Sunday, 11 February 2018 00:00

አረና ፓርቲ የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ገመገመ?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 • የገዢዎች አፈና ሲቆም የህዝቦች ግንኙነት ይጠናከራል
      • አጀንዳችን የኢትዮጵያን አንድነት ማምጣት ነው
      • በአጠቃላይ የዘር ፖለቲካው አላንቀሳቅስ ብሎናል

     ሰሞኑን አረና ትግራይ ለፍትህና ለሉአላዊነት፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን አድርጎ፣ የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ የገመገመበትን መግለጫ አውጥቷል፡፡ ለመሆኑ መግለጫው ስለ ሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ምን ይላል? በትግራይ ክልላዊ መንግስት የተደረገውን የአመራር ለውጥስ እንዴት ያየዋል? በእነዚህና ሌሎች ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ከፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ አብርሃ
ደስታ ጋር ተከታዩን አጭር ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡ እነሆ፡-


    ፓርቲያችሁ የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ነው የገመገመው?
አንደኛ፣ በሀገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ የመኖሩን ጉዳይ ነው የገመገምነው፡፡ የፖለቲካ ቀውሱ ደግሞ በኢህአዴግ አፈና ምክንያት የተፈጠረ ነው፡፡ አሁን የህዝብ አልገዛም ባይነት አለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኢህአዴግ ህዝብን መምራትና ማስተዳደር አለመቻል እየታየ ነው፡፡ ይሄ ነገር በአግባቡ ካልተመራ ወደባሰ ፖለቲካዊ ቀውስ ሊመራን ስለሚችል፣ ምን ማድረግ አለብን በሚለው ጉዳይ ላይ ተወያይተናል፡፡ ሀገሪቱን ለማዳን፣ ቀውሱን ለመፍታት ምን መደረግ አለበት በሚለው ላይ ሰፊ ውይይት አድርገናል፡፡
ታዲያ በውይይታችሁ ምን ላይ ደረሳችሁ…?
እንግዲህ ኢህአዴግ ለሀገሪቱ ችግር መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ አባባሽ ሁኔታዎችን እየፈጠረ በመሆኑ፣ እኛ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን፣ የሀገር አንድነት ማምጣት እንደሚገባንና የእርስ በእርስ ግጭት እንዲቆም ሁሉም ህዝብ እንደ አንድ ህዝብ በጋራ እንዲታገል መጣር  አለብን ብለናል። በሌላ በኩል በኢትዮጵያ አንድነት ከሚያምኑ፣ የኢትዮጵያ መፃኢ እድል ከሚያሳስባቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ትብብር በመፍጠር፣ አንድ ላይ መስራት እንዳለብን ተስማምተናል፡፡ በትግራይ አካባቢ ህዝብን ፖለቲካ ማስተማርና ማደረጃት እንደሚገባን፣ ከምንም በላይ የኢትዮጵያን አንድነት ማስጠበቅ እንዳለብን አቅጣጫ አስቀምጠናል፡፡
ከሰሞኑ ተፈፅመዋል የተባሉ ብሄር ተኮር ጥቃቶችን  እንዴት ተመለከታችሁት? መፍትሄውስ ምንድን ነው?
እርግጥ ነው የትግራይ ተወላጆች ጥቃት ደርሶባቸዋል፤ ግን ይሄ የሆነው በህውሓት ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ መፍትሄው፣ ከህዝቡ ጋር ሆኖ ህውሓትን መታገል ነው ብለን ገምግመናል። ሁሉም የሚስተካከለው የተቀናጀ ትግል ሲደረግ ብቻ ነው።
በቅርቡ በትግራይ ክልል የተደረገው የአመራር ለውጥ ምን ውጤት ያመጣል ትላላችሁ?
የህዝብ ጥያቄ በአመራር ለውጥ ብቻ አይመለስም፡፡ ህውሓት ህውሓት ነው፤ ሰዎቹም የህውሓት አባሎች ናቸው፡፡ ስለዚህ እኛ ከዚህ የአመራር ለውጥ፣ ብዙም ውጤት አንጠብቅም፡፡ ህዝቡ የፈለገውን እንዲመርጥ መፍቀድ አለባቸው  ብለን እናምናለን፡፡ አሁን በኦሮሚያ እየተደረገ  ያለው ጥሩ ነገር ነው፡፡ በህውሓትም እነሱ መርተው ለውጥ ማምጣት እንደማይችሉ አውቀው፣ የለውጥ ኃይል እንዲመጣ መንገዱን መክፈት ነው ያለባቸው። እንደ ቀድሞ ጨቁኖ መግዛት የማይቻልበት ደረጃ ላይ እየተደረሰ በመሆኑ ወይ ተገደው ይለወጣሉ ወይ እነሱ ራሳቸው በለውጡ ይሄዳሉ፡፡
ከሰሞኑ “ትግራይን መገንጠል” የሚል ነገር በአንዳንድ ወገኖች፣ በማህበራዊ ሚዲያ ተነስቷል። ይሄን ጉዳይ ፓርቲያችሁ እንዴት ይመለከተዋል?
አረና በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምን ፓርቲ ነው፤ ትግራይ የኢትዮጵያ መሰረት ነው ብለን ነው የምናስበው፡፡ ትግራይ ከሚለው ስም በፊት ኢትዮጵያ ብሎ ነው የትግራይ ህዝብ የሚያምነው፡፡ ይሄ ሃሳብ  በተለያዩ አካባቢዎች ከሚደርሱ ብሔር ተኮር  ጥቃቶች የተነሳ የመጣ ነው፡፡ ተገፋሁ የሚል አካል ይሄን ማንሳቱ የሚገርም ባይሆንም ጊዜያዊ ስሜት መሆኑ ግን አያጠያይቅም፡፡ የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያዊ አንድነቱ ፅኑ መሰረት አለው። ወደ መገንጠል ወይም ሌላ አማራጭ የሚሄድ አይደለም። ይሄ ሃሳብ የመከፋት ስሜት መኖሩን የሚጠቁም እንጂ የትግራይ ህዝብን አቋም የሚገልፅ አይደለም፡፡ የኛም እምነት የኢትዮጵያ አንድነት ነው። አጀንዳችንም የኢትዮጵያን አንድነት ማምጣት ነው፡፡
ከዚህ ቀደም አንድ ጠንካራ ሃገራዊ ፓርቲ የመፍጠር ዓላማ  እንዳላችሁ ጠቁማችሁ ነበር፡፡ ይህ ሃሳብ ከምን ላይ ደረሰ?
እርግጥ ነው እቅድ አውጥተን ነበር፡፡ ነገር ግን አልተሳካም፡፡ ከፓርቲዎች ጋር ለመቀራረብ ያደረግነው ጥረት ውጤት አላመጣም፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ፖለቲካው ወደ ብሄር ፖለቲካ ገባ፡፡ ሁሉም በብሄር ማሰብ ጀመረ፡፡ በዚህ የተነሳ ዕቅዱን መተግበር አስቸጋሪ ሆነብን፡፡ ኢትዮጵያዊነት የሚለው ነገር ብዙ ትኩረት ባለማግኘቱ፣ ውጤታማ መሆን አልቻልንም፡፡ ነገር ግን አሁንም እንቅስቃሴው አልቆመም፤ ሆኖም  ይሄን እኛ ብቻ ልናደርገው አንችልም፡፡ ሌሎች ፓርቲዎችም ይሄን ሃሳብ ይዘው መንቀሳቀስ እስኪጀምሩ ድረስ ክልላዊ ፓርቲ ሆነን እንቀጥላለን፡፡
አሁን አረና እያደረገ ያለው ፖለቲካዊ  እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
አሁን ጠንካራ እንቅስቃሴ እያደረግን አይደለም። ያላደረግንባቸው ምክንያቶች ደግሞ በርካታ ናቸው። አንዱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ነበር፡፡ በሌላ በኩል፣ ህውሓት በኛ ላይ የሚነዛው ፕሮፓጋንዳ አላንቀሳቅስ ብሎናል፡፡ በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ላይ ስንንቀሳቀስ፣ ህውሓት፣ “እነዚህ ስለ ትግራይ ህዝብ ጥቃት አያስቡም” ይለናል፡፡ ለትግራይ ህዝብ መቆርቆር ስናሳይ ደግሞ በአንዳንድ ወገኖች “ፀረ ኢትዮጵያ” እንባላለን፡፡ ይሄ ለፖለቲካዊ እንቅስቃሴያችን ከፍተኛ  እንቅፋት ሆኖብናል፡፡ በአጠቃላይ የዘር ፖለቲካው አላንቀሳቅስ ብሎናል፡፡
በሌላ በኩል ግን የትግራይ ህዝብ፣ የፖለቲካ ለውጥ በመፈለግ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ አሁን ደጋፊና ለውጥ ፈላጊ ህዝብ ስላለ፣ አረና በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል ማለት ይቻላል፡፡ አሁን የብሄር ፖለቲካው የበላይነት ስለያዘ፣ ለጊዜው ህዝብን ስለ ኢትዮጵያ አንድነት እየሰበክን ነው መንቀሳቀስ የምንፈልገው፡፡ አጀንዳው ከባድ ቢሆንብንም በኢትዮጵያ አንድነት ተስፋ አለን፡፡ በህዝቦች መካከል እየተፈጠረ ያለው ችግርም የገዥዎች የአፈና ውጤት ነው ብለን እናምናለን፡፡ ይሄ አፈና ሲቆም የህዝቦች ግንኙነት ይጠናከራል የሚል እምነት አለን፡፡

Read 1819 times