Print this page
Saturday, 27 January 2018 12:27

ዣንጥላው

Written by  ዳግማዊ እንዳለ (ቃል-ኪዳን)
Rate this item
(8 votes)

    ቀን በታዘበዉ የሰዉ ልጅ ሀጥያት ተጸጽቶ ማቅ ለብሶ፣ አመድ ነስንሶ የተቀመጠ የመሰለ ጥቁር የክረምት ሠማይ፡፡ ሠማዩ ዓይኑ ቁልቁል እንዲያይ ተደርጎ በመፈጠሩ እያማረረ፤ ቀን ስላየዉ የሰዉ ልጅ ክፋትና በደል እያነባ ነዉ፡፡
ከሠማዩ በታች በእኩለ ለሊት የሚወርድባቸዉ የሠማዩ እንባ ብቻ የሚያመሳስላቸዉ ሁለት ጎጆዎች፣ እንደተኮራረፉ ህጻናት፣ ጀርባ ተሠጣጥተዉ በብዙ ቤቶች ርቀት ቆመዋል፡፡ አንደኛዉ ጎጆ፤ በድንጋይ የተሠራና ብዙ ክፍሎች ያሉት የግል ቤት ሲሆን ሌላኛዉ በጭቃ የተሠራና ያለ አንድ ሰው አላስተኛም የምትል አመለኛ ፍራሽን ከጥቂት የቤት ዕቃዎች ጋር አጭቆ የያዘ የቀበሌ ቤት ነዉ፡፡ ሁለቱ ቤቶች፤ ሁለት ርእዮተ ዓለምን የሚያመላክቱ መኖርያዎች ናቸዉ፡፡
በሁለቱ ጎጆዎች ዉስጥ አንዳቸው ስለ አንዳቸዉ የሚያስቡ የተከፉ - ሁለት ልቦች፤ ጉራማይሌ መኖርያቸዉ የወደፊት መቃብራቸዉን የመሠለባቸዉ-ሁለት ልቦች፤ ‹ለምን?› የሚል ተመሳሳይ ጥያቄ እየጠየቁ፣ የተለያየ መልስ የሚጠብቁ እራስ ወዳድ የሆኑ-ሁለት ልቦች፤ በመራራቃቸዉ ሳቢያ የማያፈናፍን የሽብር ካባ የደረቡ፣ አብሮ መሆን ግን  መፍትሔ መስሎ የማይታያቸዉ-ሁለት ልቦች፤ ተኮራምተዉ ቁጭ ብለዋል፡፡
መስከረም ከለበሰች ውሃ ሰማያዊ ፒጃማ ጋር ተመሳሳይ ቀለም ያለዉ ዣንጥላ፣ ደረትዋ ላይ ታቅፋ፣ በሰፊ ሳሎኗ ዉስጥ ትንጎራደዳለች፡፡ አስተቃቀፏና እርጋታዋ፣ ዣንጥላውን እሹሩሩ ብላ ለማስተኛት ጥረት እያደረገች ያለች ያስመስልባታል።
‹‹ቆይ እሱ ማን ስለሆነ ነዉ፣ የኔን ስልክ የማያነሳዉ? ...ማን ስለሆነ ነው፣ ለላኩለት መልዕክት መልስ የማይሰጠው? ...ምነዉ እጄን በቆረጠዉ ኖሮ!›› ዣንጥላዉ አልተኛ ብሎ እንዳስቸገራት፣በብስጭት የእርምጃዋን ፍጥነት ጨመረች፡፡
‹‹ቆይ በቴሌቪዥን መታየት ይሄን ያህል ትልቅ ነገር ሆኖ ነው ስልኬን የማይመልሰው?...ደግሞ ስለ ፍቅር ህይወቱ ሲጠየቅ፣ ስለ ማንም ተራ ሴት ወሬውን ተርትሮ ሲያበቃ፣ ስለ እኔ ምንም ያላወራው እረስቻታለሁ ለማለት ነዉ? ...ታድያ እንዲህ በቀላሉ የሚረሳኝ ከሆነ፣ ለምን ‹መስኪ እንደዚህ ጉድ ታደርጊኝ!? ...አንቺ በኔ እንደዚህ ጨክነሽ ትለዪኝ?...መስኪዬ በኔ ጨክነሽ ጓደኛዬን ትደርቢብኝ?› እያለ ሲያለቃቅስ ኖረ?...ሥራ፣ ተሯሯጥ፣ ገንዘብ ያዝ፣ ያለ አቅምህ ገንዘብ አታጥፋ ሲባል ከማይሰማ ሰው ጋር እከኬን እያከኩ ልኖር ነበር እንዴ ታድያ?... እኔ ገንዘብ ብፈልግ ኖሮ፣ ከእሱ ጋር ያን ያህል ጊዜ እቆይ ነበር እንዴ?...ብነግረው ብነግረዉ አልሻሻል ስላለኝ ነዉ የተውኩት፡፡ ደግሞ አማረን እሱ ቢያስተዋዉቀኝም ያን ያህል የቅርብ ጓደኞች መሆናቸዉን አላወኩም ነበር!›› የታቀፈችዉን ዣንጥላ ዓይን ዓይኑን እያየች፣ ምሬቷን ስትገልጽለት፣ በሀሳቧ እንደተስማማ ዝም አላት፡፡
ልቧ ቢያውቀዉም ስልኳን ከፒጃማ ኪሷ ዉስጥ አዉጥታ ከከፈተች በኋላ የገባላት መልዕክት እንዳለ ፈተሸች፡፡ ለበልጉ ‹እንዴት ነህ?› ብላ የላከችለት መልዕክት እንደረሰዉ፣ የስልኳ መልዕክተኛ ቢያሳውቃትም ምላሽ ግን አላገኘችም-ተናደደች፡፡
ልከኛ ስስ ከንፈሯን በጥርሷን እንደነከሰች ‹‹ትሰማለህ ነገ ላገኝህ እፈልጋለሁ!›› የሚል መልዕክት ከጻፈች በኋላ ትንሽ አመንትታ ስታበቃ ላከችዉ፡፡ ደቂቃዎች አለፉ-ከበልጉ አንዳች ምላሽ አልመጣም፡፡
‹‹ደግሞ ስለሰጠኸኝ ዣንጥላ ስታወራ…እንዴት ስለኔ ማውራት ከበደህ?...ምንም ቢሆን እኮ በፍቅር እረጅም ጊዜ አሳልፈናል፡፡ ደግሞ የተለየሁህ አንተን ማፍቀር ስላቆምኩ ሳይሆን በስንፍናህ የተነሳ ነዉ።›› እንባ ከአይኗ ፈሰሰ፡፡ ሁሉ ነገር ደብዝዞ አልታይ አላት። የታቀፈችዉን ዣንጥላ ልባሱን አውልቃ፣ እግሩ ላይ ያለውን ቁልፍ ጠቅ አድርጋ ዘረጋችዉ፡፡
‹‹ማሬ፤ ቤት ውስጥ ዣንጥላ መዘርጋት የመጥፎ እድል ምልክት ነዉ›› አማረ ዓይኑን እያሻሸ፣ወደ ሳሎን ገባ፡፡
‹‹ምን ጥሩ እድል አለ ብለህ ነዉ?›› ገላምጣዉ ስታበቃ፣ ፈርጠም ብላ መለሰችለት፡፡
‹‹አሁንም ስለ በልጉ እያሰብሽ ነዉ አይደል?›› አዛጋ፡፡
‹‹አዎ!›› ዣንጥላዉን እያጠፈች፣”ባስብስ ምን ታመጣለህ” አለችው፡፡
‹‹መስኪዬ ለምንድነው ግን ይሄን ያህል ማየት የተሳነሽ? እስኪ ተመልከቺ?...አሁን የምትፈልጊውን ሁሉ አግኝተሻል፡፡ ጥሩ ትዳር እና ያያቸዉ ሁሉ አቅፎ የሚስማቸዉ ወንድና ሴት ልጆች አሉሽ፡፡ ከምንኖርበት ቤት ተጨማሪ የምናከራያቸዉ ሌሎች ሁለት ቤቶችን አሉን፡፡ እኔም አንቺም እየቀያየርን የምንነዳቸዉ መኪናዎችን ገዝተናል፡፡ አንድ ትልቅ ማተምያ ቤት፣ ሁለት የጽህፈትና የህትመት መሣሪያ መሸጫዎች፣ አንድ አስመጪና ላኪ ድርጅት አቋቁመናል፡፡ እግዝያብሔር ይመስገን ባንክም በቂ ገንዘብ አስቀምጠናል፡፡››
ፈገግ አለና ‹‹ደግሞ ለመዝናናት ከበልጉ ጋር ሳለሽ እንደምታደርጊው ካፌ ለካፌ መዞር ሳይሆን በአየር አድርገን፤ ባህር ተሻግረን እንጓዛለን፡፡ ከእሱ ጋር ብትሆኚ ኖሮ፣ ይሄን ሁሉ ነገር ማድረግ ትችዪ ነበር?›› በስኬት ደረቱን ነፍቶ ሲያበቃ ሄዶ ትከሻዋን አቅፎ በጥያቄ ዓይን ተመለከታት፡፡ ሌላም ጊዜ እንደሚያደርጉት፣ ወሬአቸዉ እንደ ባልና ሚስት ሳይሆን እንደ ንግድ ሸሪክ ነዉ፡፡
‹‹በያ ንገሪኛ?›› መልስ አልሰጠችዉም፡፡
‹‹ተመልከቺ፤ አሁን የምታዝኚላቸዉ እንጂ የሚያዝኑልሽ ጓደኞች የሉሽም፡፡ ለቤተሰቦችሽም ቢሆን ያለነሱ እርዳታ በፈለግሽው መንገድ ሄደሽ ስኬታማ ልትሆኚ እንደምትችዪ አሳይተሻቸዋል፡፡ ታድያ ከዚህ በላይ ምን ትፈልጊያለሽ?››
‹‹እኔጃ!...እኔ አላዉቅም! ግን ለምን ስለ እሱ ዋሸኸኝ? ለምን ያላደረገዉንና ያላለህን ነገር ነገርከኝ?›› ደረቱ ላይ ተለጥፋ ተንሰቀሰቀች፡፡
‹‹መስኪ ከእኔ ጋር የሆንሺዉ እኮ በልጉ አልፈልግም ብሎሻል ብዬ ስለነገርኩሽ አይደለም! ከኔ ጋር የሆንሽዉ የተሻለ ሰው ስለምትፈልጊና ከእኔ ጋር መሆን ስለመረጥሽ ነዉ፡፡ ስለዚህ ነገር ሠላሳ ጊዜ አትጠይቂኝ!፡፡ ለማንኛውም እኔ ነገ በጠዋት ሥራ ስላለብኝ ልተኛ፡፡›› ከላዩ ላይ አላቋት፣ በቆመችበት ጥሏት ወጣ፡፡ መስከረም ከአማረ ደረት ላይ ተላቃ፣ ዣንጥላዉን ደረቷ ላይ ለጥፋ ስቅስቅ ብላ አለቀሰች።
የባሏ ኮቴ እየራቀ ሄዶ ሲጠፋ ስልኳን አንስታ፣ ለበልጉ ደወለች-አይነሳም፡፡ ደጋግማ ሞከረችና አልነሳ ሲላት፣ ነገ ልታገኘዉ እንደምትፈልግ የሚገልጽ መልዕክት ደግማ ላከችለት፡፡
በልጉ የቤቱ ጣርያ ላይ የሚጨፍረው ዝናብ ያልቀማውን ተመስጦ፣ በስልኩ የገቡት መልዕክቶች ነጥቀውት ከሚያነበው መጽሐፍ ላይ አንገቱን ቀና እንዲያደርግ ተገደደ፡፡ መልዕክቱን አንብቦ በኮርኒሱ ጥግ እየሾለከ የሚፈሰዉ ዝናብን ጠጥቶ እንዳበጠዉ የቤቱ ግድግዳ፤ ፊቱን አሳብጦ ፍራሹ ላይ ተንጋለለ። የቤቱ ጣርያ ሲጠጣ እንዳደረ ሠካራም፣ የሚወርድበትን ዝናብ በመስገብገብ እየጠጣ፣ ልብሱ ላይ ይሸናል፡፡ የኮርኒሱ ሸራም እንደ ሰካራም ሱሪ፣ በጣራዉ ሽንት ተዥጎርጉሯል፡፡
‹‹ቆይ ከኔ ምን ፈልጋ ነው ከሰባት ዓመት በኋላ እየደወለችና መልዕክት እየላከች የምትጨቀጭቀኝ?›› በልጉ ተማረረ፡፡ ‹ምን ፈልገሽ ነዉ? ለምን አትተይኝም?› ብሎ ሊጽፍላት ቃጣና፣ ከዓመታት በፊት ለራሱና ለወዳጆቹ የገባዉን ቃል አስታዉሶ ስልኩን ፍራሹ ላይ ወረወረ፡፡
ከሰባት ዓመታት በፊት በክህደት ተሠበረ የሚለዉ ልቡ እያስነከሰዉ፣ በህመም ፊቱ ቅጭም እንዳለ፤ በብስጭት ግንባሩ እንደተቋጠረ፤ በቁጭት ወፍራም ከንፈሩን ነክሶ፣ ሀዘን ሊደርሱት ለመጡት ወዳጆቹ በጭብጨባ ያልታጀበ ባለአንድ ነጥብ የአቋም መግለጫ አሰማቸዉ፡፡
‹‹እነሆ ከዛሬ ጀምሮ መስከረምን፣ አማረንና ሳማክራት፤ ‹እኔ በእናንተ ጉዳይ አያገባኝም፤ ጉዳያችሁ ነዉ› ብላ የሣቀችብኝን ያቺ ክፉ እህትዋን፣ ሰማይ ዝቅ፣ ምድር ከፍ ብትል አላናግራቸዉም። በፍርድ ቀን ሠልፍ ላይ የማውቃቸዉ ብቸኛ ሰዎች እነሱ ቢሆኑ እንኳን ከአንዳቸውም ጋር ቃላት አልለዋወጥም፡፡ የገነት ሠልፍ ላይ አግኝተዉ ‹አደረግነዉ አይደል! እንኳን ደስ አለን› ቢሉኝ ወይ የገሀነም ሰልፍ ላይ እጄን ይዘው፤ ‹አይዞን! እሱ አይጨክንም! ነገን በተስፋ ማየት ነዉ…› ብለዉ ሊያጽናኑኝ ቢሞክሩ እንኳን አልመልስላቸውም፡፡››
አንድ ሁለቱ የእስዋ ነገር አይሆንለትም ብለዉ ያሰቡ ጓደኞቹ፤ የአቋም መግለጫዉን ‹ሆድ ያባዉን መከዳት ሲያወጣዉ› እንጂ ከአንጀት አይደለም በሚል ቢያቃልሉበትም እሱ ግን እንደ ምንም እየተንገዳገደ፣ ለሰባት ዓመታት በቃሉ ዘለቀ፡፡
መስከረም፤ የበልጉ ዝምታ እልህ ስላስያዛት ደጋግማ ስልክ ደወለች፡፡ በልጉ፤ ድሮ በደወለች ቁጥር፣ ስሞ የሚያነሳዉን ስልኩን፣ በደወለች ጊዜ፣ ድምጽ አልባ እያደረገ ያስቀምጠዋል፡፡
‹‹በቴሌቭዥን ያወራህለትን ዣንጥላ ልሰጥህ እፈልጋለሁ፡፡ በሚቀጥለዉ ቃለ መጠይቅህ ለወሬህ ማስረጃ አድርገህ ታቀርበዋለህ›› የሚል መልዕክት ላከችለት፡፡ አንብቦ ‹‹በኔ ሥም ለኔቢጤ ስጪልኝ። ከአሁን በዋላ አትጨቅጭቂኝ የሚል መልዕክት የስልኩን ቁልፎች በኃይል በመጫን ከጻፈ በኋላ መልሶ አጠፋዉ፡፡ መልዕክት መጻፉና ማጥፋቱ ለእሱ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ደረሰብኝ የሚለዉ ክህደት ድንገት ወደ አዕምሮዉ ዘው ሲል ስልኩን አንስቶ፤ የገባውን ቃል ዘንግቶ…
‹‹በጣም እራስ ወዳድና ጨካኝ ሴት ነሽ። በህይወቴ እንዳንቺ ማንም የጎዳኝ ሰዉ የለም፤ ወደፊትም ማንም እንዳንቺ አይጎዳኝም። ስታዋልደኝ ቀጭታኝ ሰባራ ሆኜ እንድኖር ያደረገችኝ የሠፈራችን አዋላጅ ወሰኔ እንኳን ያንቺን ያህል አልጎዳችኝም፡፡ እራስሽን እንኳን የማያሳምኑሽ ደረቅ ምክንያቶችሽ ለጥቅም ስትዪ እኔን በአማረ መለወጥሽን ጽድቅ አያደርጉትም…..›› ብሎ ይጽፍና የገባዉን ቃል አስታዉሶ የጻፈዉን መልሶ ያጠፋዋል።  እንደገና ንዴት በዉስጡ ተንቀልቅሎ ቃሉን አንድዶ ሲያቀልጥ…
‹‹እኔ በአማረ አልናደድም ለዛም ነዉ ካንቺ ጋር ግንኙነት መጀመሩን ሲያረጋግጥልኝ ‹በጣም ክፉ ሰዉ ነህ›› ከማለት በቀር ሌላ ቃል ልናገረዉ ያልቻልኩት። እኔ አንቺን ነበር ያፈቀርኩት፤ አንቺን ነበር ከራሴ አብልጬ ያመንኩት…እሱ ሳይሆን አንቺ ነሽ የከዳሺኝ! ደግሞ እራስሽን አሳልፈሽ ሸጥሽለት እንጂ እሱ አልገዛሽም›› ብሎ ይጽፋል፡፡ ንዴቱ ቀዝቀዝ ሲልና በንዴቱ እሳት የቀለጠው ቃልኪዳኑ እረግቶ ሲጠጥር፣ የጻፈዉን ያጠፋና ስልኩን ይወረዉረዋል፡፡
መስከረም ለአንድ ሰዓት ያህል አንዴ ብቻ እንዲያናግራት የሚለምኑና የሚያስፈራሩ ደርዘን መልዕክቶችን ላከች፡፡ በልጉ የሚያነበውን መጽሐፍ ትቶ፣ መልዕክቷን እያነበበ ይናደዳል፡፡ አልፎ አልፎም አሁንም የሷ እንደሆነ አድርጋ፣ ካላገኘሁህ ብላ በመቆጣቷና በማስፈራራቷ፣ የንዴት ሳቅ ይሥቃል፡፡
ዝምታዉ ሲሰለቻትና መንጎራደዱ ሲያደክማት፤ ‹‹ያለህበትን አፈላልጌ እቤትህ ድረስ እመጣለሁ። የዛኔ ወደህ ሳይሆን በግድህ ታናግረኛለህ! ደህና እደር›› የሚል መልዕክት ላከችለት፡፡ በልጉ በመልዕክቱ ፈገግ አለና…..
‹‹ሀብታሞች ሁሉን የሚያይልን ዓይን፤ ሁሉን የሚሰማልን ዦሮ አለን ስለምትሉ ፈልገሽ ድረሺብኝ። ደግሞ እኔን ፈልጎ ለማግኘት ያን ያህል ከባድ አይደለም። ምን የሚደበቅ አለኝና እራሴን ልደብቅ። አዎ!...እራስሽ ያስቀመጥሺዉን የመኪናሽን ቁልፍ ፈልገሽ ለማግኘት ከሚፈጅብሽ ጊዜ ባነሰ፣ በደቂቃዎች ዉስጥ ፈልገሽ ታገኚኛለሽ። ከደጃፌ ቆመሽ በሬን ብትቆረቁሪ ባልከፍትልሽ እንኳን ከፍተሸ መግባት ትችያለሽ፡፡ መቼም እንደቀራጩ፣ ‹አንቺ ከኔ ቤት ጣርያ ልትገቢ አይገባሽም፡፡ ይሄ ቤት አይመጥንሽም!› አልልሽም። ግን እወቂ! ቃሌ ነዉና፣ ለንግግርሽ ምላሽ የሚሆኑ ቃላት ከአንደበቴ አይወጡም፡፡ ከአንደበቴ ይልቅ ብዙ ፍቅርን ያወሩሽ የነበሩ ዓይኖቼም አያናግሩሽም። ያልሺዉ፣ ያሰብሺዉ ሁሉ ይሁን፣ ይደረግ እያልኩ በመስማማት ሳወዛዉዝልሽ የኖርኩትን አናቴን፣ ለይሁንታም ሆነ ለእንቢታ አልነቀንቅልሽም፡፡ አንቺም ደህና እደሪ›› ብሎ በረዥሙ ተነፈሰ፡፡
ውላቸዉ የጠፋ ዝብርቅርቅ ሀሳቦች፣ ሀሳቡን አዘባረቁበት፡፡ እንደማይመልስላት ቢያዉቅም ለረጅም ደቂቃ ደግማ መልዕክት ከላከች ወይ ከደወለች ብሎ ጠበቀ፡፡ እፈልግሀለዉ ማለቷ ቢያናድደዉም፣ ስለ እሱ እያሰበች እንደሆነ ማወቁ ደስ የሚል ስሜት ፈጥሮለታል፡፡ ከመስከረም ከተለያየ በኋላ ከሁሉ በላይ ሲጎዳዉ የነበረዉ ነገር፣ እኔ ስለሷ ሌት ተቀን ይሄን ያህል እያሰብኩ፣ እሷ ሁሉን ነገር እረስታ፣ ከአማረ ጋር የፍቅር ቄጤማ ስትቀነጥስ ዉላ ታድራለች ብሎ ማሰቡ ነበር፡፡
አጥፎ ያስቀመጠዉን መጽሐፍ አነሳና ገለጠ። የሚያነባቸዉ ቃላት ትርጉም አልሰጥ፤ ምስል አልፈጥር አሉት፡፡ በመሰላቸት መንፈስ ሆኖ መኝታ ዉስጥ ገብቶ ተጠቅልሎ ተኛ፡፡ ተበዳይና ተጎጂ እኔ ነኝ ብሎ ስለሚያስብ፣ የአዕምሮ እረፍትና ሰላም እሹሩሩ ብለዉ አስተኙት-ወድያው አሸለበ፡፡
በተወርዋሪ ኮከብ ተሳፍሮ፤ የቀስተደመና ቀለም በሚወክሉ ሰባት የብርሃን ክበቦች ዉስጥ ሾልኮ፣ ከህልም ዓለም ሲገባ መስከረምን ቆማ አገኛት፡፡ እንዴት በዚህ ፍጥነት ያለሁበትን አውቃ፣ ቀድማ ጠበቀችኝ ብሎ ተገረመ፡፡ ጸአዳ ልብስ ለብሳለች። ቀይ ዳማ ቆዳዋ፣ ወደ ጥቁር ዳማነት ተቀይሯል፡፡ አጭር ቁመቷ ከበፊቱ እጅግ አጥሯል-ደነገጠ፡፡ ወደ እሱ ተራምዳ በስንዝር እርቀት ቆመች፡፡ ስንዝር ቁመቷን ሲያይ…
‹‹አፍረት ነዉ መሠል እንዲህ ያሳጠረሽ!››
‹‹እጥረቴን ጠላኸዉ››
‹‹ብትረዝሚም ግድ የለኝም››
‹‹ስላለፈዉ እንድናወራ እፈልጋለሁ››
‹‹ያለፈዉ አልፏል እኮ!››
‹‹የዉሾን ነገር ያነሳ ዉሾ ይሁን ማለትህ ነዉ?…እሺ ስለ ወደፊት እናዉራ?››
‹‹ዉሾን የበላሽዉ እኮ ብቻሽን ነዉ! ከረከሰ ጋር ወደፊት የለኝም!››
‹‹እሺ ስላለፈዉ እናዉራና፣ ሀጥያቴን ተናዝዤ ንስሀ ልግባ››
‹‹ሀጥያት?...የምን ሀጥያት?...ማድረግ ያለብሽን እንዳደረግሽ፤ ፈጣሪም ምክንያትሽን እንደሚረዳሽ፤ ንጹህነትሽን እንደሚያዉቅ አስረግጠሸ ነግረሺኝ ነበር!››
‹‹በደሌን! ክህደቴን ...ገንዘብንና ምቾትን አስበልጬ፤ ፍቅርህን እረግጬ ሄድኩኝ፡፡ አሁን ግን ሁሉንም ነገር አየሁት፡፡ ሁሉ ነገር ከንቱ ሆነብኝ…አሁንም ከልብ መጸጸቴን ፈጣሪ ይረዳኛል!››
‹‹እኔ ፈጣሪ አይደለሁም! እኔ ልረዳሽ አልችልም።››
‹‹እባክህ እራሴን ዝቅ አድርጌ እየለመንኩህ ነዉ። ይቅርታ አድርግልኝ!››
‹‹ወዴት ነዉ እራስሽን ዝቅ ያደረግሽው? ወዳልተሳካለትና ወደ ወደቀ ሰዉ?››
‹‹ያን ያህል ገንዘብ አፍቃሪ አታድርገኝ፡፡ ምንም ሳይኖርህ ለዓመታት አብሬህ ኖርያለሁ። እንድትለወጥ፣ መጨረሻችን አብሮነት እንዲሆን ብዙ እድል ሰጥቼህ ነበር፡፡ ያን ለማሳካት አንተ ምን አደረክ? ያ ሁሉ የወር ደሞዝ እየተከፈለህ በዓመት ውስጥ ስንት ቆጠብክ? ንገረኝ እስኪ?››
‹‹እኔ ለመለወጥ ተአምር ሳይሆን ትክክለኛዉን መንገድ እየጠበኩ ነበር፡፡ መታገስ አልቻልሽም። ባንቺ መንገድ እንድሄድ፣ አንቺን እንድሆን ነበር ፍላጎትሽ፡፡ ያ ደግሞ ፍጹም በሰው ተፈጥሮ አይሆንም፡፡››
‹‹ችግርህ ይሄ ነዉ፡፡ ቀልጣፋ ነህ፡፡ ጥሩ አዕምሮ አለህ፡፡ ግን ተሯሩጠህ ልትሠራበትና ልትለወጥ አትፈልግም፡፡ መሥራትና መለወጥ ወደሚፈልገው አማረ መሄድ ነበረብኝ፡፡ ደግሞ ያን ያህል የቅርብ ጓደኞች እንደነበራችሁ አላውቅም››
‹‹እኔ እራሴ ያስተዋወኩሽ ጓደኛዬ፤ ስለኔና ስላንቺ ሁሉን ነገር የሚያዉቅ ጓደኛዬ፤ እህትሽን ወድጃታለሁ ካላስተዋወቅሺኝ እያለ ሲያስቸግርሽ የነበረ ሰዉ እንደሆነ፤ አንቺም ልታግባቢያቸው ስትሞክሪ እንደነበር በደንብ ታዉቂያለሽ፡፡ ለነገሩ ተይዉ…….››
‹‹እሺ በቃ ይቅርታ አድርግልኝ…አጥፍቻለሁ!››
‹‹ታዉቂያለሽ ካንቺ ጋር ለመለያየት አንድ ሚሊዮን ምክንያቶች ነበሩኝ፡፡ ግን ፍቅርሽን ብዬ ካንቺ ጋር መሆንን መረጥኩኝ፡፡ አንቺ ደግሞ ከኔ ጋር አብረሽ እንድትሆኚ የሚያደርጉ አንድ ሚሊዮን ምክንያቶች ነበሩሽ ግን መለየቱን መረጥሽ፡፡ ይሄ ደግሞ ለኔ ከአንቺ የሚያለያይ አንድ ሚሊዮን አንደኛ ምክንያት ሆነኝ፤ ስለዚህ ደህና ሁኚ!››
ሰባት የእንባ ዘለላዎች ከዓይኖቿ ዱብ ዱብ አሉ። የእንባ ዘለላዎቹ ከመሬት ላይ አርፈው፣ የስልኩን መልዕከት እንደገባ ማሳወቂያ ሙዚቃ ዓይነት ድምጽ ካሰሙ በኋላ ተፈናጥረዉ ጉንጩ ላይ አረፉ፡፡ መስከረም፤ በልጉ በእንባዋ መራሱን ስታይ ከጀርባዋ ደብቃው የነበረዉን ዣንጥላ ዘረጋችለት። እጇን ገፋዉ፡፡ ሌሎች ሰባት የእንባ ዘለላዎችን አነባች። እንባዎቹ ዳግም መሬት ላይ አርፈዉ ተመሳሳይ ሙዚቃ ካሰሙ በኋላ ተፈናጥረዉ ጉንጩ ላይ አረፉና፣ አነስተኛ ጎርፍ ፈጥረዉ ከአገጩ ወደ አንገቱ የሚወርድ ፏፏቴ አበጅተዉ፣ ቁልቁል ወደ ደረቱ ወረዱ፡፡
በልጉ በደረቱ የገባው ውሃ ሲቀዘቅዘዉ ደንግጦ ብንን አለ፡፡ ከሰማይ የሚወርደው ዶፍ ዝናብ በወንፊቱ ጣራ እየሾለከ ኮርኒሱን በዉሃ ጅራፍ ይዠልጠዋል። ኮርኒሱም ቤት ዉስጥ ካለው ትልቅ የመጽሐፍት መደርደርያ ውጪ ሁሉም ቦታ ያነባል። የቤቱን ጣራ በድቅድቁ ጨለማ ከሚወርደው ዝናብ በተጨማሪ በረዶ እንደ አንደርቢ እየወገረዉ ነዉ። ስልኩ የመልዕክት ገብቷል ሙዚቃ ካሰማ በኋላ ተንቀጠቀጠ።
በልጉ ስልኩን አንስቶ የመልዕክት ሳጥኑን ከፈተዉ። ሁለት ዓይኖቹን ከስልኩ ‹እስክሪን› ላይ ሲያጨናብስ፣ ሁለት መልዕክት እንደገባለት ተረዳ፡፡
የመጀመርያዉ መልዕክት፤ ‹‹መኖርያህ የት እንደሆነ አዉቄአለሁ፡፡ ነገ በጠዋት መጥቼ ዣንጥላውን እመልስልሀለሁ›› ይላል፤ ሁለተኛዉ መልዕክት ደግሞ…
‹‹ነገ በጠዋት እቤትህ ስለምመጣ ጠብቀኝ፡፡ የትም እንዳትሄድ!›› የሚል ዛቻ መሳይ ነበር፡፡
በልጉ መስከረምን በተለያዩ አጋጣሚዎች ብቻዋንም ሆነ ከአማረ ጋር መንገድ ላይና ሌሎች ቦታዎች አግኝቷታል፡፡ ለፈገግታዋ ምላሽ ቢነፍጋትም ደጋግማ ፈገግታዋን ለግሳዋለች፡፡ አሁን ግን እንደ በፊቱ አስባበት እሱን ለማግኘት ብላ ቤቱ እንደምትመጣ ማወቁ አስጨነቀዉ፡፡ ሲገላበጥ አድሮ አሥራ ሁለት ሰዓት ሲሆን ተነስቶ ለመውጣት፣ ልብሱን መለባበስ ጀመረ- መምጣቷ አስፈርቶታል፡፡ እንደ ምንም እንደ ምንም አባብሎ ያቆመው ወንድነቱ፣ እሷን አይቶ እንዲንኮታኮት አልፈለገም፡፡
ከዓመታት በፊት በፍቅር ከንፈዉ በነበረበት ጊዜ ድንገት በትንሽ ነገር ይጋጩና፣ በንግግር ሊተማመኑና አንዳቸዉ ሊሸነፉ ባለመፍቀዳቸዉ ‹በቃ እንለያይ› ትለዋለች፡፡ በንዴት ተዉጦ በዝምታ ቢሮዋን ለቆ ይወጣል፡፡ ተከትላ እሱ ጋር ያላትን ዕቃ እንዲመልስላት ትጠይቀዋለች፡፡ በዝምታ ወደ ታክሲ ተራ ሄደ፡፡ ተከተለችዉ፤ ታክሲ ዉስጥ ገብቶ ኋላ ወንበር ላይ ተቀመጠ፡፡ በጥቂት እርምጃ ልዩነት ተከትላዉ ታክሲ ዉስጥ ገባችና ከፊት ወንበር የተቀመጡ ልጆችን አጠጋግታ ተቀመጠች፡፡ ታክሲዉ ጉዞ ጀምሮ ረዳቱ ሂሳብ ሲሰበስብ አውጥታ የአንድ ሰዉ ሂሳብ ከፈለች። በልጉ ለሁለት ሰዉ ሊከፍለዉ አዉጥቶት የነበረዉን ገንዘብ ግማሹን መልሶ ከኪሱ ከተተዉ፡፡
ከታክሲ ወርደዉ ወደ ቤቱ የሚወስደዉ ቅያስ ዉስጥ ሲገቡ፣ ጭለማዉ እንዳያስፈራት ብሎ በቅርበት አብሯት ሊሄድ እርምጃዉን ዝግ አደረገዉ። እሷ ግን ዝግ ባለ ቁጥር ቆም እያለች፣ በመሀከላቸዉ ያለዉን እርቀት መጠበቅ ጀመረች። ቆም አለና ዞሮ ተመለከታት። መቆሙን ስታይ እሷም ቆመች፡፡
‹‹እባክሽ ከሄድሽ እንሂድ!›› አላት ምሬት በሞላዉ ድምጽ።
‹‹እንደዉም እኔ አልመጣም...እራስህ ይዘህልኝ ና!›› አለችዉ እንዳኮረፈ ህጻን ትከሻዋን እየሰበቀች። ከዛም ዞራ ወደ አስፋልት መጓዝ ጀመረች። ተከትሎ እሮጦ ያዛት፡፡ ፊቷ በእንባ ታጥቧል። ሆዱ ተንሰፈሰፈበት፡፡ ዓይኖቹ እሷ ያነባችዉን እጥፍ የሚያህል እንባ አቀረሩ። እንባዋን በእጆቹ ጠራረገላትና ቃላት ሳይለዋወጡ እጇን ይዞ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡
ቤቱን ከፍቶ መብራት ሲያበራ ገብታ አልጋዉ ላይ ቁጭ አለች፡፡ በሩን መለስ አድርጎ ሄዶ አጠገቧ ተቀመጠ፡፡ የምትፈልገዉ ዕቃ እንዳስቀመጠችው ተቀምጧል፡፡ ቃላት መለዋወጥ አልቻሉም፡፡ ዓይኖቿን ቢጠራርግላትም ፈጽሞ አልደረቁም። ዞር ብሎ ሲያያት ዓይን ለዓይን ተጋጩ፡፡ ዳግም ማልቀስ ጀመረች፡፡ አቀፋት-ደረቱ ላይ ተለጥፋ ተንሰቀሰቀች። ቃላት ከአንደበታቸዉ መዉጣት ስላልቻለ ተቃቅፈዉ ተላቀሱ፡፡
ፍቅር ላይ በነበሩባቸዉ ዓመታት ብዙ የእንለያይ ሀሳቦች በእንባዎቻቸዉ ጎርፍ ተወስደው ቀርተዋል። በልጉ ለስራ ጉዳይ ለረጅም ጊዜ ከተማዉን ለቆ በሄደበት ወቅት ዓይን ለዓይን እየተያዩ መለያየት የከበዳቸዉ ሁለት ልቦች፤ በቀጭኑ ሽቦ እየተላቀሱ ተለያዩ፡፡ አማረ የበልጉን በዙፋኑ አለመኖር አይቶ ያደረገዉ መፈንቅለ-ፍቅር በድል ተጠናቀቀ፡፡
በልጉ አሁን መስከረም ብትመጣ ምን ሊፈጠር ይችላል የሚለዉን ሲያስብ፣ ፍርሀት ከጠዋቱ ብርድ ይበልጥ አንቀጠቀጠዉ፡፡ ልብሱን ለባብሶ ሲጨርስ አቅፎት ያደረዉን መጽሐፉን ከመደርደርያ አኑሮ ቤቱን ለቆ ወጣ፡፡
ሲያለቅስ ያደረዉ ሰማይ የሚያባብለዉ ሲያጣ፣ ለአመል ያህል ደረቅ ለቅሶ እንደሚያለቅስ ህጻን ፊቱን ፈካ አድርጎ በስሱ እያካፋ ነዉ፡፡ አልፎ አልፎ አሁንም እያለቀስኩ ነዉ ለማለት ያህል በተዘጋ ድምጹ ያጓራል። በልጉ ካፊያዉን ለክረምት ብሎ በገዛዉ ወፍራም ‹ጃኬት› እየመከተ፣ መንደሩን ለቆ ወደ ዋናዉ መንገድ ወጣ፡፡ በተስኪያን የሚሄዱ እናቶች በአንድ እጃቸዉ መቋምያ፣ በሌላ እጃቸዉ ዣንጥላ ይዘዉ ይጓዛሉ፡፡ በልጉ፤ እናቶች የያዙትን ዣንጥላ ሲያይ ተናደደ፡፡
ያን ሰበበኛ ዣንጥላን ገዝቶ የሠጠበትን ቀን ረገመ። ከሠጣት ብዙ ስጦታዎች መርጣ ለምን ዣንጥላዉን መመለስ እንደፈለገች ግን አልተገለጸለትም፡፡ ደግሞ ዣንጥላዉን በጣም ነበር የምትወደዉ፡፡ እህቶቿና እናቷን እንኳን ዣንጥላዉን ከነኩባት ትጣላ ነበር፡፡
አንድ ምሽት ሲደዉልላት ‹‹በልግዬ…በጣም ተናድጃለሁ፡፡ ከቅድም ጀምሮ እያለቀስኩ ነዉ፡፡›› አለቺዉ፤ የለቅሶ ዜማ ባለዉ ድምጽ
‹‹ምነዉ ምን ሆንሽ መስኪዬ›› በመጨነቅ ጠየቃት።
‹‹ዣንጥላዬን እኮ ታክሲ ዉስጥ ጥዬዉ ወረድኩኝ››
‹‹ዉይ መስኪዬ ለእሱ ነዉ እንዴ? አይዞሽ ማሬ›› ጭንቀቱን በረጅም ትንፋሽ አወጣዉ፡፡
‹‹እንዴ ለሦስተኛ ዓመታችን የሰጠኸኝ ስጦታ እኮ ነዉ!፡፡ በጣም ነበር የምወደዉ፡፡›› መልሳ ለቅሶ ጀመረች። በማግስቱ ገና ከርቀት ስታየው እየነጋ ያለ የሚመስል ፊቱ ላይ ፊቷን እንደ ባትሪ አብርታ፣ ሮጣ ሄዳ ተጠመጠመችበት፡፡ ግራ ተጋብቶ ሲያያት፣ዣንጥላዉን እንዳገኘችዉ ከቦርሳዋ አዉጥታ አሳየችዉ፡፡
‹‹ደግሞ በቴሌቭዢን ለሷ ስለሰጠዋት ዣንጥላ ምን ተናገርኩኝ? ጭራሽ ስለ ዣንጥላ አውርቻለሁ እንዴ?›› እራሱን በጥያቄ ወጥሮ ያዘ፡፡ በነገር በመወጠሩ በካፊያዉ ከመራስ አልፎ መበስበስ መጀመሩን አልተረዳም፡፡
ሠማዩ ለቅሶዉን አላቆም ብሎ ቀኑን ሙሉ ሲያላዝን ዋለ፡፡ በልጉ እንደ ሰማዩ ባያነባም መስከረም እቤት ድረስ መጥታ እንዳጣችዉና እንዳዘነች፤ ለበደሏ ከቻለ ይቅርታ እንዲያደርግላትና ከአሁን በኋላም መልሳ እንደማታስቸግረዉ የሚገልጽ መልዕክት ከላከችለት በኋላ ፊቱን ከስክሶታል፡፡
አመሻሽ ላይ እንደ ዘላን ከቦታ ቦታ መንከራተቱ ሲሰለቸው ወደ ቤቱ አመራ፡፡ የቤቱን መዝግያ ለመክፈት ሲታገል ኮቴዉን የሰሙ ጎረቤቶቹ፣ በራቸዉን ከፍተው፣ ጥገኝነት ሰጥተዋት የነበረዉን መስከረምን ላኩበት፡፡ ከድንጋጤው የተነሳ ፊቱ ላይ ላቡ ችፍ አለ፡፡ አጆቹ ተንቀጥቅጠዉ ቁልፉን ጋን ዉስጥ መክተት ተሳናቸዉ፡፡
መዝግያዉን እንደ ምንም ከፍቶ ቤቱ ዉስጥ ገብቶ፣ መብራት ማብራት እንኳን ሳይመጣለት ተገተረ። መስከረም ተከትላው ገባችና ለአፍታ በጨለማዉ አብራዉ ቆመች፡፡ ድንገት ማብርያ ማጥፍያዉ የቱ ጋር እንዳለ እንደምታውቅ ግርግዳዉን ዳብሳ መብራቱን አበራች፡፡
ለደቂቃዎች ተፋጠው ቆሙ፡፡ በልጉ ፊቱን ላብ አጥለቀለቀዉ፡፡ መስከረም በረጅሙ ተንፍሳ…
‹‹ለምንድነዉ ጠዋት እመጣለሁ እያልኩህ…›› አረፍተ ነገሩን መጨረስ ተሳናት፡፡ እንባዋ ከዓይኖቿ ዱብ ዱብ አሉ፡፡ በልጉ እንደ ቀድሞዉ እንባዋን አይቶ እንደ ማልቀስ፣ ለወራት ብቻዉን ያነባዉን የእንባ ጎርፍ አስታዉሶ ልቡን አደነደነ። ለደቂቃዎች መናገር ተስኗት በዝምታ አለቀሰች። ዓይኖቿን ላለማየት የሚያውቀዉን ቤቱን እንደ እንግዳ ማማተር ጀመረ፡፡ ተጠጋችዉ-ፍራሹ ጋር እስኪደርስ ድረስ ሸሻት፡፡
‹‹በልጉዬ ምን ያህል እንደጎዳሁህ አዉቃለሁ…እንደጠላኸኝም አዉቃለሁ…ግን እኔ ያልተጎዳሁ ይመስልሀል? አሁን ባለኝ ህይወት ደስተኛ ሆኜ የምኖር እመስልሀለዉ? በፊትም ቢሆን በህይወቴ አንድም ቀን ተደስቼ እንደማላውቅ ታዉቃለህ፡፡ ደስተኛ የሆንኩባቸዉ ቀናት ካንተ ጋር ያሳለፍኳቸዉ የፍቅር ጊዜያት ብቻ ናቸዉ፡፡ ይሄ ሁሉ ስኬቴ ካንተ ጋር ቢሆን ምንኛ ደስተኛ እሆን እንደነበረ እኔ ነኝ የማዉቀዉ…ይህን ልትረዳኝ ይገባል እኮ!›› ሳግ ተናነቃት፡፡
‹‹ይሄን ማድረግ ነበረብኝ፡፡ የቤተሰቦቼን ነገር ከአንተ በላይ የሚያዉቅ የለም፡፡ አንድ ቀንም ፍላጎቴን አክብረዉና ከጎኔ ቆመው ለማያዉቁት ቤተሰቦቼ፣ በራሴ መንገድ ሄጄ፣ ህልሜን አሳክቼ ማሳየት ነበረብኝ። አንተ ግን ሰነፍክብኝ…›› ተንሰቀሰቀች፡፡
‹‹ቤተሰቦችሽ እንደነሱ እንድትሆኚ ማስገደዳቸዉ ስህተት መሆኑን እያወቅሽ፣ እኔ አንቺን እንድሆን ስታስገድጂኝ መኖርሽ ጥፋትነቱ እንዴት አልታየሽም? አንቺ በቤተሰቦችሽ ፊት ስኬታማ ሆኖ መቆም ብቻ ነበር ህልምሽ፡፡ የኔ አንቺን ማጣትና መጎዳት ጉዳይሽ አልነበረም! ምን ዓይነት መከራና ስቃይ እንዳሳለፍኩ ታዉቂያለሽ? እስካሁን ድረስ ልሞላው ያልቻልኩትን ጉድለት እንዳጎደልሺኝ ታዉቂያለሽ? ላንቺ ስኬት ማለት ሀብት ንብረት ማፍራትና በቤተሰቦች ፊት ሞገስ ማግኘት ነዉ፡፡ ላንቺ ገንዘብ ከሌለ ሰላምና ፍቅር ያለበት ህይወት ጉዳይሽ አይደለም፡፡›› በልጉ ንዴት ሰውነቱን እያንቀጠቀጠው፣ ያለ ቃላት በሀሳቡ ሞገታት፡፡
‹‹እባክህ አናግረኝ፡፡ እንደ ድሮ ስደበኝ፣ ውቀሰኝ…ከፈለክም በጥፊ ምታኝ ግን እንደዚህ በዝምታህ ስቃዬን አታብዛብኝ፡፡ የዛኔ እየደወልክም በስልክ መልዕክትም ትሰድበኝ አልነበር፤ አሁን ለምን አትሰድበኝም?›› መንታ መንታ የሚወርደው እንባዋ ፣ፊቷን ከቅንድቧ በታች የታጠበችው አስመሰለባት፡፡ በልጉ እንባዋን አይቶ ተሸነፈ፡፡ አንደበቱ ቃላት እንዳያወጣ መቆጣጠር ቢችልም ዓይኖቹን ከማንባት ማስቆም አልቻለም፡፡
‹‹ደግሞ ስለ ፍቅር ህይወትህ ስትጠየቅ እኔን እንዴት…? ይሄን ያህል ነው የጠላኸኝ? ለሦስተኛ ዓመታችን፣ የሰጠኸኝን ዣንጥላ እንኳን ከኔ አስበልጠህ ስታወራለት እኔን እረሳኸኝ…?›› የሚተናነቃት ሳግ፣ ንግግሯን አላስጨርስ እያላት ተቸገረች፡፡ በልጉ ለመስከረም ስለሰጣት ዣንጥላ፣ ምን እንዳወራ ዳግም ግራ ገባዉ፡፡
‹‹እንካ ይሄ ዣንጥላ ነው አይደል ከኔ የበለጠብህ…ግን ይሄን ያህል እንደ ነብሰ ገዳይ ልታየኝ አይገባም ነበር፡፡›› ዣንጥላዉን አስታቅፋው እየተመናቀረች፣ በሩን ዘግታበት ወጣች፡፡
በልጉ ዣንጥላዉን እንደታቀፈ ፍራሹ ላይ ተዘረረ፡፡ ከመስከረም መሄድ ይልቅ የዣንጥላው ነገር አሳሰበው፡፡ ዓይኑን ጨፍኖ በቴሌቭዥን የሰጠውን ቃለ ምልልስ ማሰብ ጀመረ፡፡ በቃለ ምልልሱ ጊዜ ጋዜጠኛዋ ስጦታ የመስጠት ልምድ እንዳለዉና ምን ዓይነት ስጦታ መስጠት እንደሚወድ ስትጠይቀው፤ ስጦታ መስጠት እንደሚያስደስተውና ወቅቱን የጠበቀ ስጦታ እንደሚሰጥ ገልጾ፣ ለምሳሌ ያህል በክረምት ዣንጥላ ወይ የዝናብ ልብስ መስጠት እወዳለሁ ብሎ ጋዜጠኛዋን እንዳሳቃት ትዝ አለዉ። መስከረም ንግግሩን ከሷ ጋር አገናኝታ፣ በስህተት እንደተረዳችው ገባውና በረጅሙ ተነፈሰ፡፡
ድንገት በሩ ተበርግዶ መስከረም በእንባ የታጠበ ፊቷን አስቀድማ ገባችና፣ ዣንጥላውን መንጭቃዉ ወጣች፡፡ ሊከተላት ቢያስብም ሰዉነቱ ለግሞ አልታዘዝ አለው፡፡ እንባዉ ብቻ ያለ ከልካይ መፍሰስ ጀመረ፡፡ መስከረም ዣንጥላውን እንደታቀፈች በምሽቱ ዝናብ እየበሰበሰች፣ ወደ ታክሲ ተራ ሄዳ፣ በቀጥታ ወደ ቤቷ አመራች፡፡ ከቤቷ ስትገባ ብቻዋን መሆን ስለፈለገች እንግዳ ሲመጣ ብቻ የሚያስተናግዱበት መኝታ ቤት ውስጥ ገብታ ቆለፈች፡፡
መከፋታቸዉን በድቅድቁ ለሊት ከሠማዩ ዓይኖች የሚወርደዉ ዝናብ እያገዛቸዉ ይመስላል። በመስከረም ቤት ጣርያ ላይ የሚወርደው ዝናብ፣ ጣራውን የሸፈነዉ ሸክላ ወደ ሙዚቃነት ይቀይረዋል። በበልጉ ቤት ጣርያ ላይ የሚወርደውን ዝናብ ወንፊቱ ጣርያ ወደ ኮርኒሱ ሸራ ካስተላለፈዉ በኋላ፣ ሸራዉ ከጥግ እስከ ጥግ አንሸራሽሮ፣ ወደ በልጉ አናት ያንጠባጥበዋል፡፡ በልጉን ወትሮ ዝናብ በነካው ቁጥር የሚያሳክከዉ ፎሮፎራም አናቱ ዛሬ አላሳከከዉም፡፡
ዝናብ እያፈሰሰ ያለዉ የበልጉ ጎጆ ዉስጥ ቢሆንም ዣንጥላው ግን ያለው ከእሷ ዘንድ ነዉ፡፡ የመስከረም ጣርያ ስለ መከፋቷ አብሮ እያነባ ያለውን ሠማይ፣ እንባ አላሳልፍም ብሎ ቢያግደዉም፣ ዣንጥላው ግን መንታ መንታ እየወረደ ከሚያርሳት እንባ ሊያስጥላት አልቻለም፡፡

Read 3826 times