Saturday, 21 April 2012 17:02

ለበላይ ዘለቀ ፊልም ሊሰራላቸው ነው

Written by  መልካሙ ተክሌ (melkamutekele@gmail.com)
Rate this item
(0 votes)

በጣሊያን ወረራ ወቅት ሥመጥር ከነበሩት አርበኞች አንዱ የሆኑት ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ፊልም ሊሰራላቸው ነው፡፡ በ”አቲ” ፊልም ፕሮዳክሽን የሚሰራውን ፊልም ኢያሱ በካፋ የኔነህ ፅፎት፣ ዮናስ ብርሃነ መዋ በዋናነት ሰለሞን ተፈሪ አልታዬ በተባባሪነት እንደሚያዘጋጁት ታውቋል፡፡ ፊልሙ በርካታ ወጪዎች ስላሉበት በጀቱ ከፍ ማለቱን የገለፀው የፊልሙ ተባባሪ አዘጋጅ፤ ለፊልሙ ከግብ መድረስ ኢትዮጵያውያን እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተውን ፊልም ለመስራት ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡ የፊልም ፅሁፉን ለማዘጋጀት ከነጥናቱ ከአምስት አመት በላይ የፈጀ ሲሆን ቀረፃው አንድ አመት እንደሚፈጅ እና ለውጭ ሀገር ገበያም ጭምር ታስቦ  እንደሚሰራም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ፊልሙ በአጠቃላይ ሰባት ሚሊዬን ብር ያህል ይፈጃል ያሉት የፊልሙ አዘጋጆች፤ ለስራው መጀመሪያ የሚሆን ገንዘብ እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ለፊልም ማሰሪያ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት እንደሚያደርጉ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ሆቴል በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ “በላይ ዘለቀ መልአከብርሃን ገብረጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ደም መላሽ” የሚል ማህተም ያላቸው አርበኛው፤ በጣሊያን ወረራ ወቅት በ36 ዋና ዋና ጦርነቶች ተሳትፈው አብዛኞቹን ያሸነፉ ሲሆን በመንግስት ላይ አምፀሃል ተብለው በአዲስ አበባ ተክለሃይማኖት አደባባይ በስቅላት መሞታቸው ይታወቃል፡አርበኛው በላይ ዘለቀ በሕይወት ቢኖሩ ዘንድሮ 100 ዓመት ይሞላቸው ነበር፡፡

 

 

Read 1283 times Last modified on Saturday, 21 April 2012 17:03