Sunday, 18 February 2018 00:00

መሪዎቻችንን ታዘብናቸው!

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(5 votes)

   --”እናም የኢትዮጵያ ህዝብ ከፖለቲካ መሪዎቹ፣ የላቀ አስተሳሰብ ያለው አስተዋይ ህዝብ በመሆኑ፣ ለጊዜው ከአንዣበበው አደጋ ተጠብቀናል፡፡ የሐገራችን የህዝብ ሚዲያዎችም፤ ‹‹ተነስ ወገንህ እያለቀ ነው›› ብለው ሲቀሰቅሱ፣ ዝም ብሎ የማለፍ ህሊና መያዝ ችለዋል፡፡ ራሳቸውን የስርዓቱ ባለቤትና ጠበቃ አድርገው ከሚመለከቱ የገዢው ፓርቲ የፖለቲካ አመራሮች ይልቅ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የህዝቡ ሰላም እንዳይረበሽ ከወትሮ የተለየ ጥንቃቄ ሲያደርጉ አይተናል፡፡--”
        
    ይህ መጣጥፍ በሐገራችን ሚዲያ ጉዳይ ያጠነጥናል፡፡ መጣጥፉ ለሚያነሳቸው ጉዳዮች ማዳወሪያ አድርጌ የያዝኩት፤ የተለያዩ የብሮድካስት አገልግሎት ባለፈቃዶች ተሳታፊ የሆኑበት እና ባለፈው ወር አጋማሽ (ጥር 12/2010 ዓ.ም) የኢትዮጵያ የብሮድካስት ባለሥልጣን፤ ‹‹የሐገራችን ሚዲያ አዝማሚያዎች›› በሚል ርዕስ ባካሄደው ውይይት የተነሱ አንዳንድ ጉዳዮችን ነው፡፡ በዚሁ የውይይት መድረክ፣ የብሮድካስት አገልግሎት ምህዳሩ ብቻ ሣይሆን፤ የሣይበር ምህዳሩም ትኩረት አግኝቷል፡፡ የሳይበሩን ነገር መነሻ አድርጌ የመንግስት ሚዲያዎችን እና የተቆጣጣሪውን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የተወሰኑ ችግሮች ለማየት እሞክራለሁ፡፡
የሣይበሩ ምህዳር
የሣይበር ምህዳሩን ገና በውል አናውቀውም፡፡ አዲሱ የመገናኛ ቴክኖሎጂ ዕድገት የፈጠረው ይህ አዲስ ምህዳር፤ ለእኛ ቀርቶ የዳበረ የዴሞክራሲ ባህል ላላቸው እና የቴክኖሎጂው ባለቤት ለሆኑት ህዝቦችም ጭምር ግራ አጋቢ ሁዳድ ነው፡፡ ይህ ምህዳር ከፍተኛ አደጋ መጋረጡን እያየን ነው፡፡ ሁሉንም ወገን ‹‹ኧረ መላ በሉ›› እያሰኘ ነው፡፡
በዚህ የተነሳ ዓለም ምንነቱ በውል ተለይቶ በማይታወቅ እና ዕረፍት የሚነሳ ፍጥነት ባለው ‹‹የአብዮት ጎዳና›› እየተራመደች ነው፡፡ ይህ አብዮት ከዚህ ቀደም የምናውቀው የህትመት ቴክኖሎጂ በዓለም ላይ ከፈጠረው ሁለ-ገብ አብዮት ጋር ሲነጻጸር በተጽዕኖው እጅግ የላቀ ነው፡፡ የህትመት ቴክኖሎጂ መፈጠር የዓለምን መልክን እና ባህርይ ምን ያህል እንደ ቀየረው እናውቃለን፡፡ በህትመት ቴክኖሎጂ መፈጠር የተነሳ፤ ለብዙ ጊዜ የጥቂቶች ልዩ ሐብት ሆነው የቆዩት መጻህፍት ለብዙዎች የሚዳረሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህ አብዮት፤ ሰው ከሰው ጋር ያለውን ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ሰው ከአምላኩ ጋር ያለውን ግንኘኑነት በእጅጉ ቀይሮታል፡፡
በርግጥ በወቅቱ በነበሩት የአውሮፓ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ይገኙ የነበሩት መጻህፍት በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡ አንዳንዶች፤ በአውሮፓ ቤተ መጻሕፍት የነበሩት ሁለት መጻሕፍት ነበሩ ይላሉ -መጽሐፍ ቅዱስ እና የአርስጣጣሊስ ኢንሳይክሎፒዲያ፡፡ በስተቀር ሌላ መጽሐፍ አልነበረም፡፡ እዚህን መጻሕፍት ለማየት የሚችሉት ጥቂት ቀሳውስት እና መሳፍንት ነበሩ፡፡ የጥበብ ማዕድ የሆኑት መጻሕፍት የጥቂት መሳፍንት ወይም ቀሳውስት ሐብት ሆነው ለብዙ ዘመናት ቆይተዋል፡፡
ከህትመት ቴክኖሎጂ መፈጠር በኋላ፤ የታሪክ ምሁራን ‹‹ራስን የመግለጥ ዘመን›› (The Age of Expression) ሲሉ የሚጠሩት ዘመን መጣ። ይህ ዘመን ተራው ህዝብ ነገስታቱ እና ጳጳሱ ምን እንደሚያስቡ ወይም ምን እንደሚያደርጉ እስኪነግሯቸው ድረስ በዝምታ ቁጭ ብለው የሚጠብቁ ዜጎች መሆናቸው ያበቃበት አዲስ ዘመን ነበር፡፡ ተራው ህዝብ ተደራጊ ብቻ ሳይሆን አድራጊ መሆን የጀመረበት ዘመን ነበር፡፡ ዜጎች ከህይወት መድረክ ወጥተው ተዋናይ ሆኑ፡፡ ብዙዎች የግል አስተያየት እና ሐሳባቸውን ለመግለጽ የሚፈልጉ ሰዎች ሆኑ፡፡ እንደ ፍሎሬንሱ የታሪክ ጸሐፊ ኒኮሎ ማክያቬሊ በመንግስት አመራር ጥበብ ጉዳይ የሚሉት ሐሳብ ካላቸው፤ መጽሐፍ ጽፈው፤ ‹‹ጥሩ መሪ እንዲህ ያለ ነው›› እያሉ፤ የግል ሐሳባቸውን መግለጽ የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ ታዲያ ‹‹ራስን የመግለጥ ዘመን›› መጻህፍት በመደጎስ የተወሰነ አልነበረም፡፡ ሐሳቡን በቀለም መግለጽ የሚሻ በስዕል፣ በሚዳሰስ ቁስ ሊገለጽ የሚችል ሐሳብ አለኝ የሚል - በቅርጻ ቅርጽ ወዘተ ሐሳቡን ይገልጽ ጀመረ፡፡ ሙዚቃ እና ሥነ ህንጻም ራሳቸውን መግለጽ ለሚፈልጉ ሰዎች ዘይቤ (መባያ) ሆኑ፡፡
በሐገረ ጀርመን ውስጥ ሜይንዝ (Mainz) በተባለች ከተማ ይኖር የነበረው ሰው ያመጣው ነገር የዓለምን ሁኔታ ቀይሯል፡፡ ጆሐን ዙም ጋንሴፍለሽ (Johann zum Gansefleisch) በሚል የሚጠራው እና በብዙዎች ዘንድ ጆሐን ጉተንበርግ በሚል ስም የሚታወቀው ሰው፤ መጽሐፍን የማባዛት አዲስ ጥበብ መፍጠሩ አብዮት አስነሳ፡፡ በመጀመሪያ በመላ ጣሊያን (ብዙም ሳይቆይ በመላ አውሮፓ) ‹‹በሰው ልጆች የዕውቀት፣ የውበት እና የጥበብ መጋዘን ውስጥ አንድ የምጨምረው ነገር አለ›› ብለው የሚያስቡ ሰዎች በረከቱ፡፡ ጉተንበርግ ከፈጠረው የህትመት ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ የፍትሐ-ብሔር ክስ ተመስርቶበት፤ በክርክሩ ገንዘቡን ጨርሶ በድህነት ተቆራምዶ ለሞት በቃ፡፡  የእርሱ እኩያ ሆኖ በዛሬው ዘመን የተነሳው ማይክል ዙከንበርግ ግን በሐብት እየተንበሸበሸ ነው፡፡
ጆሐን ጉተንበርግ፤ በሊድ የተቀረፁ ፊደላትን በመጠቀም ቃላት አቀናብሮ መጽሐፍ የማተም ጥበብን ለዓለም ሲያበረክት፤ በላቲን፣ በእብራይስጥ እና በግሪክ ቋንቋዎች የተለያዩ መጻህፍት እየታተሙ ይወጡ ጀመር፡፡ ዓለምም ‹‹አንዳች የምለው ነገር አለኝ›› የሚሉ ሰዎች የሚያነሱትን ሐሳብ ለመስማት በእጅጉ የምትጓጓ ሆነች፡፡ መማር ወይም ማንበብ የጥቂት ዕድለኞች ሰዎች ፀጋ ሆኖ የቆየበት ዘመን አከተመ፡፡ ድንቁርናን ታቅፈው የሚኖሩ ሰዎች የመጨረሻ ሰበብ አድርገው የሚያነሱት (‹‹መጽሐፍ የት ይገኛል ብላችሁ ነው››) የሚል መከላከያ ከዓለም ተወገደ፡፡ ለብዙሃኑ ህዝብ የሚመጥን ይዘት ያላቸው እና በርካሽ ዋጋ ሊገዙ የሚችሉ መጻሕፍት መታተም ጀመሩ፡፡ የጥንታዊ ፈላስፎች የእነ አርስጣጣሊስ፣ አፍላጦን፤ የጥንታዊ ደራስያን የእነ ቨርጅል፣ የሆሬስ እና ፕሊኒ ሥራዎችን በትንሽ ሣንቲም ገዝቶ ማንበብ የሚቻልበት አዲስ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ የህትመት ቴክኖሎጂ ሁሉም ሰዎች ነጻ እና እኩል መሆናቸውን አረጋገጠ፡፡ ዓለም በህትመት ጥበብ መፈጠር ምን ያህል እንደ ተቀየረች ለመረዳት ብዙ የታሪክ ሁነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሆኖም ነገር እንዳይረዝም በደፈናው ‹‹ዓለምን ተቀየረች›› ብዬ ልለፈው፡፡
አሁን ደግሞ አዲሱ የመረጃ ቴክኖሎጂ (ሣተላይት፣ ሞባይል፣ ኮምፕዩተር፣ ኢንተርኔት ወዘተ) ‹‹በሳይንሳዊ ልቦለድ ውስጥ የምንኖር እንዲመስለን አድርጓል፡፡›› የሰው ሰራሽ አዕምሮ ቴክኖሎጂ (Artificial Intelligence) የዓለምን መዳረሻ አጓጊ አድርጎታል፡፡ አንድምታው ገና ያልታወቀ አብዮት ይዞብን መጥቷል፡፡
በአጠቃላይ አዲሱ የመረጃ ቴክኖሎጂ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት (በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት) ለወሬ በሚያስቸግር ሁኔታ የሰውን ህይወት በጥልቀት እና በፍጥነት እየቀየረው ይገኛል። ከዚህ ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩትን አዳዲስ የአገልግሎት ዓይነቶች ለመገመት አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ መስኩ ጨርሶ ከኔ ክበብ የወጣ በመሆኑ፤ በአጭር አማርኛ ‹‹ዓለም የሚሰራትን አሳጥቷታል›› ብዬ ባልፈው ይሻለኛል፡፡ አንዱን የመረጃ ቴክኖሎጂ ትሩፋት አጣጥመን ወይም በወጉ ተረድተን ሳንጨርስ ሌላው ይመጣል። ‹‹መተግበሪያው›› በአናት በአናቱ ይመጣል፡፡ የለውጡ ፍጥነት ትንፋሽ የሚያሳጥር ነው፡፡ ቀድሞ ከምናቀው ዓለም ፍፁም የተለየ እና ገና ባህርይውን ጠንቅቀን ለማወቅ ያልቻልነው አዲስ ሰው ሰራሽ ምህዳር ተፈጥሯል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ ‹‹የት ያደርሰን ይሆን?›› የሚያሰኝ ሥጋት ፈጥሯል፡፡  
ለወትሮው የምናውቃቸው የብስ፣ ባህር፣ አየር የሚባሉ የተፈጥሮ ምህዳሮችን ነበር፡፡ አሁን የመጣው ሰው ሰራሽ ምህዳር ‹‹ሳይበር›› ይሉታል፡፡ ስሙም አማርኛ ይመስላል፡፡ ባለፉት ሁለት አስርት በፍጥነት እያደገ የመጣው፤ ይህ አዲስ ምህዳር ከዚህ ቀደም ከኖሩ ሰዎች ተመክሮ እና የህይወት ልምድ የምናገኝበት ምህዳር አይደለም፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ በአንድ ትውልድ ዕድሜ ተወልዶ፤ ለመረዳት በሚያስቸግር ፍጥነት እያደገ የሚገኝ ቴክኖሎጂ በመሆኑ፤ በትሩፋቱ እየተጠቀመና በክፋቱ እየጎዳ ያለው፤ የቴክኖሎጂ ፈጣሪው ትውልድ ነው፡፡
በዚህ ሰው ሰራሽ ምህዳር ያለውን አደጋ እና ፀጋ እየቀመስን በምህዳሩ የምንንከራተተው ሁላችንም ነን፡፡ እንደ ኮሎምበስ ወይም ማጂላን ያሉ በርካታ አሳሾች መከራ አይተው እና ተንገላተው መረጃ ከሰበሰቡ በኋላ የገባንበት ምህዳር አይደለም፡፡ ይህ ትውልድ ድንገት ሳያስበው፤ ጊዜን እና ቦታን አኮማትሮ፤ ዓለምን በመዳፍ ውስጥ ማስገባት የሚችል ቴክኖሎጂ ባለቤት ሆኗል። እንዲህ ያለውን ክስተት ለመግለጽ ‹‹ዓለም አንድ መንደር ሆነች›› እንላለን። በዚህ ቴክኖሎጂ የተነሳ፤ በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ርቀት፣ አንድ የኮምፒዩተር ቁልፍ ለመጫን በሚወስደው ጊዜ የሚመጠን ሆኗል። ‹‹ሳይበር›› የሚባለው ምህዳር የምንኖርባትን መሬት ከአንድ ጨሌ ያነሰች አድርገን እንድንቆጥራት የሚያደርግ ሰፊ ዓለም ነው፡፡ አሁን 5-ጂ ከሚባለው እጅግ እጅግ ፈጣን የመረጃ ልውውጥ ስርዓት ደርሰናል፡፡  ቴክኖሎጂው፤ በትምህርት፣ በህክምና፣ በንግድ፣ በማህበራዊ መስተጋብር ወዘተ አስደናቂ ሁኔታ እየፈጠረ ነው። በአጭሩ ‹‹በአንድ ሳይንሳዊ ልብወለድ የምንገኝ ገጸ ባህርያት አድርጎናል፡፡›› ይህ ሁኔታ እንኳን ቴክኖሎጂውን በመቅዳት ለመጠቀም ለምንሞክረው ለእኛ፤ ለባለቤቶቹም ዓመሉ ያልታወቀ አውሬ ሆኖባቸዋል፡፡
እንግዲህ አሁን የምንኖርባት ኢትዮጵያ በዚሁ ቴክኖሎጂ ፀጋ የምትጠቀምና ቴክኖሎጂው ባመጣው አደጋ የምትንገላታ ነች፡፡ ከአዳዲሶቹ ቴክኖሎጂዎች ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ለውጥ የሚተነብዩ የዘርፉ ባለሙያዎች፤ አዳዲሶቹ ቴክኖሎጂዎች ብዙ ዓመታት ሳይወስዱ በህይወታችን ወይም በአሰራራችን ላይ ለውጥ እንደሚያመጡ ይነግሩናል። ቴክኖሎጂዎቹ  በሦስትና በአራት ዓመታት ውስጥ አሁን የምንገኝበትን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ እንደሚቀይሩት ይነግሩናል፡፡ በዚህ ቴክኖሎጂ የተነሳ የቋንቋ አጥር ይረመሳል፡፡ የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ሁለት ሰዎች በዛው በሚናገሩበት ቅጽበት፣ ሐሳባቸው እየተተረጎመ፣ መነጋገር የሚችሉበት ከሞባይል ጋር የተያያዘ ቴክኖሎጂ ተፈጥሯል፡፡ ይህን ጽሑፍ በምጽፍበት ጊዜ ይህ ቴክኖሎጂ በሐገረ - በሆላንድ ሙከራ እየተደረገበት አይቻለሁ፡፡ አንድ የሲ.ኤን.ኤን ጋዜጠኛ በጎዳና ወጥቶ 80 ቋንቋዎችን ለመተርጎም የሚችለውን መሣሪያ በመጠቀም ለሰዎች ቃለመጠይቅ ሲያደርግ ተመልክቻለሁ፡፡ ‹‹ጉድ በል ጎንደር›› ማለት አሁን ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በመገናኛ ብዙሃን ቴክኖሎጂ ረገድ ይታዩ የነበሩት ለውጦች እርጋታ ነበራቸው። አሁን እርጋታ የሚባል ነገር የለም፡፡ ከአንዱ አስደናቂ ቴክኖሎጂ ይበልጥ አስደናቂ ወደ ሆነ ሌላ የቴክኖሎጂ ውጤት በቀናት፣ በሣምንት፣ በወራት ጊዜ መሸጋገር የተለመደ ሆኗል፡፡ በስልክ፣ በሬዲዮና በቴሌቭዥን መካከል የዓመታት ፋታ እያገኘን ስንሸጋገር ቆይተን ነበር፡፡ የአሁኑ ለውጥ በቅጽበት ዕድሜ የሚመጠን ነው፡፡
ብሮድካስት
ይህን ሐተታ ያመጣሁት፤ ከመነሻዬ በጠቀስኩት የኢትዮጵያ የብሮድካስት ባለስልጣን ባዘጋጀው የውይይት መድረክ የተነሱ አንዳንድ ጉዳዮችን መነሻ አድርጌ የተወሰኑ አስተያየቶችን ለመስጠት ነው። የኢትዮጵያ የብሮድካት አገልግሎት ባለስልጣን ማቋቋሚያ አዋጅ የታወጀው በ1991 ዓ.ም ነበር። የመስሪያ ቤቱ አሰራርና አዋጅ ዘመኑን የዋጀ አይደለም። የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ በታወጀ ጊዜ የያዛቸው አንዳንድ ድንጋጌዎች ኋላ ቀር ነበሩ፡፡ በመስኩ ያለው ለውጥ ፈጣን በመሆኑ፣ አሁን ይበልጥ ኋላ ቀር መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ በዚህ ዘርፍ ያሉ ፖሊሲዎች (ካሉ) እንደገና መፈተሽ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ አዋጅ በወጣበት ጊዜ የነበሩት ሁኔታዎች ዛሬ ፍጹም ተቀይረዋል፡፡ በአዋጁ ላይ በ1999 ዓ.ም የተወሰኑ መናኛ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡
አሁን በሥራ ላይ ያለው የብሮድካስት አዋጅ፤ የአየር ሞገድ ውሱን ሐብት መሆኑን መነሻ በማድረግ የታወጀ አዋጅ ነው፡፡ ሆኖም የዲጂታል ቴክኖሎጂ መፈጠር የአየር ሞገድ ውሱን ሐብት መሆኑን አስቀርቶታል፡፡ ስለዚህ የብሮድካስት አዋጁ ለመጀመሪያ ጊዜ በወጣ ጊዜ ‹‹የአየር ሞገድ ውሱን የህዝብ ሐብት ነው›› በሚል የያዘው መነሻ፣ ዘመኑን ያልዋጀ መነሻ በመሆኑ ይተች ነበር፡፡ በወቅቱ፤ አዋጁ የቴክኖሎጂ ጥበብ አልፎት የሄደ ገደብን ያስቀምጣል የሚል ክርክርም ይነሳ ነበር። ዛሬ በቀላሉ ‹‹የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን አገልግሎት›› ለመስጠት ይቻላል። በአንድ በኩል፤ የማሰራጫ ቁሳቁሶቹ፣ እንደ ሻንጣ በቀላሉ ሊያዙ የሚችሉና ከማንኛውም ሰው እጅ በቀላሉ ሊገቡ የሚችሉ ነገሮች ሆነዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ አገልግሎቱ ከኢንተርኔት ጋር ተያይዞ ይበልጥ ቀላል ሆኗል፡፡ በዚህ ሁኔታ የሐገራችን የብሮድካስት አዋጅ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሐይማኖት ድርጅቶች የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ አይሰጣቸውም›› የሚክልከላ አስቀምጧል። ይህን አዋጅ ተፈጻሚ ማድረጉ አስቸጋሪ ይሆናል። ተፈጻሚ ሊደረግ የማይችል አዋጅ ማውጣት ደግሞ ትርጉም የለሽ ይሆናል፡፡ አዲሱ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ለአጠቃቀም ቀላልና የማይገደብ የተደራሽነት ዕድል የሚከፍት በመሆኑ፤ የኢትዮጵያ የብሮድካስት ባለስልጣን የአገልግሎት ፈቃድ የሰጣቸው የቴሌቭዥንና የሬድዮ ጣቢያዎች፣ ወደ አዲሱ ምህዳር እየተሰደዱ ነው፡፡ ፋናን ወይም ኢቢሲን በኢንተርኔት ለመከታተል የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህ ሁኔታ በአዋጁ የተጠቀሰውን ‹‹ሐገር አቀፍ ስርጭት፣ የክልል ስርጭት፣ የማዘጋጃ ቤት እና የማህበረሰብ›› በሚል የሚሰጠውን የአገልግሎት ፈቃድ ትርጉም የለሽ ያደርገዋል፡፡  አሁን በሥራ ላይ ያለው የብሮድካት አገልግሎት፣ ከሁኔታዎች ጋር መጣጣም የሚገባቸው በርካታ ድንጋጌዎችን የያዘ ነው፡፡
አሁን የታየው አዲስ የቴክኖሎጂ ክስተት የብሮድካስት ባለስልጣን አሰራርን ብቻ ሣይሆን፤ ራሱ ‹‹መንግስት›› የተሰኘውን ተቋም ጊዜ ያለፈበት እንዲመስል እያደረጉት ነው፡፡ ዛሬ ለወትሮው የሚታወቀው የመንግስት የቁጥጥር አቅም በቦታው የለም፡፡ አዲሱ ምህዳር አዳዲስ ሽፍቶችን ፈጥሯል። የዘንድሮ ‹‹ሽፍታ›› ሶማ፣ ተከዜ ወይም አባይ በረሃ መሄድ አያስፈልገውም፡፡ አውሮፓ፣ አሜሪካና እዚሁ አዲስ አበባ ሆኖ መሸፈት ይቻላል፡፡ ‹‹ጉድ በል ጎንደር›› ማለት አሁን ነው፡፡
የሐገራችን የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ ሰጪ እና ተቆጣጣሪ የሆነው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን፤ ማድረግ የሚችለውና የማይችለውን ለይቶ፤ ራሱን ከአዲሱ ሁኔታ ጋር ለማስማማት እንደገና ጥናት ማድረግ አለበት፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ የኢትዮጵያ የብሮድካት ባለስልጣን፣ ፈቃድ የሰጣቸውን የመንግስት፣ የንግድና የማህበረሰብ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎችን ለመቆጣጠር የማይችል ደካማ ተቋም መሆኑን ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሆኑት ነገሮች አይተናል፡፡
ሐገር ስትቃጠል ዝም ብሎ ሲመለከት የነበረው ባለሥልጣን፣ አንዳንድ የመንግስት የመገናኛ ብዙሃንን ‹‹ህገ መንግስቱ ሲቃጠልና ሐገር ከፊቱ ሲፈርስ ዝም ብሎ ይመለከት ነበር›› ብሎ ሲከስስ ሰምተናል፡፡ እርሱ ዝም ብሎ፤ ሌሎችን በዝምታ ይከሳል፡፡ ብሮድካስት ባለስልጣን ሊያደረግ የሚገባውን ነገር ባለማድረግ፤ ሌሎች ደግሞ ማድረግ የማይገባቸውን ነገር በማድረግ፤ ሁለቱም ህገ መንግስቱን ሲጥሱትና ሲንዱት ከርመዋል። ቀልደኛ ነው፤ ‹‹ከበትሩ ካሮቱ ይለናል፡፡›› ሐገር እየፈረሰ በካሮትና በበትር መካከል ምርጫ ይዟል፡፡  
ብዙ የመንግስት ሚዲያዎች ህዝብን በህዝብ ላይ የማነሳሳት ከባድ ወንጀል ፈጽመዋል፡፡ ራሳቸው የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር፤ ‹‹ባለፉት ሁለት ዓመታት በበርካታ ሚዲያዎች የተፈጸመው ህገ ወጥ ተግባር፣ ፈቃድ ሊያስነጥቅ የሚችል ነበር›› ብለዋል። የዳሬክተሩን አስተያየት ተንተርሰው ሐሳብ የሰጡ የጉባዔው ተሳታፊዎችም፤ ‹‹የባለስልጣኑ ተግባር ከኃላፊነት የሚያስነሳ ወይም ስልጣን የሚያስለቅቅ ነበር›› ሲሉ የአጸፋ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ ይህን ሁሉ የሚሰማው የኢትዮጵያ ህዝብ ይታዘባል፡፡ የህግ ባለሙያዎች፤ ‹‹አንተ የሰው ሐብት ዘርፈሃል›› ሲባል፣ ‹‹አንተስ አልዘረፍክም›› የሚል ምላሽ ከወንጀል ነጻ አያደርግም ይላሉ፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም ሌቦች ናቸው፡፡
‹‹ዳኛ የለም እንጂ፤ ቢኖርማ ዳኛ›› እያልን፣ የባለስልጣኑንና የባለፈቃዶቹን ክርክር ሰማን። እውነቱን ለመናገር፤ ህዝብን በህዝብ ላይ ታነሳሳላችሁ›› እያለ የነጻውን ፕሬስ ሲከስስና ሲያስር በቆየው መንግስት ቁጥጥር ሥር የሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን፤ ህዝብን በህዝብ ላይ የማነሳሳት ተግባር ውስጥ ተጠምደው አየናቸው፡፡ ‹‹ዳኛ የለም እንጂ፤ ቢኖርማ ዳኛ›› እነሱም ዘብጥያ ይወርዱ ነበር። ‹‹እናከብረዋለን - እናስከብረዋለን›› የሚሉትን ህገ መንግስት ሲጥሱትና ሲያዋርዱት ተመለከትን። የባለፈቃዶቹን አሰራር የመቆጣጠር ኃላፊነት የተጣለበት የብሮድካስት ባለስልጣንም፤ ‹‹እርምጃ ያልወሰድኩት ነገሩን ላለማባባስ ብዬ ነው›› አለን፡፡ በዝምታ ወይም ባለማድረግ ህገ መንግስቱን ሲጥስ የከረመው ብሮድካስት (አሁን ያደረገውን ጉባዔ እንኳን ማድረግ ተስኖት) የችግሩ አባሪ -ተባባሪ ሆኖ ቆይቶ፤ ‹‹የደቡብ ቴሌቭዥን የተፈጠረውን ትርምስ በዝምታ ይመለከት ነበር›› ብሎ ሲወቅስ ሰማን፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከገዢው ፓርቲና ከመንግስት ይልቅ የተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ ከመንግስት ሚዲያዎች ይልቅ የግል ፕሬሶችና የንግድ ብሮድካስተሮች ሐገርን ከጥፋት ለመጠበቅ የሚያስችል የተሻለ ሥራ የሰሩ ይመስለኛል። በዚህ በኩል ያለውን ጉድ እዚህ ትተን፤ በብሮድካስት አገልግሎት ውስጥ የሚታዩ አንዳንድ ችግሮችን በማንሳት ስለ ወደፊቱ ሁኔታ እንነጋገር፡፡
የብሮድካስት ባለስልጣን በውጭ ሐገር ተመዝግበው በኢትዮጵያ የቴሌቭዥን ስርጭት የሚያካሂዱ ጣቢያዎችን እንዴት እንደሚያስተናግዳቸው የሚያውቅ አይመስለኝም። አሁን ባለው የቴክኖሎጂ ሁኔታ፣ የብሮድካስት ባለስልጣን ለመቆጣጠር ቢፈልግም፤ ለቁጥጥር አስቸጋሪ የሚሆኑ ሁኔታዎች አሉ፡፡ በመሆኑም ለማስፈጸም የማይቻል ድንጋጌ አውጥቶ፤ በድሮ በሬ ለማረስ ከመሞከር ይልቅ፤ የኢትዮጵያ የብሮድካስት አገልግሎት ለመቆጣጠር የሚችለውን ነገር በደንብ ለይቶ አውቆ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ ውሱን የጋራ ሐብት›› የሚለውን የአየር ሞገድ በተሻለ ሁኔታ ለማስተዳደር የሚችልበትን ሁኔታ መፈለግ ይኖርበታል፡፡
አሁን ባለው ቴክኖሎጂ የአየር ሞገድ ውስን ሐብት መሆኑ የቀረ ይመስለኛል፡፡ የአንዱ ጣቢያ ስርጭት ከሌላው ጋር ግጭት ሳይፈጠር በጣም ተቀራራቢ በሆኑ የአየር ሞገዶች ስርጭት ለማድረግ የሚቻልበት ቴክኖሎጂ እውን ሆኗል፡፡ በመሆኑም፤ የአየር ሞገድ ውስን ሐብት መሆኑን በመጥቀስ፤ አጠቃቀሙን ለመቆጣጠር የወጣው ህግ ከንቱ ይመስለኛል፡፡ አንድም፤ ሐብቱ ውስን ስላልሆነ፤ አንድም ለቁጥጥር አስቸጋሪ ስለሆነ፡፡
ለምሣሌ፤ በሐገራችን ህግ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሐይማኖት ድርጅቶች የብሮድካስት አገልግሎት ሥራ ፈቃድ አይሰጣቸውም፡፡ ሆኖም በርካታ የሐይማኖት ድርጅቶች፣ የቴሌቭዥን ሥርጭት ሲያካሂዱ እንመለከታለን፡፡ የብሮድካስት ባለስልጣን እነዚህን ተቋማት በዝምታ እያያቸው ነው፡፡ ይህን ሁኔታ ለመቆጣጠር የሚችልም አይመስለኝም። በአጠቃላይ በሰሞኑ ውይይት የብሮድካሰት ባለስልጣን ምን ያህል ደካማ ተቋም መሆኑን ብቻ ሳይሆን፤ የሚሰራውን የሚያውቅ መሆኑን ለመጠራጠር የሚያበቃ ሁኔታ ተመልክተናል። ሌላው ቀርቶ የሞኒተሪንግ ሥራ ለመስራት የማይችል ተቋም መሆኑን አይተናል፡፡  
በአንጻሩ፤ የሐገራችን የመንግስት ሚዲያዎችም ከምን ደረጃ ሊወርዱ እንደሚችሉ አይተናል፡፡ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ሐገርን ሊያፈርስ የሚችል ሥራ ለመስራት የሚችሉ መሆናቸውን ታዝበናል። ሐገሪቱ በህዝብ ጨዋነትና ብቃት እንደ ሩዋንዳ፣ ሰርቢያና ዩጎዝላቪያ ያለ ሁኔታ ባይከሰትም፤ የእኛ ሚዲያዎች በተጠቀሱት ሐገራት የነበሩ ሚዲያዎች ሲሰሩ የነበሩትን ነገር ሲሰሩ አይተናል፡፡ የእኛ ባለስልጣናት፤ በሩዋንዳ፣ ሰርቢያና ዩጎዝላቪያ የሐገር ሞት ሲጎትቱ የነበሩ የተለያዩ ቡድኖች፣ የጦር አበጋዞች ወይም የህዝብ አስተዳዳሪዎች ያደርጉት የነበረውን ነገር ሲያደርጉም ተመልክተናል፡፡ ‹‹ዳኛ የለም እንጂ፤ ቢኖርማ ዳኛ›› አሰኝተውናል፡፡ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችም ጸረ ህዝብ የመሆን ችሎታ እንዳላቸው አይተናል፡፡ ገዢው ፓርቲም ባለፉት አርባ ዓመታት ታሪኩ ታይቶ ከማይታወቅ የዝቅጠት ደረጃ መውረዱን ታዝበናል፡፡
በአጠቃላይ በመንግስት ሚዲያዎች የታየው ችግር፤ በገዢው ፓርቲ ውስጥ የታየው የአመራር ቀውስ መገለጫ መሆኑን ደጋግመን አስምረን፤ በዚሁ መስመር የመንግስት የሚዲያ ተቋማት ወይም ባለሙያዎች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ቁመት የሚልቅ ተክለ ሰውነት እንደ ሌላቸው መናገር ይኖርብናል። ሐገሪቱን ከተለያዩ አደጋዎች የመጠበቅና በመርህ ላይ የተመሠረተ አመራር የመስጠት ኃላፊነት የተጣለባቸው የመንግስት ተቋማትም፤ ለክፉ ቀን የሚሆን የሞራል ፀጋ እንደሌላቸው ታዝበናል። እንዲሁም፤ ኢህአዴግ የሚከተለው የብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ መብትን የማስከበር የፖለቲካ መርህ፤ ሁኔታዎች ሲበላሹ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል በቅርብ ርቀት ተመልክተናል፡፡ የብሔር፣ ብሔረሰብ እና ህዝብ መብትን ለማስከበር የሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ እንወክለዋለን የሚሉትን የቡድን መብት ለማስከበር የሚያደርጉት ጥረት ሊሳካ የሚችለው፣ የሁሉንም የሐገሪቱን ህዝቦች ጥቅም የሚያስከብር መርህ በመከተል መሆኑን መረዳት ሲቸግራቸው አስተውለናል፡፡
በዚህ ረገድ አንድ ሊነሳ የሚገባው ነገር ይታየናል። ምናልባት ለብሔር፣ ብሔረሰቦች መብት በመታገል የምናውቃቸው ድርጅቶች አንጋፋ አመራሮች አሁን በመተካካት ከመጡት አዳዲስ አመራሮች፣ የሚሻሉበት አንድ ነገር ይታየኛል፡፡ ነባሮቹ አመራሮች የርዕዮተ ዓለም መሠረታቸው ሶሻሊዝም ወይም ኮምዩኒዝም ነበር፡፡ በመሆኑም፤ የአንድ ብሔርን መብት ለማስከበር የሚያደርጉትን ጥረት፣ ከመደባዊ ጥያቄዎች ጋር አገናዝቦ የመመልከት ችሎታ ይኖራቸዋል፡፡ ቀዳሚዎቹ ታጋዮች፣ ወዛደራዊ ዓለም አቀፋዊነትን የሚያስቡ አመራሮችና ታጋዮች ነበሩ፡፡ የአንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ አባል በሆኑ፣ የተለያየ ባህልና ቋንቋ ባላቸው ህዝቦች መካከል ልዩነት ብቻ ሳይሆን አንድነትም ይታያቸዋል። በዓለም ወዛደሮች መካከል የትግል አጋርነት መኖሩን የሚያምኑ፤ የትግላቸው የመጨረሻ ግብ ወደዚህ ምዕራፍ መድረስ መሆኑን ተቀብለው ለብድን መብት የሚታገሉ በመሆናቸው፤ ርዕዮተ ዓለማዊ ዝግጅታቸው ከቋንቋና ከባህል ባሻገር ያለውን የህዝቦች ግንኙነት ለማየት የሚያስችላቸው ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡
አሁን ያሉት አመራሮች በዚህ ረገድ ሰፊ ክፍተት ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ አዲሱ ተተኪ አመራር ፈረንጆች፤ ‹‹ፕራይሞርዲያል›› በሚሉት ነገር የታጀለ አመለካከት የያዙ መስለው ታይተውኛል። ማርክሲስቶች፤ ‹‹ሐሳዊ ንቃተ ህሊና›› (false conciousness) በሚሉት ችግር ተጠልፈዋል። ከብሔር መብት ከፍ የሚል ርዕዮተ ዓለማዊ መነጽር ያላቸው አይመስሉኝም። ስለዚህ ሁኔታዎች ሲያጋድሉ በቀላሉ ይወድቃሉ። ድርጅቱ፤ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት›› የሚለው አስተሳሰብ፣ አይጠብቃቸውም፡፡ ድርጅቱ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት›› የሚለው፣ ከብሔር አጥር ሊሻገር የሚችል  እሳቤ ነው፡፡ ይህ እሳቤ ‹‹የጭቁኑን ህዝብ ጥቅምን ከሚጻረር የኦሮሞ፣ የትግራይ፣ የወላይታ ወይም ወዘተ አማራ ተወላጅ ይልቅ፤ የጭቁኑን የአማራ፣ የትግራይ፣ የኦሮሞ ወይም የወላይታ ወዘተ ህዝብን ጥቅም ለማስከበር የሚቆም፣ በብሔር የተለየ ኃይልን አጋር አድርጎ መመልከትን›› የሚያቀነቅን አስተሳሰብ ነው፡፡
አሁን የምንመለከተው ሁኔታ ከዚህ መርህ የወጣ አካሄድ ነው፡፡ እናም የኢትዮጵያ ህዝብ ከፖለቲካ መሪዎቹ፣ የላቀ አስተሳሰብ ያለው አስተዋይ ህዝብ በመሆኑ፣ ለጊዜው ከአንዣበበው አደጋ ተጠብቀናል። የሐገራችን የህዝብ ሚዲያዎችም፤ ‹‹ተነስ ወገንህ እያለቀ ነው›› ብለው ሲቀሰቅሱ፣ ዝም ብሎ የማለፍ ህሊና መያዝ ችለዋል፡፡ ራሳቸውን የስርዓቱ ባለቤትና ጠበቃ አድርገው ከሚመለከቱ የገዢው ፓርቲ የፖለቲካ አመራሮች ይልቅ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የህዝቡ ሰላም እንዳይረበሽ ከወትሮ የተለየ ጥንቃቄ ሲያደርጉ አይተናል፡፡ ይህ ሥርዓት ‹‹ከጠላቶቹ›› ብቻ ሳይሆን ‹‹ከወዳጆቹ››ም ጥቃት ሊሰነዘርበት እንደሚችል መረዳት ችለናል፡፡  

Read 3049 times