Sunday, 18 February 2018 00:00

የጠ/ሚ ኃይለማርያም ከሥልጣን የመልቀቅ አንደምታ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(21 votes)

 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከትላንት ጀምሮ ታውጇል

   ላለፉት ስድስት ዓመታት አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ ከሥልጣን መውረድ ብቻውን የተለየ ለውጥ አያመጣም የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች፤ የኅብረተሰቡን የለውጥ ፍላጐት የሚያስተናግድ፣ አጠቃላይ ማሻሻያና ለውጥ መደረግ አለበት ይላሉ። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ከሥልጣን የመልቀቅ ውሣኔ ብዙዎች የዘገየ ነው ብለውታል፡፡
ጠ/ሚ ኃይለማርያም ከትላንት በስቲያ ሐሙስ 7፡00 ሰዓት ገደማ በጽ/ቤታቸው ለጥቂት የመንግስት ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ “በአገሪቱ ለሚታዩ ችግሮች እኔም የመፍትሄው አካል ለመሆን በፈቃዴ ከስልጣን ለመልቀቅ ወስኛለሁ” ብለዋል፡፡ “ህዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ማግኘት አለበት” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳርም መስፋት አለበት ብለው እንደሚያምኑ በእርጋታና ከወትሮው በተለየ የልበሙሉነት ስሜት ተናግረዋል - በቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ፡፡
በሀገሪቱ ላይ ያንዣበበውን አሳሳቢ ሁኔታ ለመቅረፍም የሀገሪቱ ህዝቦች የመቻቻል ባህል ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጠየቁት ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ የሀገሪቱ ህዝቦች አብሮነት እንዲጠናከርም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሌላ በኩል የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄ የኢህአዴግ ም/ቤት እንደተቀበለው፣ የኢህአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ሐሙስ ማምሻው ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ከሥልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ የማቅረባቸው ዜና በመገናኛ ብዙኃን መሰራጨቱን ተከትሎ፣ የተለያዩ አስተያየቶች የተሰነዘሩ ሲሆን በተለይ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ይሆናል? የሚለው ጥያቄ የብዙዎች መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል፡፡
አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው ምሁራን በበኩላቸው፤ አሳሳቢው ጉዳይ ቀጣዩ ጠ/ሚኒስትር ማን ይሆናል የሚለው አይደለም ይላሉ፡፡ ይልቁንም ሀገሪቱን እንዴት ወደ መረጋጋት መመለስ ይቻላል? የሚለው ጥያቄ ነው ባይ ናቸው፡፡
ከውጪ አገር በስልክ ያነጋገርናቸው አቶ ክቡር ገና በሰጡት አስተያየት፤ አሁን ያለንበት ሁኔታ አስቸጋሪ በመሆኑ ጉዳዩ ጥንቃቄ ይሻል ብለዋል። “የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣን መልቀቅ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ አይመስለኝም” ያሉት አቶ ክቡር፤ “ህዝቡ ጥያቄ እያቀረበ ያለው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይሆን ለፓርቲው ነው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የመጣው ከፓርቲው ነው” ብለዋል። ትልቁ ጥያቄ ፓርቲው በምን መልኩ ሊቀጥል ይችላል የሚለው ነው እንጂ፤ ማን ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል የሚለው አይደለም ያሉት አቶ ክቡር፤ በፓርቲ ላይ የተመሠረተ መንግስት በመሆኑ፣ ፓርቲው በሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ ብዙም ለውጥ አይኖርም ሲሉ አስተያየታቸውን ገልፀዋል፡፡
ምሁሩና የፖለቲካ ተንታኙ ዶ/ር አለማየሁ አረዳ በበኩላቸው፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድርጅቱ ተገፍተውም ይሁን በራሳቸው ፈቃድ ከቦታው መነሳታቸው ለራሳቸውም ቢሆን ተገቢ ነው” ይላሉ፡፡ “ሥልጣን የሚለው ቃል ትርጉም ያለው ከሆነ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምን ሥልጣን እንደሚነሱ አይገባኝም” ያሉት ዶ/ር አለማየሁ፤ “ካላቸው የሥልጣን አቅም ይልቅ አጀባቸው የበዛ ጠ/ሚኒስትር ናቸው” ብለዋል፡፡
በቀጣይ ሀገሪቱ ወደ ተረጋጋ መስመር እንደትገባና የህዝቡ ጥያቄ ምላሽ እንዲያኝ ከተፈለገ፣ ባለሙሉ ሥልጣን ጠቅላይ ሚኒስትር ያስፈልጋል የሚል እምነት እንዳላቸው የተናገሩት ምሁሩ፤ ኢህአዴግም ይሄን ባለ ሙሉ ሥልጣን ጠቅላይ ሚኒስትር ማምጣት መቻል አለበት ብለዋል፡፡ አሁን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን መሰናበት ብቻውን ለህዝቡ ጥያቄ መልስ እንደማይሰጥም ዶ/ር አለማየሁ ጠቁመዋል፡፡
የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ በሰጡት አስተያየት፤ “በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ቢኖርም፤ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች በየዓመቱ ከዩኒቨርሲቲ እየወጡ ሥራ ጠባቂ ሆነዋል፣ ለእነዚህ ወጣቶች ፍላጐት ምላሽ የሚሰጥ አመራር ያስፈልጋል” ብለዋል - የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን መነሳት ብቻ ለጥያቄዎች መልስ እንደማያመጣ በመጠቆም፡፡
“አንድ መንግሥት በህዝብ ግፊት ሲደረግበት የሥልጣን መልቀቅ ጉዳይ የተለመደ ነው” ያሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ “ሆኖም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን መልቀቅ ብቻ በሀገሪቱ ላይ የተለየ ለውጥ አያመጣም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ፓርቲው በቀጣይ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ሾሞ፣ ለመጪው ምርጫ መንገዶችን ማመቻቸት እንዳለበትም ምሁሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
“ሀገሪቱን ከቀውስ ለማውጣት የበሰለና የተረጋጋ መሪ ያስፈልጋል” ያሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ “ከምንም በላይ ሀገሪቱ ያለችበትን ጂኦፖለቲካዊ ችግር ለመፍታት የሚያስችል አመራር መምጣት አለበት” ይላሉ፡፡
አዲሱ አመራርም የሀገር ውስጡንም ሆነ ከአካባቢው ሀገራት ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ጫና ይኖርበታል ያሉት ምሁሩ፤ “ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ይሆናል የሚለውን ለመገመት ቢከብድም፤ ሁሉም የሚያከብረው፣ የጦር ኃይሉ በሚገባ የሚያደምጠው መሪ መሾም አለበት፤ ጉዳዩ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ነው” ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የቀድሞ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር እሌኒ ገ/መድህን በፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት አጭር አስተያየት፤ “ኢትዮጵያ አሁን በመስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከልባቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፣ ልቤ የተሻለች ኢትዮጵያን እውን መሆን ይመኛል” ብለዋል፡፡ አክለው እንደፃፉት፤ “አዲስ በምትገነባው ኢትዮጵያ ውስጥ የድርሻዬን አበርክቻለሁ፤ ወጣቶቻችንም፣ ተመራማሪና ኢንጅነሮቻችንም መዋጮአቸውን ማበርከት አለባቸው፡፡ ሁሉም ነገር በእጃችን ላይ ነው ያለው” ሲሉ ሃሳባቸውን ገልፀዋል - ዶ/ር እሌኒ።
የ53 ዓመቱ አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ ቦሼ፤ በሙያቸው ሲቪል ኢንጂነር ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ በዩኒቨርሲቲ መምህርነት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡት አቶ ኃይለማርያም፤ የደቡብ ክልል ምክትል ፕሬዚደንት እስከሆኑበት ጊዜ ድረስ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ሆነው አገልግለዋል፡፡
የአቶ ኃይለማርያም ግለ ማህደር እንደሚያስረዳው፤ በሙስና የተከሰሱትን የቀድሞ የደቡብ ክልል ፕሬዚደንት አቶ አባተ ኪሾን በመተካት ወደ ፕሬዚደንትነት የመጡ ሲሆን፤ ክልሉንም በዚሁ ሥልጣናቸው ለ5 ዓመታት አገልግለዋል፡፡
የፓርላማ አባል በመሆን፣ ወደ ፌዴራል በመምጣትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የህዝብ ንቅናቄና ተሳትፎ ጽ/ቤት አማካሪ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በዚህን ወቅት በተለይ የ1 ለ5 አደረጃጀትን በመፍጠር በወቅቱ 4 መቶ ሺህ ብቻ የነበሩትን የኢህአዴግ አባላት ቁጥርን ወደ 6 ሚሊዮን እንዳሳደጉት ይነገራል፡፡
ከዚያም በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚነት፣ እንዲሁም የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበር በመሆን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሰርተዋል፡፡ የአቶ መለስ ዜናዊን ህልፈት ተከትሎም፣ አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ሥልጣን ለመያዝ ችለዋል። አሁን ጥያቄው ኢህአዴግ በጠ/ሚኒስትርነት የሚመርጠው ማንን ይሆናል የሚል ነው፡፡
ሥልጣን መልቀቅ በኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ ታሪክ ከሥልጣናቸው የለቀቁ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ መሆናቸውን የኢህአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤም ሆኑ መገናኛ ብዙኃን የጠቆሙ ቢሆንም፤ የሃይማኖት ታሪክ ተመራማሪው ዲ/ን ዳንኤል ክብረት በፌስቡክ ገፃቸው፤ በሀገራችን በህዝብ ጫናና በገዛ ፍላጐታቸው ሥልጣን የለቀቁትን መሪዎች እንደሚከተለው ይዘረዝራል፡፡
በኢትዮጵያ የተመዘገበ ታሪክ ውስጥ ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው የለቀቁ የመጀመሪያው መሪ አፄ ካሌብ ናቸው። ሥልጣናቸውን ለልጃቸው አፄ ገ/መስቀል አስረክበው፣ ገዳም በመግባት መንነዋል፡፡ በ16ኛው መቶ ክ/ዘመን ደግሞ አፄ ሱስንዮስ በሃይማኖት ምክንያት ህዝብ ባደረሰባቸው የማግለል ተግባር፣ ሰኔ 5 ቀን 1624 ዓ.ም ሥልጣናቸውን ለቀው፣ ለአፄ ፋሲል አስረክበዋል፡፡ ቀጥሎ ደግሞ አፄ አድያም ሠገድ ኢያሱ ሰኔ 21 ቀን 1698 ዓ.ም በፈቃዳቸው ሥልጣን ለቀው ገዳም ገብተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው የለቀቁ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ናቸው፡፡
በውዥንብርና በፈጣን ለውጦች የታጀበው ሳምንት
ሰኞ የካቲት 5 ቀን 2010 ዓ.ም በመላ ኦሮሚያ ተቃውሞና አድማ ተደረገ፡፡ በሂደቱም የ9 ሰዎች ህይወት አለፈ፡፡
ማክሰኞ የካቲት 6 ቀን 2010 ዓ.ም አድማውና ተቃውሞው ቀጥሎ ዋለ፡፡ አመሻሹ ላይ ህዝቡ ይፈቱ እያለ አደባባይ የወጣላቸው ፖለቲከኞች - እነ አቶ በቀለ ገርባና ባልደረቦቻቸው ከእስር ተፈቱ፡፡
ረቡዕ የካቲት 7 ቀን 2010 ዓ.ም እስረኞችን መፍታቱ ቀጥሎ፣ ፖለቲከኛ አንዷለም አራጌ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ከ700 በላይ እስረኞች ተፈቱ፡፡
ሐሙስ የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣናቸውን እንደሚለቁ ለህዝብ ይፋ አደረጉ፡፡
አርብ የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም በመላው አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ፡፡

Read 8403 times