Sunday, 28 January 2018 00:00

በወልዲያ የሰው ህይወት ያጠፉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

       በወልዲያ ለተገደሉ 7 ዜጎች ተጠያቂ የሆኑ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ መኢአድ እና ሰማያዊ ፓርቲዎች የጠየቁ ሲሆን ግድያዎችንና የዜጎችን መፈናቀል ለመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያዘጋጁ አስታውቀዋል፡፡
ፓርቲዎቹ ጉዳዩን አስመልክቶ በጽ/ቤታቸው ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፤ ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም በወልድያ ከተማ የቅዱስ ሚካኤልን ታቦት አጅበው በመጓዝ ላይ ባሉ ዜጎች ላይ ግድያ መፈፀሙን በፅኑ አውግዘዋል፡፡
“ንፁሃን ዜጎችን እየገደሉ የስልጣን እድሜን ለማራዘም መሞከር በእሳት እንደመጫወት ነው” በሚል ርዕስ ፓርቲዎቹ ባወጡት መግለጫቸው፤ “ታቦት ባለበት ቦታ አስለቃሽ ጭስ መተኮስ ሃይማኖታዊ ትውፊትንና ባህልን መፃረር ነው” ብለዋል፡፡ ለዚህም መንግስት የእምነቱን ተከታዮች በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል፡፡
ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነውን የኃይል እርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ ያስተላለፉ፣ ጉዳዩን በቸልታ የተመለከቱ የከተማ አስተዳደሮችና ግድያ በቀጥታ የፈፀሙ አካላት ተጣርተው በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን” ብለዋል ፓርቲዎቹ - በጋራ መግለጫቸው፡፡
መንግስት ሃገሪቱን ለማረጋጋት በየጊዜው የሚገባውን ቃል በተግባር አለመፈፀሙ ተአማኒነት እንዲያጣ ያደርገዋል ያሉት ፓርቲዎቹ፤ መንግስት ቃሉን አክብሮ ተግባራዊ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
በኃይል እርምጃ ደም ማፍሰስ ቆሞ መንግስት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለብሄራዊ መግባባት ራሱን ማዘጋጀት እንዳለበት የጠቆሙት ፓርቲዎቹ፤ በአሁኑ ወቅት ቀዳሚው የሀገሪቱ አጀንዳ ብሄራዊ መግባባት ብቻ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
ህዝቡ ብሶቱን ሊያሰማባቸው የሚያስችሉ ሰላማዊ ሰልፎችን በተመረጡ የሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች ለማዘጋጀት እቅድ መያዛቸውንም ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡

Read 5328 times