Sunday, 25 February 2018 00:00

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዝርዝር የአፈፃፀም መመሪያ ወጥቷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

ከአርብ የካቲት 9 ቀን 2010 ጀምሮ ለተጣለው የ6 ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ባለፈው ረቡዕ ዝርዝር የአፈፃፀም መመሪያ ይፋ ተደርጓል። መመሪያው አዋጁን ለማስፈፀም የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ስለሚወስዳቸው እርምጃዎችም ይገልጻል፡፡ ኮማንድ ፖስቱ በሀገሪቱ 8 ቀጠናዎች መደራጀቱ የተጠቆመ ሲሆን  ቀጠናዎቹም የየራሳቸውን የአፈፃፀም መመሪያ ያዘጋጃሉ ተብሏል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሚቆይባቸው በሚቀጥሉት 6 ወራት ውስጥ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን የሚጥስ ተግባር መፈፀም፣ የህዝቦችን መቻቻልና አንድነት የሚሸረሽር ተግባር መፈፀም፣ ከሽብርተኛ ደርጅቶች ጋር ግንኙነት ማድረግና ድጋፍ ማድረግ ክልክል መሆኑ በመመሪያው ተቀምጧል፡፡
በፀጥታ ጉዳይ ከኮማንድ ፖስቱ ፍቃድና እውቅና ውጪ መግለጫ መስጠትም ተከልክሏል። የወጡትን አዋጆችና ማስፈፀሚያዎችን በመቃወም ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ ማሰራጨትና ከተፈቀዱ ክልሎች ውጪ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስም ከተከለከሉት ተግባራት አንዱ ነው፡፡ የትራንስፖርት ሂደትን ማወክ፣ የመሰረተ ልማትና የልማት ተቋማትን መጉዳት፣ የህግ አስከባሪዎችን ስራ ማወክ፣ ያልተፈቀደ ሰልፍና ስብሰባ ማካሄድ፣ ትምህርትን ማወክ፣ በስፖርት ማዘውተሪያ አድማ ማድረግ፣ የሁከት ቅስቀሳ ማድረግ፣ የሸቀጦች ዝውውርን ማገድ፣ ህዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላትን ማወክና በመድረኮቹ ላይ ፖለቲካዊ አጀንዳዎችን ማስተጋባት ክልክል ነው ተብሏል፡፡
የጦር መሳሪያ ህዝብ ወደ ተሰበሰበበት ይዞ መግባት፣ በኢንቨስትመንት አካባቢዎች ኮማንድ ፖስቱ ከፈቀደው ሰዓት ውጪ መንቀሳቀስም ተከልክሏል፡፡ የፀጥታ አካላትም ይህን ተላልፈው በተገኙ ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ተጠቁሟል፡፡  

Read 1592 times