Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 28 April 2012 12:49

“እርግማንም ምርቃትም የለኝም”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ባጠለቀው ‹‹ናይክ›› ኮፍያ ሥር ብቅ ያለውን ፀጉር እያፍተለተለ ያሳለፋቸውን ስምንት ዓመታት በቁዘማ ያብሰለስላል፡፡ አናቱ ላይ ከደፋው ኮፍያ ጋር ማች የሚያደርግ ቲሸርት ያጠለቀው ፍቃዱ ጤና አሁን ላለበት ሁኔታ ምስጋናም እርግማንም እንደሌለው ይናገራል፡፡ ፍቃዱ የዛሬ ስምንት ዓመት ከጋሞጎፋ ጨንቻ ወረዳ ወልበራ ቀበሌ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ያነገበው ተስፋ ለቤተሰብ መከታ የሚያደርገው እምነት በማሳደር ነበር፡፡

የዛሬ ስምንት ዓመት በ10 ዓመት እድሜው የ3ኛ ክፍል ትምህርቱ ላይ ጨክኖ አዲስ አበባ እንዲመጣ ያነሳሳውን አጋጣሚ አይረሳም ፍቃዱ የጉራጌ ብሔረሰብ ለመስቀል ወደ ትውልድ ቀየው ገብቶ ከዘመድ አዝማድ ጋር በአልን እንደሚያከብረው ሁሉ የጋሞ ብሔር አባላትም ጥምቀትን ለማክበር ወደ ትውልድ ቀያቸው ያቀናሉ፡፡ ትውልዳቸው አዲስ አበባ ቢሆንም የወላጆቻቸውን አገር ለማየት ‹‹ጥምቀት የሚገቡም›› በርካታ ናቸው፡፡

በጋሞ ጎፋ ጥምቀት ልዩ በዓል ተደርጎ ትውልድን የሚያሰባስብ በዓል ብቻ አይደለም፡፡ ለብዙ ሀገ ወጥ ደላሎች ለበርካታ ተስፈኛ ህፃናቶች እና ወላጆቻቸው ‹‹የዕድል›› ቀንም ነች ፤ጥምቀት፡፡ ይህች እለት በድህነት የሚሳቀቁ ወላጆች ለክፉ ጊዜ የወለዷቸውንና የጥበብ ስራ ያስተማሯቸውን ልጆች ወደ ተስፋ ይ~ ከተማ የሚልኩበት ወርቃማ አጋጣሚ የሚያገኙባት ነች፡፡

በዚህች እለት አንድ አዲስ አበቤ የአርባ ምንጭ ሰው በአማካኝ ሁለት ልጆችን ይዞ ይመለሳል፡፡ ወላጆች በደላሎች ጮማ አፍ ተታለው ለተሻለ ኑሮ አለፍም ሲል ድጋፍ ያደርግላቸው ዘንድ ተመኝተው የአብራካቸውን ክፋይ ለሚያውቁት ባእድ አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡ ጨቅላዎቹ በዝና ወደሚያውቋት አዲስ አበባ ይጓዛሉ፡፡ ታላላቆቻቸው የተመኙት ህልም ሆኖባቸው ተስፋቸው ከስሞ እና ደብዛቸው ጠፍቶ ለወላጆቻቸው መከታ መሆን ቢሳናቸውም በርካቶች መጓዛቸውን ቀጥለዋል፡፡

የማያውቁትን አገር ናፋቂዎች

የጥምቀት በዓልን ልብ በሚያደርስ ደስታ አጣጥመው ሳይጨርሱ የተሻለ ኑሮን ተመኝተው የሚመጡ ህፃናት የሚያውቁት የናፈቀቻቸው አገር እንደጠበቋት አያገኛትም፡፡ “ወደ አዲስ አበባ ይዘውን የሚመጡ ሰዎች እውነተኛ ባህሪ መገለጥ የሚጀምረው አውቶብሱ ሞተሩን ካስነሳበት ቅፅበት ጀምሮ ነው” የሚለው የ17 ዓመቱ ታምሩ በቃ ነው፡፡ ታምሩ ወደ አዲስ አበባ ያመጡት አሳዳጊ አሮጊት የዋህና ደግ እንደሆኑ መገመቱን አይረሳም፡፡ ሴትየዋን ያመጣው ጎረቤትም “ደላላ መሆኑ ነው” ጨዋና ሊረዳቸው የሚችል ልጅ እንደሚፈልጉ ትምህርትና ጤናው እንደማይጓደል ቃል ገብተው ነበር የሰባት አመት ህፃን እያለ ይዘውት የመጡት፤  እንደ ታምሩ ገለፃ፡፡

አዲስ አበባ አሮጊቷ ቤት እንደደረሰ ያየውና በህሊናው የሳለው ፍፁም የተለያየ እንደሆነ የተረዳው ታምሩ ምርጫ አልነበረውም፡፡ ሌሎች ቤት ውስጥ እንዳሉ ልጆች ሲጠሩት አቤት ሲልኩ ወዴት ብቻ ሆነ፡፡ “እንደመጣሁ አካባቢ እንጨት ከሚለቅሙ ሴቶች ጋር ወደ ጫካ እሄድ ነበር፡፡ ኋላ ግን መውጣቱ ቀረና ቤት ውስጥ                                                                                               መላላክ ሽመናን መማርና መሞከር ሆነ ስራዬ፡፡ በኃላ አንድ ልጅ ከቤት ጠፍቶ ሲወጣ የሱን ጉድጓድ ተክቼ እንድሰራ ተደረኩ፡፡” የሚለው ታምሩ ለሰባት ተከታታይ አመታት በባህላዊዋ ፣ ቀዝቃዛዋ እና ጨለማዋ የሸማኔ ጉድጓድ ውስጥ በቀን ያለማቋረጥ ለአስራ አምስት ሰዓታት እንዲሰራ ተገደደ፡፡ በዓመት አንድ ጊዜ በጥምቀት አልያም በመስቀል ወላጆቹን ሊጎበኝ፣ የፊደልን ብርሃን ሊያይ እና አዲስ አበባን እንደልቡ ሊፎልልባት የተመኘው ተስፋው ሁሉ ተኖ ከቤተሰቡ ተቆራረጦ የሽሮ ሜዳን ጎዳናዎች ቤቱ ካደረጋቸው ከሰባት ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡

በኢትዮጵያ በየትኛውም ክልል የህፃናት ጉልበት ይበዘበዛል ከቤት ውስት ስራ እስከ ወርቅ ፍለጋ ህፃናት ተሰማርተዋል፡፡ የጋሞ ልጆች ፍዳ ግን ላየው የባሰ ነው፡፡ በሽሮ ሜዳ ወረዳ አንድ እና ከስድስት አካባቢ እንደ ስራቸው ባገኙት ስም የሚጠሩት ሸማ እና ጋሞ ሰፈር ያሉ ህፃናት ለ15 ሰዓታት የሽመና ስራን ይሰራሉ፡፡ እንደ አሰሪዎቻቸው ቸርነት በቀን ሁለት ጊዜ ‹‹ኩፍኩፋ›› ወይም ‹‹ከሽካ›› አልያም ‹‹የሀበሻ›› ዳቦ ይመገባሉ፡፡ ማለዳ ወፍ ሲንጫጫ በእበት ከተለቀለቀለው መሬት ላይ ተቀስቅሰው እስከ ሌሊቱ አምስት ሰዓት ድረስ በሽመና ስራ ታወክወ ይውላሉ፡፡ የእረፍት ጊዜያቸው ለምግብና ለመፀዳዳት የምትሰጣቸው ሽርፍራፊ ሰዓት ናት፡፡ በጋሞ እና በሸማ ሰፈር ዞራችሁ ፊደል የቆጠረ የጋሞ ልጅ ካገኛችሁ እሱ እድለኛው ነው፡፡ አሰሪዎቻቸው የራሳቸውን ልጆች በቀን ሲያስተምሩ ለእነዚህ ግን የሚራራ ልብ የላቸውም፡፡ በሳምንት አራት እና አምስት ሸማ ያላመረተ ልጅ በዱላ እና በምግብ ይቀጣል፡፡

አሰሪዎች አንድ ልጅ ለማምጣት መቶ ቃል ይገባሉ፡፡ ከልጁ አልፈው የዓመት ግብርን ፣ የመስቀልና የጥምቀት በዓላት ማድመቂያን ገንዘብን ለወላጅ እንልካለን እስከ ማለት የደረሰ፡፡ ሆኖም አንዱንም ሳይፈፅሙ የልጁ እድገት ቀጭጮ ወገቡ ጎብጦ ያለእድሜው ያረጃል፡፡ ተስፋ ያጣ ጎዳና ተዳዳሪ ይሆናል፡፡ በአሰሪዎቸቻቸው የተማረሩ ህፃናት ወደ ቀጨኔና መርካቶ ይገባሉ፡፡ አልፎ አልፎ ወደ ኦሮሚያ ክልል በመሄድ ለእረኝነት የሚቀጠሩም አሉ፡፡ ከደቡብ ክልል የሚሰደዱ ህፃናት የመበርከታቸው ምክንያት የከፋ ድህነት ፣ የማህበራዊ አገልግሎት አለመስፋፋት እና የህዝብ ብዛት መጨመር መሆናቸውን የተለያዩ ጥናቶች ጠቁመዋል፡፡ የኑሮ ውድነቱ እየተባባሰ ቀጥሏል፡፡ በጋሞ አንድ እናት አሁንም በአማካኝ ሰባት ልጆች መውለዷ ቀጥላለች፡፡

ድህነት እየባሰ እንደምን ይቻላል? ነገር ግን ከአርባምንጭ የመጣ መኪና ለሚያወጣው ልጅ ቤተሰብ መሆኑን የሚያረጋጥ የሸኚ ደብዳቤ ይጠየቃል፡፡ ይህ አሰራር በተሰወነ መልኩ የህፃናቱን ፍልሰት እንደቀነሰው የሚጠቁሙ ጥናቶች አሉ፡፡ ነገር ግን በሙዝ ጭነት ስር ተወሽቀውና ፎርጅድ መሸኛ እየተዘጋጀላቸው የሚመጡ ህፃናት አሁንም አሉ፡፡ በጉለሌ ክ/ከ የወረዳ አንድ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጽ/ቤት ኦፊሰር  እንደሚገልፁት የትኛውም ህፃን የተሟላ መረጃ የለውም፡፡ አሰሪዎችም ጥያቄ ሲመጣ ‹‹አላውቅም›› ‹‹ተከትሎኝ መኪና ውስጥ ገብቶ ነው የመጣው›› ‹‹አጎቱ ነኝ›› የሚሉ ምክንያቶችን ይደረድራሉ፡፡ እንደ ኦፊሰሩ ገለፃ ‹‹ህፃናቱን ተረክቦ ወደ ወላጆቻቸው መመለስም ሆነ ሰብስቦ ማስተዳደር ስለማይቻል ባሉበት የተሻለ ነገር እንዲያገኙ ጥረት ይደረጋል፡፡ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ ሁለት በጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በመተባበር የትምህርት ወጪያቸው እየተሸፈነላቸው እንዲማሩ፤ ምግብ እንዲያገኙ እና የረፍት ጊዜ እንዲሰጣቸውም ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

ህገ-መንግሥቱ በአንቀጽ 36 የህፃናትን ሙሉ መብት የሚያጎናፅፍ ቢሆንም፣ የአሰሪና ሰራተኛ ህጉ እድሜያቸው ከ14-18 የሆኑ ልጆች በቀን ከሰባት ሰዓት ላልበለጠ ጊዜ እንዲሰሩ ፣ የትርፍ ጊዜ ስራ እንዳይሰሩ ፣ የሳምንቱን የእረፍት ቀናት እና በዓላትን እንዲያርፉ ቢደነግግም በቀን 15 ሰዓታት በሳምንት 20 ብር የሚከፈላቸው የሸማ እና የጋሞ ሰፈር ህፃናት ግን እስከመኖራቸው ዘንግቷቸዋል፡፡

አብዛኛው የጋሞ ተወላጅ ህፃናት ተስፈኛ እና ትዕግስተኛ ናቸው፡፡ ልጅነታቸውን ሰውተው ለነገ የሚኖሩ፡፡ ዓለም ብትዘነጋቸውም ዛሬን ረስተው በነገ ተስፋ ተሞልተው ጥበብን ይማራሉ፡፡ ፍቃዱ ጤና የዛሬ ማንነቱ ላይ ቆሞ ትላንትን ሲያስብ “እርግማንም ምርቃትም የለኝም” ይላል እንደ ልጅ ቦርቆና ፊደል ቆጥሮ ባለማደጉ ይቆጫል፡፡

እንደ ‹‹ባሪያ›› ሌት ተቀን ሰርቶ ለሰው መኖሩ እና የእናት ናፍቆቱ እልህ ሆኖበታል፡፡ የፍቃዱ አገር ልጆች ጥበብን እያለበሱ የሚታረዙ ፣ ለነገ ዛሬን እየሞቱ ነው፡፡

ይህን አሳዛኝ ስቃይ የፈጠረው ደግሞ ፍቃዱ ጭልፊት ህገወጥ የህፃናት አዘዋዋሪ ደላሎች ጅንጀና በፍላጎቱም ይሁን ያለ ፍላጎቱ እንጭጭ በሆነው ለጋ እድሜው መማር መጫወትና መቦረቁን ትቶ ወደ ዝነኛዋ አዲስ አባባ በመምጣቱና ለከባድ የጉልበት ብዝበዛ በመጋለጡ ነው፡፡ ልጆችን ከዚህ አስከፊ ሰቆቃ የመጠበቅ ኃላፊነት የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው፡፡

 

 

Read 2376 times Last modified on Saturday, 28 April 2012 12:51