Sunday, 28 January 2018 00:00

የወዳጅነት መስፈርት በዘመነ ‘ግሎባላይዜሽን’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
‘ወዳጅህ ቢሰክር ይስምሀል፣ ጠላትህ ቢሰክር ይነክስሀል፣’ የሚሏት ነገር ነበረች፡፡ የዘንድሮ ወዳጅ ግን ሳይሰክርም የሚናከስ እየሆነ ነው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የሁሉም ነገር መስፈርት እየተለወጠብን ነው እኮ! እና…መስፈርቶቹ ግልጽ ቢሆኑ አሪፍ ነው፡፡ የዘመኑ የወዳጅነት መስፈርት ግራ ያጋባል፣ የልብ ጓደኝነት መስፈርት ግራ ያጋባል፣ የመልካም ትዳር መስፈርት ግራ ያጋባል…ግራ የሚያጋቡን ነገሮች በዙብንሳ!
በፊት የነበሩት መስፈርቶች እርስ በአርስ መተሳሰብ፣ በመረዳዳት፣ በደስታም፣ በሀዘንም ጊዜ አንዱ ከሌላኛው አጠገብ መሆን፣ለችግር ጊዜ ፈጥኖ መድረስ ወዘተ. አይነት ነገሮች የመልካም ወዳጅነት ምልክቶች ነበሩ፡፡ ይመስላሉ፡፡ አሁን በግለኝነት የምትጦዝ ሆነችና፣ በእርስ በእርስ ጥርጣሬ የምትታመስ ምድር ሆነችና…ቢያደናቅፈን “እኔን” የሚል፣ ቢያስነጥሰን “ይማርህ” የሚል፣ ብንበሳጭ “ግዴለም ይሄም ያልፋል” ብሎ የሚያጽናና እያጣን፣ ግራ የሚያጋባ ዘመን ደርሰናል፡፡
ጓደኝነት እየተባሉ የሚጠቀሱት ነገሮች ከተራ ትውውቅ የማይዘሉ፣ ከ“የሰፈራችን ሰው ነው” አይነት ነገር የማያልፉ እየሆኑብን ተቸግረናል፡፡
አሀ፣ ልክ ነዋ…አሁን እኮ “ከአንቺ ፍቅር ይዞኛል፣” ከማለት ይልቅ “ትመቺኛለሽ” አይነት ነገር ‘የመውደድ ፕላቲነም ደረጃ ምናምን እየሆነ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ዘንድሮ አንድ እየተለመደ የመጣ ፈሊጥ አለ…የሆነ ነገር ለምን ሆነ? ሲባል ጊዜው የግሎባላይዜሽን ነው ምናምን ይባላል፡፡ እናማ…‘ግሎባላይዜሽን’ ምን እንደሆነ ያወቁ ከሚመስላቸው ሳይሆን ከሚያውቁ ሰዎች ይነገረንማ!
በነገራችን ላይ እንዲህም ሆኖ፣ በራሳችን እንደ መቆም፣ በ‘ጓደኛ’ ማንነት ላይ መንጠላጠል እየተለመደ መጥቷል፡፡
“እከሌን ታውቀዋለህ?”
“ይሄ ቴሌቪዥን ድራማ ላይ የሚሠራውን ማለትህ ነው?”
“አዎ፣ እሱን፡፡”
“ማወቅ ብቻ አይደለም፣ ጓደኛዬ ነው፡፡”
“አትለኝም! ደግሞ አንተና እሱ የት ተገናኛችሁ?”
“አንድ ወዳጄ ነው ያስተዋወቀኝ፡፡”
“ብዙ ጊዜ ትገናኛላችሁ እንዴ?””
“እ…ማለት፣ እንደሱ ሳይሆን… አንድ ጊዜ ካፌ ተያይተን ሰላም ተባብለናል፡፡”
“በቃ?”
“እንዴት፣ በቃ!”
“ይሄ ነው ጓደኝነት!”
አዎ፣ የዘንድሮ ጓደኝነት ይኸው ነው፡፡ በተለይም በህዝብ ዘንድ ‘ታዋቂ’ የሆኑ ወይም በራስ ተነሳሽነት “ታዋቂ ነኝ፣” ብለው የሚያስቡ ሰዎችን ማወቅ፣ ለአንዳንዶች የራሳቸው ሰብእና መለኪያ አድርገው ሲያዩት ያሳዝናል፡፡ የምር አኮ…ለሰው ሲናገሩ እንኳን “ለእከሊት እኮ ጓደኛዋ ነኝ” አይደለም የሚሉት፤ “እከሌ ጓደኛዬ ነው” አንጂ፡፡ ‘እከሌ’ እኮ በቀደም በእሱ በሚኮራው ‘ጓደኛው’ ሰላም ሲባል... “ይቅርታ የት ነበር የምንተዋወቀው!” ብሎታል፡፡
ጓደኝነት ጥብቅ፣ አጅግ በጣም ጥብቅ ነገር ነበር እኮ፡፡ እንደውም ለቤተሰብ፣ ለወንድምና እህት የማይነገረው ምስጢር ሁሉ እኮ ‘የልብ’ ለሚሉት ጓደኛ ነበር የሚነገረው!
“ስማ፣ ያቺ ልጅ እኮ ጉድ አደረገቸኝ፡፡”
“አስደግፋህ ጠፋች?”
“ምን ታስደግፈኛለች፣ እባክህ ይዛለች፡፡”
“ምንድነው የያዘችው?”
“ይዛለች ነው የምልህ፣ አይገባህም እንዴ! ቃል በቃል ማስረዳት አለብኝ!”
“እናቴ ድረሽ! ጭራሽ! አንተ ገና አስተሳሰብህ ከጡጦ አልወጣ፣ ጭራሽ ልጅ አስቋጠርክና አረፍከው!”
“እኔ ምን ላድርግ፣ እሷ ራሷ ነች…”
እናማ… እንዲህ አይነት ከአገር ምስጢር የማይተናነስ ምስጢር የሚነገረው ለ‘ልብ ጓደኛ’ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ከዛ ተክተሎ የሚመጣው ጥያቄ፣ “ስማ የምታውቀው የሚያስፈተልክ ሰው አለ?”  ‘ማስቋጠር ለብቻ፣ ማስወጣት ለጋራ’ አይነት ነገር ነው፡፡ ይሄንን እንደ ከፍተኛ ምስጢር የሚጠብቀው፣ የ‘ልብ ጓደኛ’ ብቻ ነበር፡፡ ዘንድሮ ተለውጧል፡፡ አይደለም ‘አስቋጠርክ፣ አስፈታህ’ ደረጃ ለመድረስ በትንሹም ሹክ የተባለች ጀንበር ሳታዘቀዝቅ ለአገር ትዳረሳለች፡፡
“ትናንት ሰርግ ላይ ሳይቸግረኝ ጠጥቼ ጉድ አልሆንኩ መሰለህ!”
“ሰው ተሳደብኩ እንዳትለኝ!”
“ምን እሳደባለሁ…ያ ጉረኛው የእነሳሚ መሥሪያ ቤት ሥራ አስኪያጅ ታውቀው የለ…”
“ከእሱ ጋር ተጣላሁ እንዳትለኝ፣ ሰውዬውን ተነኮስከው እንዴ!”
“እሱን ሳይሆን የእሱን ልጅ ካልሳምኩ ብዬ…”
“የባሰው መጣ! አንተ ሰውየ ምን ነካህ?…አባትየው እኮ አይደለም፣ ልጁን ልሳም ብለህ ከወገብ በታች ካየሀት እንኳን ካልገደልኩ ነው የሚለው፡፡”
“አውቃለሁ…ምን ባደርግ ይሻላል፣ ይቅርታ ልበላት እንዴ?”
“አርፈህ ተቀመጥ…ይሄ ነገር ከወጣ ነገሬሃለሁ…አንተን በዋስ ለማስፈታት የምሸጠው እቃ እንኳን የለኝም፣” ምናምን ይል ነበር የልብ ጓደኛ፡፡
ዘንድሮ ግን በትመቺኛለሽ ዘመን…አለ አይደል…እንደዛ አይሆንም፡፡ በሦስተኛው ቀን በአንድ በኩል “ወንዳታ! አጅሬው የሰውየውን ልጅ ኪሲንግ ካላጦፍኩ ብሎ…”
“ሳማት እያልከኝ ነው?”
“ሙከራው ራሱ እንደ መሳም ይቆጠራል፡፡”
በሌላ በኩል ደግሞ…
“እሱ ሰውዬ እኮ ድሮም ነገሩ አያምረኝም ነበር።”
“እንዴት?”
“አለ አይደል… የሰከረ እያስመሰለ ነው የልቡን የሚሠራው፡፡”
እናማ… ዘንድሮ ለጓደኛ በጆሮው ሹክ የሚባል ምስጢር ‘ሀክ’ መደረግ ሳያስፈልገው ይወጣል፡፡
ዘንድሮ…እንደ ፖለቲካው ጓደኝነትም ስትራቴጂያዊ ነው፡፡ ይሄ ዝም ብሎ “ዎክ ለብ ለብ እንብላ፣” “መርካቶ ፉል ልጋብዝህ፣” ምናምን የሚለው ጊዜ አልፎበታል፡፡ ዘንድሮ ጓደኝነት የሚመሰረተው የገበያ ዋጋው እየታየ ነው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በፊት’ኮ አይደለም ንብረት… “ሚስቴን አደራ፣ እስክመለስ ጠብቅልኝ፡” ብሎ ፊልድ ሦስት ወር ከርሞ ይመጣ ነበር፡፡ አሁን “ሚስቴን አደራ” ከተባለ ገና በመጀመሪያው ቀን ምሽት… “እንዳይደብርሽ ላማሽሽ ብዬ ነው የመጣሁት፣” ምናምን ብሎ አባወራ በሌለበት ቤት ውስጥ ጥልቅ ማለት ይመጣል፡፡
ስሙኝማ… ‘ሰለጠንን’ ነው የሚባለው? ‘ዓለምን ተቀላቀልን’ ነው የሚባለው!…ወይስ ‘መላው እየጠፋን ነው’ ነው የሚባለው? እንዴት ነው፣ ስንት አስርት ዓመታት የከረመ ጓደኝነት፣ በአንድ ጊዜ የእምቧይ ካብ የሚሆነው! ግሎባላይዜሽን መሆኑ ነው እንዴ!
ስሙኝማ…በትዳሩም የመጠናናት ጊዜው እያነሰ፣ እያነሰ… አለ አይደል… “መጠናናት ማለት ያለፈው ስርአት ጥሎብን የሄደው ኋላቀር ባህል ነው፣” ምናምን ሊባል ምንም አይቀርም፡፡
“ባልሽ አዲስ ሙሉ ልብስ ለብሷል፡፡”
“አይ፣ አልለበሰም፡፡”
“ግን ሳየው የሆነ የተለወጠ ነገር አለ፡፡”
”አዎ፣ አዲስ ልብስ ሳይሆን አዲስ ባል ነው፡፡”
“ገና ሁለት ዓመት ሳይሞላ…”
“ተዪው እባክሽ፣ ደግሞ ሞልቶ ለተረፈ ወንድ!”
እናማላችሁ…ሲጀምርም “መጠናናት ጎጂ ባህል ነው፣” አይነት ትዳር ነበር ማለት ነው፡፡
የወዳጅነት መስፈርት በዘመነ ‘ግሎባላይዜሽን’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ምንድነው?
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2562 times