Sunday, 25 February 2018 00:00

“ከታሰሩብን ግማሽ ያህሉ እንኳን አልተፈቱልንም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

  · ከ120 ታሳሪዎች 30 ብቻ ናቸው የተፈቱት - መኢአድ
    · ከግማሽ በላይ የታሰሩ አባላት አልተፈቱም - ሰማያዊ

    ሰማያዊ ፓርቲና መኢአድ፤ ከታሰሩባቸው አመራርና አባላት ግማሽ ያህሉ እንኳ እንዳልተፈቱላቸው ሰሞኑን ባወጡት መግለጫ አስታወቁ፡፡ ከታሰሩባቸው 120 አባላት እስካሁን የተፈቱት 30 ያህል ብቻ መሆናቸውን የመኢአድ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡   
የፓርቲው አመራር አባላት የነበሩት መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ፣ ዘመነ ጌቴ፣ ለገሠ ወ/ሃና እና ስንዱ ዱቤን ጨምሮ ከ80 በላይ አመራር አባላት አልተፈቱም ብለዋል - አቶ ሙሉጌታ፡፡
ከሰማያዊ ፓርቲ ደግሞ የቀድሞ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዮናታን ተስፋዬ፣ አግባው ሰጠኝና አንጋው ተገኘን ጨምሮ ከግማሽ በላይ የታሰሩ አባላት አለመፈታታቸውን ፓርቲው አስታውቋል፡፡ በሽብር የተከሰሱ ሁለት የዋልድባ ገዳም መነኮሳትም ክሳቸው አለመቋረጡንና ታስረው እንደሚገኙ የመኢአድ ም/ፕሬዚዳንት ጠቁመዋል፡፡   
መንግስት በቃሉ መሰረት ቀሪ ታሳሪ ፖለቲከኞችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ ጠይቀዋል -  ሰማያዊ ፓርቲና መኢአድ በመግለጫቸው፡፡
በሌላ በኩል፤ አብዛኞቹ የወልቃይት ኮሚቴ አባላትና በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የተከሰሱት እነ ጀነራል አሳምነው ፅጌ ሰሞኑን ከእስር መለቀቃቸው ታውቋል፡፡ የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ኮሚቴ አመራር አባላት የሆኑት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ጨምሮ፣ አቶ አታላይ ዛፌ፣ መብራቱ ጌታሁን፣ ጌታቸው አደመ፣ ተሻገር ወ/ሚካኤል እንዲሁም 12 የኮሚቴው አባላት መለቀቃቸውን የጠቆሙት ምንጮች፤ ጎይቶም ህዝቃይ፣ ነጋ የኔነውና ፈለቀ ገብረህይወትን ጨምሮ  ቀሪ የኮሚቴ አባላት ከእስር አለመፈታታቸውን ተናግረዋል፡፡
 በጎንደር በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ምክንያት የታሰረችው ወጣቷ ንግስት ይርጋ እንዲሁ ባለፈው  ረቡዕ ከእስር የተለቀቀች ሲሆን አብረዋት ታስረው የነበሩ የሰማያዊ እና መኢአድ ፓርቲ አባላት ያሬድ ግርማ፣ አለምነው ዋሴ፣ አወቀ አባተና በላይነህ አለምነህም መፈታታቸው ታውቋል፡፡
በተመሳሳይ ከእስር እንዲለቀቁ ባለፈው አርብ የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም የተወሰነላቸው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በማድረግ የሽብር ወንጀል እስከ እድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸው ጀነራል ተፈራ ማሞ፣ ጀነራል አሳምነው ፅጌ፣ ኢንጂነር መንግስቱ አበበ፣ ኮሎኔል አበረ አሰፋ፣ ኮሎኔል ሰለሞን አሻግሬ፣ ሻለቃ መኮንን ወርቁ፣ ሻለቃ መሰከረ ካሳ፣ ሻለቃ ምስጋናው ተሰማና ኢንስፔክተር አመራር ባያብልን ጨምሮ 14 ግለሰቦች ከትናንት በስቲያ ከ9 ዓመት እስር በኋላ ከዝዋይ ማረሚያ ቤት መውጣታቸው ታውቋል፡፡

Read 4039 times