Sunday, 18 February 2018 00:00

የሀገር “ሞት” ትንሳዔ የለውም!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

 እንባ ባጋቱ ዓይኖች፤ ሽቅብ መስቀል ላይ የምናያት  መሰለችኝ፡፡ ቀሚስዋ ተገልቦ፣ ገመናዋ ተገልጦ፣ ጠላቶችዋ የሚሳለቁባት፣ እስትንፋስዋን ለማቆም የእሾህ አክሊል የሚጐነጉኑላት ያህል አመመኝ፡፡ “እንዳፋችሁ ያድርገው!” ብለን  የተሳለቅንበት “የከፍታ ዘመን”፣ በሚያስደነግጥ ሁኔታ  የጣዕር ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ  በትንሳዔ  የማትናፈቅ፣ መስቀል ላይ የተንጠለጠለችበት ጊዜ ዛሬ  ነው፡፡ የሚያሳዝነው መሰቀልዋ ብቻ አይደለም። ሞትዋ፤ እንደ ክርስቶስ ትንሳዔ የሚኖረው አለመሆኑ ነው፡፡
ከታሪክ እንደምንረዳው፤ ሀገራት በተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ውስጥ ገብተው ሊዳክሩ ይችላሉ፡፡ የቱም ሀገር፣ የትኛውም የመንግስት አመራር ፈተና ሳይቀምስ አያልፍም፤ ይሁን እንጂ ማዕበሉን በድል አድራጊነት ለመወጣት፣ ብልሀት የተመላበት ሳይንሳዊ አመራር  በመስጠት  መሪዎች አገራቸውን  ይታደጋሉ፡፡
ትልቅ ሀገር የፈጠረው አሜሪካዊው ትልቁ ጀፈርሰን፤ ለዝንታለም የሚሆን  ትምህርት የሚሰጡ ሥራዎችን ሠርቶ ያለፈ መሪ ስለሆነ፣ ሀሳቡ ሁልጊዜ እሸትና የቱንም ትውልድ የሚመጥን ነው፡፡ ታዲያ በዘመኑ ሀገሩ አሜሪካ በገጠማት አንዳንድ እክል፣ ሀሳቡን ያሰፈረበትን ደብዳቤ፣ ሳውልኬ ፓዶፈር፣ ሰንዶ ለትውልድ እንዲተላለፍ አድርጓል፡፡ እኔም  ያገሬን እንቅፋትና ሰበብ የሚመስለውን ጥቂት መስመር፣ እንዲህ መዝዤአለሁ፡-
“I am not a friend to a very energetic government. It is always operative.”
እውነቱን ነበር፤ መቼም ቢሆን በኃይል የተሞላ መንግሥት ጨቋኝ ነው፡፡ ምክንያቱም መፍትሔን የሚያነፈንፈው በጠመንጃ አፈ-ሙዝ ነው፡፡ ድንኳኑ ታንክ እንጂ የውይይት መድረክ አይደለም፡፡
ወደ ወቅቱ ገጠመኙ ስመለስ እንዲህ ይላል፡- “The late rebellion in Massachusetts has given alarm, than I think it should have done. Calculate that one rebellion in thirteen states in the course of eleven years, is but one for each state in a century and a half. No century should be so long without one. Nor will any degree of power on the hands of government prevent insurrections.”
ልብ በሉልኝ፤ የማሳቹሴትስ  እምቢታና አመፃ  የማንቂያ ደወል ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ስሌቱ የትየለሌ ነው፡፡ ሲጠቀለል ግን ሥልጣን ከመንግሥት እጅ አፈትልኮ ወጥቷል  ማለት ይቻላል፡፡ ግን ደግሞ ብልህ  መሪ  የማንቂያ ደወል ሲደወል፣ ከአልጋው ተፈናጥሮ በመነሳት፣ ስህተቶቹን ይገመግምና ጠማማውን ያቃናል። ማቃናት ማለት ግን “ተሳስቻለሁ!” የሚል የሽንገላ ቃላት ብቻ አይደለም፡፡ ሀገርን  ከአደጋ የሚታደግ፣ የወገንን ክብርና አንድነት የሚያፀና፣ ሥር ነቀል መፍትሄ እንጂ!
ይህ እንግዲህ የስንት መቶ ዓመታት ታሪክ ነው?... ከዚህ በኋላም አሜሪካ ታላላቅ ፈተናዎችን በመሪዎችዋ ጽናትና ብርታት አልፋለች፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ  በኃይል ወይም  በዘርና በጐሳ የተከፋፈለ ማኅበረሰብ በመፍጠር አይደለም። ለሁሉም አሜሪካዊ ቀና ህልም በማለምና መንግሥት የህዝብ አገልጋይ መሆኑን ከልብ በማሰብና በቁርጠኝነት በመተግበር ነው፡፡ ለዚህ ነው ጆንሰን  እንዲህ ያሉት፡ “A compssionate government keeps faith with the trust of the people and cherishes the fruit of their children” ይህ ብቻ አይደለም፤ መንግሥት የህዝብ አገልጋይ  እንጂ  ህዝብ  የሚያድን ሽፍታ እንዳልሆነ  ይነግሩናል፡፡ “Government fulfils its purpose as the servant of all people”
እኛ ግን ለዚህ አልታደልንም፤ ለሃያ ሰባት ዓመታት በሥልጣን ላይ  የዘለቀው ኢህአዴግ መራሹ መንግሥታችን፤ ምክር የሚሰማ አይደለም፤”ከእኔ ሃሳብ ውጭ ሞቼ እገኛለሁ” የሚልና  እንደ መንግሥትም፣ ከህዝብ ክብር ሳያገኝ የኖረ መንግሥት ነው፡፡ ምንም እንኳ አንዳንድ መሠረተ ልማቶች ላይ ጉልህ ለውጥ ቢያመጣም ተገቢውን ምስጋና አላገኘም፡፡ ህዝብን “አልሰማህም” እንዳለው ሁሉ፣ ህዝብም መንግስትን ሊሰማው ፍቃደኛ አልሆነም፡፡ እንደናቀው ንቆታል። የእጁን አግኝቷል፡፡
መንግስትም ሆነ ገዢው ፓርቲ፣ለሁለት አስርት ዓመታት ዜጎች ከኢትዮጵያዊነታቸው ይልቅ ጎጣቸውንና መንደራቸውን የሙጥኝ እንዲሉ በማድረግ፣ ብሔራዊ ስሜት እንዲሸረሸር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተጋበት ሥራው፤ ዛሬ ለነውጥና ለቀውስ ዳርጎናል፡፡ መገናኛ ብዙኃን፣ የትምህርት ተቋማትና የአስተዳደር ማዕከላት ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን አብዝተው በማቀንቀናቸው፣ ዛሬ ሀገሪቱ የመፍረስና የመበታተን አደጋ ተጋርጦባታል። ሀገሪቱ ለብዙዎቻችን የእንጀራ እናት እስክትመስል ድረስ፣ በደሉና ፍትህ እጦቱ ገንኗል፡፡ ገጣሚ ደሱ ፍቅርኤል በስንኞቹ የቋጠረውን እንፈትሽ፡-
ሃገሬ ላይ ቆሜ ሃገር የናፈቀኝ
ስላገር ሳወራ፣ ከቃል አስቀድሞ
        እንባዬ  የሚያንቀኝ፣
አርባራት ዲያቢሎስ ልቡ ያዘዘውን
        እምነት የሚያጠምቀኝ
እኔ ግን ምንድነኝ?
በአኖሊያዊ በደል በውርስ ጥላቻ
        ነፍሴ የተመታ፣
በእንባ የምታጠብ በመከራ ትብታብ
        በቡርቃ ዝምታ፡፡
    እኔ ግን ምንድነኝ?
    ምስጦችሽ እትብቴን
    አጋንንትሽ ነፍሴን
    ገዢሽ ነፃነቴን
    በሉብኝ ተሻምተው
የኤሊ እግሮች ሰጡኝ
የንስር ክንፎቼን በጉልበት ቀምተው፡፡
አገራችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ የዘርና የጎሳ ፖለቲካ አዝመራን እያጨደች መከመር ከመጀመሯ በፊት ስለ ኢትዮጵያዊነት ማውራት በአዋጅ የተከለከለ እስኪመስል ድረስ፤ የሚፈራ አጀንዳ ሆኖ ነበር። ባያስከስስና ባያሳስር እንኳን ማስፈረጁ አይቀሬ ነው። ብሔራዊ ክብርንና ኢትዮጵያዊነትን ማቀንቀን የሚኮራበት ሳይሆን የሚታፈርበት ነበር የሚመስለው። ከሀገር ልዕልና ይልቅ ለፓርቲ ልዕልና፣ ከህዝብ ጥቅም ይልቅ ለግል ጥቅም መትጋት አይሎ ከርሟል፡፡  ከአንድነት ይልቅ ለጐሰኝነት ክብርና ሞገስ ተሰጥቷል፡፡ ምንም እንኳን እኒህ ሁሉ አገሩን ለሚወደው  የኢትዮጵያ ህዝብ የማይመጥኑ ቢሆኑም፡፡ ሃቁን ለመናገር ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከቴዲ አፍሮ  ዘፈኖችና  ከጥቂት ሀገር ወዳዶች  ልብ በስተቀር  ሀገር ጥሎ የተሰደደ ነበር የሚመስለው፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት፡፡
የሚገርመው ደግሞ በእኒህ ጊዜያት መንግሥታችን፣ በዓይናችን የምናየውን ነገር ተርጉሞ ይነግረን ነበር፡፡ ከዓይናችን ይልቅ የመንግስትን ትርጉም እንድናምንም ነበር የሚጠበቀው፡፡ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት፣ ባለፉት ዓመታት፤ “ከብተና የተረፈች ሀገር!” እያለ ሲፎክር ከርሟል፡፡ ግን የትዋ ኢትዮጵያ ናት የብተና አደጋ የገጠማት?... የትናንትዋ ወይስ የዛሬዋ?... በዘረኝነት፣ በብሔርተኝነት፣ በጠባብ የቡድንተኝነት ስሜት ተከፋፍሎና ተበጣጥሶ፣ አገር ለብተና የተዳረገችው መቼ ነው? ዛሬ ነው ትናንት? ህዝብና ታሪክ ይመስክሩ!! ኢህአዴግ ግን በማን አለብኝነት ያሻውን ሁሉ ሲግተን ነው የከረመው፡፡ ይሁን እንጂ ሰሚ አላገኘም፡፡ ጠመንጃ ብቻ የሰው ልብና ጆሮ አይከፍትም፡፡ ጥይት ሰው ይገድላል እንጂ  ህልምና ሀሳብን አይንድም!!
ደርግ አምባገነን መሆኑ ለክርክር አይቀርብም፡፡ ግን ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን በሀገሪቱ ዜጐች ውስጥ ያሰረፀ፣ ለኢትዮጵያዊነት ክብር የነበረውና፣ትውልዱ ሀገሩን እንዲወድድ ሌት ተቀን  የተጋ መንግስት ነው፡፡ በእርግጥ “አንዲት ኢትዮጵያ!” ማለቱ፣ ዛሬ በኢህአዴጋውያን ያስነቅፈዋል፡፡ ግን እውነቱ፣እንደ ዛሬው ሰዎች የብሄርና የዘር ጉዳይ አያሳስባቸውም ነበር፡፡ ትዝ የሚለውም የለም፡፡ ሁሉም በመታወቂያ ላይ የሚሰፍርለት አንድ ማንነት ነበረው - ኢትዮጵያዊነት!
የዘረኝነትና የጎጠኝነትን ክፉ በሽታ  አዝሎ ያመጣብን፣ “ብሶት የወለደው ኢህአዴግ” ነው። ዛሬ ግን ኢህአዴግ ብሶቱን ህዝብ ላይ ያራገፈው ይመስላል፡፡ “ብሶት የወለደው አገር” ተፈጥሯል፡፡  
ኢህአዴግ፤ “የተሻለና  ፍትሀዊ ሥርዓት  እፈጥራለሁ” ብሎ አስቦ፣ ከተማ ሲገባ፤ ብሩና ወርቁ፣ ሀብቱና ምቾቱ፣ አስክሮት ተሳሳተ ብለን እንኳ ብናስብ፣ ስካሩ በሃያ ሰባት ዓመታትም ያለመብረዱና ወደ አቅሉ ያለመመለሱ ያሳዝናል፡፡ በ27 ዓመታት ካልበረደለት ደግሞ መቼም አይበርድለት! እንደ ዕድል ሆኖ  ሀገራችን  ያልታደለችው ሥልጣን ላይ  የተቆናጠጠ መንግሥት በማጣት ብቻ አይደለም፡፡ መንግሥትን የመገዳደርና የህዝብን ጥያቄ ይዞ የመቆም  ኃላፊነት  ያለባቸው “ተቃዋሚ ፓርቲዎችም”፣ በተመሳሳይ የዛጉና ቅዠት ያናወዛቸው ሆነዋል፡፡ እርስ በርስ በመጠላለፍና በሥልጣን ሽሚያ እየተካሰሱ፣ በተደጋጋሚ ህዝቡን በአደባባይ አሳፍረዋል።
እነዚህ ፓርቲዎች ምናልባት ኢሕአዴግ ነው ያዳከመን የሚል ምክንያት ሊያቀርቡም ይችላሉ። ያ ብቻ ግን ለዚህ ዓይነት መሽመድመድና መንኮታኮት አያበቃቸውም፡፡ ብዙ የጥቅምና  ሌሎችም ጥማቶችና ግጭቶች እንደነበሩ የአደባባይ  ምስጢር ነው፡፡ ይህም አለመታደል ነው፡፡ ምናልባት በዘራፊዎችና  ሌቦች (ሙሰኞች) እየተማረሩ መልሰው፣ ተረኛ ለመሆን የሚታትሩ ብዙ የፖለቲካ ነጋዴዎች ሳይኖሩ አይቀሩም። በሌላ በኩል ግን እነ ዶክተር መረራ ጉዲናን የመሰሉ ሀቀኛና ከዘረኝነት የፀዱ ፖለቲከኞችም ተፈጥረዋል። ከመንደርተኝነት ይልቅ ለትልቋ አገርና ለሕዝቦች አንድነት በትኩረት የሚታገሉ፡፡ ህዝብ አመኔታውንና ፍቅሩን የቸራቸው የሀገር ምርጦች!! ለዘራፊዎቹ ፖለቲከኞች ግን ከገጣሚ ዮናስ ኪዳኔ “የእግዜር የብዕር ስም” ግጥም ጥቂት መስመሮች እነሆ፡-
ሰምተሻል ሃገሬ! ሰምተሻል ኢትዮጵያ?
“ጨዋ ነን!” ባዮቹ
ሲሳካ በበርሜል፤ ሲቀር በኩባያ
ያለሽን ሀብት ሁሉ ዘርፈውሽ ሊጠፉ
በማጣትሽ ከብረው ካጠገቤ ሲያልፉ
ማስጣል ባይሆንልኝ ቢበረታ ሰልፉ
መቼስ ብር ያስታል ብትቋምጥም ነፍሴ
እኔ ስዱ ልጅሽ
በእርም ሃብትሽ ቃርሚያ አልደለበም ኪሴ
ዛሬ ግን መረረኝ!
በቀራጮች መሃል ቅዱስ መሆን የለም
እርሜን መግደፌ ነው
እኔም ልዘርፍሽ ነው፣ ማሪኝ እናት አለም፡፡
ወዳጆቼ፤ እንዲህ ነው ነገሩ! እንዲህ ነው ፖለቲካ! እንዲህ ነው ሥልጣን! እንዲህ ነው!
ከእኒህ ሁሉ ጥፋቶችም በኋላ መንግሥት ከራሱ ጋር ታርቆ፣ የተሻለና ኃላፊነት የተሞላበት እርምጃ ይወስዳል ለማለት ተስፋ አልቆረጥኩም ነበር፡፡ ምክንያቱም መንግሥትም የሰዎች ስብስብ ነውና  ስለ ነገ፣ ቢያንስ ስለ ቤተሰቦቹ፣ ስለ ልጆቹ፣ የሚያስብ አይጠፋም የሚል ግምት ነበረኝ፡፡ አሁን በተግባር የሚታየው ነገር ግን “እነዚሁ ሰዎች ነበሩ ሃያ ሰባት ዓመታት የመሩን?” ያሰኛል፡፡ በሚገርም ሁኔታ ለእያንዳንዱ የሕዝብ ጥያቄና ተቃውሞ፣ ከጥይት  ሌላ መልስ ያለው አይመስልም። ጥያቄ በተጠየቀ ቁጥር እንደ ፊሽካ፣ጥይት መተኮስ ያሳፍራል፡፡ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን፣የሺህ ዓመታት ታሪክ አለኝ በምትል ሀገር ውስጥ የዚህ ዓይነት አስተዳደር ያስደነግጣል፡፡ መወያየት ማንን ገደለ?... ህዝብን ማድመጥን ውርደት ያደረገው  ማነው? ለህዝብ  ጥያቄ መልስ መስጠትን ማነው ሽንፈት ያደረገው? ለመሆኑ እልሁና ፉክክሩ ከማን ጋር ነው? እርስ በርስ? ከተቃዋሚዎች?… ከዳያስፖራ? ወይስ… ከሕዝብ???
“መታደስ” የማይታክተው  ኢህአዴግ፤ እሥረኞችን እፈታለሁ ባለ ማግስት የምን ቅድመ ሁኔታ መደርደር ነው? አስሬ ቃሉን መለወጡ ምን ማለት ነው? በየትኛውስ መሥፈርት ይሄ  ከሀገር መሪዎች  ይጠበቃል? የሀገር መሪ’ኮ ማለት ባለ ራዕይና ሩቅ እያየ  በዓላማና በግብ ህዝቡን የሚያስከትል ነው፡፡
ሰሞኑን ያየነው ሁኔታ ግን ያንን የሚጠቁም አይደለም፡፡ ወይስ በእስረኞች መፈታት ጉዳዮች የሚከፋው የኢህአዴግ ባለስልጣናት አሉ፡፡ ግን ጊዜ ነው። የታሪክ ክስተት ነው፡፡  እስረኞቹን መንግስት በገባው ቃል መሰረት መፍታት ይሻላል ወይስ በረብሻ ተገድዶ መልቀቅ ነበር?... ለምን ነገር ማርገብን እንደሽንፈት እንደሚያዩት ባላውቅም፣ የዚህ ምልከት መሰልጠን ችግሮችን  በመነጋገር ወደመፍታትና  ወደተሻለ ህይወት ህዝብን ለመምራት ወደ መወሰን  እንጂ በነውጥና ብጥብጥ ህዝብን ግራ ወደማጋባት አይወስድም!
መንግሥት ሆይ፤ ሀገር መስቀል ላይ ናት፣ አንተ የእሾህ አክሊል እየጐነጐንክ ነው፡፡ ዘረኞችም “ስቅላት … ስቅላት” እያሉ ይጮሃሉ!... የነፃነት ጥያቄ አለን የምትሉ ወገኖች ደግሞ በትግላችሁ ላይ ማስተዋልን ጨምሩበት፤ … ዘረኝነትን አስወግዱ፡፡ ተያይዘን እንጠፋለን፡፡ የለማ መገርሳና የዶክተር ዐቢይ አህመድን የአንድነት ራዕይ መሰነቅ ያዋጣል፡፡ አንድነት ኃይል ነው!!

Read 1595 times