Sunday, 28 January 2018 00:00

“ኢህአዴግ 100 ሚሊዮን ህዝብ ብቻውን ማስተዳደር አይችልም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 የኢህአዴግ ትልቁ ችግር፣ ከራሱ ሳጥን ውጪ አለማሰቡ ነው
            የህዝብ መሰረታዊ ጥያቄ፣ የእኩልነትና የኢኮኖሚ ነው
            በህዝብ ደረጃ ብሔራዊ እርቅ ማድረግ ያስፈልጋል
            በማረሚያ ቤት ፈረንሳይኛ ቋንቋ መማር ጀምሬ ነበር

    ለ11 ወራት በእስር ቆይተው ከሰሞኑን ክሳቸው ተቋርጦ፣ የተፈቱት አንጋፋው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪና የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ዶ/ር መረራ ጉዲና፤አዲስ የዲሞክራሲ ምዕራፍ መጀመር እንዳለበት የገለጹ ሲሆን ኢህአዴግ የቀሩትንም እስረኞች በመፍታት የፖለቲካ ምህዳሩን የበለጠ ማስፋት ይገባዋል ይላሉ፡፡ ኢህአዴግ 100 ሚ.ህዝብ ብቻውን ማስተዳደር እንደማይችልም ይናገራሉ - ዶ/ር መረራ፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ፣ ቡራዩ አሸዋ ሜዳ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ድረስ በመሄድ፣ በእስር ቤት ቆይታቸው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሊሻሻል ባልቻለው የአገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ፣በመፍትሄ ሃሳቦች ዙሪያና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ አነጋግሯቸዋል፡፡ ዶ/ር መረራ ከእስር ከተፈቱበት ቀን ጀምሮ አሁንም ድረስ ደጋፊዎቻቸውን በቤታቸው እያስተናገዱ ሲሆን ጊዜያቸውን አብቃቅተው ለቃለ ምልልስ በመተባበራቸው፣ በአንባቢያን ስም፣ ከልብ ልናመሰግናቸው እንወዳለን፡፡  

    ከእስር ቤት ሲወጡ የተደረገልዎትን ከፍተኛ አቀባበል ጠብቀውት ነበር?
በጭራሽ! እንዲህ ያለ አቀባበል ቀርቶ ምንም አልጠበቅሁም ነበር፡፡ የማረሚያ ቤት ኃላፊዎቹ፣ “መኪና ያላችሁ ጥሩና  ይውሰዷችሁ” ሲሉን፣ አንድ መኪና ይመጣል ብዬ ነበር የጠበቅሁት፡፡ በኋላ ግን ቦታው ሩቅ ስለሆነ ይመስለኛል፣የማረሚያ ቤቱ ሰዎች፣ በራሳቸው መኪና ለቡ አድርሰውኝ ተመለሱ፡፡ ከለቡ በኋላ አንድ ሁለት መኪናዎች እያጀቡን ነበር፡፡ ወደ አየር ጤና አካባቢ ስንደርስ ደግሞ መኪናዎቹ እየበዙ መጡ፣ የማላውቃቸውን ሰዎችም በብዛት ማየት ጀመርኩ፡፡ ወደ አሸዋ ሜዳ ከፍ ስንል ደግሞ የህዝብ ጎርፍ ተፈጠረ፡፡ መንገዱ ሁሉ ለሰዓታት ተዘጋግቶ ነበር፡፡ እኔ ይሄን እንኳን በእውኔ በህልሜም አልጠበቅሁም ነበር፡፡ በኋላ እንደውም “ይሄ ነገር እንዴት ነው፣ ውጪ ቁጭ ብዬ ብዙ ስራ ያልሰራሁት ሰው፣ በመታሰሬ እንዴት ይህን የህዝብ ፍቅር አገኘሁ ብዬ ተገረምኩ፡፡ እኔ በ1997 ምርጫ ነው ህዝብ በዚህ ደረጃ ሲንቀሳቀስ ያየሁት። ያልጠበቅሁት የህዝብ ጎርፍ ነበር ያጋጠመኝ፡፡
የማዕከላዊ ቆይታዎ ምን ይመስል ነበር?
እኔ ስለ ማዕከላዊ ብዙ ነገር መናገር አልፈልግም። በተዘጉ ፋይሎች ላይ ብዙ ባላወራ እመርጣለሁ፡፡ ይሄ ጥያቄ ይለፈኝ፡፡
በማረሚያ ቤት ሳሉስ ምን ገጠመዎት?
እኔ ስለነበርኩበት ሁኔታ ብዙ ማውራት አልፈልግም፡፡ ግን ቃሊቲ ሳለሁ የታዘብኩትና መንግሥት ቢያስብበት ጥሩ የሚመስሉኝ ነገሮች ገጥመውኛል፡፡ ለምሳሌ፡- በደርግ ዘመን የቀይ ሽብር ፈፅመዋል ተብለው የታሰሩ ሰዎች አሉ። ዋነኛ ባለስልጣናቱ ግን ተፈትተው፣ በነፃነት እየኖሩ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከእነሱ በታች የነበሩ ሰራተኞች፣ እንደውም የቀበሌና የገበሬ ማህበራት ሊቀመንበር የሆኑ ሰዎች ሁሉ ታስረው ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ሰዎች እዚያ ማቆየቱ ለፍትህም ይሁን ለሌላ ነገር ምን እንደሚጠቅም አላውቅም፡፡ ፖሊሲውን ያወጡ፣ ያስፈፀሙ ባለስልጣናት ተፈትተው፣ ተከታዮቻቸው ታስረው መማቀቃቸው ለፍትህ ምንም የሚያግዝ አይመስለኝም፡፡ ደግሞ አብዛኞቹ ሽማግሌዎች ናቸው፡፡ ይሄ መታሰብ ያለበት ትዝብቴ ነው፡፡
ሌላው ደግሞ አካል ጉዳተኞች፣ አይነስውራን፣ የራሳቸውን ሰውነት እንኳ መታጠብ የማይችሉ አቅመ ደካማ ሽማግሌዎች---- በተለያዩ ወንጀሎች ታስረው ይገኛሉ፡፡ ምግብ እንኳ አንስተው መብላት የማይችሉ አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ቢወጡም ተጨማሪ ወንጀል መስራት የሚያስችላቸው አካላዊ ብቃት ያላቸው አይመስሉም፡፡ እነዚህን ሰዎች ለምን እዚያ ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ አይገባኝም፡፡ ከማረሚያ ቤቱ በወጣሁበት ወቅት ላናገረኝ የስራ ኃላፊ፣ ይሄን ትዝብቴን ነገሬዋለሁ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ያሳሰበኝ የተወሰኑ ሰዎች ጉዳይ አለ፡፡ አንደኛው፤ የሰሜን ሸዋ የደብረ ብርሃን አካባቢ የቅንጅት ተመራጭ ነበር፡፡ በወቅቱ በቅንጅት ምክንያት “ወንጀል ሰርቷል” ተብሎ ነው ወደ ማረሚያ ቤቱ የገባው፡፡ ይህ ሰው በዊልቼር ነው የሚሄደው፡፡ እግሩ አይሰራም፡፡ ከ10 ዓመት በላይ ታስሯል፡፡ የፓርላማ አባል ነበር፡፡ ይሄ ሰው ቢወጣ ተጨማሪ ወንጀል ይሰራል ተብሎ የሚታሰብ አይደለም፡፡ የዚህ ሰው ጉዳይ ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡ እንዲሁ አንድ ልጅ ደግሞ በኦነግ ምክንያት ነው የታሰረው፡፡ ሁለት አይኖቹ አያዩም፡፡ መራመድ አይችልም፡፡ ከ12 ዓመት በላይም ነው የታሰረው። መንቀሳቀስ አይችልም፡፡ ምግብ የሚያቀብሉት፣ ሰውነቱን የሚያጥቡት፣ ወደ መኝታው የሚወስዱት ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ሰዎች ስመለከት በጣም አዝኛለሁ፡፡ ከ70 እና ከ80 አመት በላይ የሆኑ አዛውንቶች አሉ፡፡ እነዚህ አዛውንቶች ያለ ሰው ድጋፍ መንቀሳቀስ አይችሉም፡፡ እነዚህን ሰዎች በእስር ቤት ማቆየት ጥቅሙ አይታየኝም፡፡ ከእስር ወጥተው ቀሪ እድሜያቸውን ከቤተሰባቸው ጋር ቢኖሩ ይሻላል፡፡
ጊዜዎን እንዴት ነበር የሚያሳልፉት?
ማዕከላዊ እያየሁ ምንም የማሳልፍበት ነገር የለም፡፡ ማረሚያ ቤት በነበርኩ ሰዓት ግን ሁለት ነገሮችን አደርግ ነበር፡፡ በደርግ ዘመን ታስሬ ሳለሁ፣ ቼዝ እጫወት ነበር፡፡ በአሁኑም ቆይታዬ ቼዝ እጫወት ነበር፡፡ መፅሐፍትም አነባለሁ፡፡ በዋናነት በእነዚህ ነበር ጊዜዬን የማሳልፈው፡፡ ፈረንሳይኛ ቋንቋም ራሴን በራሴ፣ ያለ አስተማሪ ለመማር ጥረት አድርጌያለሁ፡፡
እርስዎን ጨምሮ ጥቂት ፖለቲከኞች ተፈትተዋል፡፡ ቀሪዎች አሉ---?
እውነት ነው፤ ኢህአዴግ በነካ እጁ ቀሪዎችንም መፍታት አለበት፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ ከጣሊያን ወረራ በኋላ ከስደት ሲመለሱ፤“አዲስ ዘመን” ብለው ነው ለመሰየም የሞከሩት፡፡ ጋዜጣውም “አዲስ ዘመን” ነው የተባለው፡፡ አዲዝ ዘመን ሆኗል አልሆነም፤ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ኢህአዴግ ብሄራዊ መግባባት ከልብ እፈጥራለሁ ብሎ የሚያስብ ከሆነ፣ለኢትዮጵያ ህዝብ የመጨረሻ ውለታ በመዋል፣ይሄን ምዕራፍ መዝጋት ይገባዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ አንዱ ሊያደርገው የሚገባ ጉዳይ፣ የፖለቲካ እስረኞችን በሙሉ መፍታት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ይህን ሀገር ወደ ብሔራዊ መግባባት መምራት ይቻላል፡፡ የታሰሩት ደግሞ አብዛኞቹ የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች ናቸው። ብሔራዊ መግባባት፣ግማሽ ፀጉር ተላጭቶ ብቻ የሚሆን አይደለም፡፡ በዚህ ሀገር በህዝብ ደረጃ ብሔራዊ እርቅ ያስፈልጋል፡፡ ለኢህአዴግ አባሎችም ሆነ ለሁላችንም ይሄ እርቅ ያስፈልጋል፡፡
አሁን ያለውን ምዕራፍ በእነዚህ እርምጃዎች ዘግቶ፣ ወደ ሌላ ምዕራፍ መሄድ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ አለበለዚያ በየምክንያቱ ግጭቶች እየተፈጠሩ የሰው ህይወት ይጠፋል፡፡ አሁን ለምሳሌ እንደሰማነው፣ በጫት ንግድ ምክንያት ከኦሮሚያና ከሶማሌ የተፈናቀለው ህዝብ እኮ በበርማ ከተፈናቀሉት በላይ ነው፡፡ አለም ለበርማ ሲጯጯህ ተመልክተናል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መፈናቀል ግን በታሪክም ታይቶ አይታወቅም፡፡ ግን እንዴት በዓለማቀፍ የመረጃ ተቋማት ትኩረት እንዳላገኘ አስገራሚ ነው፡፡ በሚዲያ እንደሰማሁት፣ በወልዲያ አካባቢ የተፈጠረው ደግሞ በእጅጉ አሳዛኝ ነው፡፡ በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ታቦት እጅግ ክብር አለው፡፡ ለ2 ሺህ ዘመን ገደማ፣ ታቦት ባለበት አካባቢ የሰው ህይወት ለማጥፋት አይተኮስም፡፡ አሁን ግን ታቦት ተሸካሚ ካህን ሳይቀር ባለበት ቦታ ይህ መፈጠሩ በእጅጉ አሳዛኝ ነው፡፡ ትልቅ የታሪክና ባህል ክፍተት እየተፈጠረ መሆኑን ያሳየናል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በትንሹ መፍትሄ ሳይበጅላቸው እየቀጠሉ ሄደው፣ ወደ ሩዋንዳ አይነት ዕልቂት እንዳንገባ ከፍተኛ ስጋት አለኝ። ሀገሪቷ ለረጅም ዘመናት ይዛ የቆየችው የባህል፣ የማንነት እሴት ሲናጋ ጥሩ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ በዚህ ረገድ ወደ ግማሽ መንገድ ሄዶ፣ ሌሎች ተቃዋሚዎችም ወደ ግማሽ መንገድ መጥተው፣ ሙሉ ብሔራዊ መግባባት ካልተፈጠረ፣ ዕጣ ፈንታችን አሳሳቢ ይሆናል፡፡
ለኛ ብቻ ሳይሆን ልጆቻችንም በሰላም የሚኖሩባት ሀገር ለመስራት፣ ይህ ምዕራፍ ሙሉ ለሙሉ ተዘግቶ፣ አዲስ ምዕራፍ መጀመር አለበት። ለሀገሪቱ ከልብ በማሰብ ወደ ብሔራዊ መግባባት የሚኬድበት መንገድ መፈጠር አለበት፡፡
ከእስር ሲፈቱ ሀገሪቱን በምን ሁኔታ ላይ አገኟት?
እኔ ከመታሰሬ በፊት ሀገሪቷ መስቀለኛ መንገድ ላይ መድረሷን ተናግሬ ነበር፡፡ መስቀለኛ መንገዱ ላይ ሆነን ያለን አማራጭ ደግሞ ሦስት ብቻ ነው፡፡ አንደኛው፤ እዚያው መስቀለኛ መንገድ ላይ ለረዥም ዘመን እየተሽከረከሩ መኖር ነው፣ ሁለተኛው፤ ለውጥ አምጥቶ፣ ተስፋ ወዳለው ዘመን መሻገር ነው፣ ሦስተኛው ግን የከፋው አማራጭ ሲሆን ወደ አጠቃላይ ውድቀት ውስጥ መግባት ነው፡፡ አሁንም  ሦስት አማራጮች እንዳሉ ቢሆንም፣መስቀለኛ መንገዱ ላይ እየተሸከረከርን ነው፡፡ በተለይ የኢህአዴግ መሪዎች ልቦና አግኝተው፣ ሁላችንን ልታስተናግድ የምትችል ኢትዮጵያን መፍጠሩ ጠቃሚ  መሆኑን አምነውበት፣እርምጃ ከወሰዱ፣ አዲስ ተስፋ ይዘን፣ አዲስ ዘመን ልንፈጥር የምንችልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡  
መሰረታዊ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ምንድን ናቸው?
መሰረታዊ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ጥያቄዎችና የህዝቡ ጥያቄዎች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው የዳቦ ጥያቄ ነው፤ ሁሉም የተሻለ ህይወት መኖር ይፈልጋል፡፡ በሚሊዮኖች የሚርመሰመሰው ወጣትና ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ያለ ስራ በመንገድ ላይ የሚንከራተተው ሥራ አጥ በሙሉ የዳቦ ጥያቄ አለው፡፡ በሃገሩ ተስፋ ቆርጦ በየበረሃው ለስደት ሲወጣ፣ የጅብ ሲሳይ እየሆነ ያለው ወጣት፤ ይህ መሰረታዊ ፍላጎቱ ስላልተሟላለት ነው አማራጭ የፈለገው፡፡ የኢህአዴግ መሪዎች በደንብ አልተመለከቱት ይሆናል እንጂ እኔ የዛሬ አስራ ምናምን አመት፤ “ተዉ አትቀልዱ በህዝብ ኑሮ፣ የሚበላውን ያጣ ህዝብ እኮ፣ መሪዎቹን ሊበላ ይችላል” ብዬ ነበር፡፡ ነገሩን ስናገር ቀልድ ይመስል ነበር፡፡ እኔ ግን በወቅቱ የተወሰኑ ነገሮችን ወደ ፊት አሻግሬ ለመመልከት ሞክሬ ነበር፡፡ አሁን ኢህአዴግ ለ100 ሚሊዮን ህዝብ የሚሆን ኢኮኖሚ መፍጠር አልቻለም፡፡ ምናልባት ጥቂቶች ተጠቅመው ሊሆን ይችላል እንጂ ሃገርን እንደ ሀገር፣ ህዝብን እንደ ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ኢኮኖሚ አልገነባም። ለብዙዎች ተስፋ ሊሰጥ የሚችል ኢኮኖሚ እየተፈጠረ አይደለም፡፡ አንዱ መሰረታዊ ጥያቄው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ነው፡፡
ሌላው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፈራ ተባ እያሉ ኢህዴዶችም የሚያነሱት፣ የእኩልነትና የነፃነት ጉዳይ ነው፡፡ ጆርጅ ኦርዌል የተባለ እንግሊዛዊ ደራሲ፤ ”ሁሉም እንስሳት እኩል ናቸው፣ የተወሰኑ እንስሳት ደግሞ ከሁሉም የበለጠ እኩል ናቸው” ይላል፡፡ ኢህአዴግ ውስጥም ያሉት ድርጅታዊ ግንኙነቶች እንደዚያ ናቸው፡፡ ሁሉም እኩል አይደሉም፡፡ ያን የእኩልነት ጥያቄ ነው ወጣቱ፣ በተለይ እየጠየቀ ያለው፡፡ መሰረታዊ ጥያቄዎቹ የእኩልነትና የኢኮኖሚ ናቸው፡፡ በሀገሪቱ እነዚህ ጥያቄዎች ለመኖራቸው ረጅም ርቀት ተጉዞ ምስክር ማፈላለግ አያስፈልግም፡፡ በሜዲትራኒያን፣ በቀይ ባህር፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በሊቢያ በረሃ በጅብ የሚበላውና በባርነት የሚሸጠውን ወጣት ማየቱ በቂ ነው፡፡ ስለዚህ ህዝቡ የዳቦና የእኩልነት ጥያቄ አለው። የሚፈልገውን ያውቃል፤ ህዝብ እንስሳ አይደለም፡፡ በአንድ ወቅት ላይ የአልጀዚራ ጋዜጠኛ፣ እኔንና አቶ ጌታቸው ረዳን እንዲሁም አንዲት ወጣትን ለውይይት አቅርቦን በነበረ ወቅት፤ ጋዜጠኛዋ አቶ ጌታቸውን፣ “ክቡር ሚኒስትር፤ ህዝቡ የሚፈልገውን ያውቃሉ?” ስትል በተደጋጋሚ ጠይቃቸው ነበር፡፡ አቶ ጌታቸው በበኩላቸው፤ ኢህአዴግ የሰራውን ስራ ነበር ሲናገሩ የነበረው። አሁንም ኢህአዴግ ህዝቡ የሚፈልገውን ካላወቀ የትም አንደርስም፡፡
የአራቱ ግንባር ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት በቅርቡ በሰጡት መግለጫ፣ለህዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በቁርጠኝነት መወሰናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ቃላቸውን ይፈጽማሉ ብለው ያስባሉ?
ኢህአዴግ ችግሩ፣ ላለፉት 27 ዓመታት፣ በራሱ ሳጥን ውስጥ ብቻ ማሰቡ ነው፡፡ እነ ስዬ አብረሃ ሲባረሩ፣ ተሃድሶ ውስጥ ገብተናል ተብሎ ነበር። በኋላም ይህ ተሃድሶ ተደጋግሟል፡፡ ግን የትም መድረስ አልተቻለም፡፡ ያልተደረሰበት ምክንያት ደግሞ ኢህአዴግ በራሱ ሳጥን ውስጥ ብቻ ከማሰብ አለመውጣቱ ነው፡፡ አሁንም ከሳጥኑ ውጪ ማሰብ ካልተቻለ አስቸጋሪ ነው። እኔ ደጋግሜ ለኢህአዴግ መምከር የምፈልገው፣ 100 ሚሊዮን ህዝብ ማስተዳደር፣ ከአንድ ቡድን አቅም በላይ መሆኑን ነው፡፡ 100 ሚሊዮን ህዝብ በኢህአዴግ አቅም መምራት የሚቻል አይደለም። እነሱም በግልፅ አይናገሩ እንጂ ይሄን የተረዱ ይመስላል። በመፅሐፎቼ በግልፅ እንዳስቀመጥኩት፤ ያላለፍናቸው የታሪክ ፈተናዎችንና የሚጋጩ ህልሞችን ይዘን የትም አንደርስም፡፡ እነዚያን የታሪክ ፈተናዎች ማለፍ የምንችለው፣ ሁላችንም ከገባንበት ሳጥን ውጪ ማሰብ ስንችል ነው፡፡ ኢህአዴግ ትልቁ ችግሩ ከራሱ ሳጥን ውጪ አለማሰቡ ነው፡፡ ተሃድሶ እያለ የሚያጥበው፣ የራሱን ሳጥን የውስጥ ክፍል ነው። ከዚያ ሳጥን መውጣት ከቻሉ፣ ከሌሎች ጋርም መገናኘት ይችላሉ፡፡ ይሄ ሃገር የጋራ ሃገራችን ነው። ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሄውም የሁሉም መዋጮ ነው፡፡ ያ የሁሉም መዋጮ፣ ወደ መፍትሄው አደባባይ እንዲመጣ፣ ኢህአዴግ ምህዳሩን መክፈት አለበት፡፡ ለዚህ ነው ኳሱ በኢህአዴግ ሜዳ ነው የምለው፡፡ ያንን ሜዳ ለሁላችንም ካላመቻቸ፣ ሁላችንም መፍትሄ የምንለውን ሁሉ በእጃችን ይዘን ብቻ ነው የምንዞረው፡፡ ከዚህ በኋላ የ100 ሚሊዮን ህዝብን ህልውና፣ አንድ ቡድን ብቻ ይወስናል ብሎ መልፋቱ አይጠቅመንም፡፡  
በሌላ በኩል የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የአቶ ለማ መገርሳ ቡድን፣ ሰፊ የህዝብ ድጋፍ እያገኘ መሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡ ይሄ ለእርስዎ ምን ማለት ነው?
አቶ ለማን አለቃ ሆኖ ሲመረጥ፣ ወዴት እንደሚሄድ፣ ምን እንደሚሆንም አስቸገረኝ፣ ክፋት መናገርም አስቸገረኝ፡፡ ብዙ ጥሩ ነገሮችንም መናገር አስቸገረኝ፡፡ ተማሪዬ ነበር፡፡ “ፊቱ ግን ኦሮሞ ይመስላል” አልኩ፡፡ ይሄን አባባሌን ማዕከላዊም “ምን ለማለት ፈልገህ ነው?” ተብዬ ተጠይቄያለሁ። እና ይሄ ጉዳይ በዚሁ ቢቀር ይሻለኛል፡፡ አሁን ሌላ ምንም  ማለት አልችልም፡፡
አቶ ለማ ተማሪዎ ነበሩ?
አዎ! ተማሪዬ ነበር፡፡
በርካቶች እነ አቶ ለማን “የለውጥ ሃዋርያ” አድርገው ያስቧቸዋል፡፡ በእነሱ በኩል ለውጥ የሚመጣ ይመስልዎታል?
መሪዎች ከቻሉ የህዝብን ፍላጎት አውቀው ቢመሩ ጥሩ ነው፡፡ በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የተተበተበ ኢህአዴግ፣ ከሳጥን ውጪ ወጥቶ ማሰብ ይችላል አይችልም? ከሳጥን ውጪ ወጥቶ ይሰራል አይሰራም? የሚለው ነው፤ ዋናው ጥያቄ፡፡ የእነ አቶ ለማን እንቅስቃሴም፣ ከዚህ አንፃር ውሎ አድሮ የምናየው ይሆናል፡፡ ግን ከሳጥኑ መውጣት ይችላሉ አይችሉም፣ የሚለው ክርክር ውስጥ አሁን መግባት አልፈልግም፡፡ ከሳጥናቸው ወጥተው፣ ይሄን ህዝብ በስርአት ለመምራት ዝግጁ ናቸው ለማለት ግን ያስቸግረኛል፡፡ ስለዚህ የተግባር ፈተናውን ሲያልፉ፣ ጠብቆ ማየቱ ጥሩ ነው፡፡ ይሄን የተግባር ፈተና ሲያልፉ፣ የምንጣላበት ምክንያት የለም፡፡ ለውጥ ከመጣ ህዝብ ከሚፈልገው ለውጥ ጋር ፊት ለፊት ተጋትረን የምንቆምበት ምክንያት የለም፡፡ መጀመሪያ የታሪክና የተግባር ፈተናውን ይለፉ፡፡ እስከዚያ ድረስ ጥሩ ሲሰሩ፣ ደስ ብሎን እናያለን፡፡
ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት የርዕዮተ ዓለም ለውጥ የግድ ያስፈልጋል፣ ብለው የሚሞግቱ ወገኖች  አሉ፡፡  እርስዎስ ምን ይላሉ?
እኔ ለርዕዮተ ዓለም ብዙ ቦታ አልሰጥም፡፡ የርዕዮተ ዓለም ጉዳይ አይጨንቀኝም፡፡ ኢህአፓ እና መኢሶን ሶሻሊስቶች ነበሩ፡፡ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት አልነበራቸውም፡፡ ምናልባት ደርግ የማያውቀው ርዕዮተ ዓለም ውስጥ ተዘፍቆ ተቸገረበት እንጂ ኢህአፓ እና መኢሶን በርዕዮተ ዓለሙ የተጠበቡ ነበሩ፡፡ የዚህች ሀገር ችግር ርዕዮተ ዓለምን መጠቀሚያ ማድረጉ ነው፡፡ ርዕዮተ ዓለም አላቸው የምንላቸው ምሁራንና ፖለቲከኞች ቢፋቁ፣ ከፊውዳል አስተሳሰብ ብዙም የራቁ  አይመስለኝም። ሁሉም ሲፋቅ ውስጡ፣ ፊውዳል ኢትዮጵያ ነው ያለችው፡፡
አንድ ፈረንሳዊ የፒኤችዲ ዲግሪውን ሲሰራ፣ ኢህአዴግ ላይ ያደረገው ጥናት ነበር፡፡ በጥናቱ፤ የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ፤ ”አብዮታዊም አይደለም፤ ዲሞክራሲያዊም አይደለም” ነበር ያለው፡፡ ሁለቱንም አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ውስጥ አንዳንዶቹ ሃይማኖተኞች ናቸው፤ ከፊውዳሊዝም የራቁ አይደሉም፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ዝም ብሎ ከመንገድ የመጣብን፣ ባለቤቶቹም በቅጡ የማያውቁት ነገር ነው፡፡ ህዝባችን ፍላጎቱ ርዕዮተ ዓለም ሳይሆን ጥሩ ኑሮ መኖር፣ እኩልነትና ሰላም ነው፡፡ ዲሞክራሲ፤ አንዳንድ የኢትዮጵያ ባህሎች ድሮም አላቸው፡፡ የገዳ ሥርአት የስልጣን ምርጫ፣ ከኢህአዴግ ምርጫ ይሻላል፡፡
ከእስር ከተፈቱ በኋላ “አዲስ የዲሞክራሲ ምዕራፍ መጀመር አለበት” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ምን ለማለት ነው? እስቲ ያብራሩልን?
ከንጉሱ መውረድ ጀምሮ ሶሻሊዝም ብለን ብዙ ዓመት ገፋን፣ ከዛ ደግሞ ላለፉት 27 ዓመታት አብዮታዊ ዲሞክራሲ በሚል ዲሞክራሲያዊ ሥርአት እየገነባን ነው ተብሎ፣ በአየር ላይ ለፋን፤ ነገር ግን መሬት ላይ የለም፡፡ ፌደራሊዝሙም ዲሞክራሲውም የለም፡፡ ዞሮ ዞሮ አንድን ሥርአት፣ ”ህዝብ የኔ ነው” ብሎ ሲቀበለው ነው ውጤታማ የሚሆነው። ዲሞክራሲ ተብሎ የህዝብ ድምፅ ከተሰረቀ፣ እኩልነት ተብሎ የህዝብ መብት በጎን ከተደፈጠጠ፣ በቃል እንጂ በተግባር የለም ማለት ነው፡፡ እነዚህ ካልተሟሉ አንድ ሺህ ጊዜ ዲሞክራሲ እየተባለ ቃሉ ቢደጋገም፣ ከማደንቆር ውጪ ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ ህዝብ፤ “ዲሞክራሲ አለ” ካለ፣እውነትም አለ ይባላል፡፡ ገዥው፤”ዲሞክራሲ አለ” ካለ ግን፣ ህዝብ “የለም” እያለ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ የኢህአዴግ ትልቁ ችግር ይሄ ነው፡፡ ሕዝብ የለም ይላል፤ እሱ አለ ይላል፡፡ እኔ የፖለቲካ ሳይንስ አስተማሪ ነኝ፤ እኔ ብቻ ሳልሆን በርካታ የዓለም ምሁራን፣ የዚህን ሃገር ፖለቲካ አጥንተዋል፡፡ መሬት ላይ ዲሞክራሲ የለም ብለዋል፣ ፍትሃዊና ነፃ ምርጫ ኢትዮጵያ ውስጥ አልተካሄደም በማለት ፅፈዋል። ይሄን ድርቅ ብሎ እያስተባበሉ መኖር ደግሞ የኢህአዴግ ተግባር ሆኗል፡፡ ዋናው ጉዳይ፤ “ህዝብ ምን ይላል” የሚለው ነው፡፡
የዲሞክራሲ መለኪያዎች ምንድን ናቸው?
አንዱ ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ ነው። ህዝቡ ነፃ ሆኖ ፍላጎቱን በድምፁ ሲገልፅና፣ ያ ተቀባይነት ሲያገኝ አንዱ መለኪያ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ አንዱ መሳሪያ የምርጫ አስተዳደር ነው፡፡ ከድምፅ ቆጠራ ጀምሮ እስከ ውጤት መግለፅና ማስፈፀም ያለ ነው፡፡ ሁለተኛው የታዛቢዎች ሚና ነው፡፡ ሶስተኛው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠባይ ነው። እነዚህ መመዘኛዎች በ2002 ድርድር ወቅት በጥናት፣ ለኢህአዴግ ቀርበውለት ነበር፡፡  ነገር ግን ኢህአዴግ ብልጣ ብልጥ ልሁን ብሎ ሊሆን ይችላል፤ የምርጫ አስተዳደርና የምርጫ ታዛቢዎች ጉዳይን ደብቀው፣ የፓርቲዎች ጠባይ ላይ ብቻ መደራደር አለብን ብለው ቀረቡ፡፡ እኛ ደግሞ የቀሩት ሁለቱ ላይ እንደራደር አልን፤ እነሱ አልተቀበሉም፡፡
በወቅቱ መድረክ በዚህ ምክንያት ከድርድሩ ወጥቷል፡፡ ሌሎች ሃገሮች እንደ እነ ጋና ያሉት፣ ይሄን ጥናት ተጠቅመውበት ውጤት አግኝተውበታል። ስለዚህ ጉዳዩ የተደበቀ አይደለም፤ጨዋታውን ሁሉም ያውቀዋል፡፡ የኢህአዴግ ቅንነትና ፍላጎት ብቻ ነው የሚጠበቀው፡፡
ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር ተደራድረው፣ የምርጫ ሥርዓቱን መቀየራቸው ይታወቃል…
እዚህ ጋ ላስቁምህና ምናልባት ፓርቲዎቹ እንዳይቀየሙኝ እንጂ ድርድር አልተካሄደም፤ እየተካሄደም አይደለም፡፡ የኦሮሞን ሰፊ ህዝብ ከማይወክሉት ጋር ቁጭ ብሎ ተደራደርኩ ማለት፣ ለህዝቡ የሚፈጥረው ስሜት የለም፡፡ እንደ ድርድር መቁጠርም ተገቢ አይደለም፡፡ ቢያንስ የፖለቲካል ሳይንስ አስተማሪ ነኝ፡፡ የፖለቲካ ድርድር ምን እንደሆነ አውቃለሁ፤ ይሄን እንደ ድርድር መቁጠር ቀልድ ማብዛት ነው፡፡ ወሳኙ ደግሞ የምርጫ ስርአት መቀየር አይደለም፤ዋናው ምርጫው ነፃ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ መሆኑ ላይ ነው፡፡ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ መኖሩን ሳናረጋግጥ የትም ልንደርስ አንችልም፡፡   
እርስዎ ለአገሪቱ ፖለቲካዊ ችግሮች የሚጠቁሙት የመፍትሄ ሀሳብ ምንድን ነው?
 እንደኔ ከሆነ፣ አንድ ቡድን ብቻውን 100 ሚሊዮን ህዝብ ማስተዳደር አይችልም፡፡ ስለዚህ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ መፈቀድ ገባዋል፡፡ ገዥው ፓርቲ ስልጣን ማካፈል አለበት፡፡ ፈረንጆች የዘገየ ትናንሽ መፍትሄዎች የሚሉት ነገር አላቸው፡፡ አሁን ችግር እየፈጠረ ያለው ይሄ ነው፡፡ ኢህአዴግ እየተለወጥኩ ነው ይላል፤ ግን ትናንሽ ነገሮችን ነው እየሰጠ ያለው፡፡ ከዛሬ ጀምሮ በድርድር ወደ መፍትሄ እንደርሳለን፤የሚል ቁርጠኝነት እያሳየ አይደለም፡፡ ሁሉንም ነገር በስስት ነው እየሰጠ ያለው፡፡ ይሄ ደግሞ ህዝብን እያጠገበ አይደለም፡፡ ብዙ የተራበን ህዝብ ፍርፋሪ ቢሰጡት፣ ለዕለቱ ሊያሳድረው ይችላል እንጂ ለነገ ስንቅ አይሆነውም፡፡ ፍርፋሪ ብቻ መስጠቱ ነው ችግሩ፡፡ ኢህአዴግ በህዝቡ ውስጥ፤ ”ኢትዮጵያ እየተለወጠች ነው፣ ተስፋ አለኝ - ወደ ሰላም፣ ልማትና ብልፅግና እየሄድን ነው” የሚል ተስፋ መፍጠር አልቻለም፡፡ ህዝብ ተስፋ የሚሰጥ ፖለቲካ ይፈልጋል፡፡
ከዚህ በኋላ በፖለቲካ ተሳትፎ ይቀጥላሉ ወይስ ምን አሰቡ?
ይሄን ገና ከፓርቲው ጋር እመክራለሁ፡፡ ነገር ግን ከእስር ቤት ስወጣ በሁለት ልብ ነበርኩ፡፡ አንደኛው ጡረታ እወጣለሁ የሚል ነው፡፡ ሌላው ደግሞ መቆየት ይኖርብኝ ይሆናል የሚል ነበር፡፡ ግን ያየሁት የህዝብ ድጋፍና ፍቅር ደግሞ “ትንሽ ቆይ” የሚለኝ ይመስለኛል፡፡ በተለይ የቡራዩ አካባቢ የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ ህፃናት ሳይቀሩ፣ በየዙሩ መጥተው ጎብኝተውኛል፡፡ ይሄን ስመለከት ወደ አዕምሮዬ ብዙ ነገር ነው የተመላለሰው፡፡ መጪው ትውልድ የራሱን ነገ ለማስተካከል እየታገለ ባለበት ወቅት የኔ ጡረታ ለመውጣት ማሰብ ይቸግራል። ኃላፊነትም ይጥልብኛል፡፡ በተለይ የህፃናቶቹ ሁኔታ በጣም ነው የተሰማኝ፤ ከጠበቅኩትም በላይ ንቃት አላቸው፡፡ ሰው ቀስቅሷቸው አይደለም እኔ ጋ የመጡት፤በራሳቸው ተነሳሽነት ነው፡፡ ፖለቲከኛ ብዙ ጊዜ ወደ ጡረታ የሚሮጠው ደግሞ ህዝብ ሲከዳው ነው፡፡ ህዝብ ሲደግፈው ግን ትንሽ ብቆይ ብሎ ያስባል፡፡ ቢያንስ መስመሩ ላይ ቆመን የምንታገል ሰዎች፤ የህዝቡን ተስፋ ማለምለም እንጂ ማዳፈን የለብንም፡፡ ቢያንስ ሁላችንንም በእኩልነት የምታስተናግድ የተለወጠች ኢትዮጵያን አይተን ብንሞት፣ ለኛም ዘላለማዊ እረፍት ነው። እኔ የህዝቡ በተለይ የህፃናቱ ሁኔታ በጣም ነው የተሰማኝ። ህፃናቱ መፈክር ይዘው ሊጠይቁኝ ሲመጡ፣ ልገልፀው የማልችለው ስሜት ነው የፈጠረብኝ፡፡    


Read 6543 times