Saturday, 27 January 2018 11:58

የውሃ ጣዕም እንዳይቀየር የሚያደርግ የውሃ መያዥ (ታንከር) ወደ አገር ሊገባ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

ለብዙ ዓመታት የውሃ ማከሚያ (ማጣሪያ) የሆነውን አኳታብ ታብሌት በማከፋፈል የሚታወቀው ሲትሬስ ትሬዲንግ አሁን ደግሞ ከእንግሊዙ ቡታይል ፕሮጀክትስ ጋር በመሆን የውሃ ጣዕም እንዳይቀየር የሚያደርግ የውሃ ታንከር ወደ አገር ውስጥ እንደሚያስገባ አስታወቀ፡፡
ኩባንያው፣ ባለፈው ረቡዕ በጎልደን ቱሊፕ ሆቴል ከቡታይል ፕሮጀክት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እና ስደት፣ ጦርነት…በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለሚሠሩ  ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች፣ ኦክስፋም፣ዩኒሴፍ፣ የስደተኞች ድርጅትና ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣… ትልቁ ውሃ መያዥ ታንከር አቅራቢ ከሆነው የእንግሊዝ ኩባንያ ጋር ከ3 ዓመታት በፊት ሽርክና መግባታቸውን ገልፀዋል፡፡
በፋርማሲቲካል፣ በቤት ውሃ ንፅህና፣ በሃይጂንና በሳኒቴሽን ዙርያ በሚያደርገው እንቅስቃሴ እውቅናና መልካም ስም ካፈራው ሲትሬስ ኢንተርናሽናል ጋር መሥራታችን፣ ከመንግሥት ኃላፊዎች፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ከዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች ጋር የሚኖረንን ግንኙነት ያቀለዋል ያሉት የቡታይል ፕሮጀክትስ የሽያጭ ዳይሬክተር ሚ/ር ክሬጅ ቦል፣ የልማት ፕሮጀክቶችንና በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ድንገተኛ አደጋዎችን  ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምርቶቻችንን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ያስችለናል ብለዋል፡፡
ሚ/ር ክሬጅ አያይዘውም፣ ቀደም ሲል ድርጅታቸው በኢትዮጵያና አፍሪካ የተለያዩ አገሮች ፕሮጀክቶች መሳተፉን ጠቅሰው፣ በ2016 አልሻዳይ ኦርፋነጅ በተባለ አገር በቀል ድርጅት አማካይነት በትግራይ-ውቅሮ ፍሌክስገስተር V80 የተባለ ፕሮጀክት መሥራታቸውን እንዲሁም፣ ኩባንያው በቅርቡ በአፋር ክልል የውሃ ታንከር መትከሉንና በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሠራተኞች አያት አካባቢ እየሠራ ባለው ኮንደሚኒየም የውሃ ታንከር ይተክላል ብለዋል፡፡
አሁን የሚተከሉት ታንከሮች ከ10,000 -1.2 ሚሊዮን ሊትር ውሃ የመያዝ አቅም አላቸው ያሉት የሲትሬስ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ጀነራል ማናጀር አቶ ምናሴ ክፍሌ፣ ታንከሮቹ ዓለም አቀፍ የጥራት ማረጋገጫ ስላላቸው፣ ንፁህ ውሃ የማግኘት ዕድላችን የሰፋ ይሆናል፡፡ ታንከሮቹ በኮንክሪት ከሚሠሩት የተሻሉ ናቸው፡፡ ከአንድ ቦታ ነቅሎ ወደ ሌላ ቦታ መውሰድ ይቻላል፡፡ የኮንክሪት ታንከሮችን ለመትከል ወራት የሚፈጅ ሲሆን አዲሱ ታንከር ግን በሁለትና ሦስት ቀናት ውስጥ መትከል ይቻላል ብለዋል፡፡ በዋጋ ረገድም ከኮንክሪት የተሻሉ መሆናቸውን ጨምረው ገልፀዋል፡፡

Read 2855 times