Print this page
Saturday, 27 January 2018 11:52

21ኛው የዓለም ዋንጫ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

 · 130 ቀናት ቀርተውታል
     · በሽርሽር የካቲት 17 እና 18 ላይ ኢትዮጵያን ይደርሳል፡፡
     · የአዲስ አድማስ፣ የሊግ ስፖርት እና የሪፖርተር የስፖርት ጋዜጠኞች የዘገባ እድል አግኝተዋል፡፡
     · በ85 አገራት የሚገኙ 116 የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በ48 አገራት የሚገኙ ከ58 በላይ ራዲዮ ጣቢያዎች በቀጥታ
       ስርጭት ሽፋን ይሰጡታል፡፡
     · የተጨዋቾች የዋስትና ክፍያ ከ209 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡

    ራሽያ ለምታስተናግደው 21ኛው የዓለም ዋንጫ 130 ቀናት ቀርተውታል፡፡ በስፖርቱ ዓለም ያለፉትን 5 ዓመታት በክፉ እየተነሳች ቆየችው ራሽያ በተለይ ኮዶፒንግ ቅሌት ጋር በተያያዘ የአገሪቱ ስፖርት ብዙ ክስረት የገጠመው ሲሆን፤ ከኦሎምፒክ እና ከዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የውድድር መድረኮች በዶፒንግ ጥፋት በ100ዎች የሚቆጠሩ አትሌቶች ከተሳትፎ በመታገዳቸው ከፍተኛ ውጤቶች፤ ታሪካዊ ክብሮች ቀርተውባታል፡፡ በዓለም ፖለቲካ በምትከተለው አቋም የጊዜው የምታነጋግረው ራሽያ፤ ከአጎራባች አገራት ጋር በየጊዜው በምትገባበት የፖለቲካ ቀውስና ግጭትም የዓለም መገናኛ ብዙሃናት አብይ አጀንዳ እንደሚያደረጓትም ይታወቃል፡፡
21ኛው የዓለም ዋንጫ የራሽያን የደበዘዘ ገፅታ በተሻለ ብርሃን የሚያፈካ እና አገሪቱ ያላትን ዓለም አቀፍ ሚና የሚያንፀባርቅ ይሆናል፡፡ ከዓለም ዋንጫው ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ ትኩረትን የሚስቡ እግር ኳሳዊ ሁኔታዎች ጥቂት አይደሉም፡፡  የወቅቱ ሻምፒዮን ጀርመን ከ1962 እ.ኤ.አ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫውን ደግማ ታሸንፍ ይሆን? ኔይማር ብራዚልን በአምበልነት እየመራ ለ6ኛ ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን የሚሆኑበትን  ታሪክ ማሳካት ይሆንለታል? በ2014 እኤአ ብራዚል ካስተናገደችው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ወዲህ በዓለም የኮከብ ተጫዋቾች የክብር ሽልማቶች ላይ ሲፈራረቁ የቆዩት ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ሊዮኔል ሜሲ እንደየቅደምተከተላቸው ፖርቱጋልና አርጀንቲናን ስኬታማ ያደርጉ ይሆን? እነሆላንድ፣ ጣሊያን፣ ክሮሺያ፣ አሜሪካና ካሜሮን ከዓለም ዋንጫ መቅረታቸው ያስቆጫልን? ከ5 የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች መካከል ግማሽ ፍፃሜ መግባትን ማን ማሳካት ይችላል? ከ2006 እ.ኤ.አ ወዲህ በየትኛውም ዓለም አቀፋዊ ውድድር ጥሎ ማለፍ ደርሳ የማታውቀው እንግሊዝ ለሩብ ፍፃሜ የምትደርስበት እድልስ?... ሌሎችም በርካታ እግር ኳሳዊ ሁኔታዎች ከወዲሁ ማነጋገር ጀምረዋል፡፡ ራሽያ በምታስተናግደው 2ተኛው የዓለም ዋንጫ በምድብ 1 ከሳውዲ አረቢያ፣ ግብፅና ኡራጋይ ጋር ተገናኝታለች፡፡ ምናልባትም እስከ ግማሽ ፍፃሜ በመጓዝ የአገሪቱን እግር ኳስ ለከፍተኛ ደረጃ የሚያነቃቃ የታሪክ አጋጣሚ ይፈጠርላት ይሆናል፡፡ አገሪቱ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫን ከማዘጋጀቷ በፊት የኦሎምፒክ፤ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች፤ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ እና ሌሎች ግዙፍ መድረኮችን ስታዘጋጅ ቆይታለች፡፡ በስፖርቱ ዓለም 32 አገራት የሚሳተፉበትን የዓለም ዋንጫ ማዘጋጀት ትልቅ ስኬት ሆኖ ስለሚቆጠር ራሽያ በዓለም ዋንጫው የምትጠቀም ይሆናል፡፡
የዋንጫዋ ሽርሽር በ221 ቀናት 90 አገራት ያካልላል፡፡
ለ21ኛው የዓለም ዋንጫ የተዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ በዓለም ዙርያ በ6 አህጉራት የምታደርገውን ሽርሽር በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ወደ ስሪላንካ ባደረገችው ጉዞ ጀምራለች፡፡ በለንደን ከተማ በተካሄደው የሽርሽሩ መክፈቻ ላይ እንግሊዛዊው የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ጆፍ ሄርስትና ጣሊያናዊው የዓለም ዋንጫ አሸናፊ አንድሬ ፒርሎ  በክብር እንግድነት ተገኝተዋል፡፡ የዓለም ዋንጫ ዓለም አቀፍ ጉብኝትን ኮካኮላ ኩባንያ ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀው ኮካ ኮላ ኩባንያ ነው፡፡ ለጉብኝቱ በወጣው ፕሮግራም መሰረት በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በስሪላንካ ሽርሽሯን የጀመረችው የዓለም ዋንጫ  ወደ ኢትዮጵያ የምትደርስው የካቲት 17 እና 18 ላይ ይሆናል፡፡ የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ጉብኝቷን በካርቱም ሱዳን ከጀመረች በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የምትደርስ ሲሆን ናይሮቢ፤ ማፑቶ፣ ጆሃንሰበርግ፤ ካምፓላ፣ አቡጃ፣ ሌጎስ፣ ዳካር፣ አቢጃንና ካይሮ ሌሎች የምትንሸራሸርባቸው የአፍሪካ ከተሞች ናቸው፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት የዓለም ዋንጫዋ የመጀመሪያ ዙር ጉብኝት በ21ኛው የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ራሽያ 16 ከተሞችን፤ 10ሺ ማይሎችን ያካለለ ጉዞ ሲደረግ ከ220 ሺ በላይ ስፖርት አፍቃሪዎች ለጉብኝት ታድመው አብረው ፎቶዎችን ተነስተዋል፡፡
በፊፋና በኮካ ኮላ ትብብር የዓለም ዋንጫ የዓለም ዋንጫ ሽርሽር ሲዘጋጅ ዘንድሮ ለ4ኛ ጊዜ ነው፡፡ የዓለም ዋንጫዋ በዓለም ዙርያ 90 አገራትን በ221 ቀናት የምታካልልው 149,576.78 ኪ. ሜትሮች በመጓዝ ሲሆን ይህም 3.75 ጊዜ የምድር ወገብን መዞር ይሆናል፡፡ የሽርሽር ፕሮግራሙ ከ800 ሺ በላይ የስፖርት አፍቃሪዎች ፎቶ የሚነሱበትን እድል የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ ከ90ዎቹ አገራት መካከል 51 ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫ እንደምትጎበኛቸውና  ሁሉንም የዓለም ዋንጫ የቀድሞ አሸናፊ አገራትን እንደሚያካልልም ታውቋል፡፡ 1 ሚሊየን የኮካ ኮላ ምርቶች ከጉብኝቱ በተያያዘ እንደሚቀርቡ ለማወቅ የተቻለ ሲሆን በሆሎግራም የተዘጋጀ ልዩ ፊልም በጉብኝቱ ላይ ከ2ሺ ጊዜ በላይ እንደሚታይ ተገልጿል፡፡  ከ1976 እ.ኤ.አ የፊፋ ኦፊሴላዊ አጋር የሆነው ኮካ ኮላ በ1978 እ.ኤ.አ የዓለም ዋንጫ አብይ ስፖንሰር መሆን የጀመረ ሲሆን ከ2006 እ.ኤ.አ ጀምሮ ደግሞ የዓለም ዋንጫዋን ዓለም አቀፍ ሽርሽር በማዘጋጀት እየሰራ ይገኛል፡፡
የዓለም ዋንጫ ጉብኝት በ2006 እ.ኤ.አ ጀርመን ካስተናገደችው 18ኛው የዓለም ዋንጫ ጋር በተያያዘ ሲካሄድ በ29 አገራት ከ175 ሺ በላይ ስፖርት አፍቃሪዎች ከዋንጫዋ ጋር አብረው ፎቶ ተነስተዋል፡፡  በ2010 እ.ኤ.አ ላይ ደቡብ አፍሪካ ካስተናገደችር 19ኛው የዓለም ዋንጫ በፊት የዓለም ዋንጫ ጉብኝት  84 አገራትን ሲያካልል  50ቹ የአፍሪካ አገራት ነበሩ፡፡  በ2014 እ.ኤ.አ ብራዚል ካስተናገደችው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ዋዜማ በነበረው ሽርሽር ደግሞ የዓለም ዋንጫዋ በ267 ቀናት ውስጥ 90 አገራትን ያካለለ ጉዞ በማድረግ ለ1.3 ሚሊዮን ስፖርት አፍቃሪዎቹ ፎቶ የመነሳት ዕድል ተፈጥሯል፡፡
3 የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የዘገባ እድል አግኝተዋል
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ በዓለም ዋንጫው ለአባል አገራት ፌዴሬሽኖች የመገናኛ ብዙኃናት የዘገባ እድሎችን በመፍጠር ለውጭ ጉዞ የሚያስፈልገውን ፈቃድ እንዲሚሰጥ ይታወቃል፡፡ በዚህ መሰረት ከኢትዮጵያ 3  የስፖርት ጋዜጠኞች በኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበርና በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የተቃና ትብብር  ሙሉ ወጭያቸውን ሸፍነው ዓለም ዋንጫን በራሽያ ተገኝተው የሚዘግቡበትን እድል ፈጥሮላቸዋል በዚህ መሰረት የስፖርት ጋዜጠኞቹ በፊፋ ኦፊሴላዊ ድረገፅ ምዝገባ በማከናወን አስፈላጊውን የጉዞ ሂደት ጀምረዋል፡፡ 3 የስፖርት ጋዜጠኞች ግሩም ሰይፉ ከአዲስ አድማስ፣ አለምሰገድ ሰይፉ ከሊግ ስፖርት እንዲሁም ዳዊት ቆሎሳ ከሪፖርተር ጋዜጣ ናቸው፡፡
እኔ ግሩም ሠይፉ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በስፖርት አምድ አዘጋጅነት ስሰራ 14ኛ ዓመቴን ይዣለሁ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ አካላት ባገኛኋቸው የውጭ ጉዞ እድሎች በስፖርት አድማስ አምድ እና በሌሎች የአዲስ አድማስ አምዶች ሰፋፊ የዘገባ ሽፋኖችን ሰርቻለሁ፡፡ በ2008 እኤአ ላይ በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ግብዣ 27ኛውን ኦሎምፒያድ መክፈቻ በመታደም ተያያዥ የ5 ቀናት ጉብኝት በቤጂንግ እና በሌሎች የቻይና ከተሞች አድርጌ ነበር፡፡  በ2010 እኤአ ላይ ደቡብ አፍሪካ ካስተናገደችው 19ኛው ዓለም ዋንጫ ጋር በተያያዘ ከዓለም ዋንጫ ባሻገር ኢትዮጵያውያንን ህይወት ስለሚያስከፍለው ወደ ደቡብ አፍሪካ የስደት ጉዞ ላይ ያተኮሩ መጣጥፎች በቢቢሲ ዎርልድ ሰርቪስ ድጋፍ የተቀረፀ ፕሮጀክትን በመስራት ተሸላሚ ነበርኩ፡፡  በ2013 እኤአ ላይ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጋር ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመታደም የበቃሁ ሲሆን በ2013 እኤአ ላይ የራሽያዋ ሞስኮ ባስተናገደችው 14ኛ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር በተገኘ እድል መሰረት ሙሉ ዘገባ ሰርቼ ከአይኤኤኤፍ እና ከብሄራዊ አዘጋጅ ኮሚቴው የምስጋና ዲፕሎማ ተሰጥቶኛል፡፡  እንዲሁም በ2014 እኤአ ላይ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጋር በቻን የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ደቡብ አፍሪካ ላይ በመገኘት ለመስራት ችያለሁ፡፡ ዓለምሰገድ ሰይፉ ከግል ጋዜጦች ህትመቱ ሳይቋረጥ 17 ዓመታትን የሆነውን አንጋፋ የሊግ ስፖርት ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ነው፡፡ በስፖርት ጋዜጠኝነቱ ባሳለፈው ልምድ በእፎይታ መፅሄት እና ጋዜጣ፤ በእለታዊ አዲስ እና በአቴና የስፖርት ጋዜጣ የስፖርት አምድ አዘጋጅነት ሰርቷል፡፡ በ2013 እኤአ ላይ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጋር ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው የአፍሪካ ዋንጫና በፖላንድ በተካሄደ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የጉዞ እድል አግኝቶ ዘገባዎችን ለጋዜጣው የሰራ ሲሆን እንዲሁም በአሜሪካ ዋና ከተማ ዋሽንግተን ዲሲ ከተዘጋጀ የኢትዮጵያውያን የስፖርት ፌስቲቫል ጋር በተያያዘ በክብር እንግድነት ተገኝቷል፡፡ ጋዜጠኛ ዳዊት ቶሎሳ በጋዜጠኝነት እና ኮምኒኬሽን ዲግሪውን ከሰራ በኋላ ወደ ስፖርት ጋዜጠኝነቱ በመግባት እያገለገለ ሲሆን በታዋቂው የሪፖርተር ጋዜጣ እንግሊዘኛ እና አማርኛ እትሞች የስፖርት የሚያዘጋጅ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ከዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋማት ጋር በተለይ ከፊፋ እና ከአይኤኤኤፍ ጋር እንዲሁም ከአገር ውስጥ ፌደሬሽኖች ጋር በቅርበት በመስራት ለአባላቱ የውጭ ጉዞ እድሎችን በመፍጠር እየሰራ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ በቅርቡ እንኳን ለዓለም ዋንጫው ከፈጠረው እድል ባሻገር በእንግሊዝ በርሚንግሃም ለሚካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና ቫሌንሺያ ለሚካሄድ ማራቶን ወጭያቸውን በመሸፈን ዘገባዎችን ወደ ውጭ በመጓዝ ለሚሰሩ የስፖርት ጋዜጠኞች እድል መስጠቱን መጥቀስ ይቻላል፡፡
የቀጥታ ስርጭት በራድዮ፤ ቲቪና ሌሎች
ከ4 ዓመት በፊት ብራዚል ባስተናገደችው 20ኛው የዓለም ዋንጫ የፍፃሜውን ጨዋታ በቴሌቪዥን ብቻ ከ1 ቢሊየን በላይ ተመልካች ሲከታተተለው ሁሉንም የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች 3.2 ቢሊየን የዓለም ህዝብ በቲቪ ስክሪኖች ታድሟቸዋል፡፡  በወቅቱ የዓለም ዋንጫው በቀጥታ ስርጭት እና ሌሎቹ ተያያዥ ፕሮግራሞች ከ98ሺህ ሰዓታት በላይ ሽፋን ነበረው፡፡ በሞባይልና በኢንተርኔት የቀጥታ ስርጭት ደግሞ  የዓለም ዋንጫው ከ280 ሚሊየን በላይ ስፖርት አፍቃሪዎች ተከታትለውታል፡፡ የዓለም ዋንጫ በመላው ዓለም በ204 አገራት በቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት የሚያገኝ ሲሆን ከመክፈቻው እስከ ዋንጫው የሚደረጉትን ጨዋታዎች በድምሩ ከ30 ቢሊየን በላይ ተከታታይ ያገኛል፡፡
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ለ21ኛው የዓለም ዋንጫ የብሮድካስት ስርጭት መብቶችንን ለበርካታ ኩባንያዎች በአጋርነት አሰባስቦ ፈቃዶችን ሰጥቷል፡፡ ስለሆነም በ85 አገራት የሚገኙ 116 የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንዲሁም በ48 አገራት ሚገኙ ከ58 በላይ ራዲዮ ጣቢያዎች በቀጥታ ስርጭት የማከናወን መብቱን ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር አግኝተዋል፡፡
ከ209 ሚሊዮን ዶላር በላይ ክፍያ ለክለቦች
በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ የሚካፈሉ 32 ብሄራዊ ቡድኖች በሚያሳትፏቸው ተጫዋቾች ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ ለክለቦች የተጨዋቾች ዋስትና ክፍያ ከ209 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡በዓለም ዋንጫው ወቅት በቀን ለ1 ተጨዋች 8530 ዶላር በአማካይ ለክለቡ ሊከፈል እንደሚችል ሲገመት በትልልቅ ቡድኖች ተጨዋቾች ያሏቸው የአውሮፓ ክለቦች በአንድ ተጨዋች ከፍተኛውን እስከ 5 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ለተጨዋቾች የዋስትና ክፍያ የቀረበው ገንዘብ በ2014 እ.ኤ.አ ላይ በብራዚል 20ኛው የዓለም ዋንጫ በ3 ዕጥፍ እንዲሁም በ2010 እ.ኤ.አ ላይ በደቡብ አፍሪካው 21ኛው የዓለም ዋንጫ በ5 እጥፍ ብልጫ ያሳየ ነው፡፡ በ20ኛው የዓለም ዋንጫ 70 ሚ. ዶላር እንዲሁም በ19ኛው የዓለም ዋንጫ  40 ሚሊዮን ዶላር ለተጫዋቾች የዋስትና ክፍያ በሚል ለክለቦች ተከፍሎ  ነበር፡፡  በ2014 እ.ኤ.አ ላይ የጀርመኑ ባየር ሙኒክ በዓለም ዋንጫላይ ባሳተፋቸው ተጨዋቾች 1,734, 367 ዶላር ያገኘ ሲሆን ሪያል ማድሪድ 1,334,367 ዶላር ለተጫዋቾች የዋስትና ክፍያ አግኝተው ነበር፡፡
5.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መጠበቁና የስፖንሰሮች ድርቅ
በ2014 እ.ኤ.አ ላይ ብራዚል ባስተናገደችው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ፊፋ ከ4.8 ቢሊየን ዶላር ገቢ የነበረው ሲሆን በራሽያው 21ኛው የዓለም ዋንጫ የተጠበቀው ገቢ  ከ5.66 ቢሊየን ዶላር በላይ ነው፡፡  ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ከስፖንሰርሽፕ የሚኖረው ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሶበታል፡፡ በየዓለም ዋንጫው ይቀርቡ ከነበሩ 32 የስፖንሰርሺፕ ዕድሎች ማግኘት ለ21ኛው ዓለም ዋንጫ ማሳካት የተቻለው 11 ብቻ ነው፡፡ የዓለም ዋንጫ ዋና አጋሮች 8 ነበሩ በስፖንሰርሺፕ ስምምነቱ የቀጠሉት 7 ናቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ይሰሩ ከነበሩ 6 አጋሮች ሁለቱ፣ በየአህጉሩ በአጋርነት ይሰሩ ከነበሩ 20 ኩባንያዎች 2 ብቻ የስፖንሰርሺፕ     ውላቸውን አድሰው ከፊፋ ጋር የሚሰሩ ይሆናሉ፡፡
ስታድዬሞች ከ2 ወራት ቀደም ብሎ ዝግጁ ይሆናሉ
የዓለም ዋንጫውን 64 ጨዋታዎች የሚያስተናግዱት ስታድየሞች ሙሉ ለሙሉ ዝግጅታቸውን ተጠናቅቀው ብሄራዊ አዘጋጅ ኮሚቴውና ዓለማቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ)ከ4 ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ይረከቧቸዋል፡፡  ከ3 ወራት በፊት የ2017 ኮንፌዴሬሽን ካፕን በአራቱ ከተሞች ሞስኮ፣ ሴንት ፒተስበርግ፣ ካዛንና ሶቺ ላይ የሚገኙ ስታድዬሞች የተሳካ መስተንግዶ ማድረጋቸው ራሽያ  በዝግጅቷ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ አመልክቷል፡፡ 21ኛውን የዓለም ዋንጫ የሚያስተናግዱት ስታድየሞች በ11 ከተሞች ማለትም በሞስኮ፣ በሴንት ፒተስበርግ፣ በሶቺ፣ ካዛን፣ ሳራንሳክ፣ ካሊንግራድ፣ ቮልጎጋርድ፣ ሮሰትቮ ኦን ዶን፣ ኒዚሃኒ፣ ኖቮጎርድ ያካተሪንበርግና ሳማራ የሚገኙ ናቸው፡፡ ራሽያ 21ኛውን የዓለም ዋንጫ ለማስተናገድ አዲስ ለገነባቻቸውና ዕድሳት ላደረገችባቸው ስታድየሞችና ሌሎች የስፖርት መሰረተ ልማቶቹ ከ8.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ አድርጋለች፡፡ ከአስተናጋጆቹ ስታድዬሞች ሁለቱ በዋና ከተማ ሞስኮ የሚገኙ ሲሆን  በተለይ የመክፈቻና የዋንጫ ጨዋታዎቹን የሚያስተናግደው ታሪካዊው የሉዝንስኪ ስታድየም የሚጠቀስ ነው፡፡ በ1980 ዓ.ም ላይ በሞስኮ ኦሎምፒክ አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር በ10ሺ እና በ5 ሺ ሜ. ሁለት የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያዎች ያስመዘገበት ነው፤ ሉዝንስኪ፡፡
የትኬት ሽያጭ እና የደጋፊዎች መታወቂያ
የዓለም ዋንጫ ትኬቶች ሽያጭ በሶስት የተለያዩ ምዕራፎች የሚካሄድ ነው፡፡ ዘንድሮ የተፈጠረው አዲስ አሰራር ስታድየም ለሚገቡ ሁሉ ልዩ የመታወቂያ ካርድ መዘጋጀቱ ነው፡፡ በመጀመሪያው የትኬት ሽያጭ ምዕራፍ ከ1.7 ሚሊዮን በላይ ትኬቶች የተሸጡ ሲሆን ለሁለተኛው ምዕራፍ ከ4 ሚሊዮን ትኬቶች የግዢ ጥያቄ እንደቀረበ ታውቋል፡
ጥቂት ስለ ራሽያ
ራሽያ በ12 ውቅያኖሶችና ባህሮች የተከበበች አገር ስትሆን የየብስ ስፋትዋ ከዓለም 1/8 ይሆናል፡፡ አትላንቲክ፤ አርክቲክና ፖሰፊክ ውቅያኖሶች ያወስኗታል፡፡ የዓለማችን ጥልቁና ንፁሁ ሀይቅ በአይካ እንዲሁም በአውሮፖ ረጅሙ ወንዝ ቮልጋ ይገኝባታል፡፡ ከ140 በላይ ብሔር ብሄረሰቦችና ጎሳዎች ያሏት ስትሆን በህዝብ ብዛት ከዓለም 9 ደረጃ ላይ የምትገኘው በ146 ሚሊዮን ነው፡፡ 23 በዮኒስኮ የተመዘገቡ የዓለም ቅርሶች አሏት፡፡
በባህል፤ በኪነ ጥበብ፤ በስነ ጥበብ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በጠፈር ምርምር ታላላቅ ምሁራንና ሳይንቲስቶች ያፈራች ስትሆን ከ20 በላይ የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች ይገኙባታል፡፡ በሙዚቃ ፒተር እስካውስኪና ራክማኖቭ እንዲሁም በድርሰት ማክሲም ጎርኪ፣ ሊዮ ቶልስቶይ እና ፊዮዶር ዶስቶቭእስኪን ለዓለም ያበረከተች ናት፡፡ 

Read 3703 times