Monday, 05 February 2018 00:00

‘የአገር ልጅ፣ ዘው ዘው’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

  “--በፊት ከባልና ሚስቱ አንዳቸው ላይ በሚታይ በተለይ የባህርይ ችግር ነበር ዘመድ የሚከፋው፡፡ አሁን ያውም በአዲስ አበባ፣ ያውም የአፍሪካ ዋና ከተማ
ነኝ በምትል ከተማ፣ ያውም ሰልጥኗል የምንለው ፈረንጅ፣ የጉንዳን ሰራዊት በመሰለባት ከተማ… ‘የአገር ልጅ’ እያሉ ማፈላለግ ቀሺም ነገር ነው፡፡--”
    
    እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በነገራችን ላይ ይቺን ሳልላት እንዳልረሳት ብዬ ነው፡፡ መሀል ከተማ ያለ አንድ የፖስታ ቤት ቅርንጫፍ የተለጠፈ ነው… ‘Update your profile with FREE price!’ ምን ማለት ነው! በነጻ ሳይሆን ‘በነጻ ዋጋ’ ብሎ ነገር አለ እንዴ! ኸረ እባካችሁ ገጽታችንን አታበላሹብን! ቂ…ቂ…ቂ…
ተከታዩ ደብዳቤ ምናልባትም እስካሁን በሆነ ስፍራ፣ በሆነ ሰው የተጻፈ፡ ምናልባትም ወደፊት የሚጻፍ ሊሆን ይችላል፡፡
“ይድረስ ለ… (በጎደለ ሙሉልኝ)
እንግዲህ ዘንድሮ የልብን የሚያዋዩት፣ የሆድን የሚነግሩት ወዳጅ ስለተመናመነ፣አንደኛውን በኦፊሴል ልዘርግፈውና እንደሚያደርግ ያድርገኝ ብዬ ነው፣ይቺን ደብዳቤ ልጽፍ የተነሳሁት፡፡ ይቺን ደብዳቤ የምጽፍላችሁ ሰው፣ ስሜ…ግድየለም ይቅር። በቃ ስምየለሽ በሉኝ፡፡ ስም ቢኖረኝም እንደሌለኝ እቆጥረዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ዘንድሮ ስም መለያ ብቻ ሳይሆን መለያያ እየሆነ ነውና፡፡ በአስተሳሰብና በአመለካከት ሳይሆን በስም ብቻ ሰው ‘የቡድንና የቡድን አባቶች’ ሳይባል የሆነ ቦታ የሚወሸቅበት ጊዜ ነውና፡፡ ከብዙ ሺ ስሞች መሀል የእኔው አንድ ሌላ ስም መሆኑ ቀርቶ የማላውቃቸውን ‘የእነ እንትና ወገን ነው’ ስለሚያስብለኝ፣ ስም የለሽ መሆኑ ይሻለኛል፡፡ እናም… ስሜ ይቅር፡፣ (ሬድዮ ቢሆን ኖሮ በውስጥ መስመር እነግራችሁ ነበር!)
እንግዲህ የተወለድኩት…ይቅርታ፣ አሁንም መስመር ለቀቅሁ መሰለኝ፡፡ እኔ የተወለድኩበት ስፍራ ማንስ አወቀው፣ አላወቀው ምን ያደርግልታል! የትም ልወለድ፣ የትም ሰፈር፣ ጎረቤት በእኔ ስም ገንፎውን ይጠቅጥቅ ለማንስ ምን ይፈይድለታል! “የተወለደኩት…” ብዬ የጀመርኩትን ብጨርሰው ደግ አይሆንም ነበር፡፡ በየቦታው፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ “የትውልድ ስፍራው የት ነው?” እየተባለ አይደል እንዴ፣ በባዶ ሜዳ ቂም እየተያያዝን ያለነው!
ይሄ “የተወለደው፣ እዚህ ነው፣” “የተወለደችው እዛ ነው፣” እየተባለ አይደል እንዴ፣ በተዋደዱ ሰዎች መሀል እየተገባ የአፍራሽ ግብረ ሀይል አይነት የማለያየት ነገር የሚካሄደው! ‘የአንድ መንደር ልጆች ናቸው’ እየተባለ አይደል እንዴ፣ ከአንዱ አፍ እየተነጠቀ ሌላው የሚጎርሰው! ስለዚህ የተወለድኩበት በእኔው ቢቀር ይሻላል፡፡ የኖርኩበትም ሰፈር ቢሆን፣ ለማንስ ምን ያደርጋል!
“የት እንደኖረ ታውቃለህ?”
“የት ነው የኖረው?”
“እንትን ሰፈር”
“አትለኝም! እዛ እኮ ያሉት በሙሉ የእንትን አገር ሰዎች ናቸው!”
ዘንድሮ ‘የእንትን አገር ሰዎች’ እየተባለ ነው፣ ሁሉም አንድ ቅርጫት ውስጥ የሚከተተው፡፡ ስለዚህ የሰፈሩ ነገር ይቅር፡፡ አሁን ለዚያ ወዳጄ፣ “የሰፈሩ ነገር ይቅር” ብዬ ብነግረው ኖሮ፣ ገና ከአፌ እንደወጣ፣ “አጅሬው ምን ተንኮል ቢያስብ ነው፣ የኖረበትን ሰፈር የማይናገረው!” ይለኝ ነበር፡፡ ስለዚህ የኖርኩበት ሰፈር፣ ‘ኦል ኦፍ ዘ አባቭ’ ተብሎ ይያዝልኝ፡፡  
ደግሞ አግብቻለሁ፣ አላገባሁምም ማለት ይቻላል፡፡ አዎ… ዘመድ አዝማድማ ተሰብስቦ ድሮኛል፡፣ ወይንም “ዳርነው” ብለዋል፡፡ ሚስቴ፣ ወይም ሚስቴ ብዬ “ላልክድሽ/ላልክድህ፣“ የተባባልኳትም ብትሆን፣ ምንም የሚያንሳት ነገር የለም፡፡ ትሁና! ጎራዳ ብትሆንስ? ጎራድነትና አፍንጫ ሰልካካነት ከመቼ ወዲሀ ነው፣ የትዳር መለኪያ መስፈርት የሆነው!
አፍንጫ ቢገተር እንደ በር እንጨት
በደም ይበልጡሻል እነጎራዲት
--የተባለው እኮ በባዶ ሜዳ አይደለም፡፡ እንዴ ቆንጆ ዳሌ አላት ከማለት፣ ቆንጆ ጠባይ አላት ማለት ማንን ገደለ! በቀደም ዓይናቸውን ካየሁት ብዙ የከረሙ፣ የገጠር ዘመዶቼ፣ የምንኖርበት ኮንደሚኒየም መጡ፡፡ ብቻ ሰላምታ አቅርበውልኝ ሳይበቃቸው፣ በቅጡ እንኳን ሳይቀመጡ አንዱ…
“ጎሽ! ጎሽ! ቤት ማለት እንዲህ ነው፣” ይላል፡፡ ሌላኛው ደግሞ…
“ሰማይ ቤት የገባሁ መስሎኝ ወከክ ነው ያልኩት፣” እያለ አሞጋገሱኝ፡፡ ለዚቹ ለእኔ ኮንዶሚኒየም! ብቻ እዚህ ግባ የሚሉት እቃ ባይኖርም፣ ይሄ አርባ ምናምን ኢንች ፍላትስክሪን ቴሌቪዥን እኮ የላስቲክ ቤትን ሁሉ አምስት ኮከብ ሆቴል ባያስመስል ነው! የምከፍለውን ኪራይ ብነግራቸው ኖሮ፣ አገር ቤት ተመልሰው፣ አልቤናቸውን ወልውለው ባይመጡ ነው! በእኔ በዘመዳቸው፣ በእኔ በስጋቸው፣ በእኔ ‘የአገራቸው ሰው’ ላይ እንዲህ አይነት መጠነ ሰፊ ጥቃት ሲካሄድ፣ ዝም ብለው አያዩም ነበራ!
ሚስቴን ከዛ ቀደም አይተዋት አያውቁም፡፡ እንደው ከዛች የጥበቃ ቤት ከምትመስለው መኝታ ቤት፣ብቅ ስትል የጎሪጥ አየኋቸው፡ መጀመሪያ ግራ የተጋቡም፣ የተደናገጡም መሰሉ፡፡ ከዛ ቃል ሳይወጣቸው ተነጋገሩ፡- “እውነት ሚስቱ ነች፣ ወይስ የመሥሪያ ቤት ጓደኛው?” እንደተባባሉ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ከጥቂት ሴኮንዶች በፊት በብርሀን ፈክቶ የነበረው ፊታቸው፣ መከረኛው መብራታችን ሲቋረጥ፣ ምጣዱ ላይ መልኩ የሚበላሸውን እንጀራ መስለዋል፡፡ መጀመሪያ ነገር እነሱ ቆንጆ ብለው እንደሚያስቡት አይነት አይደለችም፡፡ “አወይ ደረቷ፣ አወይ ዳሌዋ” የሚባልላት አይነት አይደለችም። ለነገሩ እኔም ያገባሁት ዳሌና ደረት አይደለም፡፡ ግን በዘመድ አዝማድ መሀል እንዳልተቀባ ንጉሥ የምታየው ሰው፣ የሂሳብ ሠራተኝነቴ ሌላው በህልሙ እንኳን የማያገኘው ጸጋ ተብሎ የሚቆጠርልኝ ሰው፣ እንዴት ነው ይሄን ለእነሱ የማስረዳቸው!
የእነሱን የቁንጅና መስፈርት ካለማሟላቷ ይልቅ ዋናው ችግር ሌላ ነው፡፡ ‘የአገራቸው ልጅ’ አይደለችም፡፡ ስንት ምን የመሳሰለች ‘የአገር ልጅ’ እያለች፣ ለእነሱ ከሞንጎላዊት የባሰ ባዳ የሆነች ሴት ማግባቴ፣ ሊዋጥላቸው አልቻለም፡፡
 በፊት ከባልና ሚስቱ አንዳቸው ላይ በሚታይ በተለይ የባህርይ ችግር ነበር ዘመድ የሚከፋው። አሁን ያውም በአዲስ አበባ፣ ያውም የአፍሪካ ዋና ከተማ ነኝ በምትል ከተማ፣ ያውም ሰልጥኗል የምንለው ፈረንጅ፣ የጉንዳን ሰራዊት በመሰለባት ከተማ… ‘የአገር ልጅ’ እያሉ ማፈላለግ ቀሺም ነገር ነው፡፡
ሚስቴም ነገሩ ገብቷታል፡፡ ለነገሩ የእሷም ዘመዶች የመጡ ጊዜ፣ ገና ሲያዩኝ፣እንቆቆ ሙሉ የጨለጡ ይመስል ነው ፊታቸውን ያጠቆሩብኝ። የነሀሴ ቀን ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት እንኳን እንደዛ አይጨልምም፡፡ የእኔ ዘመዶች በልተው፣ ጠጥተው ከጨረሱ በኋላ ፈክተው እንደገቡ ጨልመው ወጡ፡፡ ቀዬአቸው ከደረሱ በኋላ፣ “አሉህ” ተብሎ የተነገረኝ ነገር…አለ አይደል… ለካ ሰዋችን…
አልታይህ አለኝ የአገሬ ሰማይ
እንዲህ ሆዴ ቆርጦ እርቄያለሁ ወይ  
--የሚለው ወዶ አይደለም ያስብላል፡፡
በነገራችን ላይ ያን ጊዜ ሚስቴ ተሰማት። ተሰማት ብቻ ሳይሆን ጠባዩዋ ተለዋወጠብኝ፡፡ ቢያንስ ምንም እንኳን በላጤነት ስንኖር ብዙ ዘመን የሆነን ቢሆንም፣ “ሁለቱም ተለዩ ከእናት ካባታቸው…” የተባለ ጊዜ ጠባዩዋ ወርቅ ነበር፡፡ በፊት እኮ ሥራ ውዬ ቤት ስገባ፣ ‘እንደ ፈረንጅ’ እንደሚባለው እንሆን ነበር፡፡ አይደለም ‘የተለመዱት፣’ ፊልም ላይ ያየነው፣ ሁሉ አይቀረንም ነበር፡፡ ቤቴ ውስጥ በእርግጠኝነት የሌለ ነገር የተደበቀ ካሜራ ነው፣ስለሆነም ‘ከተቆለፈ በር ጀርባ’ ለሚደረጉ ነገሮች፣ ዲሞክራሲ ያለ ገደብ ያለበት ስፍራ የእኔ ቤት ነው፡፡
እነኛ ዘመዶቼ መጥተው ከሄዱ በኋላ ግን በስነስርአቱ እንኳን “እንዴት ዋልክ?” አትለኝም፡፡ “‘የአገሬ ሰው’ አለመሆኗ ተሰማት እንዴ!” እያልኩ ነው፡፡ ደህና ስንሻገረው የከረምነው ‘የአገር ልጅነት’ ጉዳይ… ነገሩ ሁሉ እየተበላሸ ሲሄድ ፣“የእኛንም በር እያንኳኳ ነው እንዴ!” እያልኩ ነው፡፡
እንግዲህ መከራውን ሲያመጣው አንዴ አይደል… የእኔንም አንዴ አመጣው፡፡ የቤቴ አልበቃ ብሎ አንድ ቀን በድንገት፣ መሥሪያ ቤቴ፣ከምሠራበት ደረጃ ዝቅ አደረገኝ፡፡ (“አውርደው ፈጠፈጡኝ!” ማለቱ፣ ነገር ያገንብኛል ብዬ ነው፡፡) ምን አጠፋሁ! “ሥራ ላይ ጥይት ነው፣ የምባል፣ ታታሪ ሠራተኛ አይደለሁም እንዴ!  ነኝ…ግን ደግሞ ‘ያልሆንኩት’ ነገር ነበር፡፡ መሥሪያ ቤቱን የተቆጣጠሩት ሰዎች ‘የአገር ልጅ’ አይደለሁም፡፡ የእኔ ወንበርም፣ “ከበላይ አካል ተልኮ ነው፣” የእነሱ ‘የአገር ልጅ’ ተሰጠ፡፡ የቀጠሩኝ በሙያዬ እንዳገለግል አይደል እንዴ! ከየትም ልምጣ፣ ከየትም ልብቀል፣ ምን አገባቸው! (በእርግጥ፣ ዘንድሮ እንዲህ አይነት ‘ዲስኩር’ የሞኝነት ነው፡፡)”
እናም…በሄደበት ሁሉ ‘የአገር ልጅ’ የሚለው ነገር፣ መተንፈሻ እያሳጣው ያለ ምስኪን፣ እንዲህ ብሎ ጽፎም፣ ሊጽፍ አስቦም ይሆን ይሆናል፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1946 times