Saturday, 27 January 2018 11:29

ኦፕራ ከትራምፕ ጋር ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር አልፈልግም አለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“ኦፕራ ከኔ ጋር ልትፎካከር? አታደርገውም! የምታደርገው ከሆነ ግን፣ ግጥም አድርጌ ነው የማሸንፋት!” - ዶናልድ ትራምፕ

    በቅርቡ በተካሄደው የጎልደን ግሎብ ሽልማት ስነስርዓት ላይ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ንግግር ማድረጓን ተከትሎ፣ በመጪው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዲሞክራቶችን በመወከል ከትራምፕ ጋር ትፎካከራለች ተብሎ በስፋት ሲነገርላት የሰነበተቺው ታዋቂዋ የቶክ ሾው አቅራቢ ኦፕራ ዊንፍሬይ፣ በፕሬዚዳንትነት የመወዳደር ፍላጎት እንደሌላት በይፋ ማስታወቋን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ብዙዎች ለፕሬዚዳንትነት እንደምትወዳደር ሲዘግቡ ሰንብተዋል፤ እኔ ግን የምችለውንና የማልችለውን ነገር ጠንቅቄ የማውቅ ሰው ነኝ! የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የመሆን ፍላጎት የለኝም ስትል፣ ኢንስታይል ከተባለው መጽሄት ጋር ከሰሞኑ ባደረገቺው ቃለ መጠይቅ ኦፕራ አቋሟን መግለጧን  ዘገባው አመልክቷል፡፡
ኦፕራ በ2020 በሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደምትሳተፍ የሚገልጸው ወሬ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና በማህበራዊ ድረገጾች በስፋት መሰራጨቱን ተከትሎ፣ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ የተጠየቁት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ “ይህ እጅግ አስቂኝ ነገር ነው፤ ኦፕራ ከኔ ጋር ልትፎካከር? አታደርገውም! የምታደርገው ከሆነ ግን፣ ግጥም አድርጌ ነው የማሸንፋት!” ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 1515 times