ወሳኝ ባለድርሻ አካላትን አደረጃጀትና አሰራራቸውን በተመለከተ መሰራት ያለባቸው ወሳኝ የማጠናከሪያ ስራዎች አሉ ባይ ነኝ፡፡ ለምሳሌ የመንግስት ስልጣን ለመያዝ የሚቋቋሙት የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ የፌደራል ክልሎች የመደራጃ መሰረታቸው ብሄር፣ ቋንቋ፣ ወይም ሃይማኖት ላይ የተመሰረተ እንዳይሆን በህግ መከልከል፣ ሚዲያዎችንና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ቢያንስ ለጥቂት ዓመታት በመንግስት በጀት መደገፍ፣ ነገር ግን ጠንካራ ተጠያቂነት እንዲኖርባቸው ማድረግ፣ ሲቪክ ማህበራትንም እንዲሁ -- ወዘተ--(እነዚህን በተመለከተ በሌላ ፅሁፍ እንመለስባቸዋለን፡፡)

ትግበራው
አማራጭ-ሁለትን ይዞ በመጓዝ እውነተኛ የዴሞክራሲ መሰረት ላይ የቆመች ታላቅ ኢትዮጵያን እንደገና ለመፍጠር ወደ ተግባር ስንገባ የሚከተሉትን ማድረግ ግድ የሚል ይመስለኛል። የተጀመረውን የፖለቲካ እስረኞችን የመፍታት ስራ መጨረስ፡፡ በውጪም ሆነ በአገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና በአገሪቱ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ቡድኖች በሙሉ ለእርቅና ለአዲስ የዴሞክራሲ ግንባታ ጉባኤ ጥሪ ማድረግ፡፡ እንዲህ አይነት ጉባኤ ማካሄድ ቀላል ስለማይሆን ከታዋቂ ኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በተጨማሪ የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ እና እውነተኛ የኢትዮጵያ ወዳጅ አገሮች ጋር በመሆን መመቻቸትና እነሱም በታዛቢነት የሚካፈሉበት መሆን ያለበት ይመስለኛል። የጉባኤው ዋና አጀንዳዎችም ሚአክ እንዴትና መቼ ይቋቋም (መንግስት ከመቋቋሙ በፊት ሚአክ መቋቋሙ ግድ መሆኑ ሳይረሳ)፣ በአዲሱ አቋም ለመጓዝ ህገ-መንግስታችንን ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ተፅእኖ ነፃ ሆኖ የማሻሻል ስራ እንዴት ይሰራ፣ ወሳኝ የሆኑ የዴሞክራሲ ባለድርሻ አካላትን የማጠናከሪያ ስራዎች የትኞቹ ናቸው እንዴትስ ይሰሩ የሚሉት ይመስሉኛል፡፡ ተከታዩ ጉዳይ ጉባኤው በሚስማማበት አካሄድና ቅደም ተከተል መሰረት ስራዎቹን መስራት ይሆናል፡፡ የለውጡ ሂደት በፍሬያማነት የሚደመደመው ከላይ በተጠቀሰው መሰረት በተሻሻለው ህገ-መንግስትና ተያይዘው በሚወጡት ህጎች ላይ ተመስርቶ፣ የአገር ውስጥና የውጪ ታዛቢዎች የሚከታተሉት፣ ቀጣዩ ምርጫ ነፃና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በአገሪቱ ሲካሄድና ያሸነፈው የፖለቲካ ፓርቲ ማንም ይሁን ስልጣን ተረክቦ አገሪቱን ማስተዳደር ሲጀምር ነው፡፡
በርካታ ዜጎች እንደሚሉት፤አዲስ የሽግግር መንግስት በመመስረትም ሆነ ጀነራል ፃድቃን ገ/ተንሳይ በቅርቡ ባቀረቡት ኢህአዴግ በስልጣን ላይ እንዳለ ኮሚሽን በማቋቋም ላይ ተመስርቶ፣ ወደ አዲስ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ውስጥ መግባት፣ ሁለቱም አማራጮች ነገና ከነገ ወዲያ አምባገነኖች እንዳይፈጠሩ ዋስትና ሰጪ ናቸው ብሎ መተማመን አይቻልም፡፡
አገራችንን ጨምሮ ከብዙ አገሮች ልምድ፣ አምባገነንነት የሚፈጠረው ቀስ በቀስ መሆኑን በተደጋጋሚ አይተን መልሶ እዚያው አዙሪት ውስጥ የሚከተንን አካሄድ ለምን እንመርጣለን? ይህን ካደረግን ከትላንቱ ተደጋጋሚ ጥፋታችን ምኑን ተማርነው? ታዋቂው ሳይንቲስት አልበርት አንስታይን እንዳለው፤አንድን ነገር በተመሳሳይ መንገድ ደጋግመን እያደረግን የተለየ ውጤት የምንጠብቅ ከሆነ እብድ ነን ማለት ነው፡፡
ከትውልድ ወደ ትውልድ ተሻጋሪ የዴሞክራሲ ስርአት በመገንባት፣ ታላቅ ኢትዮጵያን መፍጠር ከፈለግን፣ ዛሬ ማድረግ የሚገባን፣ ለውጥ እናመጣለን የሚሉንን ነባርና አዳዲስ የፖለቲካ መሪዎቻችንን፣ ለቅንአታቸውና መሰጠታቸው እያከበርን፣  በሚሰጡን ተስፋ ላይ ሙሉ በሙሉ መተማመን አቁመን፣ የአዙሪት ቀለበቱን የሚሰብርና ጉዟችን ወደ ፊት ለመገስገስ የሚያግዘንን ሚአክን ወይም አንደ ሚአክ አይነት ከውስጥ ሆኖ ዴሞክራሲን በሃይል እየታገዘ የሚያስጠብቅ ተቋም በህግ በማቋቋም ለተግባራዊነቱ መትጋት ይጠበቅብናል።
(ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻቸው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል::)

Read 3371 times