Print this page
Saturday, 10 February 2018 10:35

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለኦህዴድ ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ ሰጡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)

    በ10 ቀናት የስብሰባ ማጠናቀቂያው ላይ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለሚገኙ የኦሮሞ ተቃዋሚ ኃይሎች የአብረን እንስራ ጥሪ በአቋም መግለጫው ላቀረበው ኦህዴድ፤ በዶ/ር ሌንጮ ለታ የሚመራውን የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ጨምሮ፣ የሀገር ውስጥ ፓርቲዎች አዎንታዊ ምላሽ እንደሰጡ ታውቋል፡፡
የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ በ10 ቀናት ስብሰባው የደረሰበትን ዝርዝር አቋም ባሳወቀበት መግለጫው ካነሳቸው ጉዳዮች መካከል በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ለሚገኙ የተቃዋሚ ኃይሎች ያቀረበው የአብረን እንስራ ጥሪ ተጠቃሽ ነው፡፡ “የሀገሪቱን ህልውና መታደግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው” ያለው የኦህዴድ መግለጫ፤ የኦሮሞ ህዝብ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመተባበር ሃገሪቱ የማቅናት ሚናውን ይወጣል ብሏል፡፡
እስካሁን በሃገሪቱ ህዝቦች መካከል ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል አለመኖሩን ማረጋገጡን የጠቆመው ኦህዴድ፤ በዚህ ጉዳይና አሣታፊ የፖለቲካ ስርአትን በመገንባት ረገድ የቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ጠቁሟል - በመግለጫው፡፡ ፍርድ ቤቶችን፣ አቃቤ ህግን፣ ፖሊስን፣ የወረዳና የቀበሌ መዋቅሮችን መልሶ እንደሚያደራጅም ኦህዴድ ጠቁሟል፡፡
 በብዝሃነት ለተገነባችው ሃገራችን ኢትዮጵያ፣ ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ነው ያለው ኦህዴድ፤ የሃሳብ ልዩነቶችን ማጥፋት የማይቻል ስለሆነ ሁልጊዜ የውይይትና የክርክር አውድን ማስፋት አስፈላጊ ነው ብሏል፡፡ ከሃይል የፀዳ፣ በውይይትና በክርክር የሚያምን፣ ይበልጥ ለሃገር የሚበጅ ሃሳብ የሚፈልቅበትን የውይይት ባህል ማዳበር ያስፈልጋል ያለው ኦህዴድ፤ “የሃገራችንን መፃኢ እድል በጋራ ማበጀት እንችል ዘንድ ተቀራርበን እንስራ” ሲል ለተቃዋሚዎች ጥሪ አቅርቧል፡፡
ይህን ጥሪ ተከትሎ ፈጥኖ ምላሽ የሰጠው ከ5 ዓመት በፊት በውጭ ሃገር የተመሠረተውና በአንጋፋው የቀድሞ የኦነግ አመራር አቶ ሌንጮ ለታ የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራሲዊ ግንባር (ኦዴግ)፤ ጥሪውን በአዎንታ እንቀበለዋለን፣ ሳንውል ሳናድር አብረናችሁ ለመስራት ዝግጁ ነን ብሏል፡፡
ድርጅቱ በመግለጫው፣ከኦህዴድ የቀረበው ጥሪ፣ሀገሪቱን ለማዳን ወቅታዊና ጠቃሚ መሆኑን ጠቅሶ፣ አብሮ መስራቱ ለኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ማበብና መጎብለት እጅግ ጠቃሚ ነው ብሏል፡፡ የኦህዴድ የአብረን እንስራ ጥሪ፣ የብዙ ኢትዮጵያውያንን የዘመናት የትብብርና የአብሮነት ፍላጎት የሚያሳካ፣ በጎ ሃሳብ መሆኑንም ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሰውና በዶ/ር መረራ ጉዲና የሚመራው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በበኩሉ፤ የአብረን እንስራ ጥሪውን አንደሚቀበል ነገር ግን ይህ ጥሪ ዋስትና እንዲኖረው፣ አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሌሎች የፓርቲው አመራሮችን ከእስር መፍታት ያስፈልጋል ብሏል፡፡
ሌላው የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅት የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግረስ ሊቀ መንበር አቶ ቶሎሳ ተስፋዬ፤ ኦህዴድ በስብሰባው የወሰናቸው ውሳኔዎች ጠንካራና ጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የአብረን እንስራ ጥያቄው እኛም ስናቀርበው የነበረ በመሆኑ፣ ያለ ማቅማማት እንቀበለዋለን ብለዋል፡፡
እስከ ዛሬ ኦህዴድ አሳሪ፣ እኛ ታሳሪ ሆነን ስንንቀሳቀስ ነው የሚታወቀው ያሉት አቶ ቶሎሳ፤ይሄ አካሄድ የሚቀር ከሆነ፣ አብረን  መስራት በምንችልበት ጉዳይ ላይ አብረን እንሰራለን ብለዋል፡፡ የፌደራሊዝም ስርአቱም እውነተኛ እንዲሆን ፅኑ ፍላጎት አለን ያሉት አቶ ቶሎሳ፤ኦህዴድ በዚህ ላይ ጠንካራ አቋም እንዲይዝ ፓርቲያቸው እንደሚፈልግ አስታውቀዋል፡፡   
የኦህዴድ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሌላ በኩል፣የቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ የተቋረጠባቸውን ጥቅማ ጥቅሞች ከግምት ውስጥ በማስገባት፣የህክምና ወጪያቸውን ለመሸፈንና መኪና ሊገዛላቸው የወሰነ  ሲሆን ይህ ውሳኔም በተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍን አግኝቷል፡፡  
ዶ/ር ነጋሶ በሚያምኑበት መንገድ ለሀገር ያገለገሉ ናቸው ያሉት የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ፤ የተገፈፉትን ህጋዊ መብታቸውን መልሰው ማግኘት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ አቶ ቶሎሳ ተስፋዬ በበኩላቸው፤”ዶ/ር ነጋሶ በፖለቲካ ሃሳብ ልዩነታቸው የተነሳ የዚህን ያህል መስዋዕትነት መክፈል አይገባቸውም ነበር፤ የኦህዴድ ውሳኔ ከተቆርቋሪነት የመነጨ መሆኑ መልካም ነው” ብለዋል፡፡  

Read 7536 times