Monday, 05 February 2018 00:00

የወልቂጤ ህዝብ ጥያቄዎችና የአመራሩ ምላሽ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

  · ዓለም ባንክ ማረጋገጫ ሲሰጥ ከተማዋ ትለማለች ብለን ተስፋ እናደርጋለን
     · ህዝቡ ከልማቱ አልተጠቀመም የሚለው ትክክለኛ ነው
     · ባለሃብቶች ቅጥባጣ የግብር አወሳሰን፣ በተንዛዛ ቢሮክራሲ ከከተማዋ እየወጡ ነው

    ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ ብዙ ሺ የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች ወደ አደባባይ ወጥተው ስላማዊ ሰልፍ በማድረግ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ የህዝቡ ጥያቄ ዘርፈ ብዙ ቢሆንም በዋናነት ህዝቡን ለአደባባይ ያበቃው ግን በ2007 ዓ.ም ከጣሊያን በተገኘ ፈንድ ሆስፒታል ሊገነባ በቀድሞው የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የመሰረት ድንጋዩ ተጥሎ የነበረ ሲሆን ላለፉት አራት ዓመታ በጉጉት ቢጠበቅም የውሃ ሽታ ሆኖ መቆየቱ አንዱ መሆኑን የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡
የወጣቶች የስራ ዕድል ማጣት፣ የውሃና የመብራት ችግር፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድና መብራት አለመኖር የከተማዋ ተወላጆች በከተማዋ ኢንቨስት ለማድረግ የሚያቀርቡት ጥያቄ በአግባቡ አለመስተናገድ ከዋናዎቹ ችግሮች ይጠቀሳል፡፡ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ እርስቱ ይርዳ ለወልቂጤ ወጣቶች ምላሽ ለመስጠት ዛሬ በወልቂጤ እንደሚገኙ የአዲስ አድማስ ምንጮች ገልፀዋል፡፡ ለመሆኑ ቃል የተገባው ሆስፒታል ለምን ሳይገነባ ቀረ?  የከተማዋ እድገት ማነቆ የሆኑት የመሰረተ ልማት ችግሮች በምን መልኩ ይፈታሉ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከዞኑ አስተዳዳሪ ከአቶ መሐመድ ኮርንማ ጋር በህዝቡ ጥያቄዎች ዙሪያ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡

    የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ ባለፈው ሳምንት በተለያዩ የልማት ችግሮች ምክንያት ሰላማዊ ሰልፍ ያደረገ ሲሆን ዋናው ከ8 ዓመት በፊት የመሰረት ድንጋይ ተጥሎለት ሳይገነባ የቀረው ሆስፒታል ግንባታ ጉዳይ ነው ተብሏ። እስኪ በዚህ ላይ ማብራሪያ ይስጡኝ …
እርግጥ ነው ህዝቡ የተለያዩ የልማት ጥያቄዎችን አንግቦ፣ በአደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ አድርጓል። የሆስፒታሉም ጉዳይ እውነት ነው፡፡ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ አማካኝነት የመሰረት ድንጋዩ ተቀምጦ ነበር፡፡ ሆስፒታሉ አልተገነባም፡፡፡
ለውስጥ አስፓልትና መብራት የላትም፣ የመንገድ መብራትም የላትም፣ ከፍተኛ የኃይል እጥረት አለባት፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ተሰማርተው የማኑፋክቸሪንግ ስራ የሚሰሩ ወጣቶች በኃይል እጥረት ስራቸው እየተጓተተ ነው፣ ወጣቱ የስራ እድል ተጠቃሚ አይደለም… የሚሉና ተያያዥ የልማት ጥያቄዎችን አንስቶ ነው፤ ህዝቡ ሰላማዊ ሰልፉን ያደረገው፡፡
እነዚህ የልማት ጥያቄዎች ተገቢ ናቸው፡፡ መመለስ አለባቸው፡፡ ልማታዊው መንግስትም ሆነ የዞኑ አስተዳደር፤ ልማት የሞት ሽረት ጉዳይ ነው በሚል የሚሰራ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የህዝቡ ጥያቄዎች ጤናማ ጥያቄዎች ናቸውና ምላሽ ሊያገኙ ይገባል በሚል፣ ሰሞኑን ከህዝቡ ጋር እየተወያየንና ምላሽ እየሰጠን ነው፡፡
ከነዋሪው እንደሰማነው፤ በወልቂጤና በአጎራባች ያለው የህዝብ ብዛት ከ250 ሺህ በላይ በመሆኑ ሆስፒታሎች ያስፈልገዋል፡፡ ህዝቡ በጉጉት ሲጠብቅ የነበረው የዚህ ሆስፒታል የመሰረት ድንጋይ መፈረካከሱን፣ በቦታው ላይ ህገወጥ ቤቶች መገንባታቸውን፤ እንደውም ቦታው በሊዝ ለሌላ መተላለፉንና የሆስፒታሉ ግንባታ ወደ ሌላ ቦታ ተዛውሯል የሚሉ ቅሬታዎች ከህዝቡ ይነሳሉ፡፡  በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
እርግጥ ነው የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ አንቶኒዮ ከተባለ አንድ የቢዝነስ ሰው ጋር ተነጋግረውና ተስማምተው፣ በዚህ ሰው ፈንድ ነበር ሊገነባ የነበረው እንጂ በኤምባሲው በኩል የተደረገ ስምምነት አልነበረም፡፡ ነገር ግን የመሰረት ድንጋዩ ሲጣል የጣሊያን አምባሳደር በስፍራው በክብር እንግድነት እንደነበሩ መረጃው አለኝ፡፡ የመሰረት ድንጋዩ ሲጣል የህዝቡ ደስታና ጉጉት የደመቀ ነበር፡፡ ነገር ግን አራት ዓመት ሙሉ ቢጠበቅም እውን አልሆነም፡፡ በሌላ በኩል ቦታው በሊዝ ለሌላ ተላልፏል፡፡ ግንባታው ወደ ሌላ ክልል ተዛውሯል… የሚባለው ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ህገ ወጥ ግንባታ ከተሞች ላይ ይኖራል፡፡ በዚያ ቦታ አይደለም በሌላ ቦታም ይኖራል፡፡ የህዝብን የጤና ጥያቄ በጋራ ሆነን፤ እውን የምናደርግበት ጊዜ ላይ ስንደርስ እነዚህን ህገ ወጥ ግንባታዎች እናነሳለን። በአጭሩ ቦታው የሆስፒታሉ ነው፤ ማንም ሊደፍረው አይችልም፡፡ የመሰረት ድንጋዩ ዝም ብሎ አራት ዓመት ሲቆይ ሊፈረካከስ ይችላል ወይም ሊተናኮስ የፈለገ አካል ጉዳት አድርሶበት ይሆናል እንጂ የከተማው ወይም የዞኑ አስተዳደር ፍላጎት አይደለም፡፡ ህገ ወጥ ግንባታዎችን በሂደት የማጥራት ስራ እንሰራለን፡፡ ሆስፒታሉ ቀድሞ በታሰበው፣ በእነ /ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የሚያመጡት ፈንድ ተሳክቶ ከተሰራ እሰየው፡፡ ይህ ካልሆነ ክልሉና ዞኑ በጋራ ይገነባዋል፡፡ ይህን እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይችላል፡፡
እናንተ ሆስፒታሉ ለምን እንዳልተገነባ ክትትል አላደረጋችሁም?
ለምን እንዳልተገነባና ፈንዱ ለምን እንደቀረ፣ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ጽ/ቤትና የጉዳዩን አስተባባሪዎች በመጠየቅ ምላሽ ልታገኙ ትችላላችሁ። የፈንዱ ባለቤቶች ወደዚህ ገንዘቡን ይዘው መጥተው እንዲገነቡ፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት አስተባባሪዎች መስራት የሚገባቸውን ባለመስራታቸው ነው ሳይገነባ የቀረው፡፡ ወደ ሌላ ቦታ ተዛወረ ለሚለውም ያኔ ገንዘቡን አምጥቼ እገነባለሁ ብሎ የመሰረት ድንጋይ የጣለው አንቶኒዮ፤ ሌላ ቦታ ሲገነባ አላየነውም፡፡ ቢገነባ ኖሮ ይታይ ነበር፡፡  
ሌላው ህዝቡ ያነሳው ጥያቄ፤ ከተማዋ አንድ የፌደራል መንገድ ብቻ ነው ያላት ይህ መንገድ ከአዲስ አበባ ጅማ የሚሄደው ነው፡፡ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ህግ መሰረት፤ እንደዚህ አይነት የፌደራል መንገዶች የዞን ከተማ ላይ ሲደርሱ ደብል ይሆናሉ ይላል። ወልቂጤ የዚህ ተጠቃሚ አይደለችም፤ በከተማዋ ትልልቅ ተሽከርካሪዎች በብዛት የሚተላለፉባት ከተማ በመሆኗ በየቀኑ በርካታ ባጃጆች ላይ አደጋ ይደርሳል ይላሉ። በሌላ በኩል ከተማዋ የውስጥ ለውስጥ መንገድና የመንገድ መብራት የሌላት ብቸኛ ከተማ በመሆኗ ሰው ለዝርፊያና ለአደጋ የተጋለጠ ነው፡፡ ለቡታጅራና ለወልቂጤ ከተሞች 14 ኪ.ሜ የውስጥ ለውስጥ መንገድ እንዲሰራ ተፈቅዶ፤ ቡታጅራ ላይ የተወሰነው ሲሰራ፣ ወልቂጤ ምንም አልተሰራም የሚል ነው፡፡ በዚህ ላይስ የአስተዳደሩ ምላሽ ምንድነው?
 የመንገዱን ጉዳይ በተመለከተ እርግጥ ነው ከተማዋ የውስጥ ለውስጥ መንገድ የላትም፡፡ እኛ እንደምናውቀው የውስጥ ለውስጥ  የአስፋልት ስራዎች የሚሰሩት የከተማው ገቢ ለኮብልስቶን፣ ለአስፋልትና የውስጥ ለውስጥ የፖል ዝርጋታ በመመደብ የሚከናወን ነው። ሁለተኛው በሌሎች ከተሞች የ “DGDP” ተጠቃሚ በሚሆኑበት ጊዜ ለዚህ የሚሆን ፈንድ ከዓለም ባንክ እያገኙ የሚሰሩበት አንዱ ሂደት ነው፡፡
DGDP ምንድን፣?
ለከተሞች የተለያዩ ስታንዳርዶች ይወጡና፣ ያንን መስፈርት ለሚያሟሉ ከተሞች፣ የዓለም ባንክ በጀት እየመደበ፣ በዚህ በጀት ከተሞች መሰረተ ልማቶችን የሚሰሩበት ሂደት ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ የራሱ ሂደት አለው። የህዝብ ብዛት ጉዳይ…  የተለያዩ መስፈርቶችም አሉት፡፡ ከዚህ አኳያ ወልቂጤ ተጠቃሚ አይደለችም፡፡ ሌሎች አንዳንድ ከተሞች ናቸው፡፡
እናንተ በዚህ ፕሮጀክት ከተማዋ ተጠቃሚ እንድትሆን ያደረጋችሁት ጥረት አለ?
አዎ! ወልቂጤ በዚህ ፈንድ ተጠቃሚ እንድትሆን ጥናት ተጠንቶ፣ ወደ ክልል የተላከ ሲሆን፣ ክልሉ ደግሞ ወደ ፌደራል በመላክ፣ አሁን ጉዳዩ ለዓለም ባንክ ቀርቧል። ዓለም ባንክ ማረጋገጫ ሲሰጥ ከተማዋ ትለማለች ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ያ ብቻም አይደለም፡፡ እኛም የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መሰራት እንዳለበት ስለምናምን፣ የዞኑ አስተዳደር 5.5 ኪ.ሜ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ለመገንባት  አቅደን ባለንበት ወቅት ነው  ጥያቄው የተነሳው፡፡ አሁን  ለ5.5 ኪሎ.ሜትር የመንገድ ስራ በጀት ይዘን፣ የዲዛይን ስራ መሠራት አለበት በሚል አቅጣጫ አስቀምጠናል። ዋናው መንገድ ለምን ደብል አልሆነም ለተባለው፤ ይሄ መንገድ የቆየ መንገድ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ጅማ የተሰራ ነው፡፡ ምናልባት መንገዱን ታውቂው ከሆነ፣ ቱሉ ቦሎም ላይ፣ ወሊሶም ላይ እንዲሁ ወልቂጤም ላይ ደብል መንገድ የለም፡፡ ምክንያቱም መንገዶቹ በቀድሞ ዲዛይን የተሰሩ በመሆናቸው ነው፡፡ መሰረታዊ ችግሩ ግን ወልቂጤ ከፍተኛ የሆነ የትራንስፖርት ምልልስ ያላት፣ ቁርስና ምሳ የሚበላባትና ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ያለባት ከተማ በመሆኗ፣ መኪኖች ይጨናነቃሉ፡፡ ደብል መንገድ አያስፈልጋትም ወይ? በጣም ያስፈልጋታል፡፡ ወይም ሌላ ተለዋጭ መውጫ መንገድ ያስፈልጋታል። የህዝቡን ጥያቄ እዚህ ላይ ትክክል የሚያደርገው፣ ለምሳሌ ወልቂጤ ላይ የብስክሌት ውድድር ቢኖር፤ ያው አንድ መንገድ ይዘጋና መውጫ የለም፡፡ የጥምቀት በዓል በሚከበርበት ጊዜ፣ ታቦት ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው ቦታ ሲንቀሳቀስ የመተላለፊያ መንገድ የለም፤ ስለዚህ የውስጥ ለውስጥም ሆነ ደብል መንገድ የግድ አስፈላጊ ነው። አሁን በቅርቡ አንድ ጠጠር መንገድ፣ ከክልል ገጠር መንገድ ጋር በመተባበር ሰርተናል፡፡ ልማት ለማረጋገጥ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ አንዱ የነገርኩሽን የጠጠር መንገድ ሰርተናል፡፡  የ5.5 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ አስፋልት ለመስራት ደግሞ ዝግጅት ተጠናቅቋል፡፡
ሌላው የውሃ እጥረትን በተመለከተ የተነሳው ችግር ነው፤ አካባቢው የውሃ ሀብት ችግር እንደሌለበት ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡  በከተማዋ 40 ኪ.ሜ ራዲየስ “ፍቅር ውሃ”፣ “ኤደን ውሃ” እና “ዋው ውሃ” በስፋት እየተመረቱ ሲሆን  በቅርቡ “ኬር” የተሰኘ ውሃ ደግሞ ለምርት እየተዘጋጀ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከአመታት በፊት ጥናት ተጠንቶ፣ ለ400 ዓመት ያለ ማቋረጥ ህዝቡን ያገለግላል የተባለ የውሃ ማዕከል ከከተማዋ 20 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ቢመረቅም ውሃ ከከተማው እንደ ቀልድ ለሁለትና ሶስት ወር እንደሚጠፋ በምሬት ይናገራሉ፡፡ የውሃስ ችግር ከምን የመነጨ ነው?
ውሃን በተመለከተ የሐይል ችግር የለበትም፡፡ የሶርስ ችግርም የለበትም፡፡ ከቦዤ ባህር እየመጣ ነው፡፡ ነገር ግን የሚመጣው ውሃ ቀድሞ በነበሩ ጥልቅ ጉድጓዶች ሲስተም ላይ ነው የተተከለው፡፡ ሲስተሙን የማሻሻል ስራ በመስራት፣ የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ማደግ እንዳለበት ተገንዝበናል፡፡ ሌላው የፓምፕ ችግሮች ነበሩ። ፓምፖቹ ችግር በገጠማቸውና በተቃጠሉ ቁጥር ወደ ታንከር የሚገባው የውሃ መጠን ማነስ ጀምሮ ነበር። ይህን ችግር ተመልክቶ፣ ዞኑ በሰራው ስራ ቀድሞ በሰባት ቀናት ይመጣ የነበረው ውሃ፣  አሁን በሁለትና በሶስት ቀን ህዝቡ እንደሚያገኝና ችግሩ እንደተሻሻለ ነው መረጃው ያለን፡፡ እርግጥ ነው የሚቀር ስራ አለ፡፡ ይሄውም መስመሩን የማሻሻል ነው፡፡ ሌላው ሰው ሰራሽ ችግሮች እየተፈጠሩ ቆይተዋል፡፡
እንዴት ዓይነት…?
ለምሳሌ የውሃ መስመር መቁረጥና የውሃ አገልግሎት ውስጥ የተዛባ አፈፃፀም ነበረ  በሙስና ለባለሀብትና ለግለሰቦች በመስጠት፣ ሌላው ላይ እጥረት ሲፈጥሩ የቆዩ በመሆኑ፣ እነዚህን ሰው ሰራሽ ችግሮች የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድና ግንዛቤ በመፍጠር አርመናል። አሁን የውሃው ችግር የተጋነነ አይደለም፡፡ ነገር ግን አሁንም የውሃ አቅም አለ፡፡ ቅድም  400 ዓመት  ትክክል አይደለም፡፡ ምናልባት ከ20-40 ዓመት ቢሆን ነው፡፡ ይህንን አቅም በተሻለ ለመጠቀም፣ መስመሮችን የማሻሻል ስራ በመስራት ለውጥ ለማምጣት፣ ፕሮጀክቶችን በመለየት ላይ ነው ያለነው፡፡ የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ ማለት ነው። አፋጣኝ ምላሽ ለሚሹት አፋጣኝ ምላሽ እየሰጠን እንቀጥላለን፡፡ በአጠቃላይ ግን ወልቂጤ እንደሌሎች ከተሞች አላደገችም፤ አልለማችም። ህዝቡም ከልማቱ አልተጠቀመም የሚለው ጥያቄ ግን ተገቢም ትክክለኛ ነው፡፡
ሌላው የህዝቡ ጥያቄ የከተማዋ የወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ አለመሆን ነው፡፡ የፌደራል መንግስት  ለወጣቶች የስራ ፈጠራ 10 ቢ. ብር መድቦ ሳለ፣ የወልቂጤ ወጣቶች ድርሻ የት ገባ? የሚል ነው፡፡  የኮብልስቶን ስራ እንኳን በሙስና የተተበተበና በተለያየ የቤተሰብ ስም የተደራጁ ጥቂት ሰዎች የሚያንቀሳቅሱት ነው ይባላል፡፡ በሌላ በኩል፤ የከተማዋ ተወላጅ የሆኑና በሌላ አካባቢ የሚኖሩ ባለሀብቶች ከተማዋ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የሚጠይቁት ጥያቄ በአግባቡ ስለማይመለስ፣ ከተማዋ ውስጥ በሆቴልና በሌላ የንግድ እንቅስቃሴ የተሰማሩ ባለሀብቶች ቅጥ ባጣ የግብር አወሳሰንና በተለያዩ ቢሮክራሲዎች ተማርረው፣ ድርጅቶቻቸውን እየዘጉ ከከተማዋ እየወጡ በመሆኑ የከተማዋ ልማትና እንቅስቃሴ የባሰ ችግር ውስጥ ወድቋል ይላል ህዝቡ ይህንን እንዴት ያዩታል
የስራ እድል ፈጠራ ቅድም እንዳነሳሽው፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው፡፡ የዚህን አካባቢ ወጣቶች ድርሻም ወደ ታች በማውረድ ረገድም ምንም ክፍተት የለም፡፡ አሁን እዚህ ከተማ ውስጥ ያለው አመራር፣ ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ ወጣቶቹን ለይቶ፣ አብቅቶና አደራጅቶ ወደ ስራ በማስገባት ረገድ ያለው አፈፃፀም ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህንንም በትኩረት መስራት አለብን፡፡ ጉዳዩ መሻሻል አለበት በሚል የለየነው አንዱ ዘርፍ ነው፡፡
ባለሀብቶች ወደ አካባቢው መጥተው ኢንቨስት ለማድረግ እየተቸገሩ ነው፣ ተገቢ ምላሽ እያገኙ አይደለም፤ መሬት እየቀረበ አይደለም የሚለው ጥያቄ ተገቢ ነው፡፡ የኢንዱትስትሪ ዞን በሚል የሚከለለውን ቦታ፣ በመሰረተ ልማት ጠግኖና አሟልቶ፣ የመብራት የመንገድና ሌሎችንም መሰረተ ልማቶች በመዘርጋት፣ መሬት ለይቶ፣ ለባለሀብቱ በማቅረቡም በኩል ያለውን የአፈፃፀም ዝቅተኛነት፣ ማሳደግ አለብን የሚለውን ወስደናል፡፡ አሁን ስብሰባ አቋርጩ ነው የማናገርሽለ ያልተመለሰ ካለ ሌላ ጊዜ እንገናኛለን፡፡

Read 4876 times