Print this page
Sunday, 11 February 2018 00:00

“ላለፉት 13 ዓመታት መብቶቼን ተነጥቄ ነው የኖርኩት”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

• የፌደራል መንግስቱ መብቶቼንና ጥቅማ ጥቅሞቼን እንዲያከብርልኝ መጠየቄን እቀጥላለሁ
     • እስከ ባለፈው ዓመት ድረስ በወር አንድ ሺ ሰባት መቶ ሃምሳ ብር ነበር የማገኘው
     • ጠ/ሚኒስትሩ “ከስራ ባልደረቦቼ ጋር ተመካክሬ መልስ እሰጣለሁ” ብለውኝ ነበር
     • *አዲሱን የኦህዴድ አመራርና የኢትዮጵያን ህዝብ አመሰግናለሁ

    የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ለ13 ዓመታት መንግስት የተከለከልኩትን ጥቅማ ጥቅምና መብቶች እንዲያከብርልኝ ብታገልም እስካሁን አልተሳካልኝም  ይላሉ፡፡ እስከ ባለፈው ዓመት ድረስም በወር 1750 ብር ጡረታ ያገኙ እንደነበርና በባለቤታቸው ገቢ ሲተዳደሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ የኦህዴድ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፣ ችግራቸውን ከተረዳ በኋላ ሰሞኑን የገንዘብ ድጋፍ እንዳደረገላቸውና መኪና ሊገዛላቸው መወሰኑ ታውቋል፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ ሃገር የህክምና ወጪያቸውን ለመሸፈንም ወስኗል፡፡ ለአዲሱ የኦህዴድ አመራርና ለኢትዮጵያ ህዝብም ምስጋናቸውን አቅርበዋል - ዶ/ር ነጋሶ፡፡  የፌደራል መንግስቱ መብቶቼንና ጥቅማ ጥቅሞቼን እንዲያከብርልኝ መጠየቄን እቀጥላለሁ የሚሉት  ዶ/ር ነጋሶ፤ ላለፉት 13 ዓመታት መንግስት ጥቅማ ጥቅሞቻቸውንና መብቶቻቸውን እንዲያከብርላቸው ያደረጉትን ትግልና ውጣ ውረድ ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንዲህ አውግተውታል፡፡

    እስቲ የቀረብዎትን  መብቶችና  ጥቅማ ጥቅሞች ለማስከበር ያደረጉትን  ጥረት ይንገሩኝ?
እንግዲህ እኔ ላለፉት 13 ዓመታት እንደተቀጣሁ ነው የኖርኩት፡፡ በ1997 ምርጫ መሳተፌን ተከትሎ፣ በወቅቱ የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባኤ የነበሩት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመና የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ዳዊት ዮሐንስ ውሳኔ ነበር፣በህግ የሚገባኝን ጥቅም ያጣሁት፡፡ በምርጫው በግሌ ነበር የተሳተፍኩት፡፡ በወቅቱ አዋጅ 255/94 አንቀፅ 13ን ጥሰሃል አሉኝ፡፡ እኔ ደግሞ “ማንንም አልወገንኩም፣ የማንም ፓርቲ አባል አይደለሁም፣ በግሌ ነው የተወዳደርኩት” ብዬ ብከራከርም አልተቀበሉኝም። ከዚያም ወደ ፍ/ቤት አመራሁ፡፡ ፍ/ቤትም፣ ”ምርጫ ውስጥ በመግባቱ ማንንም አልወገነም፤ ስለዚህ ህግ አልጣሰም፤ ሆኖም ፓርላማ ሲገባ ወገንተኛ ይሆናል” አለ፡፡ እኔም፤ “ገና ፓርላማው ሳይከፈት እንዲሁም እኔ መግባቴን ሳልወስን እንዴት ገና ለገና በይሆናል ይፈረዳል” አልኩ፡፡ “ፓርላማም ከገባሁ የማንም ወገንተኛ ሳልሆን ለህሊናና ለህገ መንግስቱ እንዲሁም ለህዝቡና ለሀገሪቱ ነው ወገንተኝነቴ፤” የሚል የመከራከሪያ ሃሳብ ይዤ፣ ወደ ከፍተኛ ፍ/ቤት ሄድኩ፡፡ በወቅቱ አቶ ፊሊጶስ የተባሉ ዳኛ የሚመሩት ችሎት ጉዳዬን ተቀብሎ፣ ዓለማቀፍ ስምምነቶችን፣ ህገ መንግስቱንና ህጉን በመጥቀስ ለኔ ፈረዱልኝ፡፡ በኋላም እነሱ ለጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ጠየቁ፤ ጠቅላይ ፍ/ቤቱም “እነሱ ናቸው ትክክል” ብሎ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ያስተላለፈውን ውሳኔ አፀደቀ፡፡ እኔም፤ ይሄ የህግ ትርጉም ችግር አለበት ብዬ በድጋሚ ለሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ አልኩ፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱም ጉዳዩን በደንብ ሳይመረምር፣ “ጉዳዩ ሊታይ የሚችል አይደለም፤ ፋይሉ ተዘግቷል” በሚል አቤቱታዬን ሳይቀበለው ቀረ፡፡
በወቅቱ የተከለከሏቸው ጥቅማ ጥቅሞች ምን ምን ነበሩ?
አንደኛ ጠባቂ የለኝም፡፡ ሁለተኛ፣ ሁለት መኪናዎች ነበሩ፤ ወዲያው ተወሰዱ፡፡ ቤት ውስጥ ሶስት ሰራተኛና አንድ አትክልተኛ እንዲሁም የነሱ ኃላፊ የነበረች፤ አንዲት ሴትም ነበረች፤ አምስቱንም በድንገት ያለ ማስጠንቀቂያ “ኮንትራታችሁ ተቋርጧልና ስራ ፈልጉ” ብለው አሰናበቷቸው፡፡
 በወቅቱ በወር ይሰጠኝ የነበረው ገንዘብ 5 ሺህ ብር ለኪስ፣ ተጨማሪ 5 ሺህ ብር ደግሞ ለቤት ውስጥ ወጪዎች የሚውል ነበር፤ ያንን ሙሉ ለሙሉ አስቀሩብኝ፤ ወዲያውም ከነበርኩበት ቤት እቃውን አስረክቤ እንድወጣ አዘዙኝ፡፡ እኔም ፓርላማ ስለገባሁ፣ ከፓርላማው የማገኘው ደሞዝ ነበር፡፡ ፓርላማው ከመዘጋቱ ሁለት ዓመት በፊት ደግሞ ከ”አንድነት” ፓርቲ ትንሽ ገንዘብ ይሰጠኝ ነበር፤ በዚያ እየኖርኩ ቆየሁና፣ ፓርላማው ሲዘጋ ጡረታዬ ይከበርልኝ ብዬ ጠየቅሁ፡፡ ለ18 ዓመት ያገለገልኩበትና በፓርላማው በወር 3 ሺህ ብር እየተከፈለኝ ያገለገልኩበት ጡረታ ይከበርልኝ ነበር ያልኩት፡፡ ነገር ግን የ6 ዓመት የፕሬዚዳንትነት ጊዜዬን ትተው፣ በፓርላማ የነበረኝን ብቻ አስበው ጡረታዬን አፀደቁልኝ፡፡ የፕሬዚዳንትነት ጊዜዬን ያልገመቱት፣ መደበኛ ደሞዝ ስላልነበረኝ መሆኑን ነው የነገሩኝ፡፡ እስከ ባለፈው ዓመት ድረስ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሃምሳ (1750) ብር ነበር የማገኘው፤ በኋላ ትንሽ ተጨምሮልኝ እስካሁን ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ዘጠና አምስት (2295) ብር ይከፈለኝ ነበር፡፡  እንግዲህ የኔ ደሞዝ ምንም አይደለችም፤ ዋናው የገቢ ምንጫችን ባለቤቴ የምታገኘው ነበር። ባለቤቴ አዋላጅ ነርስ ነች፤ በሌላ በኩል በጀርመን የአይን መነፅር ድርጅት ስራ አስኪያጅ ነች፡፡ በዚህ ገቢ ነበር የምንኖረው፡፡ በቤታችን ውስጥ አንድ የሚረዳኝ ተላላኪ ልጅ አለ፡፡ አንድ ምግብ የምታዘጋጅልን ሴት አለች፡፡ ሁለት የዘመድ ልጆች እኔ ጋ ይኖራሉ፡፡ እነዚህን በምናገኘው ገቢ ነበር የምናስተዳድረው፡፡
 በህክምና በኩል ድሮ ጦር ኃይሎች በነፃ እታከም ነበር፡፡ አሁን የተደራረበ የጤና ችግር አለብኝ፡፡ ጠዋት 3 ክኒን፣ ማታ 5 ክኒን እወስዳለሁ፤ በዚያ ላይ ኢንሱሊን እወጋለሁ፡፡ መድኃኒቶቹ በጣም ውድ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ኤክስፎርጅ የምትባል የደም ጥራት መድኃኒት አለች፡፡ በቅርቡ ልጄ ከጀርመን ስትመጣ፣ 94 ፍሬ ይዛልኝ መጣች፡፡ ይሄ መድኃኒት ዋጋው 140 ዩሮ ነው፡፡ ወደ 7 ሺህ ብር ገደማ ማለት ነው፡፡
ህመምዎ ምንድን ነው?
የልብ በሽታ አለብኝ፣ የደም ግፊት፣ የስኳር በሽታ፣ የደም ስር መዘጋጋት ህመም አለብኝ፡፡  ለዚህ ህመም “ስቴንት” በሰውነቴ ገብቶልኛል፡፡ እንደዚህ ነው እየኖርኩ ያለሁት፡፡
ከፍ/ቤቱ ውሳኔ በኋላ ተስፋ ቆርጠው ተቀመጡ---?
አይደለም፡፡ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ ያን ጊዜ ከዳዊት ዮሐንስ ጋር ቢፈርዱብኝም፣ እኔ ነኝ ወደ ኦህዴድ የመለመልኳቸው፡፡ ዶ/ር ሙላቱን፣ የልማት ሚኒስትር እንዲሁም ም/ሚኒስትር ሆነው እንዲታጩ ያደረግነው እኛ ነን፡፡ በኋላም በአምባሳደርነት ሰርተዋል፡፡ ሰውየው በትምህርት ብቃት አላቸው፡፡ ቻይና አምባሳደር በሆኑበት ጊዜም ከቻይና መፅሐፍ ያመጡልኝ ነበር፡፡ በተለይ በልማታዊ ዲፕሎማሲያዊ ዘርፍ ብቃት አላቸው፣ ሊያገለግሉ ይችላሉ ብዬ ለአንድ ጋዜጣ ተናግሬ ነበር፡፡ በኋላ አንድ የቻይና ጋዜጣ ይሄን ተርጉሞ በማቅረብ፣ የቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ፣ ስለ ዶ/ር ሙላቱ መስክሯል፤ የሚል ሀተታ አስነበበ፡፡ ይሄን ያዩት ዶ/ር ሙላቱ፣ በድጋሚ ከኔ ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ የተከለከልኩት ጥቅማ ጥቅም እንዲመለስልኝ የሚጠይቅ ደብዳቤ እንድፅፍ አበረታቱኝ፡፡ ይሄ የሆነው ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት ነው፡፡ እኔም ይሄን ምክር ተቀብዬ፣ ለአፈ ጉባኤ አባዱላና ለፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ካሳ ተ/ብርሃን እንዲሁም በግልባጭ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያምና ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ፃፍኩ፡፡ በደብዳቤው ላይ ይቅርታ አልጠየኩም ነበር፡፡ በኋላ የፕሬዚዳንቱ ረዳት አቶ አሰፋ ከሴቶ፣ጥሩ ደብዳቤ ነው የፃፍከው፤ ግን የረሳኸው ነገር አለ ፤ “ይቅርታ አድርጉልኝ” የሚል ቃል ቀርታለች አሉኝ፡፡ እኔም “ይቅርታ መጠየቅ ያለባችሁ እናንተ ናችሁ፤ እኔ አይደለሁም”  አልኩ፡፡ እሳቸውም፤ “ከፕሬዚዳንቱ ጋር እማከርበታለሁ” አሉኝ፡፡ በኋላ ያለፈው አልፏል ብዬ፣ ይቅርታ ሳልጠይቅ ድጋሚ ደብዳቤ ፃፍኩ፡፡ እሱን በበጎ ተቀበሉት፡፡
ሁለቱ አፈ ጉባኤዎች ከፕሬዚዳንቱ ጋር ተመካክረው፣ አቶ አባዱላ ጉዳዩን ለጠ/ሚኒስትሩ እንዲያማክሩ ይወስናሉ፤ በኋላ ምክትል ጠ/ሚኒስትር ለነበሩት ወ/ሮ አስቴር ማሞ፣ ጉዳዩን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያስታውሱልኝ ነገርኳቸው፡፡ ተነግሯቸው ይመስለኛል፣ ጠ/ሚኒስትሩ ቀጠሮ ያዙልኝና ሄጄ አነጋገርኳቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም “ጉዳዩ መታየት አለበት፤ግን የህግ ውስብስብነት ስላለው ከባልደረቦቼ ጋር መነጋገር አለብኝ” አሉኝ፡፡ በኋላም “እንዲሁ ለኑሮ የሚጠቅምህን መኪናም ገንዘብም እንሰጥሀለን፤ በዚሁ እንጨርስ” አሉኝ፤ ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ እኔም፤ “ጉዳዩ የህግ ጉዳይ ነው፤ እንዲሁ የሚያልቅ አይደለም” የሚል ምላሽ ሰጠኋቸው፡፡ “በህጋዊ መንገድ መብቴ ይከበር፤ በጎን የሚሰጠኝ ገንዘብ ከየት መጣ የሚል ጥያቄ ያስነሳብኛል፤ ስለዚህ ህጋዊ ምላሽ ነው የምፈልገው” አልኳቸው፡፡ እሳቸውም “ከስራ ባልደረቦቼ ጋር ተመካክሬ መልስ እሰጣለሁ” አሉኝ፡፡ ግን ለ1 ዓመት ብጠብቅም መልስ ጠፋ፡፡
በድጋሚ ለፕሬዚዳንቱ ደወልኩላቸው። ፕሬዚዳንቱም በድጋሚ በግልባጭ ሳይሆን ለአራታችንም ደብዳቤ ፃፍ አሉኝ፡፡ አሁንም መልስ የለም፡፡ በኋላ ቀጠሮ ይዤ ፕሬዚዳንቱ ጋ ሄድኩ። ፕሬዚዳንቱም በህግ ባለሙያዎች ደብዳቤ አፅፍ አሉኝ፡፡ በወቅቱ ገንዘብ የለኝም ነበር፤ ጠበቆችም የሚተባበሩኝ አጣሁ፤ በራሴ ዝም ብዬ ዘጠኝ ገፅ ደብዳቤ ፃፍኩ፡፡ ደብዳቤውን ለፓርላማው ነው የፃፍኩት፡፡ ከዚህ ደብዳቤ ጎን ለጎን፣ ለአቶ አባዱላ ደብዳቤውን ለምክር ቤት አባላት እንዲያቀርቡልኝ የሚጠይቅ ማስታወሻ ፃፍኩ፡፡ ግልባጩንም ለአቶ አስመላሽ፣ ለምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለና ለህግ ቋሚ ኮሚቴ መጋቢት 2009 ዓ.ም  ላኩኝ፡፡ ግን ለዚህም እስካሁን መልስ አላገኘሁም፡፡  
ጥያቄውን ለኦህዴድ አቅርበው ነበር?
ከአንዳንድ የኦህዴድ አባሎች ዘንድ አንዳንድ ጉዳዮች እሰማ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ በአንድ ወቅት ለዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ጉዳዩን እንዳስረዳ መክረውኝ ነበር፡፡ እኔም ጉዳዩን በቀጥታ ለአቶ ወርቅነህ አስረድቼ ነበር፡፡ እሳቸውም “እኛም እያሰብን ነበር፤ ግፊት እናደርጋለን፤ ግን ከአቶ ለማ ጋር ተገናኝተህ ብትነጋገር ይሻላል” ብለው መከሩኝ። ልክ የተመረጡ አካባቢ ነበር፤ አቶ ለማን ሄጄ አነጋገርኳቸው፤ “ግዴለም ጉዳዩን እንከታተላለን” አሉኝ፡፡ በኋላም ከወር በፊት ኦዳ ባስ አክሲዮን ማህበር አውቶብሶችን ሲያስመርቅ፣ “የቱምሳ” አክሲዮን ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ አበራ ኃይሉ ጋበዙኝ፡፡ አቶ አበራ ኃይሉ የድርጅቱ አባል በነበረ ጊዜ እኔ ነበርኩ ጠርናፊያቸው፡፡ ከድርጅቱ ከወጣሁ በኋላም ግንኙነታችን አልተቋረጠም፡፡ የቤቴ አጥር ሲፈርስ እንኳን ያሰራልኝ እሱ ነበር፡፡ “መኪና እልክልሃለሁ፤ ፕሮግራሙ ላይ እንዳትቀር” ብሎ ጠየቀኝ፡፡ እሺ ብዬ ሄድኩ፡፡ ፕሮቶኮሎች፣ ከአባዱላና ከአቶ ለማ አጠገብ ነበር ያስቀመጡኝ፤ ያ ደግሞ በሚዲያ ሲታይ በህዝቡ ዘንድ ጥሩ ነገር ፈጥሯል፡፡
ከ3 ሳምንት በፊት ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ቢሮው ጠርቶኝ፣ ስለ ጉዳዩ እንድነግረው ጠየቀኝ። ነገርኩት፡፡ እሱም “ለስራ አስፈፃሚ አቀርባለሁ፤ መልሱን በአንድ ሳምንት ውስጥ እነግርሃለሁ” አለኝ። በኋላም ወደ ቢሮ ጠራኝና፣ ስራ አስፈፃሚው በሙሉ ሊደግፈኝ ፍቃደኛ እንደሆነ ነገረኝ፡፡ “ትንሽ ገንዘብም እንሰጥሃለን፣ መኪናም እንዲገዛልህ ወስነናል፣ መኪናው በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ይገዛልሃል፣ ለጤንነትህ ደግሞ በሀገር ውስጥም በውጭም እንድትታከም ሁኔታዎችን እናመቻቻለን” አለኝ፡፡ እሱንም አቶ ለማንም በሞባይል ሜሴጅ አመሰገንኳቸው፡፡ እንደውም “እኔ ብቻ ሳልሆን ለ13 ዓመት ከኔ ጋር ትቸገር የነበረች ባለቤቴም ተደስታለች” ብዬ ላኩላቸው፡፡ አቶ ለማ፤ “ይሄ ያደረግነው ትንሽ ነው” የሚል ምላሽ ነው የሰጠኝ፡፡
እሁድ ማታ አንድ ሰው ደውሎልኝ፣ ፌስቡክ ላይ ጉዳዩ ወጥቷል አለኝ፡፡ በማግስቱ ሰዎች፤ “የእንኳን ደስ ያለህ” መልዕክት ሲልኩልኝ ነው የዋሉት፡፡ ብዙዎች ተደስተዋል፡፡ እኔም በኦህዴድ ውሳኔ ተደስቻለሁ፤ አዲሱ አመራር ጉዳዩን አስቦበት ስለወሰነ ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ እስካሁን ከጎኔ የቆመውን የኢትዮጵያ ህዝብንም አመሰግናለሁ። በኦህዴድ ውሳኔ ደስተኛ ብሆንም አሁንም የፌደራል መንግስቱ መብቶቼንና ጥቅማ ጥቅሞቼን እንዲያከብርልኝ መጠየቄን እቀጥላለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ አዲሱን የኦህዴድ አመራር አመሰግናለሁ፡፡ ሚዲያዎችንም አመሰግናለሁ፡፡ ሁሉም ከጎኔ ነበሩ፡፡    

Read 3500 times