Saturday, 20 January 2018 13:06

ማይክሮሶፍት በዓመቱ የአለማችን 100 ምርጥ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መሪነቱን ይዟል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ታዋቂው የአሜሪካ ኩባንያ ማይክሮሶፍት፣ ቶምሰን ሮይተርስ ባለፈው ረቡዕ ይፋ ባደረገው የዓመቱ የአለማችን ምርጥ 100 ታላላቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ዝርዝር ውስጥ በአንደኛ ደረጃ ላይ በመሪነት መቀመጡን አስታውቋል፡፡
ተቋሙ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ትርፋማነትና ተቋማዊ ብቃት በመመዘን በየዓመቱ ይፋ በሚያደርገውና ሰሞኑን ይፋ ባደረገው የዘንድሮው ዝርዝር ውስጥ፣ የኮምፒውተር መሳሪያዎችን በማምረት የሚታወቀው ኢንቴል የሁለተኛነት ደረጃን ሲይዝ፣ የኔትወርክ መሳሪያዎች አምራቹ ሲስኮ ሲስተምስ ኩባንያ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በዘንድሮው ዝርዝር ውስጥ ከማይክሮሶፍት፣ ኢንቴልና ሲስኮ በተጨማሪ የአሜሪካዎቹ አፕል፣ አልፋቤት፣ ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ማሺንስ ኮርፖሬሽንና ቴክሳስ ኢንስትሩመንት እስከ አስረኛ ባለው ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
አስከ አስረኛ ባለው ደረጃ ውስጥ የተካተቱት የሌሎች አገራት የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ደግሞ የታይዋኑ ሰሚኮንዳክተር ማኑፋክቸሪንግ፣ የጀርመኑ ሳፕ እና ተቀማጭነቱ በደብሊን የሆነው አክሴንቸር መሆናቸውን ተቋሙ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
በዘንድሮው የቶምሰን ሮይተርስ የዓለማችን ምርጥ 100 የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት ሌሎች ታላላቅ ኩባንያዎች መካከልም አማዞንና ፌስቡክ ይገኙበታል፡፡ ከ100ዎቹ ምርጥ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መካከል 45 በመቶ ያህሉ መቀመጫቸውን በአሜሪካ፣ ጃፓንና ታይዋን  ያደረጉ መሆናቸው የጠቆመው ተቋሙ፤ ሰሜን አሜሪካ 47፣ እስያ 38፣ አውሮፓ 14 እና አውስትራሊያ 1 ኩባንያ በዝርዝሩ ውስጥ ማካተታቸውንም አመልክቷል፡፡

Read 2182 times