Sunday, 18 February 2018 00:00

“እስኪ ተመልከተው ይህን አወራረድ ያልሰማው ሲመጣ የሰማው ሲሄድ”

Written by 
Rate this item
(9 votes)

  “አዝማሪና ውሃ ሙላት” በተሰኘው የደራሲ ከበደ ሚካኤል ግጥም ውስጥ የምናቃቸው ዝነኛ መስመሮች ለዛሬ የመረጥናቸው ናቸው፡፡

        አዝማሪና ውሃ ሙላት
        አንድ ቀን አንድ ሰው ሲሄድ በመንገድ
        የወንዝ ውሃ ሞልቶ
                ደፍርሶ ሲወርድ
        እዚያው እወንዙ ዳር
                እያለ ጐርደድ
        አንድ አዝማሪ አገኘ
                ሲዘፍን አምርሮ
        በሚያሳዝን ዜማ
            ድምፁን አሳምሮ፡፡
        “ምነው አቶ አዝማሪ
        ምን ትሠራለህ?”
        ብሎ ቢጠይቀው፤
        “ምን ሁን ትላለህ፣
        አላሻግር ብሎኝ
        የውሃ ሙላት
        እያሞጋገስኩት
        በግጥም ብዛት
        ሆዱን አራርቶልኝ ቢያሻግረኝ ብዬ”
        “አሁን ገና ሞኝ ሆንክ ምነዋ ሰውዬ
        ነገሩስ ባልከፋ
        ውሃውን ማወደስ
        ግን እንደዚህ ፈጥኖ
        በችኮላ ሲፈስ
        ምን ይሰማኝ ብለህ
        ትደክማለህ ከቶ
        ድምፁን እያሽካካ መገስገሱን ትቶ
        እስኪ ተመልከተው ይህ አወራረድ
        ያልሰማው ሲመጣ የሰማው ሲሄድ”

        ተግሳጽም ለፀባይ ካልሆነው አራሚ
        መናገር ከንቱ ነው ካልተገኘ ሰሚ!
*   *   *
በተደጋጋሚ ሀገራችን ባለፈችበት የለውጥ ሂደት ውስጥ የተገነዘብነው ዋና ነገር ገዢው “ያቀድኩትን ልተግብርበት እረፉ”፤ ሲል፤ ተገዢው “ኧረ ይሄ ነገር አልተሟላልኝም እያለ ሲያማርር፤ በመሀል ውዱ ጊዜ ማለፉ ነው፡፡ የጠፋው ጊዜ ከሰነበትን በኋላ ተመልሶ መፀፀቻችን ይሆናል፡፡ የተወሳሰበው ችግር መፍትሄ ማግኘት ቀርቶ የባሰ የተወሳሰበ ሆኖ ይገኛል፡፡ የባሰ ምስቅልቅሉ ይወጣል፡፡ መፍትሄ መስጠት ያለባቸው አካላት የውስጥም የውጪም ግፊትና ውጥረት ስላለባቸው፤ ሌሎች ችግሮችን ማስተናገድ አልሆነላቸውም። ቢወተወቱ አያዳምጡም፡፡ “አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይነቃም” የሚለው ተረት የበለጠ ይገልፀዋል፡፡ ለማደግም ሆነ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችለው መደማመጥ ነው። ሁሉንም ነገር ዐይኔን ግንባር ያድርገው ብለን አንችለውም፡፡ ካለመደማመጥ በተጨማሪ የሚደረገውንም ሆነ የተደረገውን አላውቅም፤ ማለትና መስማትም ማየትም እምቢ ካልን፣ ጉዟችን የዕውር የድንብር ይሆናል፡፡
ጊዜ እየረፈደ ከመጣ በኋላ ሁኔታውን ለመቀልበስ ብንሞክር ፍሬ-አልባ ሙከራ ይሆናል። ዛሬም ዐይናችንን ከፍተን ቆም ብለን እናስብ፡፡ ውጥረት ውስጥ ከመግባታችን በፊት የውጥረቱን መፈጠሪያ ቧንቧዎች እንዝጋ፡፡ አሁንም ደግመን ደጋግመን እናዳምጥ። ሀገራችን ከእንግዲህ ተጨማሪ ችግር የምትሸከምበት ጫንቃ የላትም፡፡ ካልተጠነቀቅን ሀገርም እንደ ሰው ተሰባሪ ናት፡፡ የ1966ን አብዮት አንርሳ፡፡ ገዢዎች መግዛት ሲያቅታቸው፣ ተገዢዎች አንገዛም ሲሉ፣ ሀገር ለአብዮት የበሰለ ሁኔታ ላይ እንደደረሰች አንዘንጋ፡፡ ሲመሽ ጉሮሮ ለጉሮሮ ከመተናነቅ፣ ፊት ለፊት ተገናኝቶ መነጋገር ነው፤ ወደ መፍትሄው የሚያስጠጋን። እስከ መቼ “ዴሞክራሲያችን ለጋ ስለሆነ ነው” እያልን ምክንያት እንሰማለን? እስከ መቼ “የመልካም አስተዳደር ችግር ነው” እያልን እንዘልቀዋለን? እስከ መቼስ “የፍትህ ሰጪ አካላት የአፈፃፀም ችግር አለ” እያልን እንጓዛለን? የድህነት ችግርስ እስከመቼ ነው ቁልፍ ነው እየተባለ የምንቀጥለው? ከሃያ በላይ ዓመታት ተጉዘን፣ ምንም ለውጥ አለማምጣታችን፣ የሚያሳፍረን ጊዜ አይመጣምን? ዛሬም መብራት ይጠፋል፡፡ ዛሬም ውሃ ይጠፋል፡፡ ዛሬም ኔትዎርክ ይቸግራል፡፡ ዛሬም ኑሮ አዘቅት ውስጥ እየከተተን ነው፡፡ እነዚህ የብሶትና የምሬት ምንጮች እስከ መቼ እንደተጫኑብን ይኖራሉ? እናስብ! ምንጣፉ ከእግራችን ስር ተስቦ እስኪወሰድ አንጠብቅ! “ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም” ከአርባ ዓመት በኋላ መድገም አሳፋሪ ይሆናል፡፡ “ፋታ ስጡኝ”  ለማለትም ጊዜ የለም! የነካነው ሁሉ ወርቅ ይሆናል ብለን እንደ ሚዳስ አስማት (Midas Touch) የምናስብበት ጊዜ አልፏል፡፡
“እስቲ ተመልከተው ይህ አወራረድ
ያልሰማው ሲመጣ የሰማው ሲሄድ”
የሚለውን ዛሬም ማስተዋል ይበጃል፡፡ መልካም ጊዜ ይመጣ ዘንድ ሁላችንም እንመኛለን!   

Read 8055 times