Saturday, 20 January 2018 13:04

ትራምፕ የፍልስጤም ስደተኞችን እርዳታ ከግማሽ በላይ ቀነሱ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ለኢየሩሳሌም የእስራኤል መዲናነት እውቅና በመስጠታቸው የደረሰባቸውን ዓለማቀፍ ውግዘት ተከትሎ፣ “ብዙ እየረዳኋት አታከብረኝም” በሚል ለፍልስጤም የሚሰጡትን እርዳታ እንደሚቀንሱ ሲዝቱ የነበሩት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዳሉትም፣ ለፍልስጤም ስደተኞች ይሰጡት ከነበረው እርዳታ ላይ ከግማሽ በላይ መቀነሳቸው ተዘግቧል፡፡
አሜሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኩል ለፍልስጤም ስደተኞች ስትሰጠው ከነበረው 125 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ወይም 65 ሚሊዮን ዶላሩን መቀነሷን በይፋ ማስታወቋን የዘገበው ዘ ኢንዲፔንደንት፤ ይህን ተከትሎም በዌስት ባንክ፣ ጋዛ ሰርጥ፣ ሊባኖስ፣ ዮርዳኖስና ሶርያ የሚገኙ ፍልስጤማውያን ስደተኞች ህልውና ከፍተኛ አደጋ ላይ ይወድቃሉ የሚል ስጋት መፈጠሩን አመልክቷል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፣ አገራቸው ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈቺው ማንንም ለመበቀልና ለማጥቃት በማሰብ ሳይሆን፣ ገንዘቡን ከመለገሳችን በፊት በተመድ ስር የሚገኘውን የእርዳታ ተቋም አጠቃላይ አሰራር በጥንቃቄ መፈተሽ በማስፈለጉ ነው ብለዋል፡፡ ተቋሙ ለፍልስጤም ታጣቂዎች ድጋፍ በማድረግና አድልኦአዊ አሰራር በመከተል በእስራኤል ተደጋጋሚ ትችት ሲሰነዘርበት እንደቆየ ያስታወሰው ዘገባው፤የትራምፕ አስተዳደር በተቋሙ አሰራር ላይ ፍተሻ ለማድረግ መወሰኑም ከዚህ ጋር ግንኙነት ሊኖረው እንደሚችል እየተነገረ ነው ብሏል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ ከሰሞኑ አፍሪካውያንን በአደባባይ ዘልፈዋል በሚል ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሳይቀር ከፍተኛ ውግዘት የገጠማቸውና በብዙዎች ዘንድ በአእምሮ ጤና ችግር ሲታሙ በቆዩት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ምርመራ ሲያደርጉ የቆዩት የዋይት ሃውሱ ሃኪም፣ ማክሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ፤ ትራምፕ በአእምሮም ሆነ በአጠቃላይ ጤንነታቸው ቅንጣት ታህል ችግር የሌለባቸው ጤነኛ ሰው መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብለዋል፡፡
ከምርጫ ቅስቀሳቸው ጊዜ አንስቶ በሚናገሯቸው አጉል ንግግሮችና በሚወስዷቸው አስደንጋጭ ውሳኔዎች አለም በወፈፌነት ሲጠረጥራቸው የቆዩት ትራምፕ፤ ሌሎች ምርመራዎችን ለሚያደርግላቸው ሃኪም “እባክህን የአእምሮዬንና የአስተሳሰብ ሁኔታዬንም አብረህ መርምረኝ” የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን የዘገበው ሮይተርስ፤በዚህ መሰረት በተደረገው ምርመራ ሙሉ ጤናማ መሆናቸው መረጋገጡን ገልጧል፡፡ የአእምሮ ብቃታቸው አገር ለመምራት የሚያስችልና ትክክለኛው ደረጃ ላይ ነው የተባለላቸው ትራምፕ፣ አጠቃላይ ጤንነታቸው በጥሩ ደረጃ ላይ ቢገኝም፣ እንቅስቃሴ ማድረግና ከ10 እስከ 15 ፓውንድ ክብደት መቀነስ እንደሚገባቸው በሀኪማቸው መመከራቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡

Read 1335 times