Monday, 05 February 2018 00:00

ወደ ነፍስ መመለስ ---

Written by  መሐመድ ነስሩ (ሶፎኒያስ አቢስ)
Rate this item
(3 votes)

  የጀመረውን ልብወለድ ወደፊት ለመግፋት ወንበር ስቦ ተቀመጠ፡፡ ተቀመጠና ከቆመበት ቀጠለ፡፡ ቃላትን ወረቀት ላይ እንደ ጅረት ማፍሰስ ጀመረ፡፡ ስለጠፋውን ማንነት አወጣ አወረደና ‹‹ወደ ማንነት መመለስ››ን ጊዜያዊ የልብ ወለዱ ርዕስ አደረገ፡፡
ስለጠፋው ማንነት ጥቂት ቁጭ ብሎ ካሰበ በኋላ፣ ወደ ማንነት ስለ መመለስ ካሰላሰለ በኋላ፤ እንዲህ ብሎ መጻፉን ቀጠለ፡፡
የደራሲው ልብወለድ
ሚኪያስ ቀጠን ብሎ፤ ዘለግ ያለ ወጣት ነው፡፡ በየወሬው መሀል ‹‹ዬ … ዬ!›› ማለት ይቀናዋል፡፡ የሱሪው ጫፍ መሬት ይጠርጋል፤ ሱሪው ከወገቡ ተነስቶ ወደ መቀመጫው በመውረድ የውስጥ ሱሪውን ለእይታ አጋልጦታል፡፡ ይህ ክስተት የሚዘገንን ነገር አለው፡፡ ለእሱ ግን ምንም አይመስለውም፡፡ እንዲያውም እንደዚህ በመልበሱ ኮራ ዘና ይላል፡፡ በከተማዋ አለ የተባለ ፋሽን ተከታይና አራዳ የሆነ ይመስለዋል፡፡  
ዘፈን ይወዳል፡፡ ነገር ግን ከአማርኛ ዘፈኖች አንዱን ጥቀስ ቢባል መጥቀስ አይችልም፡፡ የሚያዳምጠው እንግሊዝኛ ዘፈኖችን ነው፡፡ ከእንግሊዝኛ ዘፈኖችም በጥቁር አሜሪካውያን የሚቀነቀነውን ራፕ ያዘወትራል፡፡ ፊልም ይመለከታል፡፡ ነገር ግን የሆሊውድ፣ ቦሊውድ እና የሌሎች ውጪ ሀገራት ፊልሞችን ብቻ ነው የሚያየው፡፡ አማርኛ ፊልም ሲያልፍም አይነካካው!
አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያሉ ጭፈራ ቤቶች ቤቱ ናቸው፡፡ ሁሌ ቅዳሜ ቅዳሜ ‹ኦቨር› ይወጣል፡፡ የፈለገ ችግር ቢገጥመው ቅዳሜን አይቀርም፡፡ አሁን የበቀደሙ ቅዳሜ ክለብ H2o ነው ያነጋው፤ ሲጨፍርና ሲዝናና!
በሰፈሩ ውስጥ ቪዲዮ ቤት ከፍቶ ይሰራል፤ ስራው አርኪ፣ ገቢውም አበረታች ባይሆንም ቪዲዮ ቤትዋን በተቻለው መጠን ለመክፈት ይሞክራል። እንዲህ የሚሆነው ስራ ወዳድ ሆኖ አይደለም፡፡ ገንዘብ ስለሚያስፈልገው ነው፡፡ ቅዳሜ ወይም አርብ ‹ኦቨር› የሚወጣበትን ያህል ገንዘብ ካገኘ ሱቁን ዘግቶ ይሰወራል።
መጨፈር ይወዳል፡፡ የአጨፋፈር ሁኔታው ሲታይ፣ የሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህንን ግጥም ያስታውሳል፡፡
           ደንስ ጎበዝ ! ደንስ ጀግና
           ከረቫትክን አውልቅና
           ሃሳብክን ልቀቀውና---
የደራሲው ታሪክ
ደራሲው የራሱ ታሪክ አለው፡፡ ጎበዝ ተማሪ ነበር፡፡ የአስረኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተፈትኖ አለፈና የተፈጥሮ ሳይንስን መርጦ አስራ አንደኛ ክፍልን ተቀላቀለ፡፡ ማንበብ ይወዳል፡፡ አንዳንዴም፣ አንዳንድ ነገሮችን ይከትባል፡፡
አንዴ የአማርኛ መምህራቸው አጭር ልብወለድ ፅፈው እንዲመጡ ለተማሪዎቻቸው የቤት ስራ ሰጡ፡፡ በቆረጡት ቀን የቤት ስራውን ወረቀት ከተማሪዎቻቸው ሰበሰቡና በሌላ ክፍለ ጊዜ አርመው አመጡ፡፡ የታረሙትን ወረቀቶች ለተማሪዎቻቸው መልሰው የአንድ ተማሪን ወረቀት ብቻ አስቀሩ፡፡
‹‹ስሙ! .. ይሄ ልብወለድ አጭር ልብወለድ እንዴት መፃፍ እንዳለበት መማሪያ የሚሆን ነው፡፡›› ብለው መነፅራቸውን በማስተካከል፣ ልብወለዱን መተረክ ጀመሩ፡፡
ተርከውም ጨረሱ፡፡ ሲጨርሱ የተማሪው ጭብጨባ ተከተላቸው፡፡
‹‹ገዳሙ ካሳሁን!›› ብለው ተጣሩ፡፡
ገዳሙ ‹‹አቤት›› ብሎ ከመቀመጫው ተነሳ፡፡
‹‹ና ወዲህ!›› ብለው ጠሩት፡፡
ወጣ፡፡
‹‹ይሄ ልጅ ነው እንግዲህ ይህን የመሰለ ልብወለድ የፃፈው›› አሉ፤ ጸጉሩን እያሻሹለት፡፡
‹‹አጨብጭቡለት!›› ተጨበጨበለት፡፡
ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ ከክፍል ሲወጡ፤
‹‹ገዳሙ ና! አንዴ እፈልግሃለሁ›› ብለው ጠሩት፡፡
ተከተላቸው፡፤
‹‹በዚህ አያያዝህ ከቀጠልክ ጥሩ የቋንቋ ወይም የሥነ-ጽሁፍ ሰው መሆን የምትችል ይመስለኛል፤ በርታ!›› ብለው፤ ከደረት ኪሳቸው አዲስ ብዕር አውጥተው ከሸለሙት በኋላ ጨብጠው ተሰናበቱት፡፡
‹‹አመሰግናለሁ ቲቸር!››
ገዳሙ የመፃፍ ተሰጥኦ እንዳለው አወቀ እና መምህሩ እንዳሉት የሥነ-ጽሁፍ ወይም የቋንቋ ሰው መሆንን መመኘት ጀመረ፡፡ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናን እንዳለፈ ስነ-ጽሁፍ ለማጥናት ፈለገ፡፡ ለሱ በተሰጠው የትምህርት ክፍል መምረጫ ወረቀት ላይ የሚፈልገው የሥነ-ጽሁፍ ክፍል አልነበረም፡፡
ሲጠይቅ፤
‹‹ይሄ የተፈጥሮ ሳይንስ መምረጫ ወረቀት ነው፤ ስነ-ጽሁፍ ያለው በማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች የትምህርት ክፍል መምረጫ ወረቀት ላይ ነው›› ተባለ፡፡
‹‹የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎችን ወረቀት ወስጄ ከዛ ላይ ብመርጥስ?››
‹‹አይቻልም!››
‹‹ለምን?››
‹‹የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ስለሆንክ መቀጠል ያለብህ በዛው ነው፡፡››
ይሄንኑ ጉዳይ ሊያጣራ አራት ኪሎ የሚገኘው ትምህርት ሚኒስቴር ቢሮ ድረስ ሄደ፡፡ እነሱም እንደማይቻል ነገሩት፡፡ ገዳሙ ተበሳጨ፡፡
ከተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፎችም አልመርጥም አለ፡፡ ታላቅ ወንድሙና ጓደኛው የመሰላቸውን መርጠውና ቅፁን ሞልተው ሰጡት፡፡ ከወራት በኋላ የአዳዲሶቹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ድልድል ሲወጣ፤ እሱ በጤና ሳይንስ መስክ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ መመደቡን አወቀ፡፡
በቤተሰብ ጫና ጭምር ሊማር ሄደ፡፡ እዛ ሲደርስ ከጤና ሳይንስ ፋካልቲ በጤና መኮንንነት መስክ መመደቡን አወቀና መማሩን ጀመረ፡፡
የደራሲው ልብወለድ
ሚኪያስ ነገሮችን አቅልሎ የሚያይ ወጣት ነው። ማሰብ፣ መጨነቅ ወይም ማዘን አይፈልግም፡፡ ሌላው ቀርቶ እናቱ የሞቱ ጊዜ እንኳን ሲያለቅስ አልታየም፡፡ እናቱ በሞቱ በሶስተኛው ቀን ጭፈራ ቤት ነበር፡፡
እናቱን በቀበረ ማግስት ሲጠጣና ሲጨፍር ነበር። በተለምዶ እንደሚደረገው ጸጉሩን አልተላጨም። ጥቁር ልብስ አልለበሰም፡፡ የቀብራቸው ቀን እንኳን የአዘቦት ልብሱን ለብሶ ነው የዋለው፡፡ ድርጊቱ ለብዙዎች አስገራሚ ነበር፡፡ ለእሱ ግን የሰው ነገር ምንም አልደነቀውም፡፡ የጥፋተኝነትም ሆነ የአፈንጋጭነት ስሜት ፈፅሞ አልተሰማውም፡፡
እናትን የምታህል ፍጡር (ፍጡር ናት ፈጣሪ?) ሞታ እንደ ማንም ፊቱ ላይ ሀዘን ማንበብ አለመቻል የሚገርም ነው፡፡ እንኳን ቀብር ላይ ቆሞ ሊያለቅስ፤ ለቅሶና ሀዘን ባለበት ቦታ ራሱ መገኘት አይፈልግም፡፡ የጨፈገገ ፊት ሲያይ በሩቅ ይሸሻል፡፡ የተኮሳተረ ሰው ሲያይ ፊቱን ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ ያዞራል፡፡
ጭንቀትም ሆነ ሀዘን እንዲሰማው አይፈልግም፡፡ ሳቅን እንደ ሚዳቆ ያድናል፡፡ ሳቅና ጨዋታ ባለበት እሱ አለ፡፡ በተቃራኒው ለቅሶና ሀዘን ባለበት ሽታውም የለም። ስለ ህይወት አያስብም፡፡
‹‹የሚሆነው መሆኑ ለማይቀር ነገር ለምን አስባለሁ?! … ትርፍ ለሌለው ነገር ለምን ራሴን በጭንቀት አሰቃያለሁ?!›› ይላል፡፡
አጥብቆ አሳቢ ሲያገኝ፤‹‹አስር ሞልታ አታውቅም አለም ዘጠኝ ናት›› እያለ በማንጎራጎር፤‹‹ለዚህች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደ ማለዳ ጤዛ ለምትረግፍ ወይም ለምትጠፋ ህይወት ለምን ትጨነቃለህ? ፈታ በል … ፈታ ብለህ ኑር!›› እያለ ለማስተማርና ለመስበክ ይዳዳዋል፡፡
ሚኪያስ እንደ ሴት መሽቀርቀር የሚወድ ወጣት ነው፡፡ ፋሽን ይከተላል፡፡ ፊልም ላይ ያየው የሚማርክ አለባበስ ካለ፤ ያን ሰሞን ለብሶት ይታያል፡፡ የፀጉር ቁርጡንም በየጊዜው ይቀያይራል፡፡ አንድ ተጫዋች ላይ ለየት ያለ አቆራረጥ ካየ፤ ነገ እሱም እንደዛ ተቆርጦ ሳይታይ አይቀርም፡፡
ወደ ውጪ የሚልከው (ወይም ኤክስፖርት) የሚያደርገው ነገር ባይኖረውም፤ ወደ ውስጥ የሚያስገባው (ወይም ኢምፖርት የሚያደርገው) ነገር ብዙ ነው፡፡ በሌላ ሳይሆን ያው በአለባበሱና በፀጉር አቆራረጡ፡፡
የደራሲው ታሪክ
ገዳሙ ትምህርቱን ለመከታተል ይታገል ጀመረ። ውስጡ ግን ምንም ደስተኛ አልነበረም፡፡ በትንሽ በትልቁ ይከፋዋል፡፡ ዝም ብሎ ይነጫነጫል፡፡ ገዳሙና ደስታ ሰማንያቸውን ቀደዋል፡፡ ሳቅ ብርቅ ሆኗል፡፡ ቁዘማ በሁለመናው ነግሷል፡፡
ምክንያቱን ሊያውቀው አልቻለም፡፡ ምክንያቱን በአግባቡ ባያውቀውም ይጠረጥራል፡፡ ማንነቱን እንደ በግ በስመ-አብ ብሎ ያረደ እና ቆዳውን የሸለተ ይመስለዋል፡፡ ከታረደው ማንነቱ የወጣው ደም ቀይ አልነበረም፡፡ ደሙ ጥቁር ነበር፡፡ ሌሊቱም ቀኑም በጨለማ ቱቢት የተጋረደ ጥቁር፡፡ ከላይ ጥቁር፤ ከታች ጥቁር! ከፊት ጥቁር፤ ከኋላ ጥቁር! ዓለም ጥቁር በጥቁር ሆናበታለች፡፡
የሚፈልጉትን ነገር ማጣት እንደዚህ የሚመርና የሚያስከፋ አይመስለውም ነበር፡፡ አንድ ነገር አስቦ አለማድረግ፤ አንድ ነገር ጀምሮ አለመጨረስ፤ እንደዚህ የሚያንገበግብና ህይወት እንድታንገሸግሽ የሚያደርግ አልመሰለውም፡፡ አሁን ገባው፡፡..
ይሄ ሁሉ እውነት ለአንድ ተራ ግለሰብ ከምንም የሚቆጠር ላይሆን ይችላል፡፡ ለአንድ ደራሲ ግን የፀናና ከረር ያለ ህመም ነው፡፡ ደራሲ ከስሱነቱ አንፃር ከታየ ህመሙ የሚፀናበትና በትንሽ አሳዛኝ ክስተት እይታ እንኳን ስሜቱ በጩቤ ወይም በጦር የተወጋ የሚመስለው ነው፡፡
እንቅፋት ቢያደናቅፈው በአለት የተፈነከተ ያህል ነው፡፡ እሾህ ቢወጋው በቆንጨራ አንገቱን የተቀላ ያህል ይቆጠራል፡፡
ደራሲም ሆነ ገጣሚ ስሱ መሆናቸው፤ በደህና አንባቢ ዘንድ  የታወቀ እውነት ነው፡፡ የሆነው ሆኖ ገዳሙ ትግል ላይ ነው፡፡ ለትምህርት ሲል ወደ ጎንደር መሄዱን ለነጻነት ሲሉ ደደቢት በረሀና አሲምባ ከዘመቱት ጋር አንድ አድርጎ ይቆጥረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲ ሳይሆን ጦር ሜዳ ያለ ነው የሚመስለው፡፡
ህይወቱን ሲያስበው በጥይት አልባ ሽጉጥ የተተኮሰበት ያህል ነው፡፡ ሽጉጡ ተተኩሷል፤ ጥይቱ ግን የለም፡፡ ስለዚህ የቆሰለም ሆነ የሞተ የለም፡፡ የደነገጠ ግን ብዙ ነው፡፡ በቁጥር አንድ ደረጃ የበረገገው ደግሞ ገዳሙ ነው፡፡ ማንነቱ ወደማይፈልገው ማንነት እየተለወጠ ነው። እውነተኛውንና ትክክለኛውን ማንነቱን ጥሎ ሌላ ማንነት እየገነባ ነው፡፡ እና ይሰጋል፡፡
ከእውነተኛው ማንነቱ ጠፍቶ እንዳይገኝ ይመኛል። የፈራው አልቀረለትም፡፡ ለመጻፍም ሆነ ለማንበብ ጊዜ ማግኘት እያዳገተው መጣ፡፡ ትምህርቱ ውጥረት ውስጥ ከተተው፡፡
የደራሲው ልብወለድ
ሚኪያስ ቋንቋው ጉራማይሌ ነው፡፡ የእንግሊዝኛ ቃላትን በንግግሩ መሀል አብዝቶ ይጠቀማል፡፡
‹‹ዩኖው ዋት?›› ይላል ንግግር ሊጀምር ሲል፡፡ ‹‹ዩኖው ዋት … ፊልም እወዳለሁ››
አማርኛው በእንግሊዝኛ ቅላፄ የታጀበ ነው። ሲያወራ የወፍ ቋንቋ የሚያወራ እንጂ አማርኛ የሚያወራ አይመስልም፡፡ ቅላፄው ሙሉ ለሙሉ የነጮች ነው። ታዲያ በዛ ቅላፄ አማርኛውን ይጨቁነዋል፡፡ ይሄ ኢትዮጵያውያን ለሆኑ ሰዎች የሚጎረብጥ ነው፡፡ አማርኛችን ለዛ ሲያጣ መስማት በጣም የሚያናድድ ነገር ሳይሆን አይቀርም፡፡ ቢሆንም ሚኪያስ አማርኛችንን እየጨቆነና የእንግሊዘኛ ቅላጼውን እያነገሰበት ማውራቱን ቀጥሏል፡፡
ጓደኛ አለችው፡፡ ጓደኛው ራሄል ትባላለች፡፡ እሱ የሚጠራት ግን ‹ሪች› እያለ ነው፡፡እሷም የሱ ቢጤ ናት። ከአማርኛ ይልቅ እንግሊዝኛ የሚቀናት! መሽቀርቀር የምትወድ!  ምቾት ቦምቦሊኖ ያስመሰለው ጉንጭ ያላት! የምሽት ክበቦች አብረው ይሄዳሉ፡፡ ሲጨፍሩም ያድራሉ።
‹‹ከሁሉ ነገርህ ምን እንደሚማርከኝ ታውቃለህ?›› ትለዋለች ለብቻ ሆነው ሲያወሩ፡፡
‹‹ምን ይማርክሻል?!›› ይላታል መልስዋን ለመስማት እየጓጓ፡፡
(አንድ ደራሲ እንዳለው፣ ጉጉቱ ጉጉት አስመስሎት ይታያል፡፡)
‹‹አለባበስህ!››
‹‹አመሰግናለሁ!›› ይላታል፤ በመገረምና እውነትዋን ይሁን ውሸትዋን ለመለየት ወይም ለማወቅ እንደፈለገ ሁሉ ፊትዋን እያጠና፡፡
‹‹ሌላስ ምን ያስደስትሻል?››
‹‹ሌላ!?› ትላለች፤ ዓይን ዓይኑን እያየች፡፡
‹‹አዎን ሌላ፡፡››
‹‹የፀጉር ቁርጥህም ይማርከኛል … ባጭሩ ፋሽነብል መሆንህ እንድወድህና እንድኮራብህ ያደርገኛል፡፡ ከአንተ ጋር ሆኜ ለማንም ሆነ በማንም መታየትን አላፍርም፡፡ እኮራብሃለሁ፡፡››
‹‹ካብሽኝ እኮ … እንዴት ነው ባክሽ?››
‹‹መካቤ አይደለም፤ እውነተኛ ስሜቴን መግለፄ ነው፡፡ ያልኳቸውን ነገሮች አምነህ መቀበል እንጂ ሌላ ምንም ማድረግ አትችልም፡፡›› አለችው ፤በፈገግታ ፈክታና ደምቃ፡፡
ፍቅረኛው ራሄል ዘመኑ የወለዳቸውን እስኪኒ ሱሪዎችን እንጂ ሌላ ዓይነት ሱሪ ፈፅሞ አትለብስም። ከሱሪ ውጪ መልበስ ሲያምራትም ከጉልበት በላይ የሚውሉ አጫጭር ቀሚሶችን (ሚኒስከርቶችን) ትለብስና አምራና ተውባ ትታያለች፡፡
የዕድሜ ልክ ሳይሆን የዕለት ደስታን በማሳደድ ትታወቃለች፡፡ ስለ ዛሬ እንጂ ስለ ነገ ማሰብ አትፈልግም። ‹‹ዋናው ቀን ዛሬ ነው… የቀኖች ቁንጮና አለቃ ትላንት ወይም ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው፤ ስለዚህ ዛሬን በመዝናናትና በመደሰት ማሳለፍ አስፈላጊ ነው፡፡›› ትላለች፡፡
ፀጉርዋ አጭር ነው፡፡ እጥረቱን ግን ከሰዎች እይታ ለመጋረድ ትታትራለች፡፡ ፀጉርዋ ላይ ‹ሂዩማን ሄር› ቀጥላለች፡፡ የረጅም ጸጉር ባለቤት የመሆን አምሮትዋን በዊግ ትወጣለች፡፡ ዕድሜ ፀጉራቸውን እየቆረጡ ለሚሸጡ የህንድና የሌሎች ሀገሮች ሴቶች ይሁንና የፀጉርዋን እጥረት ከሰዎች (በተለይም ከወንዶች) እይታ ጋርዳለች፡፡ ባለረጅም ጸጉር ሴት መስላ ትታያለች (ታይታለች)፡፡
‹‹እኔን ደግሞ ምንሽ እንደሚማርከኝ ልንገርሽ?››
‹‹ደስ ይለኛል፡፡››
‹‹የተለየ ነገር አትጠብቂ… ነገሩን አንቺም ታውቂዋለሽ››
‹‹ግድየለም ንገረኝ››
‹‹ሞደርን መሆንሽ! you know? I like the way you dress, the way you think, the way you live ….you know ብዙ ሴቶች እነዚህ ነገሮች የላቸውም፡፡
በአስተሳሰብ ዘመናዊ ናቸው፤ በአለባበስ ግን ኋላቀር!
በአለባበስ ዘመናዊ ናቸው፤ በአስተሳሰብ ግን ኋላቀር!
በአስተሳሰብና በአለባበስ ዘመናዊ ናቸው፤ በአኗኗር ግን ኋላ ቀር! …
በአኗኗር ዘመናዊ ናቸው፤ በአለባበስና በአስተሳሰብ ግን ኋላቀር! …
አንቺ ከእነዚህ ሁሉ ተለይተሸ ሙሉ ለሙሉ ዘመናዊ የሆንሽ ሴት ነሽ!›› …
‹‹ስለምትወደኝ ይሆናል እንደዚህ ሙሉ አድርገህ ያሰብከኝ፡፡››
‹‹በፍፁም አይደለም፤ የተናገርኩት ከስሜቴ ሳይሆን ከአዕምሮዬ ነው፡፡ አንቺ ትለያለሽ››
‹‹አመሰግናለሁ!››
የደራሲው ታሪክ
ገዳሙ ትምህርቱን መማሩን ቀጥሏል፡፡ የደስታ ስሜት ግን ኖሮት አያውቅም፡፡ ደስታ ከምኞቱ ጋር ሞቶ ተቀብሯል፡፡ ‹‹ህይወት ግን ለምን እንዲህ ውስብስብ ትሆንብናለች?›› እያለ ያስባል፡፡ ህይወት ከአልጋዋ ቀጋዋ መብዛቱ አስገራሚ ነው፡፡ በተለይ በደሀ ሀገር ሲኖር ህይወት ጨለማ ሆና ትገኛለች፡፡
ገዳሙ አንዳንዴ የገዛ ሀገሩን ለመጥላት ይቃጣዋል። ‹‹ለዜጎችዋ የማትሆን፤ የዜጎችዋን ፍላጎት የማታሟላ ሀገር፤ ሀገር መባል የለባትም›› ይላል፡፡ ‹‹የፈለግኩትን የማላገኝባት ምኞቴን የማልፈጽምባት ሀገር፤ እንዴት ሀገሬ ለመሆን ትችላለች?›› እያለ ይጠይቃል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ የተረገመች ምድር ናት›› አለ፡፡
‹‹በበላይ ዘለቀ የተረገመችው ወንድ አይበቀልብሽ ሳይሆን ሰው አይብቀልብሽ ተብላ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የመልካም ዕድል ፀጋ የሌላት ሀገር ናት፡፡ ሰው የሚፈልገውን መሆን የማይችልባት! … ትልቅ ተሰጥዖና ክህሎት ኖሮት ሀገሩን የት ሊያደርስ የሚችል ሰው እንደ ትቢያ የሚጣልባት!››
‹‹እኔ አሁን ስነ-ጽሁፍ ብማር ይሄ መንግስት ምን ይደርስበታል?›› ብሎ ይጠይቃል፡፡ ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን አዳዲስ ህጎች በየጊዜው የሚፈራረቁብን ዜጎች ነን። መንግስት የሚያየን እንደ ሰው ሳይሆን እንደ ሙከራ አይጥ ነው፡፡
‹ሰው ከተሰማራ እንደየስሜቱ
በዋለበት ሜዳ አይቀርም ማፍራቱ›
ብላለች፤ ዘፋኝዋ እንኳን፡፡
ህይወት ላይ መሰማራት ያለብን እንደየፍላጎታችን ነው፡፡ አሳ የማጥመድ ልምድና ፍላጎት ከሌለን ቀኑን ሙሉ ሐይቁ አጠገብ ብንውልም አሳውን ማጥመድ አንችልም፡፡ ልምድና ፍላጎት ወሳኝ ነገሮች ናቸው። በተለይ ፍላጎት! ፍላጎት ካለን ልምዱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማካበት እንችላለን፡፡ ፍላጎቱ ከሌለን ግን እንኳን ያሰብነውን ልናሳካ ይቅርና አንዲት ጋት ያህል እንኳን ወደፊት ፈቅ ማለት አንችልም፡፡
ሁሉንም በአንድ ማሰሮ አጠቃሎ ከቶ ነገሮችንና ሰዎችን እንደ አንድ የፋብሪካ ምርት ወጥና አንድ አድርጎ ማየት እየተለመደ የመጣ ሀቅ ነው፡፡ ግለሰብ በማህበረሰብ ተጨፍልቆ መብቱን ይገፋፋል፡፡ የእኔ ስነ-ጽሁፍ መማር ማንንም የሚጎዳ ነገር አልነበረም፡፡ ግን ጊዜውን ጠብቆ እንደሚፈነዳ ፈንጂ ተቆጥሮ ነበር። የትምህርት ስርዓቱንና ደንቡን እንደጣስኩ ተደርጎ ነው የተቆጠረው፡፡ እና በፍላጎቴ እንዳልማር ተከለከልኩ፡፡ ስነ-ጽሁፍ የመማር መብቴ ተገፈፈ፡፡›› ይላል፤ ከአንዳንድ ቅርብ ጓደኞቹ ጋር ሲያወራ፡፡
ገዳሙ፤ ጊዜው ርቆ እንኳን ይህ ክስተት ሁሌ ይታወሰው ነበር፡፡
የደራሲው ልብወለድ
ሚኪያስ የባህሪ ለውጥ አመጣ፡፡ የቀየረው ውሎ ነው፡፡ መስፍን ከሚባል አንድ ወጣት ጋር በአጋጣሚ ተገናኝተው ጓደኛሞች ሆኑ፡፡ የመስፍን የአቻ ግፊት ሚኪያስ ላይ በረታና ተቆጣጠረው፡፡ በጣም ተስማምተዋል፡፡ መስፍን አስተዋይ የሆነ ጥሩ ልጅ ነው። ሚኪያስን መጽሐፍ ማንበብ ቀስ በቀስ አለማመደው። የተለያዩ መጽሐፍትን እንዲያነብ ይዞለት ይመጣል። ሚኪያስ ከንባቡ ገፋ እያደረገ ሲሄድ መለወጥ ጀመረ። በልብ-ወለድ የጀመረውን ንባብ ቀጥሎ በ  ታሪክና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ የህትመት ውጤቶችንና መጽሐፍትን ማንበቡን ቀጠለ፡፡ አስተሳሰቡ ተገራ፡፡ ለሰው የሚሰጠው ቦታ እና ለነገሮች ያለው እይታ እየተስተካከለ መጣ፡፡ ሰው እንደሚያከብር ሁሉ እሱም መከበር ፈለገ፡፡
አለባበሱን ቀየረ፡፡ ‹‹ወደ ውጪ ሳይሆን ወደ ውስጥ ማየት መልካም ነው!›› ብሎ አሰበ፡፡ ስለ ማንነቱ አብሰለሰለ፡፡ ይህ አሁን ያለው ማንነት የሱ እውነተኛ ማንነት እንዳልሆነና ወደጠፋው ማንነቱ መመለስ እንዳለበት ወሰነ፡፡ አማርኛ ሲያወራ ትክክለኛውን የአማርኛ ቅላፄ ለመጠቀም መሞከር ጀመረ፡፡ በንግግሮቹ መሀል የሚደነቅራቸውን የእንግሊዝኛ ቃላት ለመቀነስ ተፍጨረጨረ፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆን (ነው! ግን እንዳልሆነ ይሰማው ነበር) ኢትዮጵያዊነትን መላበስ ፈለገ፡፡ ከምዕራቡ ዓለም የመጣውን ቡትቶ ማንነት እሳት ሊለኩስበት ወሰነ፡፡
የደራሲው ታሪክ
ህይወት እድል ናት፡፡ ስንወለድ የምንወለደው ፍላጎታችንን ተጠይቀን፤ ከማን መወለድ እንዳለብን መርጠን አይደለም፡፡ አንዱ ቤተሰብ ውስጥ እንደ ዕድል ዝም ብለን ዱብ እንላለን፡፡ የፊታችንን ቀለምም ሆነ ይዘት መርጠን አልተወለድንም፡፡ ቁመታችን ይህን ያህል ይሁን ብለን አልወሰንንም፡፡ እንደ ዕጣ ነው፡፡ ከተጠቀለሉት በርካታ ወረቀቶች ውስጥ ከዕጣው አንዱን አንስተን እንደማንበብ ነወ፡፡ ሰውዬው ‹‹ዕድሌ ዕድሌ ጠማማ … ጠማማ›› ብሎ ቢዘፍን እውነት አለው፡፡ የሱ እድል መጥፎ ነገር ላይ እየጣለ ስላስቸገረው ነው፡፡
ህይወት ፍትህ አታውቅም፡፡ ለአንዱ የሆነ ተሰጥኦ ትሰጠዋለች፡፡ ለሌላው ሌላ፡፡ አንዱን በሀብታም ቤተሰብ ውስጥ እንዲወለድ ታደርገዋለች፡፡ ሌላውን በደሀ ቤተሰብ ውስጥ ራሱን እንዲያገኝ አድርጋ ታስቀምጠዋለች፡፡ ገዳሙ በህይወቱ ውስጥ የተፈጠረውን ይህን አጋጣሚ እንደ እድል ወሰደው፡፡ ‹‹ዕድሌ ነው!›› ብሎ አመነ፡፡ ትዝ ሲለው መበሳጨቱ ባይቀርም ራሱን ለማሳመንና የሆነውን አምኖ ለመቀበል ጥረት ማድረግ ጀመረ፡፡
‹‹የምትወደውን ካላገኘህ ያገኘኸውን ውደድ›› በሚለው አባባል ተሳበ፡፡
አሁን እሱ የስነ-ጽሁፍ ተማሪ ወይም ደራሲ ሳይሆን የጤና መኮንንነት ተማሪ ነው፤ይህን ሀቅ አምኖ ለመቀበል ወሰነ፡፡ እና በርትቶ ትምህርቱን መከታተል ጀመረ፡፡
የደራሲው ልብወለድ
‹‹ሁላችንም የጠፋውን ማንነታችንን ፍለጋ በየአቅጣጫው ልንሰማራ ይገባል›› አለ ሚኪያስ፡፡ ማንነት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ በብዙ ግብአቶች ደጋፊነት ወይም ተረባራቢነት የሚገነባ ነገር ነው፡፡ የማንነት ማዕከሉ ሰው መሆን ነው፡፡ ክፈፉ ግን እንደየመልካችን የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ የተለያዩ በየቦታው የምናገኛቸው ግብአቶችና የህይወት ንጥረ ነገሮች የማንነትን ምንነት ይቀምማሉ፡፡››
‹‹ኢትዮጵያዊ ማንነት ምንድን ነው?›› ብሎ ጠየቀ ሚኪያስ፡፡
‹‹ኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ በላይ በተደራረቡ ዓመታት ውስጥ፤ በተከናወኑ ታሪኮችና በታሰቡ ቁምነገሮች ድምርነት የተገነባ፤ በሶስት ሺህ ዘመን አጥር ውስጥ በተነሱና በወደቁ ታሪኮች ካብ ላይ በተደረበ ምንነት የተሰራ እውነትና ህይወት ነው፡፡ ‹‹መልኩ ምን ይመስላል?›› ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል፡፡ መልኩ እንደ ነብር ዥንጉርጉር፣ እንደ ሜዳ አህያ ገላ ደማቅና ውብ ነው፡፡ የመጀመሪያው ደረቅ እውነት ነው፡፡ ሁለተኛው ግን ከእውነት በትንሹ ርቋል፡፡ ርግጥ ነው እውነት ነው፤ እውነትነቱ ግን ለሁሉም የሚሰራ ላይሆን ይችላል፡፡ ለአንዳንዱ እውነት ፣ ለአንዳንዱ ኩሽት ሆኖ ግራና ቀኝ የሚዞር ክስተት! ወይም እንደዛ የመሰለ፡፡››
የደራሲው ታሪክ
ገዳሙ በትርፍ ጊዜው ለማንበብና ለመፃፍ እየሞከረ ትምህርቱን ቀጠለ፡፡ እንደሚፈልገው ግን ሊሆንለት አልቻለም፡፡ ጊዜውንና ትኩረቱን ትምህርቱ እየተሻማው ተቸገረ፡፡ በፊትም የፈራው ይህን ነበር፡፡ ስነ-ጽሑፍ ለመምረጥ ፈልጎ የነበረው እንደ ልቡ ለማንበብና ለመፃፍ እንዲመቸው ነው፡፡ አሁን የጤና መኮንንነቱን ትምህርት የሚከታተልበትን ጊዜ እንደ ብክነት ያየዋል፡፡ ‹ጊዜዬን እያቃጠልኩ ነው!› ብሎ ነው የሚያስበው፡፡ ነገር ግን ከትምህርቱ ጋር መታገሉን መቀጠሉ አልቀረም፡፡
ብዙ ጊዜ ለማቋረጥ አስቧል፡፡ ሆኖም የቤተሰቦቹን ተግሳፅና ቁጣ ለማስቀረት ሲል መማሩን ቀጥሏል፡፡ ትምህርቱን አቋርጦ ቢመጣ በዋዛ ፈዛዛ የሚያዩት ወይም የሚያልፉት አልመሰለውም፡፡ ጎረቤት ወይም ዘመድ ይሆናል እንጂ ይሄን ሲሰማ የሚያገን ደግሞ አይጠፋም። ነገር ጎንጉነው የሚመጡም ይኖራሉ፡፡ ከቤተሰብ ጋር መቃቃር ወይም መጋጨት ደግሞ ከባድ ነገር ነው፡፡
ስለ ቤተሰቦቹ ሲያስብ፤ እንዲህ ይላል፡- ‹‹እንዴት ብዬ ላሳምናቸው እንደምችል አላውቅም፡፡ እኔም የማሳመኑ ችሎታ የለኝም፤ እነሱም ለማመን የሚፈቅዱ አይመስለኝም፡፡››
የማይደርስ የለምና ቀኑ ደረሰ፡፡ ገዳሙ የሶስት ዓመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታውን አጠናቆ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡
ስራም ጀመረ፡፡ የስራ ዕድል ያገኘው በተማረው ትምህርት መስክ አይደለም፤ የተመረቀበትን ሞያ እርግፍ አድርጎ በመተው፤ መጽሔቶችና ጋዜጦች ላይ እየፃፈ መኖር ጀመረ፡፡ መጽሐፍትንም ለማሳተም በቃ፡፡ እዚህ የሰፈረው ልብ-ወለዱም፣ የአጭር ልብ-ወለዶች መድበል በሆነው መጽሐፉ ውስጥ ተካቶ ለህትመት የበቃ ነው፡፡

Read 2554 times