Sunday, 11 February 2018 00:00

አስገራሚው ከፕላስቲክ ጠርሙሶች የተሰራው ቪላ ቤት

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

· በብሎኬት ከሚሰራው ቤት 70 በመቶ ቅናሽና 20 እጥፍ ጥንካሬ አለው
      · ቤቱ በሶስት ሳምንት ተሰርቶ ተጠናቅቋል
         
    ሲምኮን ቴክኖሎጂስ ይህንን ከወዳደቀ ፕላስቲክ የሚሰራ ቤት እውን ለማድረግ ሲነሳ፣ ሶስት ዓላማዎችን ሰንቆ እንደሆነ የስማርት ማኔጅመንት ሰርቪስስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር አዲል አብደላ ይናገራሉ፡፡ አንደኛውና ዋናው፤ በአገራችን የተንሰራፋውን የመኖሪያ ቤት እጥረት በመቅረፍ በኩል የበኩሉን ሚና ለመጫወት ሲሆን ሁለተኛው ለቤት ግንባታ የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ እንደሆነና ለብዙ መቶ አመታት ባለመበስበስ አካባቢን ለብክለት የሚዳርጉ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን ጥቅም ላይ በማዋል፣ አካባቢን ከብክለት ለመጠበቅ እንደሆነም ዶ/ር አዲል ይናገራሉ፡፡
ይህንን ህልማቸውን እውን ለማድረግ በተለያዩ ዓለማት ማለትም፡- የህንድ፣ ባንግላዲሽ፣ ኔፓል፣ ናይጄሪያና ኡጋንዳን ተሞክሮዎች በተለይም የህንድን ተሞክሮ ጠልቆ በመመርመር፣ ለአንድ ዓመት ተኩል ጥናት ማድረጋቸውን የተናገሩት ዶ/ር አዲል፤ ይህ ግንባታ በተለይም ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን እንደደረሱበት ከትላንት በስቲያ በአዳማ ከተማ ተሰርቶ ለእይታ በበቃው ከፕላስቲክ የተሰራ ቤት የምረቃ ስነ - ሥርዓት ላይ ተናግረዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድም ቁራጭ ብረትና እንጨት ሳይቀላቀልበት በአፈርና በውሃ ተጠቅጥቀው በተሞሉ የውሃ ፕላስቲኮች ብቻ የተሰራውና በመቶ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው ይሄው ባለ ሶስት መኝታ ክፍል፣ ባለ አንድ ሳሎን ባለ አንድ ማዕድ ቤት፣ ባለ ሁለት መታጠቢያና መፀዳጃ ቤት ተሰርቶ ተመርቋል። ቤቱን ሰርቶ ለማጠናቀቅ 53 ሺህ የፕላስቲክ ጠርሙሶች ሥራ ላይ የዋሉ ሲሆን አጥሩ ብቻ 14 ሺህ የውሃ ፕላስቲኮችን መውሰዱም ተገልጿል፡፡
ቤቱ ከመሬት ወደ ውስጥ አንድ ሜትር ተቆፍሮ መሰረቱ የወጣለት ሲሆን ይህም ስራ የተከናወነው በነዚሁ የውሃ ፕላስቲክ ጠርሞሶች ነው፡፡ የቆሻሻ ውሃ ማጠራቀሚያ ጋኑ (ሴፕቲክ ታንኩም) እንዲሁ። በሶስት ሳምንት ተገንብቶ የተጠናቀቀው ይሄው ዘመናዊ ቪላ፤ የሚሰራበትን በአፈርና በአሸዋ የተጠቀጠቁ የፕላስቲክ ጠርሙሶች ለማሰናዳት ለ70 የአካባቢው ወጣቶች ባለ 1 ሊትር ተኩሉ የውሃ ፕላስቲክ አንድ ብር፣ ለባለ አንድ ሊትሩ 75 ሳንቲም፣ ለባለ ግማሽ ሊትር የውሃ ጠርሙስ ለእያንዳንዱ 50 ሳንቲም እየተከፈላቸው ለአንድ ወር ተኩል ስራ ላይ መቆየታቸውንና በዚህም ረገድ ለወጣቶቹ ያበረከተው አስተዋፅኦ ቀላል እንዳልሆነ ተገልጿል፡፡
የቤቱ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት አርክቴክቸራል ዲዛይኑና የቤቱ ጠቅላላ ወጪ በአርክቴክቶችና በመሀንዲሶች መሰራቱን የገለፁት ዶ/ር አዲል፤ በዲዛይኑ መሰረት ቤቱ እውን መሆኑን ተናግረዋል። ቤቱ በየትኛውም የሙቀት መጠን ያለበት ቦታ ላይ ቢሰራ ውስጡ ከ18 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እንደማይሞቅ፣ በደጋ ቦታ ላይ ሲሰራም ሙቀት አምቆ በመያዝ የውጭውን ቅዝቃዜ እንደማያስገባ የተገለፀ ሲሆን የጥንካሬ ደረጃውን በተመለከተ በአንድ ካሬ ሜትር ላይ 438,997 ኪ.ግ ክብደት መሸከም እንደሚችል፣ የተገነባበት ፕላስቲክ በአፈርና በአሸዋ የተጠቀጠቀ በመሆኑ ጥይት እንደማይበሳው፣ በሀይለኛ ንፋስ ወቅት በሰዓት 200 ኪ.ሜትር የሚጓዝ ንፋስ እንደማይበግረው፣ እስከ 1.5 ሜትር ድረስ ጎርፍ እንደማያስገባ፣ 9.8 ሬክተር ስኬል የመሬት መንቀጥቀጥን እንደሚቋቋምና በተለምዶ ከብሎኬት ከሚሰራው ቤት 20 እጥፍ ጥንካሬ እንዳለው በጥናት መረጋገጡን ዶ/ር አዲል አስረድተዋል፡፡ ይሄ ለሙከራ የተሰራው ቤት፤ በብሎኬት ቢሰራ 1.2 ሚ. ብር እንደሚያወጣና ይሄኛው ግን በ345 ሺህ ብር ወጪ በአጭር ጊዜ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
የቤቱ ሌላው ተመራጭነት በቤቱ ላይ የእሳት ቃጠሎ ቢነሳ፣ ራሱ የማጥፋት ሀይል እንዳለውና ከ600 ዓመት እስከ 1500 ዓመት ያለ ችግር እንደሚቆይ ጥናቶች ማረጋገጣቸውን የተናገሩት የስማርት ማኔጅመንት ሰርቪስስ ዋና ስራ አስፈፃሚ፤ ቤቱ ወደ ላይ ወለሎችን ጨምሮ አንድም እንጨትና ብረት መጠቀም ሳያስፈልግ ፎቅ መስራት እንደሚቻል ጠቁመዋል፤ በህንድ G+4 ቤት መሰራቱን፤ እሳቸውም አሁን ከተሰራው ቤት ጎን ለጎን G+1 ቤት በተመሳሳይ መልኩ ለመገንባት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አንድ ሰው አንዴ ግንባታውን ከሰራ በኋላ ዲዛይን ለመቀየርም ሆነ በመጠንም ሆነ በአይነት የተሻለ ቤት ለመስራት ቢፈልግና የመጀመሪያውን ቢያፈርስ፤ ከመጀመሪያው ቤት ፍርስራሽ የተገኙት ፕላስቲክ ጠርሙሶች መልሰው ጥቅም ላይ መዋል እንደሚችሉ የገለፁት ዶ/ሩ፣ ቤቱ ሲገነባ የመፀዳጃ፣ የፍሳሽ ማስወገጃና የኤሌክትሪክ ዝርጋታዎች ሲሰሩ ለጥገና ምቹ ተደርገው መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በቀጣይም ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመነጋገር፣ በቀላል ዋጋ በአጭር ጊዜ ከብክለት የፀዳ አካባቢን በመፍጠርና የህብረተሰቡን ፍትሃዊነት የሚያረጋግጡ ከወዳደቀ ፕላስቲክ የተሰሩ ዘመናዊ ቤቶችን ለማህበረሰቡ የማዳረስ ራዕይ እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ አሁን ለሙከራ የተሰራው ይህ ዘመናዊ ቪላ፤ በሶስት ሳምንት የተጠናቀቀ ቢሆንም 12 ፕላስቲክ ጠርሙሶችን አንድ ላይ በመጋገር፣ የጋገራ ስራው በውጭ ካለቀ በኋላ ቤቱን በአራት ቀን ሰርቶ መጨረስ እንደሚቻልም ተገልጿል፡፡
በዚህ ለሙከራ በተሰራ የቤት የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ የኮንስትራክሽን ሚኒስትር፣ የከተማ ቤቶችና ልማት ሚኒስቴር፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ተወካዮች የተገኙ ሲሆን ከቤቱ አሰራር ጋር በተገናኙ ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄዎችን አንስተው ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ስማርት ማኔጅመንት ሰርቪስስ በስሩ 11  እህት ድርጅቶችን የያዘና ከ10 ዓመት በፊት የተቋቋመ ኩባንያ ሲሆን ከሚያስተዳድራቸው መካከል በትምህርት፣ በግብርና፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በሆቴል፣ በፈጣን ምግብ ማዕከላትና አምራችነት፣ በትራንስፖርትና በሌሎችም ዘርፎች ላይ የሚሰሩ ይገኙበታል፡፡ የተመረቀውን ቤት የያዘው ድርጅት ደግሞ በኢንጂነሪንግ ዘርፍ የተሰማራውና በአርቴፊሻል እብነበረድና ግራናይት ምርቶቹ የውጭ ምንዛሬን በማስቀረት ጉልህ ሚናን የሚጫወተው ሲምኮን ቴክኖሎጂስ ነው፡፡ በስማርት ማኔጅመንት ሰርቪስስ ስር ካሉ ኩባንያዎች መካከል በትምህርት ዘርፍ ኢትዮጵስ ኮሌጅ፣ በትራንስፖርት አሊያንስ የከተማ አውቶቡስ፣ በፈጣን ምግብና በሆቴል ዘርፍ ሩሚ በርገርና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

Read 4364 times