Sunday, 18 February 2018 00:00

በሞት የተከፈለ የነጸነት ዋጋ

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(2 votes)

 በወርኃ የካቲት የሚካኤል ለታ
ትልቅ ጠብ ተነስቶ መሬት ተቆጥታ
ቆስሎ ግራዚያኒ ሰበብ ሆናው ደሙ
ብዙ ሰው ታረደ ተናወጸ አለሙ፡፡
በየቤቱ ለቅሶ ጩኸት በየሜዳ
ይሰማል ይታያል በዚህ በዚያ ፍዳ፡፡
የሰው ልጅ እንደከብት ወድቆ እየታረደ
ሶስት ለሊት ሶስት መዓልት ከተማው ነደደ፡፡
ሽንትም እንደ ውኃ ተሸጠ በገንዘብ
ብልህ የሆነ ሰው ይህንን ይገንዘብ፡፡
ኢዮብ ነሽ ኢትዮጵያ የእግዚአብሔር ወዳጅ
ወድቀሽ አልቀረሽም በጠላትሽ እጅ፡፡
መስፍን ተፈሪ
አዲስ ዘመን ጋዜጣ፤ የካቲት 12/1961
በልማዱ አንድ ሰው ሲሞት ከቅርብ ዘመድ ጀምሮ ለወዳጅና ለጓደኛ መልክተኛ ይላካል፡፡ ሟች ክርስቲያን ከሆነ ፍትሐት እየተፈታ እየተለቀሰ ሐዘንተኛው እስኪሰባሰብ ድረስ ይጠበቃል፡፡ በእስልምና እንዲህ ያለ ነገር የለም፤ ይሁን  እንጂ ሁለቱም በእንባ እየተራጩ፣ የሟችን ቀብር  ሲያስፈጽሙ ኖረዋል፡፡
በውጊያ ላይ በሆነ ጊዜ ደግሞ ከኋላ ያለው ኃይል የቆሰለውን እንዳይማረክ እንደሚያሸሽ ሁሉ የሞተበትን የጓዱን እሬሳ  ቦታ አሲዞ ቆይቶ፣ ጦርነቱ ጋብ ሲል ተገቢውን ክብር ሰጥቶ፣ ቀብር ማስፈጸሙ የኖረ ጉዳይ ነው፡፡
የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም  የተገደለ ማንም  የአዲስ አበባ ኗሪ አንዲህ አይነት የክብር ሞትና አቀባበር አላጋጠመውም፡፡ በየደረሰበት በጥይት ተደበደበ፤ ቤቱ በላዩ ላይ እየተዘጋ፣ ቤንዚን እየተርከፈከፈ፣ በእሳት ነድዶ እንዲሞት ተደረገ። የሰውን ሕይወት ለማጥፋት የሚውል መሣሪያ ሁሉ በሥራ ላይ በዋለበት በነዚያ ቀናት ውስጥ፣ ያለ ርህራሄ ሰው እንደ እንጨት በፋስ (መጥረቢያ) ተፈለጠ፡፡
‹‹ኢትዮጵያን ቢቻል ያለ ኢትዮጵያዊያን አስረክብሃለሁ›› ብሎ ለሞሶሎኒ ቃል የገባው ጀኔራል ግራዚያኒ፤ ገጣሚው እንዳለው፣ “መቁሰሉን ሰበብ አድርጎ በልቡ ሲያስበውና ሲያንሰላስለው የነበረውን ኢትዮጵያዊያንን ከምድረ ገጽ የማጥፋት ሃሳብና ፍላጎት  በፍጹም ጭካኔ ተግባራዊ አድርጓል።
እነ አብርሃ ደቦጭ በጣሉባቸው አደጋ ጣሊያኖች የሞተባቸው አንድ ሰው፣ የቆሰለባቸው ሰላሳ ሆኖ እያለ፣ አንዱን በሁለትና በሶስት ሺ ሰው መንዝረው ነው የአዲስ አበባን ሕዝብ የተበቀሉት፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብ ያለቀው በቅርብ ስለተገኘ እንጂ ለሌላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የተውት አዝነውለት እንዳልነበረም መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ስለዚህም ነው ‹‹ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ከወለወል እስከ ጎንደር፤ ከግንቦት 1927 - ህዳር 1934›› መጽሐፍ ደራሲ፣ ተድላ ዘዮሐንስ ‹‹ጣሊያኖች እራሳቸው ብዙዎችን ወግተዋል፤ እንግሊዞችን ግሪኮችን ጭምር፤ እንደ ኢትዮጵያ የጨከኑበት በታሪክ ውስጥ ያለ አይመስለኝም›› በማለት አስተውሎቱን የገለጠው፡፡
የጣሊያኖች የግፍ አገዳደል አይነቱ ብዙ ነው። ‹‹ጎንደሬው በጋሻው›› ደራሲ ገሪማ ጣፈጠ፣ መጀመሪያ እሳት ነድዶ ብረት ምጣድ እንደሚጣድ፣ እዚያ ላይ ሞራ ተደርጎ እንዲቀልጥ ከተደረገ በኋላ፣ በቀለጠው ሞራ በጋለው ምጣድ ላይ ሰዎችን እንዲቀመጡና እንዲጠበሱ በማድረግ አሰቃይተው እንደሚገሏቸው ጽፏል፡፡ እዚያው ጎንደር ብላታ ግፊ የተበሉ ሰው፤ ‹‹ጣሊያን ከአምስት አመት በላይ አይገዛም›› ብለው ትንቢት በመናገራቸው ሲገደሉ፣ ልጃቸው አርበኛውን ፊታውራሪ ወርቁ ስንቄን፣ እቤትህ አሳድረሃል ተብለው ተከሰው፣ ከሌሎች አስራ ሁለት ሰዎች ጋር እላያቸው ላይ እንጨት ተረባርቦ፣ በእሳት ተቃጥለው  እንዲሞቱ ተደርጓል፡፡
አንድን ሰው እግሩን አንድ መኪና ላይ፣ እጁን ሌላ መኪና ላይ በማሰርና መኪናዎቹ በተቃራኒ አቅጣጫ እንዲሽከረከሩ በማድረግ፣ ሰውዬው ተበጣጥሶ እንዲሞት ማድረግ፣ ብዙ የተጠቀሙበት የግድያ  መንገዳቸው  ነው፡፡ ሰውን መኪና ላይ አስሮ እንደ ግንድ  በመጎተት የመግደል ሥራቸውም መጠቀስ ያለበት ነው፡፡
ከእነ ነፍሳቸው ጉድጓድ ውስጥ እየከተቱ የገደሏቸውም ቢሆን  ብዙ ናቸው፡፡ የጎጃሙ የቀኛዝማች ሰውነቴ ታሪክ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ቀኛዝማች ሰውነቴ “ለአርበኞች መሳርያ ታቀብላለህ ተብለው ተከሰው ይቀርባሉ፡፡ አልፈፀምኩም ቢሉም የሚያምናቸው አላገኙም፡፡ ሲጨንቃቸው፤ ‹‹እኔ እኔን  ወደ ቡሰታ ነው›› ይላሉ፡፡ ይህ አነጋገራቸው የእሳቸውን ሕይወት ቢያተርፍም ቡሰታ አካበቢ የሚገኙ የውኃ ጉድጓዶች ጣሊያኖች ሰዎችን ከእነ ሕይወታቸው የሚቀብሩባቸው እንደነበሩ ምስክር ሆኖ መኖር ችሏል፡፡ ከነዚያ ጉድጓዶች አንዱ አኔም የማወቀው የአቶ ንጉሤ አባተ የጉድጓ ውኃ ነው፡፡ የውኃው  ሰው ስለተገደለበት ለልብስ ማጠቢያ ብቻ ይውል እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡
ከራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ ጋር ተባብረዋል ያሏቸውን ሰዎች፤ እግራቸው ላይ ድንጋይ እያሰሩ፣ ከእነነፍሳቸው ጣና ሐይቅ በመክተት፣ የገደሉ ጣሊያኖች ፣ እንግዳ ዘውዴ የተባሉትን የጎንደር ሰው፤ እንደ ከብት ቆዳቸውን ገፈዋቸዋል፡፡ ኪዳነ ማርያም የተባለውን የስነ ጥበብ ሰውና አንዳንድ  የጥቁር አንበሳ ሠራዊት  አባላትን የገደሉት ደግሞ  ከአይሮፕላን ላይ  ወደ መሬት ወርውሮ በመፈጥፈጥ  ነው፡፡
ወደ የካቲት 12 እንመለስ፤ ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ ስለተነገረ፣ እኔን ጨምሮ  የየካቲት 12 ጭፍጨፋ ለሶስት ቀናት ብቻ የቆየ የሚመስላቸው አሉ። ከዚያ መአት የተረፉት መጋቢ መዕምራን ሞገስ ዘወልደ ማርያምን ጋዜጠኛ ንጉሤ አክሊሉ በ1962  አነጋግሯቸው ነበር፡፡ መጋቢ መዕምራን ሞገስ፣ ለንጉሤ ያወጉት እንዲህ በማለት ነው፡-
‹‹እለቱ አርብ፣  ወሩ የካቲት፣ ቀኑ 12 ሲሆን ሰዓቱ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ ነው፡፡ ፋሽሽቶች የከተማውን ሕዝብ በአዋጅ ሰብስበውት ነበር፡፡ ግራዚያኒ ሲደሰኩር፣ በብሔራዊ ስሜት የተነደፉ ሁለት ኢትዮጵያዊያን አደጋ ጣሉ፡፡ ወዲያው ትላልቅ ማርሻሎችና ሶልዳቶች በሰኬንቶ (ሰቸንቶ) እየተፋጠኑ፣ በአዲስ አበባ ውስጥ በዙሪያው ያሉትን ፋሽሽቶች፤ ሰላማዊውን ሕዝብ እንዲፈጁ፣ ከግራዚያኒ የወጣ ትዕዛዝ አስተላለፉ፡፡ ያን ጊዜ ዋናው የአዲስ አበባ ገበያ መናገሻ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ አቅራቢያ ስለነበር፣ ለገበያ የተሰበሰበው ሕዝብ ባላወቀው ምክንያት የጥይት በረዶ ወረደበት፡፡ በፍልጥ፣ ባካፋ፣ በዶማና በመጥረቢያ ተጨፈጨፈ።
ዛሬ ያንን መከራ ያላዩና ያልቀመሱት ወሬውን ስናጫውታችው እንዴት ያምናሉ? የፋሽሽት መሪዎች ከብዙ ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ላይ ሊጥሉት ያሰቡትን ለመፈጸም ወደ መናግሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አመሩ፡፡ በበሩ በኩል ወደ ውስጥ መተኮስ ጀመሩ፡፡ ቅኔ ማኅሌት ውስጥ በአገልግሎት ላይ የነበሩትን ካህናት ገደሏቸው፡፡ ያንን መከራ ከተቀበሉት መካከል አንዱ እኔ ነኝ፤ እንደነሱ ባልሞትም መሰቃየቴ አልቀረም፡፡
የካቲት 12 እልቂቱ የተጀመረበት እንጂ ያለቀበት አይደለም፡፡ እስከ የካቲት 15 ሰዎችን የማሰርና የመግደል ሥራ ቀጥሎ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ለሙታን የፍትሐት ጸሎት ማድረስ፣ የዘመድ ሬሳ ማየትና በሥርዓት መቅበር አልፎም  ድምጽ ሰምቶ ማልቀስ ለሕዝብ የተነፈገ ነበር፡፡
የዚህ ጽሑፍ አላማ በመጪው ሰኞ  የካቲት 12 ቀን 2010 ታስቦ የሚውለውን 81ኛውን የየካቲት 12ን እልቂት ማለትም፣ የሰማዕታትን ቀን ለማስታወስ ብቻ አይደለም፡፡ ይህች አገር ለህልውናዋ የሞቱላትንና የሚሞቱላትን፣ እንደ ጧፍ ነድደው ብርሃን የሰጧትን ልጆⶪን ልታስብበትና ልታከብረበት የሚገባ ቀን ልታቆም ይገባል በማለት ከዚህ ቀደም  በዚሁ ጋዜጣ (በ05/5/2010) ያቀረብኩትን ሀሳብ ይበልጥ ለማጠናከር ነው፡፡
በንጉሡ ዘመን የካቲት 12 በየአመቱ በብሔራዊ በዓልነት ይከበር የነበረ ሲሆን አከባበሩ ከፍና ዝቅ ያለበት ጊዜ ነበር፣ እነዚያ ጊዜዎች ደግሞ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተደረገበት 1953 ዓ.ም  እና ግርማዊት እትጌ መነን ያረፉበት  የካቲት 5 ቀን 1954  የፈጠሩት ተጽእኖ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ደርግ ቀኑን ከብሔራዊ በዓልነት አውርዶ፣ ተስቦ የሚውል በማድረጉ፣ መድፍ ተተኮስ፤ አበባ ተቀመጠ ከማለት በላይ የሚጠቀስ ነገር አላደረገም፡፡ የኢሕአዴግ ዘመን ቢብስ እንጂ የተሻለ አይደለም፡፡ ከአባል ድርጅቶቸ አንዱ የሆነው ህወሓት የተመሠረተው የካቲት 11 በመሆኑ የተነሳ የሚጻፍለትና የሚተረክለት እሱ ነው። የከቲት 12 ላይ ከፍ ያለ ተጽዕኖ አሳድሮበታል፡፡ የህወሐት ምሥረታ ስብሰባዎች  በዝርዝር ሲገለጡ፣ ለሰማዕታት ቀን የሚደርሰው የዘገባ ሽፋን ‹‹በሰማዕታት ሐውልት ሥር አበባ ተቀመጠ›› የሚል ነው፡፡ አበባ አስቀማጭ ሹሞች ራሳቸው ለቀኑ የሚመጥኑ ሆነው አልተገኙልኝም፡፡ የ2009 ዓ.ም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ደግሞ ጨርሶ ትዝ እንዳላለው መጥቀስ አለበት፡፡ በነገራችን ላይ ለትዝብቴ ብቸኛው የመረጃ ምንጬ እራሱ አዲስ ዘመን ነው፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ  የየካቲት 12 እልቂት ያስከተለውን ተጽዕኖ ለማሳየት አዲስ ዘመን ጋዜጣ የካቲት 12 ቀን 1960 ከጻፈው ርዕሰ አንቀጽ በማስረጃነት መጥቀስ ተገቢ እንደሆነ አምናለሁ። እጠቅሳለሁ፤ ‹‹ያን እለት የተፈጠረው እልቂት የተራፊዎችን ልብ አደንድኖ ጫካ እንዲገቡ ማድረጉን አንረሳም፡፡ ያ እለት የፈጠራቸው አርበኞች፤ ጦርነቱ ማብቂያ ጊዜ ድረስ ከጠላት ጋር ተጋፍጠው በመሰዋእትነታቸው ለሀገሪቱ መድህን አስገኝተዋል።›› በዚህ የአዲስ ዘመን ሃሳብ፣ ታሪክ ጸሐፊው ተድላ ዘዮሐንስና ሌሎችም ይስማማሉ፡፡
የየካቲት 12 ሰማዕታት፣ ተራ ሞት የሞቱ ሰዎች አይደሉም፤ ለኢትዮጵያ ነጸነት ደግም መመለስ በሞታቸው ዋጋ የከፈሉ ናቸው፡፡ እነሱ እንደዚያ በግፍ ባይጨፈጨፉ ኖሮ ሁሉም ወደ አርበኝነት አይገባም፤ እስከ መጨረሻውም አምርሮ አይታገልም ነበር፡፡ እነሱ ባይሞቱ ኖሮ የእትዮጵያ ሕዝብ ከኢጣሊያ የቅኝ አገዛዝ ጋር ጨርሶ ሊኖር አለመቻሉን አያረጋግጥም ነበር፡፡ የእነሱ ሞት አርበኛውን ባያነሳሳው ኖሮ አድዋ ላይ የተገኘው ድል ተጠብቆ፣ ዛሬ  ለእኛም ለጥቁር ሕዝብም መመኪያ መሆን አይችልም ነበር፡፡ እነሱ ላይ ያ መራራ ግፍና በቀል ባይፈጸም ኖሮ፣  ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም የተገኘው የሀገራችን ነጻነት ሁለተኛው አድዋ ማለት ይቻላል፡፡ በጣሊያን ቅኝ አገዛዝ ላይ አይገኝም ነበር። የየካቲት 12 እልቂት ማለትም  የሰማዕታት ቀን ተስቦ መዋሉ ቀርቶ በአግባቡ የሚከበር ብሔራዊ ቀን መሆን ያለበትም በዚህ  አስተዋጽዖው  ነው፡፡
ብሔራዊ በአል ሆኖ በሚከበርበት ጊዜ ደግሞ የትምህርት ተቋማት፣ ቀኑን ምክንያት አድርገው፣ የምርምር ሥራዎችን እንዲሠሩ ያነሳሳቸዋል። የመገናኛ ብዙኃን በማስታወቂያ ሥራቸው ሳይቀር ቀኑን እንዲያስታውሱ ስለሚገደዱ ታሪክን ለተተኪው ትውልድ ለማሻገር የተመቸ  መንገድ ይፈጥራል፡፡ ስለ አድዋ፣ ስለ ሚያዝያ 27 የምንናገረውን ያህል ስለ የካቲት 12 መናገር ይኖርብናልም እላለሁ፡፡
ከታሪክ ትዝብት
ለመዳን ታሪክን
ማክበር ይገባል!!!

Read 1461 times