Sunday, 18 February 2018 00:00

በገዛ ውሳኔው አመድ አፋሽ እየሆነ ያለው ኢህአዴግ መራሹ መንግስት

Written by  በታምራት መርጊያ
Rate this item
(4 votes)

 ኢህአዴግ በገዛ ውሳኔው እና በራሱ ቃል ታስሮ፤ እራሱ የገባውን ቃል ለማክበር እየተናነቀው በማመንታቱ፤ እራሱን በራሱ አመድ አፋሽ እያደረገና፥ ሊመሰገንበት ይችል በነበረውን የፖለቲከኛ እስረኞችን ከእስር የመፍታት ተግባር በምልዓት ላለመፈፀም በመዳዳቱ፤ እራሱን በራሱ ተወቃሽ እንዲሆን እያደረገ ይገኛል ወይም  በካድሬዎች ቋንቋ “ያለበት ሁኔታ ነው ያለው”።
እንደሚታወሰው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ሦስት ሳምንታት ገደማ የፈጀውን የግምገማ ችሎት ካጠናቀቀ በኀላ፤  የጥቂት ቀናት አፍታ ወስዶ ሲያበቃ፤ የአራቱን የግምባሩ አባል ድርጅቶች ሊቃነመናብርት የዝግ ስብሰባዉን ሒደትና ውሳኔዎች በጋራ ያብራሩለት ዘንድ በአንድ ጠረጴዛ መሳ ለመሳ ደርድሮ በቴሌቪዥን አቀረባቸው።
 እናም የጋራ በተባለው ማራሪያ ላይ፥ ለብዙዎቻችን የጋራ ያልመሰለንን ማብራሪያ የድርጅቶቹ ሊቃነ መናብርት በገባቸውና በተረዱት መጠን ሲያቀርቡ ቆዩ።  
በዚሁ ማብራሪያ ላይም ብዙዎችን ጮቤ ያስረገጠና፤ የብዙዎችን ቀልብ የሳበ የግንባሩ ውሳኔ በደህዴኑና በግንባሩ ሊቀመንበር በጠ/ሚ አቶ ሐይለማሪያም ደሳለኝ አማካኝነት ከሞላ ጎደል እንደሚከተለው በሚል ይዘት ቀረበ፦
“በአቃቤ ህግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር የሚገኙና የተፈረደባቸው የተለያዩ ፖለቲከኞችን የተሻለ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ፤ ማንም ሳያስገድድኝና የማንም ምክር ሳያሻኝ፤ እራሴዉ አስቤና ወስኜ ፓለቲከኛ እስረኞችን ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በይቅርታ  እንዲለቀቁ ወስኛለሁና፤ እነሆ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ደስይበላችሁ”።
በዚህ ብስራት መነሾም በርካታ ኢትዮጵያዊያን ሳይታወቅ እንደ ደራሽ ውሃ ውስጣችንን ፈንቅሎ በወጣ የደስታ እምባ ጎርፍ ተጥለቅልቀን በደስታ እንባችን ተራጨን። የደስታ ጮቤም ረገጥን...። ኢህአዴግም እንዳለው ከዚህ ቀደሙ በተለይ መልኩ  የእውነት ከልቡ ሊቀየር ነዉ፥ ብለን ልባችን በሐሴትና በተስፉ ተሞላ።
ዳሩ ምን ያደርጋል፤ ለደስታ ያላደለን ሆንና፥ ከግብታዊ የደስታ ስሜታችን ገና በቅጡ እንኳን ሳንወጣ፤ ብስራቱን ወደ መርዶነት ቀይሮና ደስታችንን አደፍርሶ ወደ ጥርጣሬ የለወጠ፣..... ሀሴታችንን ወደ ሀዘን፣.... ተስፋችንንም ወደ ቀቢፀተስፋነት በቅፅበት የሚቀይር ዜና ለመሰማት ከአንድ ጀምበር የበለጠ ጊዜ ሳይወስድ ቀረ።
ይህ ዜና የወጣው ደግሞ፥ የኢህአዴግ አራቱ አባል ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት የጋራ መግለጫ ከሰጡ በኋላ፤ አፍታ እንኳን ሳይቆይ ነበር።
የዚህ መርዶዓዊ ዜና ይዘት በግርድፉ፥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ትክክለኛ በሆነ መንገድ አልተተረጎመም ወይም በተሳሳተ መንገድ ተተርጉሟል (misquoted) የሚል ነበር።
ይህንኑ ተከትሎም መንግሥት ውሳኔውን በድጋሚ እንደሚያጤነው ማስታወቁን የሚዘግብ ዜና በተለያዩ የሐገር ውስጥና የውጭ የመገናኛ አውታሮች በስፋት ይናኝ ያዘ።
ተያይዞም፤ ይህ ውሳኔ የተገለፀበት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት፥ ይፋዊ ድህረ ገጽ፤ የዉሳኔውን ይዘት በተደጋጋሚ ጊዜ  በአዲስ ዓይነት የይዘት አቀራርብ እየቀያየረ ያቀርብ ገባ።
ይህ አድራጎትም ብዙዎችን ከማስገረም ባሻገር በአያሌ ዜጎችና የውጭ አካላት ዘንድ ትዝብትን አጭሮ፥ የጽሕፈት ቤቱን የመረጃ ክፍል የሙያ ብቃት (Competency) በጅጉ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አደረገው።
በሌላ በኩል ደግሞ፥ በደስታ ማእበል ተጥለቅልቆ ይዋኝ የነበረው ድፍን አገሬው  ኩም አለ። የጨበጠው እንደ ሐገር የመለወጥ የተስፋና የምኞት ጉም እንደ ጤዛ ተነነ። ቅፅበታዊ ሐሴቱም በቅፅበት ወደ ሐዘንና ሰቀቀን ተቀየረ።
ምክንያቱ ደግሞ፥ ከቀደሙት የተለለየ የመሰው የኢሕአዴግ ስህተቴን አውቄዋለሁ እናም ተለዉጫለዉ አይነት ኑዛዜ፥ ግንባሩ የመለወጥ-መቀየሩን እጅግ ቀላሉ ማሳያ፤ ድርጅቱንም ሆነ መንግስቱን ምንም አይነት ዋጋ ሊያስከፍል የማይችለው፥ እዳው ገብስ የሆነው እና ኢሕአዴግ እንዳለው መለወጡን በተግባርና በቅፅበት (immediately) ለህዝቡ ሊያሳይበትና በቀላሉ ሊተገብረው ከሚችላቸው ተጨባጭ ተግባራት መካከል ይኽው የፖለቲከኛ እስረኞችን የመፍታት ድርጊት እንደሆነ በሕዝብ ዘንድ በመታሰቡ እና በመታመኑም ጭምር ነበር።
ሌላው ከዚሁ ጋር ተያይዞ እጅግ በጣም አስገራሚው ጉዳይ ደግሞ፤ ኢህአዴግ ፖለቲከኛ እስረኞችን በራሱ ተነሽነት እንደሚፈታቸው ለህዝብ አሳውቆና ቃል ገብቶ ሲያበቃ፤ በህዝብ ዘንድ የሚያስመሠግነውንና የፖለቲካ ትርፍ የሚያስገኝለትን ይህንን ተግባር በምልዓት መፈፀም ሲገባው፤ ዘገየም ፈጠነ ሰሞኑን እየተመለከትን እንዳለነው አንድ፤ አንድ እያለም ቢሆን መተግበሩ ላልቀረ፤ ማመንታትና ማወላወለል (hesitation)፤ ማሳየቱ  በገዛ ውሳኔው አመድ አፋሽ ከመሆኑም በለፈ በፖለቲካ ሳይንስ ልሒቃን ዘንድ (Committing Political suicide) ተብሎ የሚገልፅ ድርጊት መፈፀም ይመስላል ብሎ ለመናገር ያስደፍራል።
በሌላ መልኩ የተመለከትነው እንደሆነ ደግሞ፤ የመልካም አስተዳደር ችግር መንሰራፋት ጉዳይ፥ መቼም የዚህች ምስኪን ሐገር አዋልዶች እስኪያቅለሸልሸንና እጅ እጅ እስኪለን ድረስ ዘለግ ላሉ ዓመታት ሲለፈፍልንና ስንሰማው የቆየ፥ አሁንም እንደ ብሔራዊ መዝሙር በነጋ በጠባ ቁጥር እየሰማነው የቀጠለ ጉዳይ ነው።
እንደውም፥ በዚህ ረገድ  በተደጋጋሚና ለረጅም ጊዜያት “የመልካም አስተዳደር ችግር አለብኝ፤ ይህ ችግርም ለመንግስቴም፥ ለስርዐቴም አደጋ ሆኖብኛል” ብሎ በመናገር የሆነ አለም ዓቀፍ የውድድር ዘርፍ ቢኖርና፥ ውድድር ቢካሔድ፤ የኢትዮጵያ መንግስት  ከአለም አንደኛ ወጥቶ፥ እንደ አትሌቶቻችን ሁሉ፤ መንግስታችንም ሐገራችንን አስጠርቶ፥ ባንዲራችንን በዓለም አደባባይ እንዲውለበለብ እንደሚያደርግ ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም።
ይኸው የመልካም አስተዳዳር ችግር አለብኝ ማለት የማይታክተው ኢህአዴግ መራሹ መንግስታችን በቀደምም፤ ከበር መልስ 17 ቀናት የፈጀውን ድርጅታዊ ዝግ ግምገማዉን ማጠናቀቁን ተከትሎ፤  አንደተለመደው “በጥልቀት ከገመገምኳቸው አበይት ችግሮቼ ውስጥ፤ አንዱና ዋነኛው “የመልካም አስተዳደር ችግሬ ነው” ብሎ በድህረ ግምገማ መግለጫው ላይም ደገመው።
ርግጥ ነው፤ ኢህአዴግ ችግሮቼ ብሎ የዘረዘራቸው ህልቆ መሳፍት ችግሮች ናቸው። ሆኖም የመልካም አስተዳደርን ችግር  እዚህ ላይ በተለየ ለመመልከት የወደድኩበት አብይ ምክንያት፥ ይህንን ክልሼ ሐሳብ በመድገም፥ በቸከና በተሰለቸ ጉዳይ አንባቢን ለማሰልቸት አይደለም።
ይልቁንም፥ የመልካም አስተዳደር መለኪያ ሚዛን ከሆኑት አበይት ነጥቦች ውስጥ፤ አንዱና ዋነኛው የሆነው፥ የመንግሥትን ታአማኒነት (government credibility) የሚለው ሐሳብ (Good Governance indicator) ስለሆነ፤ በዚህ የሐሳብ መነፅርና በራሱ በመንግሥት የማያባራ የኑዛዜ ቃል፥ ራሱን መንግስትን ለመሞገት ይቻል  እንደሁ ከሚል እጅግ ቀላል አመክንዮአዊ መነሻ ነው።  እናም መንግሥት ፖለቲከኛ እስረኞችን ለመፍታት የገባውን ቃል በተጨባጭና በአፋጣኝ አለመፈፀሙና ማመንታቱ፤ በመልካም አስተዳደር መነፅር ተመልክተን እንደሚከተለው ለአፍታ እንጠይቅ፦
የመንግሥታት የመልካም አስተዳደር መለኪያ የሆነው አንዱና አንኳሩ መለኪያ ሚዛን (Major government indicator)፤ ታእማኒነት (Credibility) ከሆነ፤ ኢህአዴግም ይህ ችግር እንዳለብኝ በሚገባ ተረድቻለሁ፤ እናም ይህንን ችግሬን እደከዚህ ቀደሙ ሳይሆን በተግባር እቀርፈዋለሁ፤ ብሎ ያውም በከፍተኛ አመራሩ አማካኝነት ገቃል ገብቶ ከነገረን በኀላ። አፍታ እንኳን ሳይቆይ ተአማኒነቱን በእጅጉ የሚሸረሽረውን፤ እንደ መንግሥት የገባውን ቃል ለማክበር ማመንታቱ፤ ከማስተዛዘቡ ባለፈ አሁንም ከፍተኛ አመራሩ የመልካም አስተዳደር ችግሩን ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት  ጥያቄ ውስጥ አይጨምረውም ወይ??
በከፍተኛ አመራሩ ያልታየውና ያልተተገበረው የመልካም አስተዳደር ችግርን የመፍታት ቁርጠኝነትስ፥ አረቦች እንደሚሉት “የፊተኛው ግመል ከሸና፤ የሗለኝውም ግመል ይሸናልሸናል” ነውና፤ ለማሕበረሰቡ ቅርብ በሆነውና ሕብረተሰቡን ለከፍተኛ ምሬትና እሮሮ እየዳረገው በሚገኘው መካከለኛ እና ዝቅተኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው አመራርስ፥ ችግሩን የከፋ ይሆን እንደሆን እንጂ፥ ከቶ እንደምን ሊቀረፍ ይችላል???  
ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሩ በአደባባይ ችግሬ ነው ያለንን ጉዳይ ከመቅረፍ ይልቅ፤ በማግስቱ አንዱንና ዋነኛውን የመልካም አስተዳደር አንጓ “የተዓማኒነት” ጉዳይ በዜጎች ዘንድ ጥርጣሬ በሚፈጥር መልኩ፤ የገባውን ቃል በመቀያየር መፈፀሙ፤ አሁንም ድርጅቱ ይህንን ችግሩን በማያዳግም ሁኔታ ሊቀርፈው መዘጋጀቱን እንደምን መቀበል ይቻላል???
የሚሉ አመክንዮአዊ ተጠየቆችን በማንሳት ድርጅቱ እራሱን በድጋሚ ይመለከትበት ዘንድ ማቅረቡ ተገቢና ምክንያታዊ ይሆናል።
የሆነው ሆኖ መንግሥት፤ ዘግይቶም ቢሆን፤ ዶ/ር መረራን፣ አቦ በቀለ ገርባን፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ወዘተ... ጨምሮ የተወሰኑ ፖለቲከኛ እስረኞች አንድ፥ አንድ እያለም ቢሆን በተለያየ ጊዜ መፍታት መጀመሩ፤ ድርጅቱ ለህዝብ የገባውን ቃል ሙሉ ባያደርገውም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን  በጎና አበረታች ጉዳይ መሆኑን በርካቶች ይስማሙበታል።
እንደ እውነቱ ከሆነ ግን፤ ኢህአዴግ እራሱ ልፈታቸው ነው፤ ያላቸውን ፓለቲከኛ እስረኞችን  ያለአንዳች ማመንታት በምልዓትና በተግባር ተፈፅሞት ቢሆን ኖሮ፤ ድርጅቱ ከልቡም ይሁን ከአንገቱ እንዳለው፤ የተሻለ ሃገራዊ መግባባትን (National consensus) ከመፍጠርና ሐገራዊ የዲሞክራሲ ምህዳሩን ከማስፋት ባለፈ፤ ለኢህአዴግም ለራሱ ቢሆን፥ በሐገር ውስጥም ይሁን በአለም አቀፍ የፓለቲካ መድረክ ላይ ከፍተኛ የፖለቲካ ትርፍ ሊያስገኝለት ይችል የነበረ ከፍተኛ እድል እንደነበር ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነበር።
በርግጥ ይህ እድል ለኢሕአዴግ፥ “ነበር” ተብሎ የሚታለፍ፤ ያመለጠ ወይም የባከነ እድል (Missed opportunity) ነው ተብሎ የሚወሰድ ጉዳይ አይደለም። ምክንያቱም አሁንም ድርጅቱ ሳይረፍድ መጠቀም ከቻለ፥ አሁንም በእጁ ላይ የሚገኝ ነውና።
ነገር ግን፥ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ፤  ማንኛውም ነገር የጊዜ ዋጋ (Time value) እንዳለው ነው።  ምክንያቱም፥ እድልም ቢሆን በጊዜና በቦታው ካልተጠቀሙበት የሚባክን እንጂ ዘላቂና ዘላለማዊ ሆኖ የሚቆይ ነገር አይደለምና ነው። ይህንን አውነት በአግባቡ መገንዘብ ደግሞ በሳልነትንና አስተዋይነትን ይጠይቃል።  እድልን በወቅቱና በጊዜው ያለመጠቀምና የማባከን ተግባር፤ በተለያዩ የአለም የፓለቲካ መድረኮች ላይ ብልሀትና ብስለት በጎደላቸው አያሌ መሪዎችና በርከት ባሉ የፖለቲካ ስርዐቶች ላይ የፈጠረውን ውድቀት መለስ ብሎ ማስተዋሉ ተገቢ ይሆናል።
ስለሆነም እንደነ ዶ/ር መረራ ጉዲና ሁሉ፤ ቀሪዎቹምም ፓለቲከኛ  እስረኞች ፓለቲከኛ እንጂ፥ ከወራሪ ሐይል ጋር በተደረገ ውጊያ፤ በጦር ግንባር የተማረኩ ምርኮኛኞች ስላልሆኑ፤ እነ ዶ/ር መረራ በተፈቱት አግባብ ዛሬ፥ ሳይባል ቀሪዎቹም ታሳሪዎች ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ መፈታት ይኖርባቸዋል።
እዚህ ላይ ሊነሳ የሚገባው ሌላው አብይ ጉዳይ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሒውማን ራይት ዎችስ እንዲሁም በምህፃረ  ሲ.ፒ.ጄ ተብሎ ከሚጠራው የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅትና፤ ቀደም ብለው ከተጠቀሱት ዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጋር ፓለቲከኞችና ጋዜጠኞችን “አስረሀለል፤ አላሰርኩም” በሚል ረዘም ላለ ጊዜ የፓለቲካ ሙግት ውስጥ ሲነታረክ ቆይቷል።
እንደ አውነቱ ከሆነ ግን ፤ አሁን ጊዜው የሚጠይቀውና ለሐገር የሚበጀው ጉዳይ እንዲህ ያለ ጉንጭ አልፋ ሙግት ሳይሆን፤ በሳል ፓለቲካዊ ውሳኔ መሆኑን መንግሥትም ይሁን ኢሕአዴግ ሊገነዘቡት የሚገባው የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ መሆኑን ነው።
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፤ በተቃራኒው፥ መንግሥት ለህዝቡ የገባውን ቃል ቸል ባለ መልኩ፤  የተለመደ የፖለቲካ ትርፍን ለማግኘት በሚመስል የፖለቲካ ስሌት “ወንጀል በመስራቱ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር፤ በፖለቲካ አመለካከቱ፣ መንግስትን በመተቸቱ ወይም ሐሳቡን በነፃ በመግለጹ ምክንያት ያሰርኩት አንድም ፓለቲከኛ ወይም ጋዜጠኛ የለም፤ በሚል የተለመደና ጊዜውን  ያላገናዘበ  ትርክትና  የፕሮፓጋንዳ ስራ መጠመዱ ፈፅሞ ፓለቲካዊ ብልሐትን የሚያሳይ አይደለም።
በመሆኑም እራሱ መንግሥት እንዳለው ቃሉን ጠብቆ፤ እነ እስክንድር ነጋን፣ አንዱአለም አራጌን፣ አህመዲን ጀበል፣ አህመድ ሙስጠፋ እና ወዘተ.... ሌሎች በእስር ላይ የሚገኙ፤ ፖለቲከኛና ጋዜጠኛ ቢሆኑም ወንጀለኞች ናቸው ያላቸውን ታሳሪዎች፤ የተሻለ “ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በይቅርታ  እንዲለቀቁ ወስኛለው” ባለውነና ቃል በገባው አመክንዮ መሰረት፥ ቃሉን አክብሮ ለቃሉ ታምኖ እራሱ እንደገለፀው “በአቃቤ ህግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር የሚገኙም ይሁኑ የተፈረደባቸውን የተለያዩ ፖለቲከኞች” መፍታት ይጠበቅበታል።
ይህን ማድረግ ከተሳነው ግን መንግስቱ በህዝብ ዘንድ የሚኖረውን ታዕማኒነት በእጅጉ ጥያቄ ውስጥ የሚከተው እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል። ይህም በአኳያው የመንግሥትን ሀገር የመምራት ብቃት አጠያያቂ የሚያደርግና በራሱ ውሳኔ አመድ አፋሽ የሚያደርገው መሆኑን አመራሩ ሊገነዘበዉ የሚገባ ጉዳይ ይሆናል።

Read 5437 times