Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 28 April 2012 12:50

“እንቅቡም ሰፌዱም…”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

በእርግጥ የሆነ ነገር ስሙኝማ…ባልና ሚስቱ ይጋጩና ጠዋት ሁለቱም አኩርፈው ከቤት ይወጣሉ፡፡ እናላችሁ…ምሽት ላይ እሷም ከሌላ ወንድ ጋር፣ እሱም ከሌላ ሴት ጋር ወደ መዝናኛ ይሄዳሉ፡፡ ታዲያማ…አለ አይደል…”ቅዳሴ ቢያልቅበት ቀረርቶ ጨመረበት…” እንደተባለው ቀሺም ቄስ…ታሪክ ሲያልቅበት ቅዠቱን ሁሉ ጽሑፉ ውስጥ እንደሚጠቀጥቀው የእኔ አይነት “ፀሐፊ ተብዬ” ሥራ አይነት ነገር የተከሰተው ይሄኔ ነው፡፡ አንደኛ ነገር ሁለቱም ጥንዶች የገቡት አንድ የባህል ምግብ ቤት ነው፡፡ ሁለተኛ ነገር (ይሄኛው የእውነተኛ ታሪክና የሳይንስ ፈጠራ ቅልቅል ይመስላል) ተይዞ የመጣው ሌላኛው ወንድና ተይዛ የመጣችው ሌላኛዋ ሴት ባልና ሚስት ነበሩ፡፡ መጀመሪያ ምንም እንደሌለ ሁም ዝም ብለው ለመተላለፍ ሞክረው ማን እንደጀመረው ባልታወቀ ትንኮሳ ቤቱ ቀውጢ ሆኖ ነበር አሉ፡፡ (ስክሪንፕሌይ ፀሐፊዎች በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ብላችሁ ፊልም ብታደርጉት አንቃወምም፡፡)

እርስ በእርስ በማይተማመኑና አንደኛቸው ሌላኛቸውን በሚጠራጠሩ ተቃራኒ ጾታዎች ብዛት ዓለም ላይ ያለን ደረጃ ይነገረንማ! የግሎባላይዜሽን ብቻ ሳይሆን የጥርጣሬ ዘመን ሆኖላችኋል፡፡

ስሙኝማ…አንዳንዴ ጥሎብን የድሮ ናፋቂ ምናምን ያደርገን የለ…ይቺ የጥንት ስንኝ ትዝ አለችኝማ!

መሄዴ ነው መልቀቄ ነው ከአገር፣

እንቅቡም ሰፌዱም ነካካኝ በነገር፡፡

ያኔ፣ ግጥም ማለት “የመጨረሻ ሆሄያት ፎቶ ኮፒ” ብቻ ባልነበረበት ዘመን እንዲህ ይሉ ነበር እላችኋለሁ፡፡ ልክ ለዚህ ዘመን በልክ የተሰፋች ስንኝ አትመስልም! ተጠራጣሪነት ሲበዛ ሰው ብቻ ሳይሆን እንቅቡና ሰፌዱም በእኛ ላይ የሚያሴር ነው የሚመስለን፡፡

እኔ የምለው…አንዳንዴ ግርም አይላችሁም! ማለቴ፤ እንዲህ ጥርጣሬ በበዛበት ዘመን፤ ሁሉም ጠርጣሪ ሁሉም ተጠርጣሪ በሆነበት ዘመን እንዴት ተደርጐ ነው ሥራስ የሚሠራው? ወይ ወደፊት የሚወጡ ቢ ፒ አር አይነት ነገሮች ላይ… “አጉል ጥርጣሬን ስለመከልከልና አጉል ተጠራጣሪዎች የሚቀጡበት ዝርዝር ሁኔታ” የሚል አንቀጽ ይካተትልና! ብቻ ምን ያደርጋል…ማንም የማይጠረጥር በሌለበት እንዲህ አይነት አንቀጽ ማን ሊጽፍ ነው ያሰኛል፡፡

ምን መሰላችሁ…ምልክት የሌለው፣ መነሻ የሌለው ጥርጣሬ በዛ!

እናላችሁ…ጥርጣሬ ከመብዛቱ የተነሳ የምንፈልገውን ነገር ለማድረግ እንኳን አሥሬ ለክተን አንዴ ሳንቀድ እንደገና ሌላ አሥር ጊዜ እንለካለን፡፡ ሸሚዝ መለወጥ ባስፈለገ ቁጥር “ደግሞ ከምን ጋር ያያይዙብኝ ይሆን?” የሚባልበት ጊዜ አያሳዝናችሁም!

ስሙኝማ …ድሮ እኮ አለ አይደል ቡና ቤት ምናምን የሆነ ሰው ጐናችሁ ያለውን ባዶ መቀመጫ እያሳየ፤ “እዚህ ሰው አለ?” ሲል “የሚያጫውተኝ መጣ” በሚል መንፈስ በደስታ “የለም” ትሉ ነበር፡፡

ጥርጣሬ የለ፤ “ማን ላከብኝ?” የለ፣ “የመደብ ጀርባው ምን ይሆን?” የለ! እንደውም እንደነገሩ ገና እንደተቀመጠ… “የዚህ ቤት ሴቶች እኮ የሌሎቹን ሴቶች ዳሌ ሁሉ ሰብስበው የወሰዱት ነው የሚመስለው!” እያላችሁ በ”ወንድ ወሬ” ትሳሳቃላችሁ፡፡ በቃ…ይኸው ነው፡፡ ከ”ጀርባ” ከ “ጓሮ” ከ”ዕቃ ቤት” ቅብጥርስዮ የሚሉት አጉል ጥርጣሬ አልነበረማ!

ዘንድሮ ግን የሆነ ሰው…”እዚህ ወንበር ላይ ሰው አለ?” ሲል ከእግር እስከ ራሱ ይታይና “ይሄ ደግሞ ማነው?” ሆኗል ነገርዬው፡፡ ምን አለፋችሁ… “አጅሬ ማን ልኮት ነው?” አይነት መላ ምት ይደረደራል፡፡ እኔ የምለው…ሻይ ቤቱ ግጥም ብሎ ሞልቶ ያለችውን አንዲት ወንበር…አለ አይደል…”እዚህ ወንበር ላይ ሰው አለ?” ማለት ምን “ስውር ሴራ” ነገር ሊኖረው እንደሚችል አንድዬ ይወቀው፡፡ የዛች ሴትዮ ዳሌ ምናምን መባባልማ ተዉት “አሁን ካልጠፋ የሰውነት ክፍል …ዳሌዋን የጠቀሰልኝ ምን ለማለት ነው?” አይነት ጥርጣሬ ይመጣላችኋል፡

ለነገሩ…አንዳንዴ እንክት አድርጐ የሚያጠራጥር መአት ነገር አለ! ምን መሰላችሁ…ካፌ ውስጥ ያለው ወንበር ሁሉ ባዶ ሆኖ እናንተ ያላችሁበትን መቀመጫ መርጦ የሚመጣ ሰው ቢጠረጠር አይገርምም፡፡ መጥቶ እኮ ደግሞ ሊናገር ነው… ልክ የሦስተኛው ራይክ የስታሊንግራድ ጦር አዛዥ ይመስል መጨማደድ የሚችሉትን የሰውነት ክፍሎቹን በሙሉ ያጨማድድላችኋል፤ (በነገራችን ላይ ይህ “የቅብ አራዳ” መኮሳተርን እንደ ስታንድ አፕ ኮዲ እያየነው እንደምንሳሳቅበት ይኸው ምስጢር አወጣሁ፡፡ ስሙኝማ…ቅብ አራድነት በስሙኒ አንድ ዳውላ እየተሸጠ መሆኑን ብጠረጥርም ቦታውን የሚጠቁመኝ እየፈለግሁ ነው፡፡)

ለነገሩ እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ያለንበት ጊዜ “ቅርጫቱ ውስጥ ከጥቅም ውጪ የሆኑ ቲማቲሞች…” የበዙበት ዘመን ነው፡፡ አይደለም የማታውቁት ሰው…ከልጅነት እስከ እውቀት “ሆዴ! አንጀቴ!” የምትባባሉት ሰው ድንገት ዶሮ አንዴ ሳይጮህ ስምንት ጊዜ አሳልፎ ሲሰጣችሁ ታያላችሁ፡፡

ስሙኝማ…”የሁሉም ሃጢአቶች፣ ችግሮች መነሻና መድረሻ የግል ጥቅም ነው፣” የሚባለው ነገር…አለ አይደል…እንዴት ሸጋ ነገር መሰላችሁ፡፡ ምንም አይነት አለመግባባት በሉት “ፍልሚያ” በባይዶዋ አድርጐ ይሽከርከር፣ በማዳጋስካር ቀለበት ሠርቶ ይምጣ…የሆነ ቦታ ስትደርሱ የግል ጥቅም መሆኑን ታያላችሁ፡፡

እናማ … ይሄን ነገር መናገር ያለብኝ ይመስለኛል፡፡ አሁን አሁን በአንዳንድ ኃይማኖቶች ህዝቡ ዘንድ በግላጭ በሚደርሰው ሚዲያና ህዝቡ ዘንድ በሽፍንፍን የሚደርሰው ክርክር … (እሰጥ እገባ ያልከው ወዳጄ … ተመችቶኛልማ!) አርቲፊሻል ነገሩ እየበዛብን ነው፡፡ ነገርዬውን ፈረንጆች “ሪዲንግ ቢትዊን ዘ ላይንስ” በሚሉት መንገድ ስትመነዝሩት “የኃይል ምንጩ” የግለሰቦች ጥቅም ሆኖ ታገኙታላችሁ፡፡ የ”ዶግማ” ጉዳይ ከሆነማ “አፈር ይብላ!” “ዓይንህ ጨለማ እግርህ ቄጠማ ያድርገው!” ምናምን አይነት ዘለፋ አያስፈልገውም፡፡ ሁሉም ወገን መከራከሪያውን አቅርቦ የሚመለከተን የራሳችንን ውሳኔ ብንሰጥበት አሪፍ ነው፡፡

እናላችሁ … የእኔ ብቻ ነገር ሲበዛ በዛው መልክ ሌላውን ሰው ሁሉ፤ ሲብስብን ደግሞ ጥላችንን ሁሉ መጠራጠር እንጀምራለን፡፡ ዓለም ሁሉ በእኛ ላይ ሲያሴር የሚያድር የሚመስለን መአት ነን፡፡ እንደ እኔ ለጋዜጣ የውስጥ ገጽ እንኳን የሚበቃ “ሀባ” ነገር ሳይኖረን ሌላው ሰው ሁሉ የእኛ የሆነውን “ሊነጥቀን” ያሰፈሰፈ እየመሰለን የተረፈን ነገር ቢኖር የራስ ምታት ማስታገሻ ኪኒን ምናልባት እሱ “አንቺን ቢነጥቅ” ውጤቱ ተመሳሳይ ከሆነ ኤስ.ኤም.ኤስ አድርጊልኝማ! ግን አሳስተሽ መልእክቱን ወደ አንዱ ኤፍ.ኤፍ. እንዳትልኩና “ይህኛው ትንግርት ነገር የተፈጸመው አሜሪካ ወይም ካናዳ ሳይሆን እዚሁ እኛው ዘንድ፤ አዲስ አበባ መሀል ፒያሳ ነው …” ምናምን ብለሽ መተረቻ እንዳታደርጊኝ፡፡

እናላችሁ … ሳትወዱ ተጠራጣሪ የሚያደርጋችሁ ዘመን ነው፡፡

ከጓደኛችሁ ሚስት ጋር ምስር ወጥ ምናምን በልታችሁ ስትወጡ “አጅሬ ጭራሽ የሰው ሚስት ፊቱ አስቀምጦ ምስር ወጥ ይበላ ገባ!” ”ነገርዬውን ተካፍለን እንብላ ሆነ እንዴ!” ምናምን የሚባልበት ዘመን ሆኖላችኋል፡፡

እናላችሁ … አዲስ ወንበር በገዛችሁ ቁጥር “ሰውዬዋ ተቀላቅላ ገንዘብ ይቆረጥላት ጀመር እንዴ?” ልትባሉ ትችላላችሁ፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ ሴት ልጅ … “ስማ፣ ሻይ ምናምን ብንባባል ምን ይመስልሀል?” ስትል ገና የጥያቄ ምልክቱ ሳይሰማ “ምን መጠየቅ ያስፈልጋል?” ይባል ነበር፡፡ በቃ ሻይ ነዋ! (እንትና የሻይ ቅጠል የሆነ ነገር “ሲምቦል” ምናምን የሚሆንበት ጊዜ አለ እንዴ!) ዘንድሮ ግን እንደዛ የምትል ሴት … አለ አይደል … “ሴትየዋ ምን ሀራባና ቆቦ ትረግጣለች!” ፊት ለፊት አውጣኝ አትልም እንዴ?” ምናምን ሊባል ይችላል፡፡

ከመንገድ ማዶ ሆኖ እጅ አውለብልቦ ሰላም ሲል “ያልለመደበትን እዛ ሆኖ ሰላም ያለኝ ለምንድነው?” ሊባል ይችላል፡፡ ከምታስቡት ዘመን በጣም ተጠራጣሪነት የበዛበት ዘመን ነው፡፡ “ስማ ቅዳሜ በውስኪ ነው የማጥብህ …” ምናምን የሚል ሰው “አጅሬው ውስኪ ብሎ ሊያነካካኝ ነው እንዴ!” ሊባል ይችላል፡፡ አሀ ልክ ነዋ … አብረው ውስኪ ሲጠጡ ታይተዋል መባሉ ይቀራል!

እናላችሁ … ጣለብንና የምንጠራጠረው ነገር እየበዛብን የቱን ይዘን የቱን እንደምንለቅ ግራ እየገባን ነው፡፡

ቦሶቻችንን እንጠራጠራለን፣ ጓደኞቻችንን እንጠራጠራለን፣ ጎረቤቶቻችንን እንጠራጠራለን፣ “ለእናንተ ስንል ነው እንዲህ የምንሆነው” የሚሉንን ሁሉንም ወገኖች እንጠራጠራለን … ምን እናድርግ … ነገርዬው ሁሉ የጭቃ ሹምና የምስለኔ ሲያስመስሉብን የማንጠራጠርሳ!

ሹሮ መበዳደር እንኳን ያለፈ ታሪክ እየሆነ ነው፡፡ እንጠራጠራለና! … ነገርዬው “የዛን ቤት ሹሮ ማን ያበደ አለ ድስት ውስጥ የሚከተው! ወደ እኛ ቤት ሲላክ ምን እንደተደገመበት ይታወቃል!” እያልን በጥርጣሬ የተነሳ ጥሬ እንኳን እያጣን ነው፡፡

አንድ የዶሮ ስንኝ እንድንጨምር ይፈቀድልኝማ!

እንቆቆና እሬት አስደቁሼ ጠጣሁ፣

እኔ እንደ ሰው ነገር የሚመረኝ አጣሁ፡፡

እንዲህ ማለትን ጠራርጎ የሚወስድ ተአምሩን ይላክልንማ! “መጠርጠርን” ለጥሬ ብቻ እንዲሆንልን ያድርግልንማ!

ደህና ሰንብትሉኝማ!

 

 

Read 2865 times Last modified on Saturday, 28 April 2012 12:54

Latest from