Sunday, 11 February 2018 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(9 votes)

       “ሰይጣንን የሚያናድደው ማነው?”
            
    ሰውየው ሞተ፡፡ ሰማይ ቤት ሲደርስ ሚዛን ጠበቀው፡፡ ምድር ላይ ያቆመው መልካም ስራውና ሃጢአቱ ተመዘነ፡፡ ዕኩል ተዕኩል ሆነ፡፡
“ከእኔም ካንተም አልሆነም”… አለ እግዜር፡፡
“ምን ይሻላል?”… ጠየቀ ዲያብሎስ፡፡
“ወደመጣበት እንመልሰውና እንየው”
“ለምን አንፈትነውም?”
“እንደሱም ይቻላል”
አምስት፣ አምስት ጥያቄዎች አዋጥተው ፈተኑት። ፈተናውን ካለፈ ገሃነም፣ ከወደቀ ገነት እንዲገባ ተስማሙ፡፡ ዲያብሎስ ያወጣቸው ጥያቄዎች በጣም ቀላል ነበሩ - ሰውየውን ለማሳለፍ፡፡ የእግዜር ደግሞ በእጅጉ ከባድ ሆነ - ሰውዬው እንዲወድቅለት፡፡… ውጤቱ ዕኩል ተዕኩል ሆነ - እንደ በፊቱ፡፡
“ምን ይሻላል?”…ጠየቀ እግዜር፤ በተራው፡፡
“እኔ እንጃ!” አለ አጅሬው፤ ትከሻውን እየነቀነቀ።
የነሱን ንግግር ያዳመጠው ሟች፤ “በገዛ ፍቃዴ ገሃነም መግባት ነው እምፈልገው” አላቸው፡፡
“መብትህ ነው” አለ ዲያብሎስ፡፡
“ምክንያቱን ማወቅ እንፈልጋለን” … አለ እግዜር።
“ከኛ በላይ ሃይማኖተኛ የለም፤ ያዙን ልቀቁን የሚሉ በተግባር ግን እዚህ ግቡ የማይባሉ አስመሳዮች ምድር ላይ አበሳዬን ሲያሳዩኝ ነው የኖርኩት፡፡ እዚህ ግን ከእንደነሱ አይነት ጋር መኖር አልፈልግም፡፡” አለ ሟች፡፡
“ምን በወጣህ፣ ካልፈለግህ አልፈለግህም ማለት ነው”…. አጅሬ ነበር፡፡
“እሱ ያንተ ፈቃድ ነው፡፡ ምርጫህ የተሟላ እንዲሆንልህ ግን ሁለቱንም ቦታዎች አይተህ ብትወስን አይሻልህም?” ሃሳብም፣ ጥያቄም አቀረበለት፤ እግዜር፡፡
“እሽ” አለ ሰውየው፡፡
አጅሬውም “በጣም ጥሩ” በማለት ተስማማ፡፡
ሶስቱም ተያይዘው ወደ ገሃነም አቀኑ - ቅርብ ከነበረው ለመጀመር፡፡ እዛ እንደደረሱ ሁለቱ አለቆች በር ላይ ቀርተው ሰውየው ደርሶ እንዲመጣ ላኩት። ሟች ወደ ውስጥ እንደዘለቀ የሚያየው ነገር ሁሉ አስደሰተው፡፡፡ አስመሳዮች፣ ጉበኞች፣ ዘረኞች፣ የመሳሰሉት አልነበሩም፡፡ የሚመለከተው ሰው ሁሉ ቅን፣ ደጋግና አስተዋይ ከመሆኑም በላይ መንገዱ፣ አትክልቱ፣ ምንጣፉ ልዩ ነው፡፡
ጉብኝቱን ጨርሶ ሲመለስ…
“እህሳ፣ እንዴት አገኘኸው?”…አጅሬ ጠየቀው፡፡
“ቆይ እስቲ አትቸኩል፤ ያኛውንም ይይና አንድ ላይ ይነግረናል”… አለ እግዜር፡፡
“አይ በቃ…ምንም ችግር የለም፡፡ ባላየውም ይሄኛውን መርጫለሁ፤ ቻዎ ጌታው” ብሎ ዲያብሎስን ተሰናበተ - ሰውየው፡፡ እግዜር ምንም አላለም፡፡ የሟችን አጅ ይዞ ወደገነት ሲያመራ…
“ቡዳ!” አለ፤ አጅሬ ጮክ ብሎ፡፡
እግዜር ሳቀ፡፡…
“ማንን ነው እሚሳደበው?.... የፈለግከውን ምረጥ አይደል እንዴ ያላችሁኝ?”…ጠየቀ ሰውየው፡፡
“ዓመሉ ነው…አርቴፊሻል ገነት አዘጋጅቶ ሊያታልልህ መሞከሩ ስለተነቃበት ነው፡፡” …አለ እግዜር፡፡
“እንዴ?... ያ ሁሉ ውበት፣ ያ ሁሉ ምቾት የውሸት ነበር?”
“አዎ…አንድም ዕውነት የለበትም፡፡”
“ታዲያ እኔ መች አወቅሁ?... እንዲያውም እዛ መቅረት ፈልጌ ነበር፡፡ ምን እንደነካኝ እንጃ እንጂ…”
“እንዳትቀር ያደረግሁህ እኔ ነኝ፡፡”
“እንዴት?”
“ሀሳብህ ሆንኩ፣ አንተን ራስህን ሆንኩ፡፡”
“አልገባኝም”
“እንኳን ያንተን የሟቹን፣ የሱን ሃሳብ በማወቄ አይደል፣ አዘጋጅቶ ስላሳየህ ውሸት የነገርኩህ!”
“ሃሳብማ ከሆንክ…ይኽ ሁሉ ድካም ለምን?”
“ገብቶኛል”… አለ እግዜር ሳያስጨርሰው። ቀጠለናም፤ “…እሱ ሊያታልልህ ባይሞክርና ዕውነተኛውን ገሃነም ቢያሳይህ ኖሮ፣ እኔም ሀሳብህን አልሆንም ነበር፡፡ ምርጫው ያንተና ያንተ ብቻ በሆነ”
“ታዲያ ለምን ዝም አልከው?”
“ቻይ መሆን ያስፈልጋል፤ ያለ ተቃራኒ መኖር አይቻልም፣ እሱ ባይኖር እኔን ማን ያውቀኛል?”
“አቦ ይመችህ፣ ምድር ላይ ነው እንጂ… እዚህ ፍትሃዊ ትመስላለህ”…አለ ሰውየው፡፡
እግዜር እየሳቀ፣ በሩን ከፍቶ አስገባውና ተመለሰ።
ወዳጄ፤ እግዜር “ያለ ተቃራኒ መኖር አይቻልም፤ ተቀናቃኝ ባይኖረኝ እኔን ማን ያውቀኛል” ማለቱ ዕውነትነት አለው፡፡ ሰይጣን ባይኖር የእግዜር ደግነት፣ ርህሩህነት፣ አሳቢነትና ፍትሃዊነት በምን ይታወቃል? ...”እግዜር ይመስገን፣ ለሱ ምን ይሳነዋል፣ በሱ ቸርነት እንዲህ ሆኛለሁ፣ በሱ ፈቃድ እዚህ ደርሻለሁ ምስጋና ይግባው...፣” የምንለውን ያህል…ግጭት በሚኖርበት፣ ጠብ በሚነሳበት ጊዜ “ሰይጣን መሃል ገብቶ ነው”፣ ክፋትና ተንኮል ሰርተን “ሰይጣን አሳስቶኝ ነው፤ ሰይጣ ገፋፍቶኝ ነው፤ ያ ከይሲ ነው ጉድ ያደረገኝ” እንላለን፡፡
አንድ የቆየች ቀልድ እነሆ፡- በገዳም የሚኖሩ እማሆይ፤ ዕንቁላል መብላት አማራቸው፡፡ በዓቢይ ፆም ወቅት ነበር፡፡ አንድ እንቁላል አነሱና፤ “ጌታዬ ይቅር በለኝ” አሉ፡፡ እሳት ማቀጣጠል፣ መጥበሻ መጣድ ፈሩ፡፡ ጧፍ ለኮሱና ጠፍጣፋ ድንጋይ አጋሉ፡፡ እንቁላሏን ቀጭ አድርገው ሲያፈሱበት፣ አሪፍ ኦምሌት ሆነላቸው፡፡… ሽታ የለ፣ ምን የለ!... ከጫፉ ቆረስ አድርገው ቀመስ ሲያደርጉ፣ ከዚህ መጡ የማይባሉ መነኩሴ ከች አሉ፡፡
“እግዚኦ! እግዚኦ! ምነው? ምነው እማሆይ?” እራሳቸውን ይዘው ጮሁ፡፡…
እማሆይ ክው፤ ድርቅ አሉ፡፡ ነፍሳቸው ስትመለስ፤ “አባቴ ይቅር በሉኝ፣ ያ ከይሲ አሳስቶኝ ነው” አሉ፡፡ አጅሬ እዛ አካባቢ ሆኖ ሲያደርጉ የነበረውን ሁሉ ይመለከት ነበርና ሳቁን መቆጣጠር አልቻለም፡፡  “እንኳንስ ላሳስታቸው፣ እንቁላል እንደዚህ እንደሚጠበስ ለመጀመሪያ ጊዜ በማየቴ ገርሞኛል” አለ አሉ፡፡
የሰይጣንን ነገር ካነሳን አይቀር፣ ካህሊል ጂብራን “ሳታን” በማለት የፃፋት ትንሽ መጽሐፍ አለች፡፡ እዛ ላይ “…አጅሬው ታሞ ከመንገድ ዳር ተኝቶ ያቃስታል፣ በሰው ተመስሎ፡፡ ለስርዓተ ፀሎት የሚጣደፉ አባ በዚያ በኩል ሲያልፉ፡-
“አባቴ አይለፉኝ፣ በጠና ታምሜአለሁ” አላቸው፡፡
እሳቸውም፤“ልጄ ቸኩያለሁ፣ እግዜር ይማርህ” በማለት ሲጣደፉ፤ “ትተውኝማ እንዳይሄዱ፣ በኋላ እንዳይቆጭዎት፣ ልሞት እችላለሁ፤ እኔ ከሞትኩ ደግሞ ስራዎን ያጣሉ፣ ይራባሉ፣ እስከ ዛሬ ድረስ የሚሰብኩት፣ የሚናገሩት ነገር ሁሉ ዜሮ ይሆናል።” አላቸው፡፡
“እ … ምን አልክ?....” አሉ አባ፤ በመገረም፡፡ ቀጥለውም፤ “ማነህ አንተ ለመሆኑ?” … ሲሉ ጠየቁ።
“እኔማ ሰይጣን ነኝ” አላቸው፡፡
አባ ደንግጠው፤ “በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፣ አንት ከይሲ…” አላስጨረሳቸውም፡፡
“እሱን ተወውና ዕውነቱን እንነጋገር፡፡ … ሁሉን ነገር በኔ ታሳብባላችሁ፣ እኔ ባልኖር የናንተ ስራ ምንድነው? ይሄ ሁሉ ቤተ እምነት፣ ይሄ ሁሉ መስጂድ፣ … ይሄ ሁሉ አዳራሽ ምን ይደረግበት ነበር? … ስምንት ሺ ዓይነት  እምነት አለ፡፡ በነዚህ ተቋማት የሚተዳደሩ ሁሉ ምን ይሆኑ ነበር? … የሚገባህ ከሆነ የምኖረው ለናንተ ነው፡፡ ደግሞ ባንተ ብሶ …” እያለ ሲቆጣና ሲዘረዝር አባ ቀዘቀዙ፡፡ አሰቡ፣ አሰቡናም “እውነት ነው” አሉ፤ለራሳቸው፡፡ “… አንተ ብትሞት ምን እናስተምራለን? ሐጢአታችንን በማን እናሳብባለን? ደግሞስ ምን እንበላለን?” እያሉ በሆዳቸው… አጅሬውን ደግፈው፣አንስተው እንዳይሞትባቸው ሊንከባከቡት ወደ ቤታቸው ተመለሱ” .. ይለናል ፤ ካህሊል ጂብራን፡፡
ወዳጄ፤ “…አቤት የሰው ነገር፣ አበሻ ሲባል …” ምናምን እያልን፣ ጥፋታችንን በሌላው ላይ ስናላክክ ዘመናት አለፉ፡፡ ለስህተታችን ኃላፊነት የምንወስደው መቼ ነው? … ‹ሰው› የምንለው ሰው፣ የት ጋ ነው ያለው? … ‹ሀበሻ› የምንለው ሀበሻ፣ ማን ነው? … እኛው አይደለን?
ቅዱስ መጽሐፍ … “ከናንተ መሃል ሃጢአት ያልሰራ እሱ ይውገራት” በማለት የሰጠው ምሳሌ ለምን ይመስልሃል? … በነገራችን ላይ እኛ በሰይጣን እንናደዳለን፡፡ … ሰይጣንን የሚያናድደውስ ማነው?
ሠላም!!!

Read 5170 times