Sunday, 11 February 2018 00:00

እነ ኢ/ር ይልቃል፤ “የኢትዮጵያውያን ሀገር አቀፍ ንቅናቄ” የተሰኘ አዲስ ፓርቲ ሊያቋቁሙ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

    የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነትና ባልደረቦቻቸው፣ ከአዲሱ የፓርቲው አመራር ጋር የተጀመረው እርቅ በመሰናከሉ፣ “የኢትዮጵያውያን ሀገር አቀፍ ንቅናቄ” የተሰኘ አዲስ ፓርቲ ለማቋቋም እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ለአዲስ አድማስ አስታወቁ፡፡
በሰማያዊ ፓርቲ የቀድሞ አመራሮችና በአዲሱ የእነ አቶ የሸዋስ አሰፋ አመራር መካከል ያለውን ችግር በእርቅ ለመፍታት ከስምምነት ላይ ተደርሶ እንደነበር ያወሱት ኢ/ር ይልቃል፤ በተፈፃሚነት ሂደቱ ላይ ከእነ የሸዋስ አሰፋ በኩል ዳተኝነት በመታየቱ፣ ፊታችንን ወደ አዲስ አማራጭ አዙረናል ብለዋል፡፡
የሁለቱን ወገኖች የእርቅ ሂደት ሲያከናውን የነበረው የሽማግሌዎች ቡድን፣ ጥር 28 ቀን 2010 ዓ.ም ለአቶ የሸዋስ አሰፋ በፃፈው ደብዳቤ፣ ስምምነት የተደረሰበት እርቅ እንዲፈፀም ማሳሰቡ ታውቋል፡፡
ሆኖም ጠቅላላ ጉባኤ በድጋሚ ተጠርቶ፣ችግሩ ይፈታ የሚለው የእርቅ ስምምነት፣ በእነ አቶ የሸዋስ ምክንያት መጓተቱን የጠቀሰው የሽምግልና ቡድኑ፤ከዚህ በኋላ ለተፈፃሚነቱ እነ አቶ የሸዋስ የማይንቀሳቀሱ ከሆነ ሂደቱን ሲከታተል ለነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ የተፈፀመውን አፍራሽ ድርጊት እንደሚያጋልጥ አሳስቧል፡፡
የተጀመረው የእርቅ ሂደት ተስፋ አልሰጠንም ያሉት ኢ/ር ይልቃል ጌትነትና ባልደረቦቻቸው በበኩላቸው፤ ሰባት የኮሚቴ አባላትን በመምረጥ፣ አዲስ የሥነ መንግስት ማህበር (ፓርቲ) ለመመስረት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡ አዲስ የሚመሰረተው ፓርቲ በስፋት ወጣቶችንና ሴቶችን ያሳትፋል ያሉት ኢ/ር ይልቃል፤ ስያሜውም “የኢትዮጵያውያን ሃገር አቀፍ ንቅንቄ” (Ethiopian National Movement) እንደሚሰኝ አስታውቀዋል፡፡
ይህን ማህበረ ፖለቲካ ለማቋቋምም፣ የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባላት የነበሩት አቶ ስለሺ ፈይሳ፣ ወ/ሮ መዓዛ መሃመድ፣ አቶ አዲሱ ጌታነህ፣ ወ/ት ወይንሸት ሞላ፣ ወ/ት ምዕራፍ ይመር፣ አቶ ቴዎድሮስ አስፋውና አቶ ደምሳሽ በኃይሉ በአስተባባሪ ኮሚቴነት መመረጣቸው ተጠቁሟል፡፡
የሚቋቋመው ፓርቲ በአስተሳሰብ ደረጃ በሀገር ግንባታ ሂደት ወሳኝ ሚና ባላቸው ነፃነት፣ እኩልነትና ወገናዊነት በሚሉ መሰረታዊ የዜግነትና የሃገር ግንባታ እሴቶች ላይ አተኩሮ ይንቀሳቀሳል ተብሏል፡፡ አስፈላጊው ቅድመ ሂደት እንደተጠናቀቀ፣ በአጭር ቀናት ውስጥ የፓርቲው መስራች ጉባኤ እንደሚካሄድም ኢ/ር ይልቃል አስታውቀዋል፡፡

Read 6895 times