Saturday, 28 April 2012 12:55

ዳያስፖራዎች የእኛ ኢትዮጵያ አልተስማማቻቸውም!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(2 votes)

የኢቴቪን ኢትዮጵያ ይሞክሩዋ!

እኔ እኮ የኢህአዴግ ባለስልጣናትና ካድሬዎች አንዳንድ ነገሮችን የሚኮርጁት ከ”ፕሪሚየራችን” ብቻ ይመስለኝ ነበር፡፡ አሁን በቅርቡ ግን እርስ በእርስም እንደሚኮራረጁ ገባኝ፡፡ ለነገሩ አይፈረድባቸውም፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ “ባተሌ” እየሆኑ ስለመጡ ላያገኟቸውም ይችላሉ፡፡ ካላገኟቸው ደግሞ የሚኮረጅ ነገር የለም ማለት ነው፡፡ (ጉድ ፈላ!)

ከወር ገደማ በፊት ይመስለኛል፡፡ አንድ የዘይት ጉዳይ የሚመለከታቸው “ልማታዊ መንግስታችን” የሾማቸው ቱባ ሃላፊ፤ በኢቴቪ ብቅ አሉና እስካሁን ወደ አገር ውስጥ የገባውን የዘይት መጠን በሊትር ከገለፁልን በኋላ ወደ ዋናው አጀንዳቸው ገቡ - ይሄ ሁሉ ዘይት በመንግስት ተደጉሞ እየተገዛ ለምን እጥረት ተፈጠረ ወደሚለው ማለት ነው፡፡ እኔ በበኩሌ የዘይት እጥረት ምስጢሩ ግልጥልጥ ያለልኝ የዛን ዕለት ነው - ሃላፊው በኢቴቪ ሲያብራሩልን፡፡ እናም እንዲህ አሉ (እጠቅሳለሁ) “ችግሩ የሥርጭት ነው! በቂ የዘይት ክምችት አለን” እንዲህ ቅልብጭ ያለች መልስ ከየት ብልጭ አለችላቸው ይሆን? እርግጠኛ ነኝ ለ5 ባለስልጣናት የምትሆን መልስ ናት (ለ1 ዓመት ሻሩ ማለት ነው!)

አንዳንድ ጨለምተኞች ግን ዘይቱ ሺህ ጊዜ ቢከማች ምን ዋጋ አለው? ሲሉ ተስፋ ሊያስቆርጡን መሞከራቸው አይቀርም፡፡ እኔ በበኩሌ ግን ተስፋ አልቆርጥም፡፡ የሃላፊው መልስ አሳምኖኝ ግን እንዳይመስላችሁ! አይዲያዋን ስለወደድኩላቸው ነው!! ዘይቱን ባላገኘውም አይዲያ መውደድ እኮ መብቴ ነው፡፡

ሰሞኑን ደግሞ ሌላ ቱባ የስኳር ጉዳይ የሚመለከታቸው የመንግስት ባለሥልጣን፤ ለተወካዮች ም/ቤት ይገነባሉ ስለተባሉ የስኳር ፋብሪካዎች ሲያብራሩ ከቆዩ በኋላ እሳቸውም የእጥረቱን መንስኤ ገለፁልን፡፡ የቃላት ለውጥ እንጂ ከዘይቱ የእጥረት ምስጢር ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ እሳቸው እንዳሉት “ችግሩ የስርጭት እንጂ የአቅርቦት አይደለም” ክምችት በአቅርቦት ተቀይራ ከች አለች፡፡ አሁን ከአንባቢያን መሃል ጨከን ብሎ “ምን ትዘባርቃለህ ዘይት አለ የለም?” ቢለኝ… ዘይትም ስኳርም የለም ነው መልሴ፡፡ ለምን? በስርጭት ችግር!! ክምችቱ ግን በሽ ነው፡፡

የስኳርና የዘይቱስ ምስጢር ታወቀ! (የስርጭት ነው!) አሁን ግራ ያጋባን ደግሞ የስጋ ነው፡፡ ስንት ገባ ነው ያሉት? ኪሎው 120 ነው 140 ብር የተባለው? ቆይ ለምን እንዲህ ዋጋው የናረ ይመስላችኋል? በስርጭት ችግር ነው ብቻ እንዳትሉኝ! ባይሆን በሁለቱም ሊሆን ይችላል - በክምችትም በስርጭትም!! አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠበበ የሚባለው በስርጭት ችግር ይሆን እንዴ? መድረክ ፓርቲም ሁሌ መሰብሰቢያ አዳራሽ አጣሁ የሚለው በስርጭት ችግር ሳይሆን አይቀርም! አዳራሽማ ሞልቷል እኮ!

በሉ ወደ ሥጋው ጉዳይ እንመለስ:- እናላችሁ የሥጋ ዋጋ የናረው የቁም ከብቶች በኮንትሮባንድ ወደ ጐረቤት አገር በመሻገራቸው ነው ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ (እንደልባሽ ጨርቅ?) እኔ የምለው ግን ኢህአዴግ ድንበር መጠበቁን ትቶታል እንዴ? ታዲያ እነበሬ፣ እነበግ፣ እነፍየል በህገወጥ መንገድ ከአገር ሲወጡ ወዴት ነው እንኳን አይባልም እንዴ? ወይስ መብታቸው ነው ብሎ ነው? (በመብት ጉዳይ ቀልድ አያቅም ብዬ እኮ ነው!)

ባለፈው የፋሲካ ሰሞን የስጋ ዋና መናሩን በተመለከተ አንድ እናት ተማረው ለአንድ ጋዜጣ የተናገሩት እንዲህ ይላል:- “በከብት ብዛት ከአፍሪካ አንደኛ በሆነች አገር አንድ ኪሎ ስጋ ለምን በ120 ብር ይሸጣል? በወሬ ብቻ ጠገብን እንጂ ለእኛ ጠብ ያለልን ነገር የለም!”

አሁንስ እውነታቸውን ሳይሆን አይቀርም፡፡ ቆይ ነጋ ጠባ ከምንሰማው የ11.4 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ምን ጠብ ያለልን ነገር አለ? ይልቅስ ኢህአዴግ በዚህ ቁጥር የመጥራት ክፉ አባዜው ከአንዳንድ ለጋሽ አገራት ጋር እንዳያቃቅረን፡፡ እነሱ እንኳን ይሄን ባለሁለት ዲጂት ዕድገት ሰምተው ትንሽ እኮ ነው የሚበቃቸው “እናንተ ካደጋችሁ…እስቲ ደግሞ ወደ አላደጉት እንሂድ” ብለው ሸርተት ቢሉብንስ? እኔ በበኩሌ አጉል መጀገን አልወድም፡፡ ለምን መሰላችሁ? ሳይዙ መታበይ ምን ይሰራል? በዚያ ላይ ፕሮፖጋንዳ ለፖለቲካ እንጂ ለኢኮኖሚ እኮ ምንም አይፈይድም (ኢኮኖሚ በገሃድ ይታያላ!)

ይሄን ኢህአዴግ ነጋ ጠባ የሚነዘንዘንን የ11.4 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት በተመለከተ እኔ ምን አሰብኩ መሰላችሁ? ስንፈልግ ብራችንን ወደ ዶላር እንደምንቀይረው ሁሉ ባለሁለት ዲጂት የኢኮኖሚ ዕድገቱን ወደ ስንዴ፣ ወደ ዘይት፣ ወደ ስጋ፣ ወደ ጤፍ፣ ወደ ደመወዝ፣ ወዘተ የሚቀይርልን አንድ ባለሙያ ከኢንተርኔት ላይ እያፈላለግሁኝ ነው፡፡ በሳይንሳዊ መንገድ ይሁን በአስማት ግዴለኝም፡፡ እኔ የምፈልገው ውጤቱን ብቻ ነው!! ማን ያውቃል ኢንተርኔት ስበረብር ምስጢሩ እኔ ጋ አለ የሚል ተዓምረኛ ፈረንጅ ወይም ቻይና ከች ይል ይሆናል! (ሻርናታ!) መቼም ያደጉት አገራት ሁሉ አሃዙን የኢኮኖሚ ዕድገት ወደ ተጨባጭ ጥቅም መንዝረውት ነው ሰው የሆኑት! እንደኛማ እስከመቼ? ይኸውላችሁ - ባለሁለት ዲጂቱ ወደ ጥቅምና ሃብት ከተመነዘረልን እኮ 11.4 በመቶ አይደለም 8 በመቶ እድገት ራሱ ከበቂ በላይ ነው፡፡

ከዋጋ ንረትና ከኑሮ ውድነት እሮሮ ልገላግላችሁ ብዬ ወደ ሌላ አጀንዳ ልወስዳችሁ አሰብኩና ሰሞኑን ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ውይይት ስላደረጉት ዳያስፖራዎች ላወራችሁ ወሰንኩ፡፡ በኋላ ሳስበው ግን የእነሱም ውይይት ለካ በእሮሮ የተሞላ ነው ተብሏል፡፡

ይሁንና መቼም ከእኛ ሮሮ የዳያስፖራ ሳይሻል አቀርምና ወደ እነሱው እንገስግስ፡፡

እኔ የምለው ግን ለምንድነው እንደዚያ የጠመዱን? በቃ ደብረናቸው ብቻ ከሆነ ጣጣ የለውም…እኔ የፈራሁት ግን ምን መሰላችሁ? ድብቅ አጀንዳ እንዳይኖራቸው ነው! የሞለጩንን ብትሰሙ እኮ ፍርሃቴንና ስጋቴን ትረዱልኛላችሁ፡፡ አንድ ጥያቄ ግን አለኝ፡፡ ለመሆኑ የደም ምርመራ አድርገዋል? (የኤች አይቪ አልወጣኝም!) ከሽብርተኞች ጋር ንክኪ እንደሌላቸው፣ የኒዮሊበራሊዝም ተላላኪ አለመሆናቸው፣ ኪራይ ሰብሳቢነት እንደማይነካካቸው፣ ወዘተ መረጋገጥ ያለበት ይመስለኛል (አንዳንድ ቫይረሶች ከሰው ወደ ሰው ስለሚተላለፉ እኮ ነው)

እስቲ ዳያስፖራዎቹ የሞለጩንን እናስታውስ:- አንደኛ:- ዳያስፖራ ሰነፎች ናችሁ አሉን፡፡ ሌላኛው ደግሞ ነፃ ገበያ አታውቁም! (እኚህ እንኳ በደርግ ዘመን የተሰደዱ መሆን አለባቸው!) ከሁሉም ግን ብግን ያደረጉኝ ሥራ ግዴታ ይሁን ያሉት ዳያስፖራ ናቸው፡፡ (እኚህን ከፋሺስቱ ጣልያን ለይቼ አላያቸውም!) እንዴ የባሪያ ሥርዓትን የመመለስ ድብቅ አጀንዳ ያላቸው እኮ ነው የሚመስሉት፡፡ ሌሎችም ደሜን ያንተከተኩ ዳያስፖራዎች ነበሩ …ግን ተውኳቸው፡፡ ለምን መሰላችሁ? “ከአንደኛው ዓለም” ቢመጡም ምስኪን ወገኖቻችን ናቸው፡፡

የዳያስፖራዎች ወግ ተጀመረ እንጂ ገና አልተነካም፡፡ ከዚያም በፊት ግን አንድ ቀልድ ላስቀድምና ዘና ላድርጋችሁ፡፡

የቀልዱ መቼት እዚያው ዳያስፖራዎቹ አገር ነው፡፡ አማሪካ!! አንድ ወጣት መንጃ ፈቃድ ያወጣና በቀጥታ ወደ ሚኒስትር አባቱ ጋ በመሄድ አንዳንዴ መኪናቸውን የሚጠቀምበትን ሁኔታ እንወያይበት ሲል ይጠይቃቸዋል፡፡ አባት ልጃቸውን ወደ ራሱ ጥናት ክፍል ይዘውት ይሄዱና “አሁን እኔና አንተ እንደራደራለን፡፡ አንተ በመጀመሪያ በትምህርትህ ጥሩ ውጤት ታመጣለህ፡፡ የመፅሃፍ ቅዱስ ጥናትህ ላይ ትንሽ በርታ ትላለህ፡፡ እና ደግሞ ፀጉርህን ትቆረጣለህ፡፡ ከዛ በኋላ ስለመኪናው ልንነጋገር እንችላለን” በማለት ምላሽ ይሰጡታል፡፡ ከወር በኋላ ወጣቱ አባቱ ጋ በመሄድ “አሁንስ ማውራት እንችላለን?” ይላቸዋል፡፡ አባት አሁንም ልጁን ወደ ጥናት ክፍሉ ይወስዱትና “ልጄ፤ በእውነቱ በጣም ኮርቼብሃለሁ፡፡ በትምህርትህ ከፍተኛ ውጤት አምጥተሃል፡፡ የመፅሃፍ ቅዱስ ጥናትህን በትጋት ተከታትለሃል፡፡ ያልኩህን አንድ ነገር ግን አላደረክም”

“ምን?” ጠየቀ ልጅ

“ፀጉርህን አልተቆረጥክም!” ወጣቱ ለአፍታ በዝምታ ሲያስብ ቆየና “ዳድ ታውቃለህ - ነገሩ ሳስብበት ነበር፡፡ ሳምሶን እኮ ረዥም ፀጉር ነበረው፡፡ ሙሴም ረዥም ነበር ፀጉሩ፡፡ ኖህም እንዲሁ፡፡ ኢየሱስም ቢሆን ረዥም ፀጉር ነበረው፡፡” ሲል አስረዳ፡፡ አባቱም “ያልከው ትክክል ነው ልጄ! … እነሱ ግን የትም የሚሄዱት በእግራቸው ነበር፡፡”

በነገራችሁ ላይ እቺ ቀልድ ማስታወሻነቷ “መኪና ያለቀረጥ!” ላሉት ዳያስፖራዎች ይሁንልኝ!! (ቀልድ ወግ ደረሳት!) ዳያስፖራዎቹ መኪና ያለቀረጥ የጠየቁት ግን ሲሞላቀቁ እንዳይመስላችሁ፡፡ እዚህ አገር መኪና ከማስገባት አውሮፕላን ማስገባት ይቀላል፡፡ (300 ፐርሰንት እኮ ነው ታክሱ!)

በእርግጥ ሙልቅቅቅ ያሉም ዳያስፖራዎች ነበሩ (በቀጣዩ ውይይት የእኔም ስም መነሳቱ አይቀርም!)

ግን ወደው እኮ አይደለም፡፡ ተሳስተው ነው፡፡ ተሸውደው!! እየቀለድኩ እንዳይመስላችሁ፤ ከምሬ ነው፡፡ ዳያስፖራዎች በኑሮ ውድነትና በዋጋ ግሽበት ክፉኛ እየተናጠች ወደምትገኘው የጥንት የጠዋቷ ጦቢያ አይደለም እኮ የመጡት፡፡ (በነሱ ቤት!)

በትንሳኤ በዓል የስጋ ዋጋ በኪሎ 140 ብር ያሻቀበባት ጦቢያ አይደለም እኮ የመጡት (በነሱ ቤት!) እውነቴን ነው… ዳያስፖራዎቹ ተሸውደዋል!! የሸወዳቸው ደግሞ ማን መሰላችሁ? “ጀግናው ኢቴቪ” ነው፡፡

እነሱ አልመው የመጡት የኢቴቪን ኢትዮጵያ ነው - “ኢትቪዮጵያ” የሚሏትን፡፡ እነሱ በያሉበት ዓለም ኢቴቪ ሲሞላቸው የነበረችውን ኢትዮጵያን ነው አስበው ከች ያሉት! የኢቴቪን የምናብ ልጅ ማለት ነው፡፡ እናም በውይይቱ እንደታዘብኳቸው የእኛዋ ኢትዮጵያ ፈፅሞ አትመቻቸውም፡፡ ለዚህ እኮ ነው - የሙያ ችሎታ የላችሁም፣ ሥራ አትወዱም፣ ሥነ ምግባር ይጐድላችኋል፣ ኋላቀር ናችሁ ወዘተ ወዘተ እያሉ የወረዱብን፡፡ እኛ ግን ይቅር ብለናቸዋል፡፡ ደግ ስለሆንን ግን አይደለም፡፡ ኢቴቪ ስላሳሳታቸውና “ከአንደኛው ዓለም” ቢመጡም ወገኖቻችን ስለሆኑ ነው፡፡ በመጨረሻ ምን እንዳማረኝ ነግሬአችሁ ልሰናበት፡፡ ዳያስፖራ መባል በጣም ነው ያማረኝ!

ለ3 ወር አሜሪካ እንድቀመጥ ስፖንሰር የሚያደርገኝ ባገኝ እኮ በቃ “ዳያስፖራ” ተብዬ ከች እል ነበር - አገሬ!!

 

 

Read 3665 times Last modified on Saturday, 28 April 2012 13:01