Saturday, 27 January 2018 11:16

የቻይናው ኩባንያ የግዙፍ ባቡር ጣቢያ ግንባታን በ9 ሰዓታት አጠናቅቆ አስረክቧል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ቻይና ቴሲጁ ሲቪል ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የተሰኘው የቻይና የግንባታ ተቋራጭ ኩባንያ፣ ፉጂያን በተባለው የአገሪቱ ደቡባዊ አውራጃ የሚገኘውን የአንድ ግዙፍ የባቡር ጣቢያ ግንባታ ፕሮጀክት፣በ9 ሰዓታት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ አጠናቅቆ ማስረከቡን ዴይሊ ሜይል ዘግቧል፡፡
ናንሎንግ በተባለው ግዙፍ የባቡር ጣቢያ ፕሮጀክት የግንባታ ስራ ላይ 1 ሺህ 500 ቻይናውያን የግንባታ ሰራተኞች መሳተፋቸውንና ይህንን ግዙፍ ፕሮጀክት በ9 ሰዓታት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ የተቻለው የተጠናና የተቀናጀ ስራ በማከናወናቸው መሆኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ሰራተኞቹ በሰባት ቡድኖች ተከፋፍለው እንዲሰሩ የተደረገ ሲሆን፣ በአንድ ጊዜ የተለያዩ ስራዎችን ማከናወን የሚያስችላቸውን ስልጠና አግኝተው ወደ ስራ መግባታቸውም ይህንን ግዙፍ ፕሮጀክት በዚህ የሚገርም ፍጥነት እንዲያጠናቅቁ እንዳስቻላቸው ተነግሯል፡፡
ባለፈው አርብ በተከናወነው በዚህ እጅግ ፈጣን የግንባታ ስራ፣ ሰባት ባቡሮችንና 23 የቁፋሮ ማሽኖችን ጨምሮ የተለያዩ የግንባታ መሳሪያዎችን መጠቀሙን የጠቆመው ኩባንያው፣ በግንባታው ሶስት የባቡር ሃዲዶችን ወደ አንድ የማቀላቀል፣ የትራፊክ መብራቶችን የመግጠም፣ የተለያዩ የእንቅስቃሴ መቆጣጠሪያ መሳሪያዎችን የመትከልና ሌሎች ስራዎች በሚገርም ፍጥነትና ጥራት መጠናቀቃቸውንም አመልክቷል፡፡


Read 928 times