Sunday, 18 February 2018 00:00

አቶ ሞሼ ሰሙ - በወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ አለመሻሻል
የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ መሻሻል ከማሳየት ይልቅ የበለጠ እየተበላሸ መጥቷል፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ ለረጅም ጊዜ ችግሮች ተገቢውንና ቀጣይነት ያለው መልስ ያለማግኘታቸው ያመጣው ድምር ውጤት ነው፡፡ ማህበረሰቡ በተለያየ መንገድ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ነበሩት፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችም አሉት፡፡ ለነዚህ ጥያቄዎች ደግሞ አፋጣኝ መልስ ያለማግኘት፣ ትኩረት ማጣት፣ በቂ ክትትል አለመኖር አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች እርባና ቢስ እንደሆኑ ተደርጐ መቆጠሩ ማህበረሰቡ መጨረሻ ላይ በራሱ መንገድ መፍትሄ እንዲፈልግ ነው ያስገደደው፡፡ የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ መገለጫው፣ ማህበረሰቡ በዚህ መልኩ የራሱን ጥያቄ አንግቦ ጐዳና ወጥቶ፣ መንግሥትን በቀጥታ መታገል ሳይገባው፣ በወኪሎቹ በኩል የሚታገልበትና ጥያቄዎቹን የሚያቀርብበት መንገድ ነው፡፡ ይሄ አሁን በኢትዮጵያ እንዳይኖር ተደርጓል፡፡ በዚህ ምክንያት ተቃውሞ መሪ የለውም፡፡ የተደራጀ ጥያቄ የለውም፡፡ እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ምላሽ ለመስጠትም ሆነ ለመቆጣጠር የተወሳሰበና አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ እያየን ያለነውም ይሄንን ነው፡፡
በሌላ በኩል መንግሥት ለችግሮቹ ምላሽ ለመስጠት እየሞከረ ያለው ጊዜያዊ መፍትሄዎችን ብቻ በማስቀመጥ ነው፡፡ አግባብ ያለው መልስ እየሰጠ አይደለም፡፡ ስር ነቀል ለውጥ አካሂዶ ጥያቄዎቹን በዘላቂነት የመመለስ ስራ አይደለም እየተከናወነ ያለው፡፡ ዝም ብሎ እግር በእግር እየተከታተለ ነው፣ ትንንሽ መልሶችን  ለመስጠት እየሞከረ ያለው፡፡ ይሄ ህዝቡን አያረካም፡፡ ማህበረሰቡ ደግሞ አሁን ተጨባጭና ቀጥተኛ ምላሽ ነው የፈለገው፡፡ በአሁኑ ወቅት ህዝቡ ዛሬውኑ መልሱን አምጣ ነው እያለ ያለው፡፡ ከዚህ በፊት ማህበረሰቡ ላሉት የፖለቲካ ጥያቄዎች ትእግስት ነበረው፤ ምክንያቱም ሀሳብን በነፃነት መግለፅ የመደራጀት፣ ሰላማዊ ሰልፍ የመውጣት፣ የፕሬስ ነፃነት ጉዳይ ለአብዛኛው ህዝብ የልሂቃኑ ጥያቄ መስሎ ነበር የሚታየው፡፡ በዚህ ምክንያት ማህበረሰቡ ህይወቱን እስከ መሰዋት ሊሄድ አይችልም ነበር፡፡ አሁን ግን ነገሮች ተቀይረዋል። ሲከማቹ የቆዩት ችግሮችና ጥያቄዎች፣ አግባብ ያለው አፈታት ባለማግኘታቸው፣ ማህበረሰቡ ታግሶ ታግሶ፣ የራሱን አማራጭ ሊወስድ ችሏል፡፡ የተጠራቀሙ ጭቆናዎችና ፍረጃዎች ናቸው ለዚህ ያበቁት፡፡

ብሄር ተኮር ጥቃቶች   
ከብሄር ጉዳይ ጋር ተያይዞ የሚነሱት ውዝግቦች ለረጅም ጊዜያት ህብረተሰቡ ውስጥ ሲብላሉ የነበሩ ናቸው፡፡ አሁን ከመብላላት አልፈው ዋነኛ ችግር ሆነዋል፡፡ እውነቱን ለመናገር በዚች አገር፣ አንዱ ብሄር አንዱን እንዲያጠቃው የሚፈቅድ ማህበረሰብ ፈፅሞ የለም፡፡ በሌላ በኩል፣ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ይሄ የብሄር ጉዳይ ያልተነሳበትና ያለመግባባት መንስኤ ያልሆነበት ጊዜ የለም፡፡ በወቅቱ አግባብ ያለው ውይይት ተደርጐ መልስ ቢሰጠው ኖሮ፣ ዛሬ ተመልሶ አይከሰትም  ነበር፡፡ ሰዎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የመኖር መብታቸው፣ አስቀድሞ መተግበር ነበረበት፡፡ በወቅቱ እነዚህ ነገሮች ባለመታከማቸው ዛሬ ላይ ፈጠው ወጥተዋል፡፡ ከዚህ ችግር  ለመውጣት አሁንም ውይይት ያስፈልጋል፡፡ ሁነኛ የግጭት አፈታት ስልት መነደፍ አለበት፡፡ እርግጥ ነው ከህዝባችን ታሪክ ስንነሳ፣ የብሄር ግጭት ተፈጥሮ አያውቅም፡፡ ግጭቶች ሲኖሩም፣ ከድንበርና ከግጦሽ መሬት የባለቤትነት ጥያቄ አያልፍም፡፡ አሁን ግን ትንሽ ነገሮች የተቀየሩ ይመስላል፡፡
 ባለፉት 27 ዓመታትም አንዱ አንዱን ሲጨቁን፣ ሲበድል፣ ሲበዘብዝ እንደነበር ነው ሲተረክ የተኖረው። አንዱ አንዱን በጥርጣሬና በጥላቻ እንዲያይ ተደርጐ ነው፣ የማህበረሰቡ ቀደምት ግንኙነቶች ሲተረኩ የኖሩት፡፡ ታዲያ ከዚህ ተረክ ምን በጐ ፍሬ ነው የሚጠበቀው፡፡ ማህበረሰቡ “እገሌ ሀብትህን ሲበዘብዝ ነበር” ሲባል ነው የኖረው። በዚህ የተነሳ  አንዱ በሌላው የአገሪቱ ክፍል ሰርቶ ሲኖር፣ እንደ ሀብት በዝባዥ ነው የሚታየው። ንብረቴን ዘረፉኝ ነው፤ ብሶቱ፡፡ እንግዲህ ካለፉት ዓመታት ተረኮች ያተረፍነው ይሄንን ነው፡፡ ችግሩ የበለጠ አድማሱን ሳያሰፋና የአገሪቱን ህልውና ሳይፈታተን በጊዜ እልባት ማግኘት አለበት፡፡

የፖለቲከኞች መፈታትና ፋይዳው
እነዚህ ሰዎች ሀሳባቸውን በነፃነት በመግለፃቸውና በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት እስር ቤት የገቡ ናቸው፡፡ የእነዚህ ሰዎች መፈታት በእርግጥም ህዝቡ የበለጠ ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ይረዳዋል፡፡ መንግሥት እነዚህን ሰዎች በመፍታቱ ብቻ ለህዝቡ ጥያቄ በቂ መልስ ሰጥቻለሁ ብሎ ካሰበ በእጅጉ ተሳስቷል፡፡ ምክንያቱም የእስረኞች መፈታት ጉዳይ ከህዝቡ ጥያቄዎች አንዱ እንጂ ዋነኛ ግብና ዓላማ አይደለም፡፡ እርግጥ ነው ማህበረሰቡ እንዲፈቱ ታግሎላቸዋል፡፡ ስለዚህ መፈታታቸው እንደ አንድ ድል ነው የሚቆጠረው፤ ግን የጥያቄዎች ሁሉ መልስ አይሆንም፡፡

የህግ የበላይነትና ሰብአዊ መብት
የህግ የበላይነትን ማስከበር የመንግስት ዋነኛ ሃላፊነት ነው፡፡ ጥያቄው የህግ የበላይነትን ማስከበር ሲባል በምን መንገድ የሚለው ነው፡፡ የህግ የበላይነትን በሌላ የህግ ጥሰትና ጥፋት ለማስከበር ጥረት የሚደረግ ከሆነ ውጤት አያመጣም፡፡ መንግሥት ደግሞ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሲጥር፣ የማህበረሰቡን የህግ ንቃተ ህሊና ማገናዘብ አለበት፡፡ መፍትሄው የህይወት ማጥፋት ሳይሆን አጥፊዎችን በህግ ጥላ ስር ማዋል ነው፡፡ የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሚወሰደው እርምጃ የበለጠ ጥፋት የሚያስከትል ከሆነ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ችግሮችን የመፍታት አቅም ከሌለው፣ ከሚችሉ ሰዎች ጋር ህብረት ፈጥሮ መፍታት ነው የሚበጀው፡፡ እስካሁን ይሄን ማድረግ አልቻለም፡፡ ከዚህ በኋላም ይሄን ለማድረግ ጊዜ አለው፡፡ ወደ ህብረተሰቡ ቀርቦ በመነጋገር፣ ተከታታይ የመትሄ ሀሳቦችን ማመንጨትና ተግባር ላይ ማዋል ያስፈልጋል፡፡

Read 1403 times