Saturday, 27 January 2018 11:58

“ቆብ አስጥል - የትውፊት አምባሳደር”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

    የዘንድሮን የጥምቀት በዓል በጎንደር ለመታደም ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ ወደዚያው ያመራችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በከተማዋ “የትውፊት አምባሳደሮች” እየተባሉ የሚጠሩትን የባህልና የምግብ አዳራሾች ጎብኝታለች፡፡ ለዛሬ
“ቆብ አስጥል” የተባለውን የባህልና የምግብ አዳራሽ፣ በባለቤቱና ሥራ አስኪያጁ አቶ ወንደሰን ብዙአለም አንደበት አማካኝነት
ቤቱን ታስቃኘናለች፡፡ አቶ ወንደሰን ከምን ተነስተው የት እንደደረሱም ያሳያል - ቃለ ምልልሱ፡፡

   ከስያሜው እንጀምር … “ቆብ አስጥል” ምን ማለት ነው?
በንጉሱ አፄ ፋሲል ዘመን “ቆብ አስጥል” የሚባል ድልድይ ነበር፡፡ ቤተ-ክርስቲያኖች ከፋሲል ቤተ መንግስት ጋር በድልድይ የተገናኙ ነበሩ፡፡ በዚያ ድልድይ ስር የአካባቢው ሰው ሲመላለስ፣ገና ለገና ንጉሱ ከላይ ይኖራሉ በሚል ቆቡን ያወልቅ ነበር፡፡ ንጉሱ ቢኖሩም ባይኖሩም ጎንበስ ብሎ እጅ ይነሳል፣ በዚህም የተነሳ ድልድዩ “ቆብ አስጥል” ተባለ። ይሄ ታሪክ ተፅፎ፣ የባህል አዳራሻችን መግቢያ ላይ ሁሉም በሚያየው መልኩ ተለጥፏል፡፡ የባህል አዳራሻችንን “ቆብ አስጥል” ብለን የሰየምነው፣ እንግዶቻችንን እንደ ንጉስ አክብረን፣ ቆባችንን አንስተንና ጎንበስ ብለን የምስተናግዳቸው መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡
የባህል አዳራሹ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ይንገሩኝ?
በሙዚቃ ረገድ ቤቱ የአማራ ክልልን፡- የጎንደር፣ ጎጃምና ወሎ ዘፈኖችና ውዝዋዜዎችን ብቻ ሳይሆን ከ24 በላይ የብሔር ብሔረሰቦች ዘፈኖችና ጭፈራዎችን (ከእነ አልባሳቱ) በተሟላ ሁኔታ፣ በ”ቆብ አስጥል” ባንድ ታጅበው፣  ይቀርባሉ፡፡ ሌላው ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች ናቸው፡፡ ዶሮ ወጥ፣ ስጋ ቁርጥ፣ ጠጅ፣ ጠላና ባህላዊ አረቄም-- በየዓይነቱ ጥራታቸውን ጠብቀው ለእንግዶች ይሰናዳሉ፡፡ ሁሉም የተሟላበት ቤት በመሆኑ እንግዶቻችን ምንጊዜም ተደስተው ነው የሚሄዱት። በተደጋጋሚም እየመጡ  ይዝናናሉ፡፡
ወደዚህ ዘርፍ ለመሰመራት ያነሳሳህ ምንድን ነው?
ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪዬን ያገኘሁት በቱሪዝም ማኔጅመንት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ አራት ኮከብና ከዚያ በላይ ደረጃ ባላቸው ሆቴሎች በተለያየ ሀላፊነት ላይ ሰርቻለሁ፡፡ በትውልድ አካባቢዬ ደብረታቦር በሚገኘው ህብረት ሆቴል ነው ሥራ የጀመርኩት፡፡ በኋላም አዲስ አበባ ፍሬንድሺፕ፣ ደሳለኝ ሆቴል፣ ሀዋሳ፣ ደቡብ ሪዞርት፣ ጎንደር ላንድ ማርክ ሆቴል---ተቀጥሬ ሰርቻለሁ፡፡ ከዚያ ሁሉ በኋላ ወደ ጎንደር ስመለስ፣ በከተማው ያለውን ክፍተት ማጥናት ጀመርኩኝ፤ ክፍተቱም አሁን የተሰማራሁበት ዘርፍ ሆኖ አገኘሁት፡፡  ከዚያ ቀጥታ ወደ ስራ ገባሁ፡፡
በተለያዩ ሆቴሎች ተቀጥረህ ነበር የምትሰራው። “ቆብ አስጥል”ን ለመጀመር ደግሞ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚያስፈልገው ይመስለኛል፡፡ ገንዘብ ከየት አገኘህ ?  
እርግጥ ገንዘብ በጣም ያስፈልገኝ ነበር፡፡ ሆቴል በምሰራበት ወቅት ትጉህ ከሆኑ ዋለልኝ በላይ የሻነው የተባሉ ባለሀብት ጋር ተገናኝተን ተነጋገርን። ጎንደር ከተማ ታሪካዊና ትልቅ የባህል ትውፊት ያላት ከተማ እንደመሆኗ፣ በርካታ የውጭም የአገር ውስጥም ዜጎች የሚጎበኟት ናት፡፡ ስለዚህ ምን ያስፈልጋታል? በሚል አጥንተንና ፕሮፖዛል ቀርፀን ስንጨርስ፣ ባለሀብቱ በጀት ለቀቁልንና በአክሲዮን ተመሰረተ፡፡
ከቅጥር ወጥተህ ወደ ግል ሥራ ለመግባት ስትወስን፣ ባይሳካልኝስ ወይም ደግሞ ብከስርስ ብለህ አልሰጋህም ነበር?
ከዘመናዊ የሆቴል ሥራ ወጥቶ፣ በግል በእንደዚህ አይነት ባህላዊ ዘርፍ መሰማራት፣ በመጠኑም ቢሆን ስጋትና ፍርሀት ማምጣቱ አይቀርም፡፡ ሆኖም ስንጀምረው በጥናት ላይ ተመሰርተን ስለነበር፣ይህን ያህል ስኬት እናመጣለን ባንልም፣ ሥራው እንደሚሳካ እርግጠኛ ነበርን፡፡
ቤቱ የተለያዩ የብሄር ብሄረሰቦች ዘፈኖችን የሚጫወቱ ጎበዝ ድምፃዊያንና ተወዛዋዦች አሉት፡፡ ለመሆኑ የየብሄሮቹን ባህል- አለባበስ፣ አዘፋፈን፣ ቋንቋ፣ ጭፈራ ወዘተ---እያጠናችሁ ነው የምትሰሩት?
ቤቱ “ቆብ አስጥል” ባንድ አለው፡፡ የራሱ የባንድ መሪና አሰልጣኝም አለው፡፡ ተወዛዋዦች እስከ ብሄራዊ ቴአትር ድረስ ተልከው፣ የአንድን ብሄር አለባበስ፣ ጭፈራ፣ ባህልና ትውፊት ይሰለጥናሉ። እንኳን ለተወዛዋዥና ድምፃዊያን ቀርቶ በመስተንግዶ ላይ ለተሰማሩትም በየጊዜው ስልጠና ይሰጣቸዋል፡፡ አንድ እንግዳ እንዴት መስተናገድ እንዳለበት? አለባበስ ምን መምሰል ይገባዋል? ንፅህና አጠባበቅስ?--- በሚሉት ዙሪያ በየጊዜው ይሰለጥናሉ፡፡ እናም ደንበኞቻችን በምንሰጠው አገልግሎት፣ እረክተው ተደስተውና ተዝናንተው ነው የሚወጡት፡፡ እኔም እንደ ማንኛውም አስተናጋጅ፣ በሥራዬ ላይ በመገኘት አብሬ እሰራለሁ፡፡
“ቆብ አሰጥል” በምን ያህል ካፒታል ነው የተቋቋመው? በአሁኑ ወቅት ምን ያህል ሰራተኞች አሉት?
የተመሰረተው በ1.5 ሚ. ብር ሲሆን አሁን 53 ሰራተኞችን ያስተዳድራል፡፡ ይኸው ከታህሳስ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በጥሩ ሁኔታ እየንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
የወጣትነት ዕድሜ ፈታኝ በመሆኑ፣ በአጭር ጊዜ፣ በቢዝነስ ስኬታማ መሆን አስቸጋሪ ነው ይባላል፡፡ ያንተ የስኬት ምስጢር ምንድን ነው?
እርግጥ በወጣትነት ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ ሁሉ ነገር ያምርሻል፣ ገንዘብ መቆጠብ ያስቸግራል፡፡ ብቻ ወጣትነት የብዙ ፈተናዎች ወቅት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ይመስለኛል፣ ጥያቄውንም ያነሳሽው፡፡ እኔ እንግዲህ ከዩኒቨርሲቲ ከወጣሁ በኋላ በተለያዩ ሆቴሎች፣ ከምግብና መጠጥ ቁጥጥር እስከ ከፍተኛ የሃላፊነት ቦታዎች  ሰርቻለሁ። በዚህም ጊዜ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ተገናኝቻለሁ፡፡ የሥራው ባህሪም ገብቶኛል፡፡ በተፈጥሮዬም መዋል የምፈልገው፣ በእድሜም በእውቀትም ከኔ ከሚበልጡ ሰዎች ጋር ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ትንሽ በሰል እንድል አግዞኛል፡፡ ስለዚህ የወጣትነቱ ፈተና ብዙ አልተገዳደረኝም። ኑሮዬን በእቅድ እመራለሁ፤ የአላማ ፅናት አለኝ፡፡ ስኬቴ ከዚህ የመጣ ነው፡፡ አሁን ስኬት ገና መጀመሩ ነው፤ ብዙ የሚቀር ነገር አለ፡፡ ብዙ እቅድ አለ፡፡
ለምሳሌ?
የ”ቆብ አስጥል” ሌሎች ቅርንጫፎችን የመክፈትና ብራንዱን የመሸጥ እቅድ አለኝ፡፡ ገና ብዙ መስራት እፈልጋለሁ፡፡
በከተማዋ ከሚገኙ የባህል ቤቶች፣ “ቆብ አስጥል” በምን ይለያል? እንግዶች ለምን ይመርጡታል?
በበኩሌ በብዙ ነገር ይለያል ባይ ነኝ። ለምሳሌ ቤቱ እጅግ በርካታ ሰው የሚገባበት ነው። አንቺም የጥምቀት ዕለት ምሽት መጥተሸ፣ ቤቱ ሞልቶ ተመልሰሻል፡፡ በዚህ የሰው ብዛት ሌብነት እንዳይከሰት፣ መስተንግዶ እንዳይጓደልና ያልተገቡ ነገሮች እንግዶች ላይ እንዳይፈፀሙ----- በቤቱ ውስጥ አምስት ዘመናዊ የቅኝት ካሜራዎች (CCTV) ተገጥመዋል፡፡ ደህንነቱ የሚጠበቅ፣ ብቸኛው የባህል ቤት ነው፡፡ ሌላው ሰራተኞቻችን በየጊዜው ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሚመጡ ባለሙያዎች እየሰለጠኑ፣ ስራቸውን የሚያቀላጥፉ ጎበዞች ናቸው፡፡ ተወዛዋዦችም ሆኑ ድምፃዊያኑ የተመረጡና ብቃት ያላቸው ናቸው፡፡ ይህን ራስሽ በአይንሽ አይተሻል፡፡ ከስሙ ጀምሮ ይለያል እኮ! በጣም መዋቅሩ የተደራጀ፣ የሽያጭ መሳሪያው ምርጥ ሶፍትዌር የተገጠመለትና ዘመናዊ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ልዩ የሚያደርገው ይመስለኛል፡፡
በመጨረሻስ----
ከየትኛውም ቦታ---- ከአዲስ አበባም ሆነ ከሌሎች ቦታዎች የሚመጡ እንግዶችን፣ እጃችንን ዘርግተን በመቀበል፣ አስደስተን እንልካለን፡፡ ጎብኙን --- እላለሁ፡፡ “ቆብ አስጥል” በሁለት እግሩ እንዲቆም አስተዋፅኦ ላደረጉ ግለሰቦች፣ ለ”ቆብ አስጥል” ሰራተኞችና በየጊዜው እየመጡ በመዝናናት፣ አድናቆታቸውን ለሚገልጹልን ደንበኞችም ልባዊ ምስጋና እናቀርባለን፡፡ በመጨረሻም፣ እየመጣችሁ ጎብኙን --- እላለሁ፡፡   

Read 4693 times