Sunday, 18 February 2018 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(5 votes)

   ‘ዕውነትና ጥቅም፣ መሆንና መኖር አንድ ናቸው’
            
   አንድ ከኔ በላይ ሃይማኖተኛ የለም የሚል ሙስሊም ነበር - ጊዜውን ሁሉ በጾም በፀሎት፣ ቁርዓን በመቅራት፣ ሃዲስ በማጥናት የሚያሳልፍ፡፡ አንድ ቀን አላህ በህልሙ ተገለጠለትና፡-
“ተነስ ወደ ከተማዋ ጥግ ሂድ፡፡ … እዛ አንዲት ሞቅ ያለች ሱቅ ታገኛለህ፡፡ ባለቤቷን አነጋግረውና ተመለስ”… አለው፡፡ ምልክቱንም በዝርዝር አሳወቀው፡፡ ሰውዬው አላህ ስለተገለጠለት በአንድ በኩል ደስ ሲለው፣ በሌላ በኩል ደግሞ … “ይኽ ነገር ዕውነት ይሆን?... ወይስ ስቃዥ ነው?” በማለት እያሰበና እየተጨነቀ አደረ፡፡
በማግስቱ በጠዋት ተነስቶ የሆነውን ለማረጋገጥ ወደተባለው ቦታ ሄደ፡፡ እዛም ሲደርስ ሁሉ ነገር እንደተነገረው ሆኖ አገኘው፡፡ ሰውዬው የፈጣሪውን ትልቅነት እያመሰገነ፣ ከሱቋ ደረሰና ትንሽ ራቅ ብሎ መመልከት ጀመረ፡፡ … ብዙ ሰዎች ተሰልፈው የተለያየ ዕቃ እየተሻሙ ይሸምታሉ፡፡ ባለቤቱ ያለ መሰልቸት ሁሉንም እንደየ አመላቸው እያስተናገደ ገንዘብ ይሰበስባል፡፡ ሰውዬውም፡-
“አላህ ምን ነካው?... ወደዚህ … ለሶላት እንኳ ጊዜ የሌለው ነጋዴ ጋ የሚልከኝ?” በማለት ለነጋዴው ሰላምታ ካቀረበለት በኋላ፣ “አላህ ወዳንተ ልኮኝ ነው የመጣሁት”… አለው፡፡ … ነጋዴውም፡-
“ወ አሌይኩም መሰላም!... እንኳን በሰላም መጣህ፡፡” በማለት ከመለሰለት በኋላ … ትንሽ አሰብ አድርጐ… “እንደምታየው ስራ በጣም በዝቶብኛል፣ እነዚህን ሰዎች አስተናግጄ ስጨርስ አነጋግርሃለሁ” ብሎት ወደ ስራው ተመለሰ፡፡ ሆኖም የሰውዬውን ትዕግሥት ማጣት በማየቱ፡-
“… እንደውም እዚህ ከምትቆም… እዛ ወዲያ አደባባዩን ዞረህ ብትመጣ ይሻላል”… አለው፤በእጁ እያመለከተው፡፡ ቀጠለናም፡-
እግረ መንገድህን ይቺን ነገር ይዘህ ሄደህ፣ እንደነበረች ይዘሃት ተመለስ፣ ጠብ እንዳትልብህ ተጠንቀቅ“… ብሎ በማንኪያ ላይ የምትዋልል፣ ፈሳሽ ሜርኩሪ ሰጠው፡፡
ከትንሽ ጊዜ በኋላ እንግዳው ሰው፣ የያዘው ዕቃ ጠብ እንዳይል፣ እየተጠነቀቀ አደባባዩን ዞሮ ተመለሰ። ሱቋ ጋ እንደደረሰ፣ ነጋዴው የመጨረሻውን እንግዳ ሸኝቶ…
“መጣህ ወዳጄ?... አንተ በጣም ጐበዝ ሰው ነህ፣ የሰጠሁህን ዕቃ በጥንቃቄ ይዘህ ተመለስክ” በማለት ካመሰገነው በኋላ … “ፈቃድህ ከሆነ፣ አንድ ነገር ልጠይቅህ” አለው፡፡
“እሺ… አላህ ከፈቀደ” በማለት መለሰ ሰውዬው። ነጋዴውም… “እዛ ደርሰህ እስክትመለስ ድረስ አላህን ስንት ጊዜ አሰብከው?”… ብሎ ጠየቀው። … እንግዳው ማሰብ ጀመረ፡፡ … ሃሳቡ በሙሉ የያዘው ነገር እንዳይፈስ መጠንቀቁ ላይ ስለነበር፣ አላህን አላስታወሰም፡፡ ይህንኑ … ሳይዋሽ ለነጋዴው አስረዳው፡፡
ነጋዴውም… “አየህ ወንድሜ፤ ቅድም እንዳየኸው ያንን ሁሉ ሰው ያለ ዕረፍት ሳገለግል፣ አንደኛ ለአንድ ሰከንድ እንኳን አላህ ከአእምሮዬ አልጠፋም፡፡ … ሁለተኛ ሸማቾቹ የሚፈልጉትን ነገር አግኝተው፣ ደስ ብሏቸው እንዲሄዱ እየረዳሁዋቸው ነበር። ሦስተኛ … ለራሴ የሚበቃኝን፣ የሚገባኝን ብቻ እንጂ የምወስደው፣ በፍፁም አላተርፍባቸውም፡፡ በዚህ ደግሞ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡… አሃምድልላሂ! … እምነት ማለት ዕውነተኛ ተግባር መሆኑን አላህ ራሱ ነው ያስተማረኝ፡፡ አንተን ወደ’ኔ የላከህም…” እያለ ለማስረዳት ሲሞክር…
“በቃ ተወው! ሹክረን!”… አለ ሰውዬው፤ ከእንቅልፉ እንደ ባነነ ሆኖ፡፡ “አላህን መውደድ ማለት ጾምና ስግደት፣ ሃጂና ዘካ ወዘተ ሳይሆን በዋናነት ሌሎችን መውድድ፣ ሌሎችን መርዳት፣ ስግብግብ አለመሆን፣ ቸርነቱ እንዳይርቀን ሁሌም እሱን ማሰብ መሆኑን አላህ ራሱ ተገልጦ እንዲገለጥልኝ በማድረጉ አመሰግነዋለሁ” በማለት ነጋዴውን አመስግኖ፣ ወደ ሰፈሩ ተመለሰ፡፡
ወዳጄ፤ እስልምናና ተግባር፣ ተግባርና ኑሮ የተሳሰሩ ናቸው፡፡ በዚህ መንገድ እስልምና ከእምነቱ ባሻገር የኑሮ መገለጫ (Way of Life) እየሆነ የመጣ ይመስላል፡፡ ይህ ማለት ዕምነት በተግባር ሲገለጥ፣ ህይወትና እውነት ሆኑ ማለት ነው፡፡
ዞሮ፣ ዞሮ ማንኛውም ሃሳብ ሆነ ፍልስፍና፣ ዕምነት ሆነ አምልኮት በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ፣ስጋዊና መንፈሳዊ ጥቅም ሊኖረው ይገባል እንደ ማለት ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ይህንን ጥቅም በማጣት ወይም ለመፈለግ ሲሉ፣ ከአንዱ እምነት ድርጅት ወደ ሌላው ይሰደዳሉ፡፡ በእንደዚህ ዓይነት መንገድ ላይ ነው፣ ብዙ “የእምነት ድርጅቶችና አንዳንድ የፍልስፍና እሳቤዎች የሚገጣጠሙት። ሲገናኙ ደግሞ ሰላም ተባብለው፣ ተሳስመው ይተላለፋሉ፡፡… አይገፈታተሩም፡፡
ወዳጄ፤ ከሁለቱ መንታ የፍልስፍና መንገዶች (Theoretical & Practical Philosophy) ያንደኛው (Practical) አካል ከሆኑት የቅርብ ጊዜ አስተሳሰቦች ውስጥ የፕራግማቲዝም ቲዎሪ (Theory of pragmatic philosophy)… የታነፀው፤ ‘ዕውነትና ጥቅም፣ መሆንና መኖር አንድ ናቸው’ በሚል ጽኑ መሠረት ላይ ነው፡፡…
ፕራግማቲስቶች አንድን ነገር ወይም ሃሳብ “ሎጂካል ነው?... ተጨባጭነት አለው?” … ብለው ከመጠየቅ ይልቅ.. “ለሰው ልጆች ኑሮና ፍላጐት የሚሰጠው ጥቅም ምንድነው?”… ማለትን ያስቀድማሉ፡፡… ይህንንም ጉዳይ ከአስተሳሰቡ ፊታውራሪ ሊቃውንቶች ዋነኛ የሆነው ዊሊያም ጀምስ የሚያረጋግጥልን…
“ስኮላስቲሲዝም (scholasticism) አንድን ነገር… ምንድነው? ብሎ በመጠየቅ ሲጀምር፣ ዳርዊኒዝም ደግሞ ነገርየው ከየት መጣ?... እንዴት ተፈጠረ? በማለት ምንጩን ይመረምራል፡፡ ፕራግማቲዝም ግን ጥቅሙንና ውጤቱን በማሰላሰል ጀምሮ፣ ከዕውነት ጋር ያለውን (መኖር እውነት ነውና) ዝምድና አስልቶ፣ ትርፍና ኪሳራችንን ይነግረናል።”  በማለት ነው፡፡
ወዳጄ፡- ለነፍስም ሆነ ለሥጋ፣ ለህሊናም ሆነ ለልብ ሥርዓት የማይጠቅመን ሃሳብና ፍልስፍና፣ እምነትም ሆነ ፖለቲካ፣ በግድ ካልተጫነብን ወይም በድንቁርናና በጥቅም ካላነሆለለን በስተቀር በፍቃዳችን እጃችንን አንሰጠውም፡፡
ወደ ታሪካችን ስንመለስ፤ እምነት፣ እውነትና ህይወት አንድነታቸውን፣ ግባቸው ወይም ጥቅማቸው ደግሞ እውነተኛውን ደስታ ከራሳችን ውስጥ ቆፍሮ ማውጣት መሆኑን መገንዘብ፣ መሳሪያውም መልካም ተግባር ብቻ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
 ወዳጄ፤ እምነት ድርጅት አይደለም፣እምነት ፋሽን አይደለም፡፡ እምነት የእያንዳንዱ ሰው ውስጣዊ መንፈስ ነው፡፡ ‘አለማመን’ በራሱ እምነት የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡ … የግል ጉዳይ በመሆኑ!! … ማስመሰል ግን ራስንም ሌላውንም ማታለል ነው፡፡ ዕድሜህን ለዋሸህበትና ላልመሰልክበት ጊዜ ስታካፍለው የኖርከው ትንሽ፣ ወይም ምንም ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባትም ጨርሶ እየኖርክ አይደለህም። ፅድቅና ኩነኔህን፣ በዚህ ሂሳብ ብታሰላው ታውቀዋለህ፡፡
የሰለጠኑ ህዝቦች አያስመስሉም፡፡ የሚጠቅማቸውን ያውቃሉ፡፡ የሚፈልጉትን ይሆናሉ፤ የማይፈልጉትን አይሆኑም፡፡ ለነሱ… ማመን ‘መሆን’፣ አለማመንም ‘መሆን’ ነው፡፡ ራስን መሆን ፅድቅ ነው እሚባለው እንደዚህ ነው!!
“ራስህን ፈልገህ፣ ራስህን ሁን፤ ማንም አንተን የሚመስል የለም፡፡” (Find yourself and be yourself, remember, there is no one like you in this whole world) በማለት የፃፈልንን ዴል ካርኒጌን እናመሠግናለን፡፡
ሠላም!!
* ምንጭ፡- ‘Great Islamic Teachings’

Read 2229 times