Saturday, 17 February 2018 14:51

የክራርና የዋሽንት ሊቁ መላኩ ገላው አረፉ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 “የኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ ሕያው መሆን አለበት”

     የክራርና የዋሽንት መምህርና የኦርኬስትራ ኢትዮጵያ መስራች የነበሩት አርቲስት መላኩ ገላው በሰማንያ ዓመት ዕድሜያቸው አሜሪካ ውስጥ አርሊንግተን - ቨርጂንያ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አርፈዋል።
አርቲስት መላኩ ገላው በጣልያን የወረራ ዘመን መጋቢት 12 ቀን 1929ዓ.ም ከአባታቸው ከአቶ ገላው ተክሌና ከእናታቸው ከእማሆይ ትኩነሽ ተሰማ በላስታ ላሊበላ ተወለዱ፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ የተፀነሰው የሙዚቃ መሳሪያ የመጫወት ፍቅር ከልጅነት ባለፈ በ1956 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲና የኦርኬስትራ ኢትዮጵያን በመቀላቀል በክራርና በዋሽንት ተጫዋችነት፣ ከዚያም ከ1959 ዓ.ም ጀምሮ በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በሁለቱም ባሕላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች በመምህርነት ከ28 ዓመታት በላይ አገልግለዋል።
በተለይ በኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ከተስፋዬ ለማ፤ ከአሜሪካዊው መሲንቆ ተጫዋች ቻርለስ ሳተን እና ከአርቲስት ጌታ መሳይ አበበ ጋር በመሆን የባህል አምባሰደርነታቸውን በዓለም ለማስመስከር ችለዋል፡፡ በያሬድ ሙዚቃ ት/ቤትም የባህል የሙዚቃ መሳሪያ መጫወት በማይበረታታበት ጊዜ የራሳቸውን የማስተማር ልምድ በመጠቀም ትምህርቱን መስጠት እንደጀመሩና መሰረት እንደጣሉ ተማሪዎቻቸው ይመሰክራሉ፡፡ ታላላቅ የሚባሉ የሙዚቃ ባለሙያዎችን እንደ ጥላሁን ገሠሠ፤ ብዙነሽ በቀለ፤ ሂሩት በቀለንና ሌሎች አንጋፋ ድምፃውያንን በዋሽንትና በክራር በማጀብ የሙያ ድርሻቸውን የተወጡ ባለሙያ ነበሩ፡፡ ለአርቲስት ጌታ መሳይ አበበም “የሽምብራው ጥርጥር” የሚለውን የሙዚቃ ድርሰት በመስጠትም ይታወቃሉ፡፡ የእጅጋየሁ ሽባባውን የአገው ባህላዊ ሙዚቃንም በልዩ መልክ በማጀብ የዋሽንት ችሎታቸውንም አስመስክረዋል፡፡
ኑሯቸውን በአሜሪካ ካደረጉበት ጊዜ አንስቶ በግላቸው በርካቶችን ክራር በማስተማር የቆዩ ሲሆን በአቶ ተስፋዬ ለማ በተቋቋመው ሙዚየም ውስጥ የባህል ሙዚቃ መሳሪያዎችን በማስተዋወቅ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ከማበርከታቸውም በተጨማሪ ከቀድሞ የሙዚቃ አጋሮቻቸው ከተስፋዬ ለማ፤ ቻርለስ ሳተን እና ጌታ መሳይ አበበ ጋር በመሆን “ዞሮ ገጠም” የሚል ሙዚቃን በመስራት ለባህል ሙዚቃ ህዳሴ የበኩላቸውን ተወጥተዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 ለባህል የሙዚቃ መሳሪያ ዕድገት ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽዖ የፊደል ዕድሜ ዘመን ተሸላሚ ክብርን አግኝተዋል፡፡ “የኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ ሕያው መሆን አለበት” የሚለውን ጽኑ አቋማቸውን ህይወታቸው እስካለፈችበት ጊዜ ድረስ ሌሎችን በማስተማርና በተለይም ሙያውን ለልጆቻቸው በማውረስ ታላቅ ታሪክ የሰሩ የባህል ሙዚቃ አምባሳደር ሆነው አልፈዋል፡፡
አርቲስት መላኩ ገላው ባለትዳርና የ7 ልጆች አባት ሲሆኑ 12 የልጅ ልጆችም አይተዋል፡፡ ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 3 ቀን 2010 ዓ.ም በአርሊንግተን ቨርጂኒያ ቤታቸው በ80 ዓመት ዕድሜያቸው ሕይወታቸው አልፏል፡፡ አስክሬናቸውም በመጪው እሁድ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የሚሸኝ ሲሆን ቀብራቸውም የፊታችን ሰኞ የካቲት 12 ቀን 2010ዓ.ም በፈረንሳይ ደብረ ፀሀይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ከቀኑ በ9ሰዓት እንደሚፈጸም ከቤተሰቦቻቸው የተገኘ መረጃ ያስረዳል፡፡

Read 3888 times