Monday, 05 February 2018 00:00

18ኛው የዱባይ፤ 11ኛው የቶኪዮ፤ 122ኛው የቦስተንና 38ኛው የለንደን ማራቶኖች እና 11ኛው የማራቶኖች ሊግ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

  · በዱባይ ማራቶን የተመዘገበው ውጤት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ለውጥ መኖሩን ያመለክታል
    · መሠረት በቶኪዮ ማራቶን የመጀመሪያ ማራቶኗን ትሮጣለች
    · የቦስተን ማራቶን የሚካሄደው ለ122ኛ ጊዜ ነው
    · የኢትዮጵያን ማራቶን ሪከርድ የያዙት ጥሩነሽና ቀነኒሳ በለንደን ማራቶን ለዓለም ሪከርድ ይፎካከራሉ

   ከሳምንት በፊት በተካሄደው 18ኛው የዱባይ ማራቶን ላይ ኢትዮጵያውያን ማራቶኒስቶች በሁለቱም ፆታዎች ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ለውጥ መኖሩን ያመለክታል፡፡ የማራቶን ውጤቶች በፈጣን ሰዓቶች መጠናከራቸው፤ የማራቶን ስልጠናዎች ማደጋቸውና የአትሌቶች ማኔጅመንት በተሻለ ግንኙነት መዳበሩ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል በሚቀጥሉት 6 ወራት በመላው ዓለም ከ20 በላይ ትልልቅ የማራቶን ውድድሮች ሲካሄዱ በርካታ የኢትዮጵያ ማራቶኒስቶች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ በተለይ በ2017/18 የማራቶኖች ሊግ ላይ ከሚካሄዱ 6 ትልልቅ ማራቶኖች መካከል ሶስቱ በቶኪዮ፤ ቦስተንና ለንደን ከተሞች የሚካሄዱት ሲሆኑ ከፍተኛ ፉክክርና ድምቀት እንደሚኖራቸው ተጠብቋል። በማራቶኖች ሊግ የ2017/18 ሻምፒዮን ሆኖ ለመጨረስ በትልልቅ አትሌቶች የሚኖረው ፉክክር እንዲሁም የዓለም ማራቶን ሪከርዶችን ለማሻሻል በተያዙ እቅዶች ነው፡፡ ከ3 ሳምንታት በኋላ በጃፓን የቶኪዮ ማራቶን ለ11ኛ ጊዜ፤ ከ6 ሳምንታት በኋላ በአሜሪካ የቦስተን ማራቶን ለ122ኛ ጊዜ እንዲሁም ከ7 ሳምንታት በኋላ ደግሞ በእንግሊዝ የለንደን ማራቶን ለ39ኛ ጊዜ ይካሄዳሉ፡፡ ከማራቶኖች ሊግ ግዙፍ ማራቶኖች ባሻገር በጣሊያን የሮም ማራቶን፤ በፈረንሳይ የአንሴ ሃይቅ ማራቶን፤በቻይና የግሬት ዎል ማራቶን ፤ በብራዚል የሪዮ ዲጄነሮ ማራቶን ፤ በኖርዌይ የትሮምሶ ማራቶንም  ይደረጋሉ፡፡
በ18ኛው የዱባይ ማራቶን በወንዶች ከ1-10 በሴቶች ከ1-7  
ባለፈው ሰሞን በዩናይትድ ኤምሬትስ በተካሄደው 18ኛው የዱባይ ማራቶን ላይ በሴቶች 16 በወንዶች 15 የኢትዮጵያ ማራቶኒስቶች ተሳትፈው፤ በሁለቱም ፆታዎች የውጤት የበላይነታቸው የቀጠለ ሲሆን በወንዶች ምድብ ሞሰነት ገረመው እንዲሁም በሴቶች ምድብ ሮዛ ደረጀ የቦታው ሪከርዶችን በማስመዝገብ አሸንፈዋል፡፡ ሞሰነት ገረመው በ2:04:00  እንዲሁም  ሮዛ ደረጀ በ2:19:17 ጊዜያቸው አዳዲስ የዱባይ ማራቶን ክብረወሰኖችን  ይዘዋል፡፡ የኢትዮጵያ ማራቶኒስቶች በወንዶች እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ  በሴቶች ደግሞ እስከ ሰባተኛ ደረጃ ያገኙ ሲሆን፤ በወንዶች ሞሰነት ለ9ኛ ጊዜ በሴቶች ሮዛ ለ14ኛ ጊዜ የኢትዮጵያን አሸናፊነት አሳክተዋል፡፡  በዱባይ ማራቶን ላይ አዳዲስና ወጣት አትሌቶች መውጣታቸው እንዲሁም ፈጣን የማራቶን ሰዓቶች እየበዙ መምጣታቸው በማራቶን ስልጠናዎችና የአትሌቶች ማኔጅመንት ኢትዮጵያ ውስጥ አሰራሮች እየተሻሻሉ መምጣታቸውን ያመለክታል፡፡
የ25 ዓመቱ  ወጣት ማራቶኒስት ሞሰነት ገረመው ዱባይ ላይ የሮጠው ሶስተኛ ማራቶኑን ሲሆን  በቻይናው የዣይናሜን ማራቶን  እንዲሁም በጀርመኑ የበርሊን  ማራቶን ላይ በተመሳሳይ ሁለተኛ ደረጃዎችን ካገኘ በኋላ ያመዘገበው የመጀመርያ የማራቶን ድል ነው፡፡ በዱባይ ማራቶን ያሸነፈበትና የቦታ ሪከርድ ሆኖ የተመዘገበው ሰዓቱ፤ በማራቶን የምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች ላይ በ10ኛ ደረጃ የተቀመጠ ሲሆን፤ በ2014 እኤአ ላይ በኬንያዊው ዴኒስ ኬሜቶ ከተመዘገበው የዓለም ሪከርድ በ63 ሰከንድ ርቀት ላይ አስቀምጦታል፡፡ ከሞሰነት ባሻገር ሌሎቹ 7 የኢትዮጵያ ወንድ ማራቶኒስቶች ከ2 ሰዓት 05 ደቂቃዎች በታች መግባታቸውም አስደንቋል፡፡
በሴቶች ምድብ 5ኛ የማራቶን ውድድሯን የዱባይ ማራቶንን በመሮጥ ያሸነፈችው ሮዛ ደረጀ ከዓመት በፊት በተመሳሳይ ማራቶን ሁለተኛ ደረጃ፤ ከዚያም በፊት በቪዬና ማራቶን 3ኛ ደረጃ፤ በሻንጋይ ማራቶን በ2016 እና በ2017 እኤአ ላይ አከታትላ በማሸነፍ ልምድ  ነበራት፡፡ ሮዛ በዱባይ ማራቶን አሸናፊነት ያስመዘገበችው ጊዜ በምንግዜም ፈጣን ሰዓት ደረጃ ላይ 7ኛ ስፍራ ላይ ሲያስቀመጣት ሲሆን ሌሎቹ የኢትዮጵያ ማራቶኒስቶች እስከ 4ኛ ደረጃ ሲያገኙ ከ2 ሰዓት 20 ደቂቃዎች በታች መግባታቸው ታውቋል፡፡
በ11ኛው ቶኪዮ ማራቶን
ለአሸናፊዎች በሁለቱም ፆታዎች በነፍስ ወከፍ 108 ሺ ዶላር (በአጠቃላይ 400 ሺ ዶላር)
የተመልካች ብዛት 1.6 ሚሊየን
የፈጣን ሰዓትና የሪከርድ ቦነስ 677 ሺ ዶላር (ለዓለም ሪከርድ 267 ሺ ዶላር ለቶኪዮ ማራቶን ሪከርድ 26,725 ዶላር)
የጃፓኑ ቶኪዮ ማራቶን ለ11ኛ ጊዜ የካቲት 18 ላይ የሚካሄድ ሲሆን በሴቶች ምድብ ኢትዮጵያዊቷ የ5ሺ ሜትር የምንግዜም ውጤታማ አትሌት መሠረት ደፋር ለመጀመርያ ጊዜ  በማራቶን ውድድር መሳተፏ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ በወንዶች ምድብ ደግሞ ያለፈውን ዓመት አሸንፎ የነበረው ኬንያዊ ዊልሰን ኪፕሰንግ የሚጠበቅ ሲሆን የዓለም ማራቶን ሪከርድን በድጋሚ ለመስበር ትኩረት ማድረጉን አስታውቋል፡፡ በ11ኛው የቶኪዮ ማራቶን ላይ ከመሠረት ደፋር ጋር የሚሮጡት ሌሎቹ የኢትዮጵያ ሴት ማራቶኒስቶች ሩቲ አጋ፤ ብርሃኔ ዲባባ እና ሹሬ ደምሴ ሲሆኑ ኬንያዊው የቀድሞ ሪከርድ ባለቤት ዊልሰን ኪፕሳንግን በመፎካከር የሚጠበቁት የኢትዮጵያ ወንድ ማራቶኒስቶች ተስፋዬ አበራ፤ ፀጋዬ መኮንን እና ፈይሳ ሌሊሳ ናቸው፡፡ ሌሎቹ የኬንያዎቹ ማራቶኒስቶች ዲክሰን ቹምባ፣ ቪሴንት ኪፕሩቶ፣ ጌዲዮን ኪፕኬተርና አምሶ ኪፕሩቶ ናቸው፡፡
አትሌት መሰረት ደፋር በወሊድና በጉዳት ምክንያት  ከ2014 እኤአ ወዲህ ብዙ ውድድር አላደረገችም፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ የሮጠችው በ2017 እኤአ በአሜሪካ ኬፕ ኤልዛቤት የ10 ኪሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ነበር፡፡ ከዚያ በፊት በ2015 እኤአ በሆላንድ፤ ሄረንበርግ   የ15 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በመሳተፍ ማሸነፏም ይታወሳል። በሁለት የግማሽ ማራቶን ውድድሮች በ2013 እኤአ ላይ ተወዳድራ ያሸነፈች ሲሆን፤ በአሜሪካ ኒውኦርሊዬንስ በ1:07:25 እንዲሁም በእንግሊዝ ሳውዝ ሺልድስ በ1:06:09 የሆኑ ሰዓቶች አሸንፋለች፡፡ አትሌት መሠረት ማራቶንን ለመጀመርያ ጊዜ ስትሮጥ ከ15 ዓመታት በላይ በፓውላ ራድክሊፍ ተይዞ የቆየውን የዓለም ሪከርድ እንደምታሻሽል የጠበቀ ባይኖርም፤ ጥሩና ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ አጀማመሯን ልታሳምር እንደምትችል ይገመታል፡፡ አትሌት መሰረት ደፋር  በትራክ 5ሺ ሜትር፤ ቤት ውስጥ አትሌቲክስ 3ሺ እና 5ሺ ሜትር እንዲሁም በሌሎች የጎዳና ላይ ሩጫዎች ከ15 ዓመታት በላይ ከፍተኛ ልምድ እንዳላት ይታወቃል፡፡
በ122ኛው የቦስተን ማራቶን
ለአሸናፊዎች በሁለቱም ፆታዎች በነፍስ ወከፍ 150 ሺ ዶላር (በአጠቃላይ 806 ሺ ዶላር)
የተመልካች ብዛት ከ500 ሺ በላይ
የፈጣን ሰዓትና የሪከርድ ቦነስ 150 ሺ ዶላር (ለዓለም ሪከርድ 50 ሺ ዶላር ለቦስተን ማራቶን ሪከርድ 25 ሺ)
በአሜሪካዋ ግዛት ቦስተን ለ122ኛ ጊዜ በሚደረገው የቦስተን ማራቶን በዓለም ሪከርድና እና በማራቶኖች ሊግ ፉክክር ተፅእኖ ስለማይፈጥር ትኩረት አልተሰጠውም። 6 የቀድሞ የቦስተን ማራቶን አሸናፊዎች፤ 23 ኦሎምፒያኖች፤ 100 ማራቶኖች ያሸነፉ ማራቶኒስቶች እና 17 ጊዜ የማራቶኖች ሊግ ማራቶኖችን ያሸነፉ ቦስተን ማራቶን ላይ መካፈላቸው ግን ድመቀት ፈጥሮለታል፡፡ በወንዶች ምድብ ከኢትዮጵያ ማራቶኒስቶች የሚሳተፉት የሁለት ጊዜ አሸናፊው ሌሊሳ ዴሲሳ፤ 1 ጊዜ ያሸነፈው ለሚ ብርሃኑ እና በማራቶን የኦሎምፒክ የብር ሜዳልያ ያለው ታምራት ቶላ ሲሆኑ፤ ዊልሰን ቺቤት ከኬንያ እንዲሁም ጋለን ሩፕ ከአሜሪካ ዋና ተፎካካሪዎች ይሆናሉ፡፡
በሴቶች ምድብ ለኬንያዊቷ ኤድና ኪፕላጋት ከፍተኛ ግምት የተሰጠ ቢሆንም፤ በለንደን ማራቶን አንዴ በዱባይ ማራቶን ሶስቴ ያሸነፈችው አሰለፈች መርጊያ፤ በ2017 በቦስተን ማራቶን ያሸነፈችውና የቦታውን ሪከርድ ያስመዘገበችው ብዙነሽ ዳባ እንዲሁም በፍራንክፈርት፤ በሂውስተንና በዱባይ ማራቶኖች ያሸነፈችው ማሚቱ ደስካ የኢትዮጵያን የበላይነት እንደሚያስጠብቁ ግምት የተሰጣቸው ማራቶኒስቶች ናቸው፡፡
በ38ኛው የለንደን ማራቶን
ለአሸናፊዎች በሁለቱም ፆታዎች በነፍስ ወከፍ 55 ሺ ዶላር (በአጠቃላይ 313 ሺ ዶላር)
የተመልካች ብዛት 750 ሺ
የፈጣን ሰዓትና የሪከርድ ቦነስ 850 ሺ ዶላር (ለዓለም ሪከርድ 125 ሺ ዶላር ለለንደን ማራቶን ሪከርድ 25 ሺ)
ከ7 ሳምንታት በኋላ በእንግሊዝ የለንደን ማራቶን ሲካሄድ የዓለም ማራቶን ሪከርድ በሁለቱም ፆታዎች ሊሻሻል እንደሚችል እየተጠበቀ ሲሆን፤ በማራቶኖች ሊግ የ2017/ 18 የውድድር ዘመን ላይ በነጥባቸው አንደኛ ደረጃ ይዘው የሚያሸንፉት ማራቶኒስቶች በሁለቱም ፆታዎች የሚለዩበት መሆኑ ምርጥ ያደርገዋል፡፡
በ38ኛው የለንደን ማራቶን ላይ በሁለቱም ፆታዎች የኢትዮጵያ የማራቶን ሪከርድን የያዙትና  በረጅም ርቀት የምንግዜም ምርጥ ሯጮች የሆኑት ማራቶኒስቶች ጥሩነሽ ዲባባና ቀነኒሳ በቀለ የሚሳተፉ ሲሆን በኬንያ በኩል ደግሞ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት ከፍተኛ ጥረት ላይ የሚገኘው ኤሊውድ ኪፕቾጌ  እንዲሁም በማራቶን ሁለተኛውን የምንግዜም ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበችው ማሪ ኪታኒ የሚሮጡ ናቸው፡፡ ዋናው ፉክክር በኬንያ እና በኢትዮጵያ ማራቶኒስቶች መካከል ቢሆንም በወንዶች ኤርትራውያን፤ በሴቶች የእንግሊዝ ፤ የአሜሪካ እና የጃፓን ማራቶኒስቶች ተቀናቃኞች ናቸው።
በወንዶች ምድብ የለንደን ማራቶንን ለሶስተኛ ጊዜ ከሚሮጠው ቀነኒሳ በቀለ ጋር   ጉዮ አዶላና ቶላ ሹራ ተወዳዳሪ ሌሎቹ የኢትዮጵያ ማራቶኒስቶች ሲሆኑ ባለፈው ዓመት ያሸነፈው ዳንኤል ዋንጂሩ፤ የዓለም የማራቶንንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባች እየሰራ የሚገኘው ኤሊውድ ኪፕቾጌ፤ ስታንሊ ቢዎት፤ አቤል ኪሪዊ፤ ላውረንስ ቼሮኖና ቤዳን ካሮኪ ኬንያ የሚወክሉ ማራቶኒስቶች ናቸው፡፡  እንግሊዛዊው የረጅም ርቀት አትሌት ሞ ፋራህ የመጀመርያ ማራቶኑን የሚሳተፍም ይሆናል፡፡ በ38ኛው የለንደን ማራቶን ላይ ኪፕቾጌ፤ ሞፋራህ እና ቀነኒሳ መገናኘታቸው የዓለም ማራቶን ሪከርድ የሚሰበርበትን ሁኔታ የሚያጠናክረው ነው።  ቀነኒሳ በቀለ በለንደን ማራቶን በ2016 እኤአ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ ሲሮጥ 3ኛ ደረጃ እንዲሁም ባለፈው ዓመት ሁለተኛ ደረጃ ማግኘቱ የሚታወስ ሲሆን ዘንድሮ በሚኖረው ተሳትፎ  ዋናው ፍላጎቱ ማሸነፍ ብቻ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ቀነኒሳ በቀለ  በ2፡02፡57 የኢትዮጵያን የማራቶን ሪከርድን ማስመዝገቡ ይታወሳል፡፡
የኬንያው ኤሊውድ ኪፕቾጌ በ2015 እና በ2016 እኤአ ላይ የለንደን ማራቶንን ያሸነፈ ሲሆን ዘንድሮ ለ3ኛ ጊዜ ለማሸነፍ ማነጣጠሩን አስታውቋል፡፡  ባለፈው መስከረም ላይ በበርሊን ማራቶን ካሸነፈ በኋላ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባ በሚሰራበት ፕሮጀክት እየተጋ የሚገኘው ኤሊውድ በዓለም አትሌቲክስ ባለሙያዎች ሪከርድ መስበር እንደሚችል በተደጋጋሚ የተመሰከረለት ነው፡፡የኬንያው ማራቶኒስት ዴኒስ ኪሜቶ በ2014 እኤአ በበርሊን ማራቶን በ2 ሰዓት ከ02 ደቂቃዎች ከ57 ሴኮንዶች የዓለም ሪከርድ ማመዝገቡ የሚታወቅ ነው፡፡
በሴቶች ምድብ ጥሩነሽ ዲባባ በለንደን ማራቶን ለ3ኛ ጊዜ የምትካፈል ሲሆን፤  ማሬ ዲባባ፤ ትግስት ቱፋና ታደለች በቀለ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ሴት ማራቶኒስቶች ናቸው፡፡ ኬንያዊቷ የ36 ዓመት ማራቶኒስት ማሪ ኪታኒና የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን የበቃችው የባህሬኗ ሮዝ ቼሊሞ ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው ሲሆን፤ ቪቪያን ቼሮይት፤ ግላዲስ ቼሮኖና ብሪግድ ኮሴጊ ይወዳደራሉ፡፡ የለንደን ማራቶን የውድድር ዲያሬክተር ሁግ ብራሸር ማሪ ኪታኒና ጥሩነሽ ዲባባ  በ2017 እኤአ ላይ በተመሳሳይ ቦታ የነበራቸውን ፉክክር የሚደገም ከሆነ የዓለም ማራቶን ሪከርድ በሴቶች የመሰበሩን እድል ሰፊ እንደሚያደርገው ገምተዋል፡፡ ለ3 ጊዜያት በለንደን ማራቶን ያሸነፈችው ማሪ ኪታኒ የማራቶን ሪከርዱን ለማሻሻል ብዙ ዓመታን እንደሰራች ተናግራ፤ ዘንድሮ በወንድ አሯሯጮች በመታገዝ የመስበር እቅድ አለኝ ብላለች፡፡ ያለፉትን 15 ዓመታት እንግሊዛዊቷ ፓውላ ራድክሊፍ  2፡15.25 የዓለም ሪከርድ ያመዘገበችው ከ15 ዓመታ በፊት በወንድ አሯሯጮች በመታገዝ በለንደን ማራቶን ላይ ነበር፡፡
አምና ኬንያዊቷ ማሪ ኬይታኒ የለንደን ማራቶንን ስታሸንፍ ርቀቱን የጨረሰችበት 2፡17፡01 በሴቶች አሯሯጭነት አዲስ የዓለም ማራቶን ሪከርድ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፤ ፓውላ ራድክሊፍ በ2005 እኤአ ላይ በሴቶች አሯሯጭነት ያስመዘገበችውን 2፡17፡42 በአርባ አንድ ሰከንዶች በማሻሻሏ ነው፡፡
ከቺካጎ ማራቶን የመጀመርያ ድሏ በኋላ በለንደን ማራቶን የምትሳተፈው ጥሩነሽ ለለንደን ማራቶን በቂ የዝግጅት ጊዜ ወስዳ እየሰራች መሆኗን ገልፃ፤ ማሸነፍ የማይቻል ነገር አይደለም  የሚል አስተያየት ሰጥታለች፡፡ በ37ኛው የለንደን ማራቶን  ጥሩነሽ ዲባባ በሁለተኛ ደረጃ ስትጨርስ ያስመዘገበችው 2፡17፡56 አዲስ የኢትዮጵያ ማራቶን ሪከርድ ሆኖ እንደተመዘገበ የሚታወስ ነው፡፡ በ2012 እኤአ ላይ በለንደን ኦሎምፒክ ቲኪ ገላና በ2፡18፡58 ሰዓቷ የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ሆና የወርቅ ሜዳልያ ስትጎናፀፍ ያስመዘገበችውን የኢትዮጵያ ማራቶን ክብረወሰን በ62 ሰከንዶች ያሻሻለ ነበር፡፡
በ11ኛው የማራቶኖች ሊግ
የማራቶኖች ሊግ Abbott World Marathon Majors በ2017/ 18 የውድድር ዘመን ሲቀጥል 11ኛው ሲሆን የተጀመረው በ2017 እኤአ መስከረም ወር ላይ በበርሊን ማራቶን ነበር፡፡  ከዚያም የቺካጎና የኒውዮርክ ማራቶኖች የፈረንጆቾች ዓመቱ ሳይጠናቀቅ ተካሂደዋል፡፡
11ኛው የማራቶኖች ሊግ በ2018 የሚቀጥለው የቶኪዮ፤ የቦስተንና የለንደን ከተሞች በሚያስተናግዷቸው ግዙፍ ማራቶኖች ሲሆን በተለይ በርካታ ምርጥ እና ፈጣን ማራቶኒስቶች የሚሳተፉበት የለንደን ማራቶን በሁለቱም ፆታዎች ሻምፒዮኖቹ የሚለዩበት እንደሆነ ተጠብቋል።  የማራቶኖች  ሊግ በሁለት የውድድር ዘመናት የሚካሄዱ 6 ግዙፍ እና እውቅ ማራቶኖችን እንዲሁም የዓለም ሻምፒዮና እና የኦሎምፒክ ማራቶኖች ውጤት በመደመር በነጥብ አሸናፊዎቹ ተለይተው ከፍተኛ ሽልማት እና የክብር ዋንጫዎች የሚያገኙበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡  ዘንድሮ በሁለቱም ፆታዎች ከፍተኛውን ነጥብ በማስመዝገብ በአንደኛ ደረጃ የሚጨርሱት ማራቶኒስቶች በነፍስ ወከፍ 200ሺ ዶላር ሲሸለሙ፤ ለሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃዎች ደግሞ  50ሺ እና 25ሺ ዶላር እንደቅደም ተከተላቸው ይበረከትላቸዋል፡፡
በ11ኛው የማራቶኖች ሊግ በወንዶች ምድብ የመሪነቱን ስፍራ የያዘው የኬንያው ኤሊውድ ኪፕቾጌ ሲሆን ከባለፈው የለንደን ማራቶን አሸናፊ ዳንኤል ዋንጂሩ፤ ከቺካጎ ማራቶን አሸናፊ ጋለን ሩፕ እና ከዓለም የማራቶን ሻምፒዮኑ ጂዮፍሪ ኪሩዊ ጋር በእኩል 25 ነጥብ ተጋርተውታል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ጉዬ አዱላ ፤ ቀነኒሳ በቀለ፤ ታምራት ቶላ ከኬንያውያኑ አቤል ኪሪዊ እና ዊልሰን ኪፕሳንግ ጋር በ16 ነጥብ እስከ 10 ባለው ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡
በሴቶች ምድብ ደግሞ ጥሩነሽ ዲባባ በቺካጎ ማራቶን የመጀመርያ የማራቶን ድሏን ካስመዘገበች በኋላ  25 ነጥብ እንዲሁም በለንደን ማራቶን ባለፈው ዓመት ባገኘችው ሁለተኛ ደረጃ 16 ነጥብ በድምሩ 41 ነጥብ አስመዝግባ እየመራች ነው፡፡ 3 የኬንያ አትሌቶች ሮዝ ቼሌሞ፤ ማሪ ኪታኒ እና ግላዲስ ቼሮኖ በእኩል 25 ነጥቦች ይከተሏታል፡፡  ባለፈው የውድድር ዘመን በ10ኛው የማራቶኖች ሊግ  ያሸነፉት ኬንያውያኖቹ  ማራቶኒስቶች ኤልውድ ኪፕቾጌ እና ኤድና ኬፕላጋት ነበሩ፡፡

Read 2907 times