Saturday, 27 January 2018 12:41

“ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር” ኮንሰርት - ተጀምሮ እስከሚያልቅ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 ባለፈው እሁድ በባህርዳር የተካሄደው “ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር” የተሰኘው የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት እንቅፋት ገጥሞት እንዳይበጠበጥ ከፍተኛ ጥንቃቄና ዝግጅት መደረጉን የኮንሰርቱ አስተባባሪዎች ይናገራሉ፡፡ ጥቂት ሰዎች ተሰባስበው ወደ አደባባይ በወጡ ቁጥር ተቃውሞና ግጭት እየተፈጠረ፣ ዜጎች ህይወታቸውን በሚያጡበት በዚህ አስፈሪ ወቅት በስኬት መጠናቀቁ ብዙዎችን አስደንቋል፡፡
በኮንሰርቱ ላይ የታደመችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከአስተባባሪዎቹ ሁለቱን እንዲሁም “ከማር እስከ ጧፍ” ቪዲዮ ክሊፕ ላይ በዛብህን ወክሎ የተጫወተውን ወጣትና የሜካፕ ባለሙያዋን አነጋግራቸዋለች፡፡ እነሆ፡-

              በሰላምና በስኬት መጠናቀቁ ብዙዎችን አስደንቋል
             “በዛብህን ሆነህ ትሰራለህ ስባል፣ በህልሜ ነበር የመሰለኝ”
                አምሳለ ገነት፤ የ“ከማር እስከ ጧፍ” በዛብህ)

   ተወልጄ ያደግኩት ጎጃም፣ ናዳ ማርያም በተባለ የገጠር መንደር ውስጥ ነው፡፡ በህፃንነቴ ቄስ ት/ቤት ተምሬአለሁ፡፡ በትውልድ መንደሬ፣ እስከ 4ኛ ክፍል ተምሬ፣ ትምህርቴን ለመቀጠል ወደ ባህርዳር መጣሁ፡፡ ባህርዳር በቆየሁባቸው ጊዜያት ወደ ኪነ-ጥበቡ ጎራ በማለት፣ የተለያዩ አጫጭር ስልጠናዎችን ወሰድኩ፡፡    በሙሉ አለም የኪነጥበብ አዳራሽ ለዕይታ የበቁ ስድስት ቴአትሮችን ሰርቻለሁ፡፡ እነሱም፡- “የእውነት ሞት”፣ “መልዕክተኛው”፣ “ራስን በራስ”፣ “ባልና ሚስት”፣ “መጨረሻው” እና “የሰፈር እድር” ናቸው፡፡
ወደ “ማር እስከ ጧፍ” የገባሁበት አጋጣሚ፣ በጣም የሚገርምና ለማመን የሚከብድ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴአትሪካል አርት ት/ቤት መምህር የሆነው ሰለሞን ጋሻው፣ ለ25 ቀናት፣ በሙሉዓለም የባህል አዳራሽ ስልጠና ይሰጥ ነበር፡፡ እኔም በወቅቱ፤ “መልዕክተኛው” የተባለውን የገጠር ሰፊ ገፀ-ባህሪ ወክዬ እሰራ ነበር፡፡ ከዚያ ልዑል ተፈሪ የተባለ ልጅ መጥቶ፣ “ፎቶ ፈልጌ ነው፤ ላንሳህ” አለኝ፤ እሺ ብዬ ተነሳሁ፡፡ “ከመድረክ ስትወርድ እፈልግሃለሁ” ብሎኝ ሄደ፡፡
በነጋታው ጠዋት 1፡00 ላይ ደወለና፣ “ሙሉዓለም የባህል ማዕከል እንገናኝ” አለኝ፤ ተገናኘን፡፡ “በቴዲ አፍሮ ማር እስከ ጧፍ ላይ የበዛብህን ገፀባህሪ እንድትሰራ ተመርጠሃል፤ ነገ ወደ ማርቆስ ሄደህ ሰው አናግር” አለኝና፤ ሰርክአዲስ ከምትባል ልጅ ጋር አገናኘኝ፡፡ በነጋታው ደብረማርቆስ ሄድኩኝ፣ እኔ በሄድኩ በነጋታው አምለሰትም መጣች፡፡ ወደ ሥራ ገባን፡፡
ሆኖም መጀመርያ ላይ አላመንኩም ነበር፤ በህልሜ ነው የመሰለኝ፡፡ አንደኛ ስራው እንደሚሰራ አልሰማሁም፤ ብሰማም እኔ እመረጣለሁ ብዬ አላስብም፡፡ ሁለተኛ ከቴዲ አፍሮ ጋር መስራት፣ ለእኔ ምን ማለት እንደሆነ አስቢው፡፡ የሆነ ሆኖ ህልም ሳይሆን እውን ሆኖ፣ ወደ ስራው ገባን፡፡ ደስ በሚል ቆይታ፣ የተዋጣ ስራ ሰራን፡፡  ከቴዲ አፍሮ ጋር እቤቱ ተገኝቼ አውርተናል፡፡ ቴዲ ድምፃዊ ብቻ ሳይሆን መምህርም ጭምር ነው፡፡ ራሴን ከጠበቅሁና ጠንቃቃ ከሆንኩ፣ ብዙ ነገር መስራት እንደምችል ነግሮኛል፡፡፣
ወደፊት ለመራመድ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አስተምሮኛል፤ተገቢውን ምክር መክሮኛል፡፡ በአጠቃላይ ቴዲ ተምሮ የሚያስተምር፣ ትልቅ መምህር ነው፡፡ በስራዬ ደስተኛ ነኝ፤ ከቴዲ ጋር በመስራቴም እድለኛ ነኝ፡፡
ወደ ኮንሰርቱ ስመጣ፣ በኮንሰርቱ ላይ ያየሁት የባህርዳር ወጣቶችን ትህትናና ታላቅነት ነው፡፡ ወጣቶቹ፤ “የቴዲን ጉዳይ ለእኛ ተውት” ብለው ሃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣታቸው፣ እኔም በግሌ እንደ ወጣትነቴ በጣም ተደስቻለሁ፡፡ ከአራት ዓመት በኋላ ያውም በምኖርባት ከተማ፣ ይህ ታሪክ ሲሰራ ሳይ፣ በቃላት የማልገልፀው ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ ለከተማዋም ለህዝቡም ትልቅ ድል ነው፡፡ ሁላችንም፤ እንኳን ደስ ያለን!! ለማለት እፈልጋለሁ፡፡

----------------

            “ለኮንሰርቱ መሳካት የባህርዳር ወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነው”
              (ተሾመ አበበ፤ የኮንሰርት አስተባባሪ)


     የባህርዳ ከተማ ነዋሪ ነኝ፡፡ የተሾመ መልቲ ሚዲያ ፕሮሞሽን ባለቤት ስሆን በአማራ ቴሌቪዥን “የቴክኖሎጂ ሰው” ፕሮግራምን አዘጋጃለሁ፡፡ በአስተባባሪነት የተመረጥኩት ከተማው ላይ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን፣ በማደርገው የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ ስለምታወቅ ነው፡፡ ኮንሰርቱ ያለ እንከን በስኬት እንዲጠናቀቅ በጣም ስንሰራ ነበር፡፡ አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ፣ ኮንሰርቱ እንደሌሎች ኮንሰርቶች፣ ተቃውሞ እንዳይገጥመው የሚል ስጋት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ይህንን ስጋት ለማስቀረት በመጀመሪያ ከተማው ላይ የምንታወቅ 20 ወጣቶች ተመረጥን፡፡ በኋላ አራት ተጨመሩና 24 ሆንን፡፡ እያንዳንዳችን በስራችን፣ አስር አስር ወጣቶችን እንድንመለምል ተደረገ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስራችንን ጠንክረን መስራት ጀመርን፡፡ የከተማው ህዝብ ደግሞ ኮንሰርቱን ለመታደምም ሆነ ችግር ቢፈጠር አጋር ሆኖ ለማገዝ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው፡፡ አስተባባሪ ኮሚቴው፤ በስራው ላይ እንከን እንዳይገኝ ከአስተዳደሩ፣ ከከንቲባ ጽ/ቤት፣ ከኮሚኒኬሽን ጽ/ቤትና ከቴዲ ማናጀር አቶ ጌታቸው ማንጉዳይ ጋር የተለያዩ ስብሰባዎችንና ምክክሮችን አድርገናል….
ያ ሁሉ ህዝብ ገብቶ ኮንሰርቱ ያለ እንከን በመጠናቀቁ፣ እድለኞች ነን፡፡ የሚገርምሽ ኮንሰርቱ ምን እንደሚመስል አላየሁትም፡፡ ምክንያቱም በማስተባበሩ ስራ ላይ ነበር ያተኮርኩት፡፡ ሁላችንም የየድርሻችንን፣ እንግዳ ከመቀበል፣ ትኬት ከመፈተሽና ወደ ውስጥ ከማስገባት ጀምሮ በጥሩ ሁኔታ ሰርተን ነው የተጠናቀቀው፡፡ በሰላም ለመጠናቀቁና ለመሳካቱ አስተዋፅኦ ያላቸውን ሁሉ እናመሰግናለን፡፡ ኮንሰርቱ በመካሄዱ ከተማዋና ህዝቡ ተጠቅሟል፡፡ ከሊስትሮ እስከ ትልቅ ሆቴሎች ድረስ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡

------------

               “ውጤቱ የወጣቱና የህዝቡ ነው”
                 (አቶ ደሞዝ፤ የአሮዲዮን የባህል ሙዚቃ ትዕይንት አዘጋጅ)

    ቴዲን ወደ ባህርዳር በማምጣት የባህርዳር ፕሮሞተር ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ ኮንሰርቱ እንዲሳካ ከተመረጠው አስተባባሪ ኮሚቴ አንዱ ነኝ፡፡ ኮንሰርቱን የራሴ ነው ብሎ የተረከበው ወጣትና የህዝቡ ተባባሪነት የስኬቱ ድምር ውጤት ነው፡፡ ያ ሁሉ ህዝብ፤ አንድ ላይ ስለ ሀገሩ፣ ስለ ፍቅርና ስለ አንድነት ዘምሮ፣ ተግባብቶ መጠናቀቁ ትልቅ ውጤት ነው፡፡ ለእኔ ከዚህ በላይ ድል የለም፡፡
እኔ በበኩሌ፣ ባህር ዳር አስተማሪ ናት እላለሁ፡፡ ከአሁን በፊትም በዚሁ ስታዲየም ትልቅ የስፖርት ውድድር ተደርጎ፣ ብዙ ህዝብ ገብቶ በሰላም ተጠናቅቋል፡፡ ይህን ይህን ስናይ ባህርዳር፤ ለኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካ ብሎም ለአለም ቱሪስቶች አስተማሪና ተመራጭ ከተማ ናት ባይ ነኝ፡፡ በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ በተለይ ስለ ባህርዳር ወጣት የምገልፅበት ቃል የለኝም፡፡ እያንዳንዱ ነገር በቡድን በቡድን ተመድቦ፣ መድረክ ላይ፣ ከመድረክ ጀርባ፣ በር ላይ፣ መሀል ላይ፣ ዙሪያውን ሆነን … ምንም ችግር እንዳይፈጠር፣ በጥንቃቄ ሰንሰራ ነበር፡፡
እንኳን ይህን ለሚያህል ዝግጅት፣ለትንሽ ድግስም ስጋት ይፈጠራል፡፡ አንደኛ፤ ቴዲ በህብረተሰቡ ተቀባይነት ያለው፣ በጣም ትልቅ ባለሙያ ነው፡፡ ሁለተኛ፤ ወደዚህ ክልል መጥቶ ሰርቶ አያውቅም፤ ስለዚህ ይህን ሰው የሚወድ እንዳለ ሁሉ የሚጠላ አይጠፋምና፣ አንድ ነገር እንዳይከሰት ሰግተን ነበር፡፡ ግን የፈጣሪ ፈቃድ ስለሆነ ተሳካ፡፡ እኛም፤ “ይሄ ቢሆን ምን እናድርግ?” እያልን ተወያይተን፣ በደንብ ተዘጋጅተን ነበር፡፡ ያሰጉን ችግሮች አልተከሰቱም፡፡ ይሄ ስኬት በኮንሰርት ደረጃ ብቻ የሚገደብ አይደለም፡፡ ከተማዋ የዓለም ቱሪስቶች መነሀሪያና ምቹ ናት፡፡ አምስት አይነት ቱሪስት ያላትም ከተማ ናት፡፡ አንደኛው በ200 ኪ.ሜ ራዲያስ የሚመጣው የአካባቢው ቱሪስት ነው፡፡ ከተማዋ ቀደም ብሎ በነበረው አለመረጋጋት ይህን አጥታለች፡፡ ሁለተኛው አገር አቀፍ ማለትም፣ ከየክልሉ የሚመጣው ነው፡፡ ይህንንም እንዲሁ፡፡ ከአፍሪካም ከአለምም ቱሪስት ይጎርፍ ነበር፡፡ ሁሉም ነገር ተቀዛቅዞ ባለበት ሰዓት ነው፣ ይሄ ውጤታማ ኮንሰርት የተካሄደው፡፡ ሊስትሮና ወዛደር … ሳይቀር እንዲጠቀም፣ ከተማዋ እንድትነቃቃ ያደረገ ኮንሰርት ነው፡፡
ወደፊትም ከተማዋን ለማነቃቃት፣ ሌሎች ሁነቶችን ለማዘጋጀት የሚያነሳሳ ነው፡፡ እንግዲህ እኔ የዚህ ታሪክ አካል የሆንኩት፣ በቴዲ ማናጀር ተመርጬ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚያስደስት ነው፡፡ ለከተማዋ፣ ለባህርዳር ህዝብና ለወጣቶች ትልቅ ስኬት ነው፡፡


------------


            “ከማር እስከ ጧፍ ላይ በገፅ ቅብ ስራ መሳተፌ ያኮራኛል”
                 (ሔለን ይሰማው፤ የገፅ ቅብ ባለሙያ)

    ተወልጄ ያደግኩት አዲስ አበባ ቦሌ ነው፡፡ የኮስቹምና የካራክተር ሜካፕ ባለሙያ ነኝ፡፡ በብዙ ፊልሞች፣ ማስታወቂያዎችና የሙዚቃ ቪዲዮዎች ላይ በሜካፕ፣ አርት ዳይሬክቲንግና ኮስቹም  እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ የቴዲ አፍሮ “ማር እስከ ጧፍ” ቪዲዮ ላይ ሜካፕም ሰርቻለሁ፡፡ ለዚህ ሥራ እንድመረጥ የረዳኝ፣ የ”ሳቢሳ ፊልምስ” ተባባሪ መስራች የሆነው፣ ሰው መሆን ይሰማው (ሲሚክ) ነው፡፡
ታሪኩን ካነበብኩ በኋላ የአልባሳትና የገፅ ቅብ ስራ እንድንሰራ ነበር የታዘዝኩት፡፡ ከዚያ ቦታው ላይ ሄጄ በመፅሐፉ ላይ ያነበብኳቸውን ታሪኮች፣ባህሉን አለባበሱን አየሁ፡፡ በፊት ቴአትርና ሙዚቃ ላይ ፍላጎት ነበረኝ፤ቴአትርም እማር ነበር፤ ነገር ግን ወደ ሜካፕ አርቲስትነት በአጋጣሚ ተሳብኩ፡፡ እንደውም ተዋናይ ትሆኛለሽ ነበር የተባልኩት፡፡ በተማሪዎች ፕሮዱዩስ በተደረገ አንድ ፊልም ላይ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ በሜካፕ አርቲስትነት የሰራሁት፡፡  
ለዚህ ሁሉ ያበቃኝ አርቲስት ፍቃዱ ከበደ ነው፤ እሱ ቴአትር ይጋብዘን ነበር፤ ሲያስተምርም በጣም ጎበዝ ነው፡፡ እስካሁን በተለያዩ ፊልሞችና ማስታወቂያዎች ላይ በሙያዬ ተሳትፌአለሁ፡፡ የያሬድ ነጉን “ያጉቴ” የሚካኤል በላይነህ፣ የአስጌ ዴንዳሾ፣ የአንበሳ ጫማ ማስታወቂያ፣ የበርገርና የፈርኒቸር ማስታወቂዎች፣ ከፊልም ደግሞ፡- “የህልሜ ናት”፣ “የትኖራ”፣ “ወፌ ቆመች”፣ “ስስት ሁለት” (በዚህ ፊልም በሜካፕ የ”ጉማ አዋርድ” እጩ ሆኛለሁ) ጨርሶ ያልጠበኩት ነበር፡፡ “የአራዳ ልጅ ሁለት” እና ሌሎችም ላይ ሰርቻለሁ፡፡ አሁንም አንኮበር ለሁለት ወር የተቀረፀ ስራ አለ፡፡ ወደፊት ብዙ ነው ህልሜ፡፡ በአጠቃላይ በስራዬ ደስተኛ ነን፡፡ በቴዲ “ማር እስከ ጧፍ” ስራዬም ተደስቻለሁ፡፡ በኮንሰርቱም በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ ቴዲን፣ ማናጀሩን እንዲሁም የባህርዳር ከተማን ወጣቶችና ህዝቡን፤ እንኳን ደስ አላችሁ! ለማለት እፈልጋለሁ፡፡

Read 2377 times