Saturday, 20 January 2018 12:50

“ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ትቀጥል ዘንድ ማን ምን ያድርግ?”

Written by  ዳሰሳ፡- ሰአቸ
Rate this item
(2 votes)

 ርዕስ፡- የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መሣፍንት እና ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የማስቀጠል ፈተና
ደራሲ፡- ዘለቀ ረዲ (ኢንጅነር)
ዘውግ፡- ፖለቲካ
የህትመት ዘመን፡- ሐምሌ፣2009 ዓ.ም
የገጽ ብዛት፡- 236
ዳሰሳ፡- ሰአቸ
በፖለቲካው መድረክ የምናውቀው መሐንዲስ ዘለቀ ረዲ፤ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን  የመፈራረስ አጣብቂኝ  በመጽሐፍ አቅርቧል፡፡ ሀገሪቱ ያለችው በመሣፍንታዊ አገዛዝ ሥርዓት ውስጥ እንደኾነም ይገልፃል፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት ሀገሪቱን በመሣፍንታዊ ሥርዓት ውስጥ ከትቷታል፤ይላል፡፡ “የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መሣፍንት” ያሰኘውም  ይኼው ነው፡፡
ወደ ኹለት መቶ ተኩል ገጾች በሚጠጋው መጽሐፍ፣ ይህንኑ ነግሮ ሲያበቃ፣ “ምን ቢደረግ ነው የሚበጀው?” የሚለውን ጥያቄ አንስቶ፣ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ መንግሥት ድረስ ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ይገልጻል፡፡  
ረዣዥም የኾኑ ኹለት ርዕሶች ያሉት መጽሐፍ ነው፤ ልክ የአካዳሚ ጥናታዊ ወረቀት ርዕሶች ዓይነት። “የ21ኛው ክፍለ ዘመን  መሣፍንት” የሚለው ዋነኛው ርዕስ ነው፡፡ በ ‹እና› የተያያዘው “ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የማስቀጠል ፈተና” ራሱን የቻለ ንዑሥ ርእስ ነው፡፡ ንዑሥ ርዕሱ በአንድ የተቆጠረ ምዕራፍ የሚቀርብ ቢመስልም፣፡፡ እንደ ሀገር ለማስቀጠል ምን ይደረግ የሚል ርእስ ነው፤ በመጽሐፍ ውስጥ የሚቀርበውና የመጽሐፉ ማሳረጊያ የሚኾነው፡፡ ፈተናው የሚገኘው ከ2ኛው ምዕራፍ ጀምሮ ባሉት መሣፍንታዊነቱ በሚገለጽባቸው ምዕራፎች ኹሉ ነው፡፡
በዐሥራ አራት ምዕራፎች ተከፍሎ የቀረበው መጽሐፉ፤ ዘመነ መሣፍንት እስከሚባለው ዘመን  (1775-1845) ድረስ የነበረችቷን ኢትዮጵያ በመጀመርያው ምዕራፉ አሳምሮ ያቀርባታል፡፡ ከጥንቷ ጀምሮ እስከ “ተፍጻሜተ መንግሥቱ” ድረስ ያለችውን ኢትዮጵያ፤ በተለይም፣ ኃያል፣ ገናና እና ሥልጡን የነበረችባቸው የጥንቱን ዘመን በአጭሩ ቀምሞ ጥሩ ምንባብ አድርጎታል፡፡ ምዕራፍ ኹለት “ረጅም የአስተዳደር ታሪክ ያላት” እንደ ነበረች፣. በአንድ ማዕከላዊ መንግሥት የተረጋጋችና ሰላማዊ ሀገር ኾና ለመዝለቅ ያልቻለች መኾኗን ለማምጣት፣ በ18ኛው መቶ የመጨረሻው ሩብ መቶ ዓመት መነሻ ላይ የሚጀምረውን የዘመነ መሣፍንት አገዛዝ ያቀርባል፡፡
ትልቁ የመጽሐፉ ጉዳይ ወይም የጸሐፊው ዘለቀ ረዲ ግኝት፣ በዚህ በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመንም  ኢትዮጵያ በዚያው መሣፍንታዊ አገዛዝ ሥርዓት ውስጥ መገኘቷ ይመስላልና ይህን ዘመን መግለጹ ግድ ነው፡፡ በቅድሚያ ለአዳዲስ አንባብያን ወይም ይህን የታሪክ ዘመን ለማያውቁት “ዘመነ መሣፍንት” የሚባል ሥርዓት (ዘመን) በሀገሪቱ እንደነበረ ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡ ከዚህም ይልቅ ግን፣ የ21ኛው ክፍለ ዘመን አገዛዝ (ኢሕአዴጋዊውን ዘረኛ አገዛዝ) “መሣፍንታዊ” ለማለት የበቃበትን ምክንያት እንረዳ ዘንድ ያን ምዕራፍ ለይቶ ማቅረቡ ተገቢ ነው፡፡ ደራሲው ሌላውንም መሣፍንታዊ ሊል የበቃበትን፣ የዚያኛው ዘመነ መሣፍንት መልኮችን እንዲያቀርብ እንጠብቃለን፡፡
በእርግጥ፣ የምንጠብቀውን ያህል በጥልቀት የዳሰሰው አይመስልም፡፡ ያላንዳች ማቅማማት ሌላውንም ዘመን “እውነትም ዘመነ መሣፍንት!” እንድንል የሚያበቁን የዚህ ዘመን መለያዎች ቀርበዋል ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር ባንችልም፣ በአጭር (በጥቅልሉ) የዚያ ዘመን መለያዎች ቀርበውበታል፡፡
“የ21ኛው መቶ ክ/ዘመን መሣፍንት” በሚለው ርዕስ ተወስደን እንጂ፣ በመጽሐፉ ውስጥ በተለያዩ ምዕራፎች የሚቀርቡት መሣፍንቶቹ ኢሕአዴጋውያን ብቻ አይደሉም፡፡ እንዲያውም፣ ከዚሁ በታሪክ “ዘመነ መሣፍንት” ተብሎ ከተጠራው ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ፤ ይልቁንም፣ ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጀምሮ እስከ ኢሕአዴግ ዘመን ድረስ ሀገሪቱ በመሣፍንታዊ አገዛዝ ውስጥ እንዳለች ነው ከመጽሐፉ የምንረዳው፡፡
ደራሲው፤ በተለያዩ ምዕራፎች አበክሮ የሚያነሳው የዘመነ መሣፍንታዊነት መለያው፣ “የራስ ጥቅም እንጂ ሀገርንና ሕዝብን የማያስብ መኾኑ” ነው፡፡ በታሪክ የሚታወቀው ዘመነ መሣፍንት ውስጥ የነበሩት መሥፍኖች፣ ከዚህ በበለጠ መለያ ሊገለጡ የሚችሉ መኾናቸው አይታይም። ይልቁንም፣ ለዚህም “ዘርንና ሃይማኖትን ይጠቀሙበት እንደነበር” ለማሰብ ቢቻልም በዚህ መደምደሙ ግን ሳያጠያይቅ አይቀርም፡፡
የዘመኑ “መሣፍንቶች” ኢሕአዴጋውያን ብቻ ሳይሆኑ፣ ግለሰቦችና ሌሎች ፓርቲዎችም ሳይቀሩ ተመሳሳይ መሆናቸውን ራሱን በቻለ አንድ ምዕራፍ ቀርቧል (ም. 4) - በመጽሐፉ፡፡ ደራሲው ራሱም የነበረበትን ፓርቲ ጨምሮ በሚያጋልጥበት በዚህ ምዕራፍ፤ ዘረኝነቱ በተቃዋሚዎች ውስጥም የሠረጸ መሆኑን  ይገልጻል፡፡ ፓርቲዎቹ የግለሰቦች ገንዘብና ኃብት ማከማቻም እንደኾኑ ይጠቁማል፡፡ ለዚህም ጸሃፊው ራሱ የነበረበትን “አንድነት”  ፓርቲን ለአብነት ይጠቅሳል፡፡
“አንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲን ስለነበርኩበት እንደ ምሳሌ ልጥቀሰው” ይልና፣ “እንደሚታሰበው ፓርቲው የፈራረሰው በኢሕአዴግ የሴራ ፖለቲካ ሳይኾን፣ የግል ጥቅማቸው በተነካባቸው የፓርቲው አባላት ደባ” እንደነበር ይገልጻል፡፡
“ኢንጅነር ግዛቸው ሽፈራው ለፓርቲው ከውጭ ሀገር  የሚላከው ገንዘብ በፓርቲው አካውንት እንጂ በግለሰቦች አይደለም መግባት ያለበት!” በማለታቸው፣ በዚህ አሠራር የጥቅም “ኔት ወርካቸው” እንደሚዘጋ ያሰቡ አባላት ባደረጉት እንቅስቃሴ ፓርቲው እንዲዳከም ኾኗል” (ገጽ 75-76)
ከእነዚህም መካከል አንዳንዶች ባለመኪኖች፣ ባለሱቆች እና ባለማተሚያ ቤቶች እንደኾኑም ያክላል፡፡ (መኪናውና ሱቆቹስ ይኹኑ፣ ማተሚያ ቤቱን ለይተው የመረጡበትን ምክንያት  ባውቀው ያሰኛል!)
በባሕር ማዶ የመሸጉት “መሣፍንት” የተባሉት  በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በመጽሐፉ ይነሳሉ፡፡ ከ2 ሚሊዮን በላይ፣ ከነዚህም ሩብ ሚሊዮን ያህሉ በአሜሪካ ብቻ እንደሚኖሩ በመጥቀስ፣ ከእነዚህ በውጭ ነዋሪ ከሆኑ ኢትዮጵያውያን ግን ሊገኝ የሚችለውን ያህል ጥቅም ማግኘት እንዳልተቻለ ያስረዳል፡፡ በተለይ በፖለቲካው ረገድ በውጭ ሀገር የሚገኙት ኢትዮጵያውያን (ዲያስፖራ ላለማለት) እርስ በርሳቸው በዘር ጦስ ተበጣጥሰው የሚሻኮቱ ኾነዋል፡፡ “የዲያስፖራ ፖለቲካ” (የምዕራፉም ርዕስ ነው) የተባለው “ራሱን የቻለ ደንቃራ” መሆኑ  ነው የጎላው፡፡
የሀገሪቱ ፈተና ከውጭ ኃይሎች ፍላጎትና እርምጃ የሚመጣ መኾኑንም ለብቻው ራሱን በቻለ ምዕራፍ ይተርካል፡፡ “ቅኝ ገዥዎችና ተገዥዎች” ተብሎ 12ኛው ምዕራፍ የተደረገው፣ በወረራም በሌላም ኢትዮጵያን ለመበታተን ሲጥሩ የነበሩ የውጭ ኃይሎችን በስም ይዘረዝራል፡፡ በቀጥታ በወረራ በመያዝ ያልኾነላቸውን ቅኝ የማድረግ ፍላጎት፣በእጅ አዙር በገዛ የሃገሩ  ሰዎች እንዲፈጸም እያደረጉት መኾኑንም ጸሃፊው ያስረዳል፡፡
“ኢትዮጵን ለማፈራረስ ከጀርባ ተሰልፈው የኖሩ ብዙ ናቸው” በማለት፣ ከአውሮፓ፡- እንግሊዝ፣ ጣልያንና ፈረንሳይ ከአፍሪካ፡- ግብፅ፣ ሊቢያ፣ አልጀርያ፣ ሱዳንና ሱማሊያ፣ ከመካከለኛውና ከቅርብ ምሥራቅ፡- ሶርያ፣ ሳዑዲ ዐረብያ፣ የመንና ኢራቅን ይጠቅሳል፡፡ በሰሜንና ምሥራቅ አፍሪካ እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅም ለኢትዮጵያ መፈራረስ ያዋጡትን የየበኩላቸውን ድርሻ  አንድ በአንድ እያቀረበ፣ ዛሬ የእነርሱም መጨረሻ የከፋ ሊሆን እንደበቃ ይጠቁማል፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ ላይ የሚነሳ መጨረሻው እንደማያርም የሚናገር መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡  
ሀገሪቱ በምን ዓይነት አጣብቂኝ ውስጥ እንዳለች፣ሰብሰብ አድርጎ በየምዕራፉ ስለሚያቀርብ ወቅታዊነቱ አለፈበት የሚባል አይደለም፡፡ ይልቁንም ደግሞ፣ ችግሩንና ፈተናውን አቅርቦ ብቻ የሚተው ባለመሆኑ  መጽሐፉን ጥሩ ያሰኘዋል፡፡ ከቤተሰብ ጀምሮ መገናኛ ብዙኃን፣ የፍትህ አካላት፣ በሥልጣን ያለው መንግሥት ኹሉ በየፊናቸው ሀገሪቱን በሀገርነት እንድትቀጥል የሚፈልጉ ከኾነ፣ ሊያደርጉት የሚገባቸውን ጨምሮ የሚገልጽ ነውና ሁሉም ሊያነባው  የሚገባ መጽሐፍ ነው፡፡  
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1785 times