Sunday, 18 February 2018 00:00

መስማት ያለብንን ሳይሆን መስማት የምንፈልገውን…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

   ‘“--ኔኦ ሊበራሊዝም ሸሸ፣ ወይስ አፈገፈገ?’ አሪፍ አጄንዳ አይደል! እንዲህ አይነት ስብሰባ ተጀመረ! ድሮ እኮ “ኢምፔሪያሊዝምን እንደመስሰላን!”፣ “የድሮ ታሪከ ነው የምናደርገው!” ሲባል ነበር፡፡ አሁን ደግሞ “ሸሸ ወይስ አፈገፈገ?” የሚል ቦተሊካ መጣ! እውነት ተሰብሳቢዎቹ፣ ኒኦ ሊበራሊዝም በቅርብ የሚወጣ ‘ሲንግል’ ይሁን፣ የእንትን ከነማ ቡድን ከማላዊ ያስፈረመው የእግር ኳስ ተጫዋች ይሁን…ከጤፍ ጋር ተቀላቅሎ የተገኘ ባእድ ነገር ይሁን…ምኑን ለይተውት ነው!--”


    አንዴት ሰነበታችሁሳ!
የመሸነጋገል ዘመን ነው፡፡ እየተዋወቁ የመተናነቅ ዘመን ነው፡፡ አና አሁን እኛ “በሀሰት አትመስክር” የተባለውን ሰማያዊ ህግ ጥሰሃል ተብለን ልንኮነን ነው!
የሆነ ጓደኛ ወይም ዘመድ ቤት እንሄዳለን። ተግደርድርንም ሆነ ምን ብለንም ማእድ ላይ እንቀርባለን፡፡ የሆነ ቀይ ወጥ ምናምን ይቀርባል፡፡ ቀይ ወጥ!…አለ አይደል… ምኑ ቀይ እንደሆነ ራሳችሁ ግራ ይገባችኋል፡፡ በሆዳችሁም “የቀለሞች መጠሪያ ወጥ ላይ ሲሆን ይለወጣል እንዴ!” ምናምን ትላላችሁ፡፡
የመጀመሪያውን ጉርሻ ስትጎርሱ… አለ አይደል…በርበሬ ተራ አንድ ፈረሱላ እንኳን ሳይቀር እንዳለ የጎረሳችሁት ነው የሚመስለው፡፡ ቃጠሎ በቃጠሎ! የምር ግን… “እኔ የምለው ‘ቆጭቆጫ ወጥ’ የሚል መሥራት ተጀመረ እንዴ!” ምናምን ትላላችሁ፡፡
“ብላ እንጂ…”
“እሺ...አየበላሁ ነው፡፡” በሆዳችን “እየበላኝ ነው ነው እንጂ ምኑን በላሁት!” እንላለን፡፡
“ወጡ አይጣፍጥም እንዴ?”
ከእነ መልሱ የተነገረ ጥያቄ ማለት ይህ ነው፡፡ እና… የሆነ ምግብ ቀርቦ “አይጣፍጥም እንዴ?” ብሎ ሲጠየቅ፣ መልሱ ግልጽ ነው፡፡
“ኸረ አሪፍ ነው! በጣም ይጣፍጣል፡፡” ጋባዦች ደስ ይላቸዋል፡፡  
“እንዴ፣ በደንብ ጎረስ፣ ጎረስ አድርግ እንጂ!” ‘ቆጭቆጫ ወጡ’ በቡልዶዘር ጭልፋ ችልስ፡፡
አና ጋባዦቻችን መስማት ያለባቸውን… ማለትም “ይሄ ምን ምግብ ነው፣ ቅጣት ነው እንጂ!” ሳይሆን የምንለው፣ መስማት የሚፈልጉትን ማለት “አሪፍ ምግብ ነው” እንላለን፡፡
እና… “በሀሰት አትመስክር” የተባለውን ሰማያዊ ህግ ጥሰሃል ተብለን፣ ልንኮነን ነው!
ስሙኝማ…ስለ ምግብ ካነሳን አይቀር… ‘ምች ምግብ ቤት’ የሚባል አለ አሉ፡፡ አና…በአባባው ያሉት የመንግሥት ሠራተኞች ናቸው አሉ፡፡ በወር ሦስት ቀን ብቅ ይሉና፣ ሀያ ሰባት ቀን ግን ድርሽ አይሉም፡፡ ለዛ ነው አሉ…‘ምች ምግብ ቤት’ የተባለው፡፡ እነሱም ያችን ሦስት ቀን ሲመጡ “አከሌ መጣ፣” “እከሊት መጣች” ሳይሆን “ምቾች መጡ፣” ነው የሚባሉት አሉ፡፡ ደግነቱ ፌጦ ምናምን ሳይነሰነስባቸው፣ በራሳቸው ጊዜ በሦስተኛው ቀን ይጠፋሉ እንጂ!…
 “ስማ፤ እጮኛዬን አየሀት አይደል!”
“አዎ…”
“እና?”
“እና ምን?”
“አስተያየት አትሰጥም እንዴ!”
“እውነቱን ልንገርህ አይደል፣ አኔ እኮ የነገርከኝ ጊዜ እንዲህ ቆንጆ አትመስለኝም ነበር፡፡ የፓሪስ ሞዴል ነው እኮ የምትመስለው!”
“አይደል!...”
“በጣም ቆንጆ እኮ ናት፣ አጅሬ እኮ በዚህ፣ በዚህ የሚችልህ የለም፡፡”
እናማ… አሱዬው መስማት ያለበትን ማለት…“ምንም የተለየ ነገር አላየሁባትም፣ መንገድ ላይ እንደምናያት ማንኛዋም ተራ ሴት ናት፣” የሚል ሳይሆን መስማት የሚፈልገውን፣ ማለትም “ቆንጆ ነች…” የሚለውን ነው፡፡
አና ሰውየው ደስ ብሎት ደረቱን ነፍቶ ይሄዳል፡፡ ተናጋሪው በሆዱ እኮ እሷ “የአንተ ቆንጆ ከሆነች፣ የእኔዋ ጎራዳ ሚስ ኢትዮዽያ ነች ማለት ነው፣” ይላል፡፡
እናማ… ሰውየው “በሀሰት አትመስክር” የተባለውን ሰማያዊ ህግ ጥሰሃል፣ ተብሎ ሊኮነን ነው!
ህይወት ውሸት ለመናገር እያስገደደችን ነው። ልክ ነዋ… ‘እውነትን ተናግሮ የመሸበት ማደር’ የሚባለው ነገር ተረት ብቻ ሆኗል፡፡
ሰዎች መስማት ያለባቸውን ሳይሆን መስማት የሚፈልጉትን መናገር፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ሁለቱ ነገሮች ብዙ ጊዜ አይገጥሙም፡፡
“የጻፍኩትን ልብ ወለድ አነበብከው?”
“አ…አዎ፡፡”
“እንዴት ነው?”
“አንተ፣ ግሩም ጽሁፍ ነው፡፡ እኔ እኮ እንዲህ መጻፍ የምትችል አይመሰለኝም ነበረ፡፡”
“ወደኸዋላ!”
“መውደድ ብቻ! እናንተ እያላችሁ ነው፣ ማንም እየተነሳ ጸሃፊ ነኝ የሚለው!”
ከዛ በኋላ ያው፣ ብዙዎቻችን እንደምናደርገው ሰውየው አገር ይጠበዋል፡፡ “እንግሊዞች ሚዲያውን ስለያዙት አእምሯችንን እየለወጡት ነው እንጂ አሁን ሼክስፒር ይሄን ያህል ጸሃፊ ሆኖ ነው!” ማለት ይጀምራል፡፡ ምን ይደረግ…እዚሀ አገር ‘የአዋቂነት መግለጫ’ ዋናው መንገድ፣ ሌላኛውን ‘ስም አለው’ የሚባለውን፣ ወይም ራሱ “ስም አለኝ” የሚለውን አንስቶ ማፍረጥ ሆኗል፡፡  ግን አስተያየት ሰጪው፣ በሆዱ “ልብ ወለድ ከሚጽፍ ፍርድ ቤት በራፍ ቁጭ ብሎ ማመልከቻ ጸሃፊ አይሆንም!” ምናምን ይል ይሆናል፡፡
እናማ…አስተያየት ሰጪው፤ ‘በሀሰት አትመስክር’ የተባለውን ሰማያዊ ህግ ጥሰሃል” ተብሎ ሊኮነን ነው!
“ልብሴ እንዴት ነው…አያምርብኝም!”
“እ…ምን መሰለሽ! እ…”
“ምን ታልጎመጉሚያለሽ! አያምርብሽም ልትይ ፈልገሽ ነው!”
በቃ… ያን ጊዜ የአእምሮ ‘ሀዛርድ መብራት’ ብልጭ ድርግም ማለት ይጀምራል፡፡ ጥያቄው ለእሷዬዋ እውነቱን መናገር ሳይሆን መስማት የፈለገችውን መናገር ነው፡፡
“እንዴት እንደወደድኩት አልነግርሽም፣  የምለው እኮ ነው የጠፋኝ!”
“አይደል!”…”
“ልዕልት ነው እኮ ያደረገሽ፣ ጓደኛዬ!”
ልክ ነዋ…ታዲያ ምን ትበላት፤ “ልብስ እንዴት እንደማይለበስ ዘጋቢ ፊልም ሊሠራብሽ የተዘጋጀሽ ትመስያለሽ፣” ብላ እውነቱን ታፍርጥ! ትርፍና ኪሳራ ለሌለው ነገር እውነቱን አፍርጣ፣ ጓደኝነታቸውንም አብራ ‘ታፍርጠው!’
እናላችሁ…ጊዜ የምናስበውንና የምናምንበትን ሳይሆን ሌሎች መስማት የሚፈልጉትን እንድንናገር እያደረገን ነው፡፡
አሁን ለምሳሌ ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች’ ሲናገሩ ስንሰማ፣ “አቤት ውሸት! እንዲህ ሲተረትረው ትንሽ እንኳን ትከሻውን አይከብደውም!” ምናምን ማለት ልክ አይደለም፡፡ አሀ… ካሜራው እኮ የተደቀነባቸው ዝም ብሎ አይደለም፡፡ የሚፈለገው እነሱ ያሰቡትንና የሚያምኑበትን ሳይሆን ሊያስቡና ሊያምኑበት የሚፈለገውን ነዋ!  እዛ የተጠሩት እኮ ደውለው፣ “ማታ ቲቪ ላይ ስለምታይ እንዳያመልጥሽ፣” ለማለት ብቻ ሳይሆን “በእውነት እየተሠራ ያለው ሁሉ በጣም የሚያስደስት ነው፣” ምናምን ብሎ ለሆነ ነገር ማረጋገጫ እንዲሰጥ ነው፡፡
“በወረዳው ውስጥ እየታየ ስላለው የልማት ሥራ ምን ያስባሉ?”
“በእውነቱ በጣም ነው የሚያስደስተው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሃላፊዎቹን ማመስገን እፈልጋለሁ…” ምናምን ይላሉ፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…አለቆች የሆነ እንደ አራስ የሚያደርጋቸው ነገር አለ ልበል፡፡  ልክ ነዋ…በትንሽ ትልቁ ሊንቆለዻዸሱ ይፈልጋሉዋ! ሚጢጢዬ ጎጆ እንኳን በሌለበት…አለ አይደል… “ህንጻው ግሩም ነው፣” አይነት ነገር ሊባሉ ይፈልጋሉዋ! ባስመዘገቡት ስኬት ሳይሆን ባካሄዱት የስብስባ ርዝመት ሊመሰገኑ ይፈልጋሉዋ፡
“በእውነቱ ሰሞኑን ያካሄድነው ስብሰባ ሥራ አመራሩን በጣም የሚያስመሰግነው ነው፣” ሊባሉ ይፈልጋሉዋ!
እኔ የምለው… የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው…ሰሞኑን በየቦታው ስብሰባ በዛ ልበል! ‘ሥራ እየደከመ ነው፣’ ‘ምርት እየቀነሰ ነው፣’ ‘አይደለም ሙሉ ለመሉ፣ የእቅዳቸውን ግማሽ እንኳን የማያሳኩ ድርጅቶች ቁጥር አየናረ ነው…’ ምናምን እየተባለ እያለ፣ በስብሰባ ጊዜ ማጥፋት ምንድነው! ያውም የታሸገ ውሃና አበል የሌለበት ስብሰባ!
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የያነው፣ የተሰበሰቡ የመንደር ሰዎች ካሉበት ፎቶ ጋር ስለ ስብሰባው ጉደኛ አጄንዳ ምን እንደሆነ አንብበን ሲያስገርመን ከርሟል፡፡ ‘ኔኦ ሊበራሊዝም ሸሸ፣ ወይስ አፈገፈገ?’ አሪፍ አጄንዳ አይደል! እንዲህ አይነት ስብሰባ ተጀመረ! ድሮ እኮ “ኢምፔሪያሊዝምን እንደመስሰላን፣” “የድሮ ታሪከ ነው የምናደርገው!” ሲባል ነበር፡፡ አሁን ደግሞ “ሸሸ ወይስ አፈገፈገ” የሚል ቦተሊካ መጣ! እውነት ተሰብሳቢዎቹ፣ ኒኦ ሊበራሊዝም በቅርብ የሚወጣ ‘ሲንግል’ ይሁን፣ የእንትን ከነማ ቡድን ከማላዊ ያስፈረመው የእግር ኳስ ተጫዋች ይሁን…ከጤፍ ጋር ተቀላቅሎ የተገኘ ባእድ ነገር ይሁን…ምኑን ለይተውት ነው!
አይደለም እኛ ተራዎቹ፣ ‘የጨስን ፖለቲከኞች’ ነን ከሚሉት መሀል ‘ቁጥራቸው ቀላል የማይባል’ (‘ዲፕሎማቲከ አነጋገር’ እንደሚሉት) “እስቲ ኒኦ ሊበራሊዝ ምናምን ስለሚሉት ትንሽ አስረዳኝ፣” ቢባሉ የልብ ምታቸው ፍጥነት፣ ለጊነስ ክብረ ወሰንነት ባይበቃ ነው!
እናላችሁ…ጊዜ የምናስበውንና የምናምንበትን ሳይሆን ሌሎች መስማት የሚፈልጉትን እንድንናገር እያደረገን ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5824 times