Sunday, 11 February 2018 00:00

ፍቅርን ከአድማስ ወዲያ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

     ስለ ፍቅር ሲነሳ ከሦስቱ የፍቅር ዘውጎች አንዱ የሆነው “ኢሮስ” ደመቅ ብሎና ጎልቶ ይታያል፡፡ ብዙ ቅኔ የተቀኘንለት፣ በርካታ ዜማ የፈሰሰለትም ይሄው ራሱ ኢሮስ ነው፡፡ አጋፔ በልኩ፣ ፊልዎም እንደዚሁ ድንኳን በጣሉለት እልፍኝ ይሞሸራል፡፡ ምሥጋና ተችሮ ይቀበላል፡፡
ይሁንና በሬዲዮና በቴሌቪዥን፤ በመጽሔቶችና በመጽሐፍት፣ በአበባና እሾህ አጀብ የሚተረክለት ይህ ኢሮስ የተሰኘው የተቃራኒ ፆታ ፍቅር ነው፡፡ በዚህ ፍቅር ምክንያት ጨርቅ የጣሉ፣ ህይወታቸውን ሳይሳሱ በገዛ እጃቸው የቀጠፉ ብዙ ናቸው፡፡ ጎበዞች እጅ ሰጥተው፣ ሃያላን ተማርከው ታሪካቸው በታሪክ ድርሣን ተቀምጧል፡፡ ይህንን ፍቅር አላውቅም የሚል ቢኖር ራሱን ያብላል፣ ራሱን ያታልላል ነው፤ የብዙዎች መቋጫ!
የሥነ- ልቡናና የሥነ ጋብቻ ምሁራን ሌትና ቀን የሚያጠዛጥዘው ይህ ፍቅር፣ የገጣሚያኑንም ገመና ገልጦ፣ የጥበብን ቀለም አንጠፍጥፎ ዛሬም አልበቃውም፡፡ ይሁንና ይህ ፍቅር ብዙ ጊዜ ሥነ ልቡናዊያን “Adolesence” በሚሉት የዕድሜ ክልል የሚጀመር ነው፡፡ Late childhood በሚባለው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወይም የቡድን
(gang) ዕድሜ መራራቁ እንደሚያመዝን ምሁራኑ ይናገራሉ፡፡
በዚህ የእሳት ምላስ ዕድሜ ግን ስሜታቸው ሲንተከተክና ውበታቸው ሲፍለቀለቅ ወንዱ በሴቷ ላይ፣ ሴቷም በወንዱ ላይ ዓይን ይጥላሉ፡፡… እንደየ ሁኔታው አጠቃላይ የህይወታቸው መሥመር ቦይ፣ ዜማና ግጥሙ፣ ህልምና ራዕዩን ወደ ተቃራኒ ፆታ ያፈሥሣል፡፡… ያሁኑን ባላውቅም እህል የማይቀምሱ ከእንቅፍል የሚጣሉ ብዙ ነበሩ፡፡ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ እንኳ ለሰላሣ ዓመታት ገደማ ፍቅረኛውን የሚጠብቅበት ቦታ ቆሞ የምታገኙት ሰው አለ። እርሷ ትታው ከሀገር ብትወጣም እርሱ ግን ዛሬም ሠዓት መቁጠር ባቆመ ልቡ ይጠብቃታል፡፡ እውነተኛ ፍቅር ተዓምርነቱም ይሄኔ ነው፡፡ ፍቅር ከዚህም በላይ ነው፡፡
ፍቅር ውስጥ ናፍቆት አለ፡፡… ፍቅር ውስጥ ሰቀቀን አለ፡፡ ይህንን ሰቀቀን እስኪ ከገጣሚያን ገፆች እንመልከት፡፡... ገጣሚ ትዕግሥት ማሞ እንዲህ ትላለች፡-
ምንድነው መናፈቅ?
ምንድነው ትርጉሙ?
ምንድነው መሰሰት?  እንዴት ነው ህመሙ?
እያልኩኝ ከራሴ፣ ሙግት እገጥማለሁ፤
እንዲህ ያለ ስንፈት፣ እንዲህ ያለ ሽንፈት
እኔ ምን አውቃለሁ፡፡
ስለይህ አይደለም፣ ስትርቀኝም አይደል…
የናፍቆቴ ህመም፣ የሚጀማምረኝ
ካፍህ ነው መውደድህ፤ በእውነት ዜማ መሃል…
የሚያሽቀነጥረኝ፡፡
እንጃ መክረሚያዬን!
እንጃልኝ ነገዬን!
ታዲያ ይህ ፍቅር በወጉ ከያዙት ለቁም ነገር በቅቶ ሊዘልቅ ይችላል፡፡ በዚህ ዝልቀትም የተሻለ ትውልድና ቤተሰብ ሊመሠረትና ሊበቅል ይችላል። አለዚያ ግን ሁለቱንም ወገን ዐላማ ቢስ አድርጎ ዘመንን በማባከን የቁጭት ቁሥል ሊሆን ይችላል። በተለይ ደግሞ በለጋ እድሜ፤ ያለ ብስለት፣ በእንጭጭነትና ስሜታዊነት ከተጀመረ አደጋው የትየለሌ ነው፡፡… ክፋቱ ደግሞ አዶለስንስ ላይ የሚገነፍለው ፍቅር ባብዛኛው የሚጠነስሰው፣ በለጋ  የልጅነት ዕድሜ ነው፡፡ ዎው የተባሉ ፀሀፊ፡- “Teenagers need love and want to know about love more than anything else” ይላሉ፡፡
በዚህ ዕድሜያቸው ከምንም ነገር ይልቅ ስለ ፍቅር ማወቅን ይሻሉ፡፡ ዕውቀቱንና ግንዛቤውን የሚያገኙትም ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና ፊልሞች ሊሆን ይችላል፡፡ የሥነ-ልቡና ምሁራኑም እንደሚስማሙበት፤ ይህ ዕድሜ ብዙ መረጃዎችን ከጋዜጣ፣ ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮና ከሌሎችም የሚሰበሰቡበት ነው፡፡ በዚህ ዘመን  ደግሞ ሁሉንም ጠቅልሎ የሚይዘው ኢንተርኔት በእጃቸው ነው፡፡
ይሁን እንጂ የሥነ- ጋብቻና የቤተሰብ ጉዳይ ምሁራን፣ አሁንም ዕዳውን የሚጥሉት በወላጆች ላይ ነው፡፡ በተለይ በቤት ውስጥ በሚኖረን አርቴፊሻል ያልሆነ እውነት፣ ልጆችን ስለ ፍቅር ማስተማር እንችላለን፡፡ ፍቅርና ፀብ፣ በትይዩ የሚጓዙ ስለሆኑ፣ ሁለቱንም ከነምክንያታቸው በማስረዳት የፍቅርን አበባና  እሾህ ማሣየት ይቻላል፡፡ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው ፀሀፊ እንዲህ ሲሉ ያሠምሩበታል፡-
“You, the parents, carry the first responsibility to show your teenager what geniune love is. Your differences and even your conflicts won’t hurt him at all if he sees you resolved them.”
ወላጆች በተለይ ልዩነታቸውን ከልጆቻቸው እየደበቁ ካሳደጓቸው፣ እነዚያ በፍቅር ነፍዘው ወደ ጋብቻ የገቡ ልጆች፣ በትንሽ ፀብ ተደናግጠው ሊደነብሩ ይችላሉ፡፡ ክፉም ደግም በምክንያት ለልጆች ሊነገራቸው ይገባል፡፡ ፍቅር ያለ ግጭት፣ መልአካዊ ሊሆን አይችልም፡፡… በፍቅር የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት ግን ብልህነትና ትዕግስት ሲታከልበት  ለስኬታማነት ያበቃል፡፡
ፍቅር ወደ ጋብቻ የመግቢያ ሃይል ከሆነ፣ በለጋነት እንዳይቀጠፍ መጠንቀቅም ግድ ይላል፡፡ ከዚህ ቀደም አንድ ወጣት ሴት፣ ባል አግብታ ሣምንት ሳይሞላት ወደ ቤተሰቦችዋ በርራ የመጣችበትን ምክንያት ወዳጄ ሲያወጋኝ፣ በድብቅነታችን መዘዝ በእጅጉ ከንፈር መጥጫለሁ፡፡ ይህቺ ሙሽሪት ከወላጆችዋ ጋር ስትኖር፣ “ማሬ-ወተቴ” ሲባባሉ እንጂ ክፉ ቃል ሲወራወሩ ሰምታ  አታውቅም። በቁልምጫ እየተጠራሩ፤ በፍቅር እየተጎራረሱ ---- ገነት የሚመሥል የትዳር ህይወት ነበር ያሳዩዋት፡፡ ይሁን እንጂ በመኝታ ክፍላቸው ከፍቅር ውጭ የሚሠሯቸው ሥራዎችም ነበሩ፡፡ በሃሣብ ካልተግባቡ፣ ክፍሉን ዘግተው፣ በነገር ይጠዛጠዛሉ። ያቺ እርግብ ይሄ አምልጧት ነበር፡፡ እናም ከአዲሱ ሙሽራ ጋር ባንዳንድ ነገሮች ሲጋጩ፣ ጋብቻ ቀድሞ የምታውቀው ገነት ሳይሆን ሲዖል ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ ከዚያም ወደ ቤተሰቦችዋ በርራ ሄደች፡፡ ወላጆችዋ ተደናገጡ፡፡ ይሁን እንጂ ጉዳዩን ስትነግራቸው፣ ችግሩ የልጅቷ ሣይሆን የራሳቸው ነበረና ተፀፀቱ፡፡… ከዚያ በኋላ ምን ላይ እንደደረሱ ስላልሰማሁ  ዝም ብዬ ባልፈው ይሻላል፡፡
ባልና ሚስት ከፍቅራቸው ይልቅ ዘልቆ አናታቸው ላይ የሚወጣው ግጭት መነሻ የተለያየ ቢሆንም በገንዘብ አያያዝና አጠቃቀም የሚነሳው ከሁሉም የላቀና ዋነኛ ከሚባሉት ሰበቦች አንዱ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ለዚህም ነው፣ W.Clark Ellxy “conflict over money ranks high among the top cause of trouble in marriage” የሚሉት:: በተለይ ከስልጣኔና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጋር ተያይዞ፣ ባደጉ ሀገራት ሴቶች ከወንዶች እኩል፣ አንዳንዴ በተሻለ ሁኔታ የገቢ ምንጭ ማሥገኘት መጀመራቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ደግሞ የሴቶችን እኩልነት መቀበል ለሚተናነቃቸው ወንዶች የፀብ መንስኤ እየሆነ ነው፡፡
በተለይ ወደ እኛ ሀገር ባህልና አስተሳሰብ ሥናመጣው፣ እኛ ወንዶች በሴቶች መበለጥን መቀበል በእጅጉ ይቸግረናል፤ ሴቶቹም ቢሆኑ  ሴቶችን ዝቅ አድርጎ በሚያይ ባህል ውስጥ ስላደጉ፣ከወንዱ የተሻለ ነገር ሲኖራቸው ወንዶቹን (ባሎቻቸውን) የሚይዙበት መንገድ ሚዛን የጠበቀ አይሆንም፡፡ ስለዚህም ለብዙ ወራትና ዓመታት እየተንቀለቀለ የሚነድደው የፍቅር እሣት፣ ዓመድ ሆኖ በፍቺ ለመለያየት ያበቃቸዋል፡፡
ለጊዜው ይህንን የችግር መነሻ ጠቀስኩ እንጂ በሀገራችንና በአህጉራችን ዋነኛ ሊባል የሚችለው የፀብ መንስኤ የዘመድ አዝማድና የቤተሰብ ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ ከሁሉ ይልቅ ትዕግሥትን የሚፈታተነውና የሚጠይቀውም ጉዳይ ይህ ነው። Cecil Osborne የተባሉ የሥነ ጋብቻ ባለሙያ  እንዲህ ሲሉ ይመክራሉ፡- “A basic rule in marriage is to never, never criticize the relatives of your marriage partner.”
ትዳር ከፍቅር ይልቅ የትዕግሥት ልጓም የሚሻ እጅግ ውስብስብ የሆነ ተቋም ነው፡፡ ናፍቆቱ …መፈላለጉ…. እንቅልፍ ማጣቱ … ሁሉ በኋላ ሁሉን ወደ ማጣት ይወሥድና፣ በቁጭት የሚከተለውን ግጥም ያስገጥማል፡-
እዩት  የእሷን አድማስ
ፀሀይ ተንተርሶ፤
ፅጌረዳ ያቀፈ ውበት ተለውሶ፤
ጎጆዋም ደምቃለች
ሣቋ ድንኳን ሞልቷል፤
በጎፈሬዋ ላይ ሚዶ- ተሰክቷል፡፡
የኔ ሠፈር ሰማይ- በጭጋግ ተሞልቷል፤
የእንባ ጠጠር ሆኖ- በሠቀቀን ቀልቷል፤
ያኔ---
የኔና የርሷ ሠፈር-ኩራዞቻችን ባንድ ላይ ሲነዱ፤
ከዋክብቶቻችን
በቀያችን መሀል - ከሰማይ ሲወርዱ፤
ፀሀይ አያሻንም - ጨረቃም አንጓጓ፤
ቃል ህይወት ነበረ
ከከንፈሮቻችን- ህልማችን ሲነጋ!
“ያኔ” የሚለው በትዳር ዓለም፤ በደመቀ ፍቅር፣ ከዋክብትም በወረዱባቸው ሌሊት ነበር፡፡ አበባና አበባ፤ ሣቅና ፍንደቃ!...ፍቅር ከአበባ ጀምሮ፤ ለፍሬ እንዲበቃ ከልጅነት የሚጀምር ጥንቃቄና ክብር  ይፈልጋል፡፡ “ኢሮስ” የተሰኘው የፍቅር መዝገብ ውስጥ ሣቅ ብቻ ሳይሆን ለቅሶም  ተመዝግቧል። በተለይ በዚህ ዘመን፣ በተለይ በዚህ ትውልድ፣ ፍቅርን ሸቀጥ እያንገዳገደው ስለሆነ፣ “ፍቅር” ተረት እንዳይሆን እርሻችንን እንኮትኩት፤ በልጆቻችን ልብ፣ በሀገራችን አደባባይ ፍቅር ይለምልም!...ገጣሚያንና ሌሎችም የጥበብ ሰዎች፣ ከብር አድማስ ወዲያ የፍቅርን ጀንበር ፈልጉ፡፡

Read 2518 times